Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከወሊድ ጋር በተያያዘ የሕክምና ስህተት 66 እናቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተገለጸ

ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሕክምና ስህተት 66 እናቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተገለጸ

ቀን:

የአዲስ አበባ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከመጋቢት 2007 እስከ መጋቢት 2016 ዓ.ም. በግልና በመንግሥት ጤና ተቋማት በተፈጠረ የሕክምና ስህተት 66 እናቶች ሕይወታቸው ማለፉን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ የስምና የመለያ (ብራንዲንግ) ለውጥ ባደረገበት ወቅት የተሠሩ ሥራዎችንና የታዩ ክፍተቶችን እንዲሁም የቀረቡ አቤቱታዎችን አቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና ባለሙያዎች ሥነ ምግባርና የሕክምና ስህተት ክትትል ኮሚቴ፣ ከሕክምና ስህተት ጋር በተያያዘ 297 አቤቱታዎች ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እንደቀረቡ ተናግሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል 66 እናቶች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ሰላሳ ሦስቱ በግል የሕክምና ተቋማት እንዲሁም፣ ቀሪዎቹ በመንግሥት ጤና ተቋማት በኩል መሞታቸውን የሚያሳይ አቤቱታ መቅረቡ ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም 39 ጨቅላ ሕፃናት በወሊድና በግርዛት ወቅት መሞታቸውን ከሪፖርቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም 51 ሰዎች በሌሎች ምክንያቶች መሞታቸው በሪፖርቱ የተመላከተ ሲሆን፣ በ95 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የሚገልጹ አቤቱታዎች መቅረባቸው ታውቋል፡፡

ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ 109 በመንግሥት እንዲሁም 177 በግል ጤና ተቋማት በአጠቃላይ 297 አቤቱታዎች መቅረባቸውን የሚያሳየው ሪፖርቱ፣ ከቀረቡት ቅሬታዎች ውስጥ 214 የሚሆኑት ተገቢውን ውሳኔ ማግኘታቸውን፣ 72 ያህሉ በማጣራት ሒደት ላይ መሆናቸውን፣ እንዲሁም 11 አቤቱታዎች ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  መላካቸው ተጠቁሟል፡፡

የጤና ባለሙያዎች አስፈላጊውን የሙያ ሥነ ምግባር ተላብሰው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ጤና ባለሙያዎች የሥነ ምግባር ኮሚቴ አፈጻጸም መመርያ 1/2007›› መውጣቱን የተናገሩት የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የሕክምና ሥልትና የባለሙያዎች ሥነ ምግባር ክትትል ቡድን መሪ አቶ ሰናይ አበባየሁ ናቸው፡፡ 

ኮሚቴው በመንግሥትም ሆነ በግል ጤና ተቋማት የሚሰጠው የሕክምና  አገልግሎት ጥራቱን፣ ደረጃውን፣ እንዲሁም የጤና ሙያ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ  የታካሚዎችን ፍላጎት ያገናዘበ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን የቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡

ስህተት ስለሠሩ ባለሙያዎች መረጃ በወቅቱ አለመቅረብ፣ እንዲሁም ከጤና ተቋማት  እንዲቀርቡ የሚታዘዙ ሰነዶች የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ለቀረበባቸው አቤቱታ በተሰጠ ቀጠሮ መልስ አለመስጠት፣ ከሰባት ዓመታት በላይ ለሕግ ባለሙያ   ክፍት የሥራ መደብ ቅጥር አለመፈጸም፣ ጉዳት የደረሰባቸው ቅሬታ አቅራቢዎች  በወቅቱ  ምላሽ እንዳያገኙ ከሚያደርጉት ችግሮች ጥቂቶቹ መሆናቸውን አቶ ሰናይ ተናግረዋል፡፡

በሕክምና ስህተት ከሚፈጠሩ ችግሮች ባሻገር ለባዕድ ምግብና መጠጦች፣ እንዲሁም ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውርና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከኅብረተሰቡ ጥቆማና አስተያየት እንደሚቀርብላቸው የተናገሩት ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት  ባለሥልጣን  ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ታደሰ ናቸው፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከኅብረተሰቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ባለፉት ስድስት ወራት የዋጋ ግምታቸው ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕገወጥ ምግቦችና መጠጦች መወገዳቸውን ወ/ሮ ሙሉእመቤት አስረድተዋል፡፡

‹‹የሚቀርቡ ቅሬታዎች ሁሉ የሕክምና ስህተት ናቸው ማለት አይቻልም›› ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጇ፣ አንዳንዶቹ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት  ካገኙ በኋላም ሊሞቱ ይችላሉ ብለዋል፡፡ 

ነገር ግን ስህተቶች እንዳይፈጠሩ የብቃት ማረጋገጫ ወረቀትን ከመስጠት ጀምሮ ክትትል እንደሚያደርጉ አክለዋል፡፡

ሕገወጥ አሠራሮችንና ክፍተቶች ሊታረሙ እንደሚገባ ተናግረው፣ በቸልተኝነት ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ተቋማቸው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ወ/ሮ ሙሉእመቤት አስረድተዋል፡፡

የሕክምና ስህተት እንዳይኖር ባለሥልጣኑ ድጋፍና ክትትል፣ እንዲሁም ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ እንደሚያከናውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጇ፣ ኅብረተሰቡ በምግብ ደኅንነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ጥቆማ በመስጠት የመኖር ጣሪያን ከፍ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረውን ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን›› የሚለውን ስያሜ፣ ‹‹የአዲስ አበባ  የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን›› ወደሚል መቀየሩን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...