Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ብቻ የተወሰነ የኪራይ ተመን የለም አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ባፈው ሳምንት በነበራቸው የውይይት ፕሮግራም ላይ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሼድ የወሰዱ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚከፍሉት የሊዝ ዋጋ በዶላር መተመኑ ጥያቄ ቢቀርብም፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ግን ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ብቻ ተብሎ የተወሰነ የኪራይ ተመን እንደሌለው አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሼድ በመገንባት እያመረቱ የሚገኙ ባለሀብት፣ ‹‹የሊዝ ኪራይ ዋጋ እንድንከፍል ውል የገባነው ክፍያው በሚፈጸምበት ቀን ባለው የባንክ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መሆኑ ተገቢ አይደለም፤›› በማለት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ‹‹በዶላር ዋጋ ላይ ያለው ጭማሪ ሥጋት ላይ ጥሎናል፤›› ያሉት ባለሀብቷ ‹‹የምንከፍለው የኪራይ ዋጋ እጅግ የተጋነነ ነው፤›› ብለው መንግሥት ሊያግዛቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገቡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሼድ ኪራይ የሚከፍሉት በዶላር ከሆነ፣ በአገር ውስጥ ኩባንያዎችና በውጪዎቹ መካከል ምን ልዩነት አለ? ይኼ ከየት የመጣ እንደሆነ ብዙ አልገባኝም፣ እነ አቶ ማሞ (የብሔራዊ ባንክ ገዥ) ብታዩት ጥሩ ነው፤›› ብለው ነበር።

በማስከተልም፣ ‹‹አንደኛ የአገር ውስጥ ኮባንያዎች የመሥሪያ ቦታ ወይም የሼድ ኪራይ ክፍያ በብር መሆን አለበት፣ ሁለተኛ ዶላር ይወጣል ይወርዳል ብለው መጨነቅ የለባቸውም፡፡ ለውጭ ኩባንያዎች የምናደርገውን ድጋፍ በግማሽ እንኳን ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ብናደርግ ጥሩ ነው፤›› ሲሉ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ማብራሪያ ለሪፖርተር የሰጡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ኃላፊ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሼዶችን በመረከብ ወይም በመገንባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲደረግ የተለየ የሊዝ ኪራይ ተመን እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት የተወሰደውን ብድር መመለስ እንዲቻል የሊዝ ኪራይ ክፍያው በዶላር እንዲሆንና ሼዶቹም የውጭ ባለሀብቶች ብቻ ገብተው እንዲያመርቱ ሲደረግ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለማበረታታት በሚል መሬቶችን በመረከብና ሼዶችን በመገንባት እንዲሠሩ መፈቀዱንና የሼድ ኪራይ ተመኑንም በዶላር እንዲከፍሉ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፣ የዶላር እጥረት እያጋጠማቸው መሆኑን በመረዳት የኪራይ ተመኑን በባንክ የዶላር ተመን ዋጋ በማሰብ እንዲከፍሉ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አሠራር ውጪ ግን ለአገር ውስጥ አምራቾች የተለየ የሼድ ኪራይ ተመን አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ፣ እንዴት ይመለከተዋል በሚል ለኃላፊው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በባለሀብቷ የቀረበውን ጥያቄ ግልጽ አለመሆኑን ተናግረው፣ ‹‹ጥያቄው ጠቅላይ ሚኒስትሩም አልገባቸውም፡፡ ሲያነሱ እንደሰማነው ክፍያው በዶላር ነው የሚለው አልገባኝም ነው ያሉት፤›› ብለዋል። በኮርፖሬሽኑ በኩል አሁንም በዶላር እየተከፈለ ነው የሚል አረዳድ መኖሩን፣ ነገር ግን ማንም የአገር ውስጥ አልሚ በዶላር እየከፈለ አለመሆኑን ማረጋገጥ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች