Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ሊያካትት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየማነ ብርሃኑ

ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የተካተቱበት የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኑስ ወርቁ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹ቀደም ሲል በቴሌ ብር፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ለነዳጅ ውጤቶች ግብይት ዲጂታል የክፍያ አማራጮች ሆነው ቆይተዋል፡፡

ሆኖም ከሦስቱ የክፍያ አማራጮች በተጨማሪ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን፣ በተለይም ሁሉንም ባንኮች በማካተት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት የክፍያ አማራጮች ውስን በመሆናቸው ምክንያት፣ አንዳንድ ባንኮችና ተገልጋዩ ማኅበረሰብ ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ሔኑስ፣ ደንበኛው በተመቸው የክፍያ አማራጭ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማስቻል፣ የሌሎችንም ባንኮች ተሳትፎ ለማረጋገጥና ገበያውንም አካታች ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ወሳኝ ድርሻ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡

የነዳጅ ግብይቱን ዘመናዊ ለማድረግና የክፍያ አማራጮችን ለማስፋት እንዲያስችል ሆኖ ሊተገበር በታቀደው የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት፣ የአስተዳደር ማኑዋል ላይ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከነዳጅ አከፋፋይ ማኅበራት ተወካዮችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሔኑስ ገለጻ አዲሱን የኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ማስተግበሪያ ሥርዓት ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ፈጅቷል፡፡ በቀጣዮቹ ሁለትና ሦስት ወራት ሥራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት በየዓመቱ ከ4.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ እንደሚገኝ፣ ወጪው አገሪቱ ከተለያዩ መስኮች በኤክስፖርት የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚበልጥ አክለው ገልጸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች