Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትዝታዋ የተረፈው ፒያሳ

ትዝታዋ የተረፈው ፒያሳ

ቀን:

አራዳ ጊዎርጊስ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣  ጣሊያን ሠፈር፣ ሽክና ሠፈር፣ ገዳም ሠፈር፣   ክቡር ዘበኛ፣ ደጃች ውቤ፣ ውቤ በረሃ፣ ሠራተኛ ሠፈር፣ እሪ በከንቱ፣ አትክልት ተራ፣ አፍንጮ በር፣ ብቅ እንቅ፣ ዶሮ ማነቂያና የመሳሰሉት ሠፈሮች የፒያሳ መለያዎች ናቸው፡፡ 

ትዝታዋ የተረፈው ፒያሳ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የብዙዎች ትዝታ ታትሞ የሚገኝባት ፒያሳ ደሃና ሀብታሙን አቻችላና አስተቃቅፋ ያቆየች፣ እናቶች ጉሊት ቸርችረው ጥሬና ብስል ድንች ሸጠው፣ ነጋዴዎች ወርቅና ብሩን ቸብችበው፣ ብቻ ሁሉም እንዳቅሙ ተሯሩጦ የዕለት ጉርሱን የዓመት   ልብሱን ችሎ የሚያድርባት የመዲናዋ ርዕሰ አድባር ናት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በቅርስ የተመዘገቡና የአገሪቱ ታሪካዊ አሻራ ያረፈባቸውን ጨምሮ ዕድሜ ጠገብ ቤቶች ተዛዝለውና ተደጋግፈው የሚገኙባቸው የተለያዩ ሰፈሮችም፣ የፒያሳን ዕድሜ ጠገብነትና ታሪካዊነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ነበሩ፡፡

ለዘመናት የዘለቀ የነዋሪዎች ማኅበራዊ መሥተጋብር፣ ጉርብትናና ተካፍሎ መኖር የሚገለጽበትም ነበር፡፡

የጠፉ መጻሕፍት ተፈልገው የሚገኙባት፣ አንባቢና ታሪክ አዋቂ፣ መካሪና ዘካሪ ሰዎች የሞሉባትና መናገሻ እየተባለች የምትጠራዋ ፒያሳ፣ ዛሬ ላይ ትዝታ እየሆነች ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነባር ቤቶችንና ሱቆችን በማንሳት በምትካቸው ዘመኑን የዋጁ ከአዲሱ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ጋር ትይዩ የሆኑ ቤቶችን ለመገንባት እንዲሁም ሰፋፊ መንገዶችንና መሠረተ ልማቶችን ለማልማት ወደ ሥራ መግባቱን ማስታወቁን ተከትሎ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች ከሥፍራው ተነስተው ሥፍራውን ማፍረስ ተጀምሯል፡፡

ልማቱ ‹‹የአዲስ አበባ የመንገድ ዳር (የኮሪደር) ልማት በሚል በሌሎች የከተማዋ ክፍሎችም በመከናወን ላይ ሲሆን፣ ልማቱ ለሚነካቸው ነዋሪዎች ምትክ ቤትም ሆነ የንግድ ቦታ እንደሚሰጣችው በከተማ አስተዳደሩ ቃል እንደገባላቸው ነዋሪዎቹ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ የዶሮ ማነቂያና አካባቢው የተለያዩ ነዋሪዎች አስተያየቶችንና ቅሬታዎችን በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡ አንዳንዶች የአራዶቹ ሠፈር የምትባለው ፒያሳ ያረጁ ቤቶች ተነስተው ልትሞሸር ነው እያሉ ነጋሪት ሲጎስሙላት፣ ትዝታዋና ሽታዋ፣ መልክና ገጽታዋ ከዓይነ ህሊናቸው አልጠፋ ብሎ የሚዳክሩ ነዋሪዎች ደግሞ፣ አራዳ ከነብዙ ትዝታዋ ልትቀበር፣ እንደ ሞተ ዘመድ ላንረሳት ግን ዳግም ላናገኛት ነው ይላሉ፡፡ 

ባረጁና በፈራረሱ፣ ጣሪያቸው በሚያፈስና ግድግዳቸው በገጠጠ፣ መጸዳጃ ቤት በሌላቸውና ያሉትም እንዳሉ በማይቆጠሩ ቤቶች ለሚኖሩ ነዋሪዎች፣ ለልማት መነሳት የውዴታ ግዴታ ቢሆንም፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በነበራቸው ውይይት የተሠራ ቤት ከማግኘት ጀምሮ ቀደም ሲል ይኖሩበት እንደነበረው አብሮነት ሳይነጣጠሉ ይኖሩ ዘንድ በአንክሮት ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

አካል ጉዳተኞችም እነሱን ታሳቢ ያደረገ ቤት እንዲዘጋጅላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ ተከራዮችና ደባሎችም የአከራዮች ቤት ሲፈርስ ባለው የቤት ኪራይ ውድነት የምንጠጋበት የለንም በማለት አሳስበው ነበር፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም.  በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አካባቢ የነበሩ የልማት ተነሺዎችን ሁኔታ ተመልክቶ ነዋሪዎችንም አነጋግሮ ነበር፡፡

በተለይ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ ግርግር በዝቷል፣ ቤቶች በመፍረስ ላይ ናቸው። ነዋሪዎች ዕቃችሁን በወቅቱ ካላወጣችሁ ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነት የሚወስድ የለም ስለተባሉም አሮጌውንም አዲሱንም ዕቃ በመሰብሰብ ላይ ነበሩ።

የገንዘብም ሆነ የጉልበት አቅም ያላቸው ቀደም ብለው ማረፊያቸውን አዘጋጅተዋል፣ ንብረታቸውንም ጭነዋል።

ወ/ሮ መቅደላዊት አበበ ፒያሳ ዶሮ ማነቂያ በተለምዶ ሾፌር ሠፈር እየተባለ  በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳቸውና ሌሎች ቀድመው መልቀቅ ባለመቻላቸው ዕቃቸውን ጠቅልለው በራቸው ላይ አድርገው የሚሆነውን በአጽንኦት ይመለከታሉ።

ዕድሜያቸው ጠና ያሉ አዛውንቶች ያሳለፉትን ሁሉ በትዝታ ወደኋላ ተስበው  የሚነጉዱ ይመስላሉ፡፡ ለዘመናት በፍቅር የኖሩባት ዶሮ ማነቂያ ዛሬ ላይ ፊቷን  አዙራባቸዋለች፣ ብርሃኗ ጠፍቷል፡፡ መብራት የለም፡፡ ውኃም ብትሆን ቀድማ ተሰናብታቸዋለች፡፡ ልጆች  ትምህርት ቤት መሄድ ካቆሙ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡

ሠፈራቸውን ለቀው ለመሄድ የሞት ያህል የከበዳቸው ፊቶች በትንሽ በትልቁ  ስሜታቸው ሲለዋወጥ ይታያሉ። ወ/ሮ መቅደላዊትም ሁለት ክራንቻቸውን በሁለት እጆቻቸው ተደግፈው ግማሽ ጎኑ ከፈረሰው የቤታችው ደጃፍ ላይ አላፊ አግዳሚውን ይመለከታሉ።

አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው እንደ ብዙዎቹ ከወዲያ ወዲህ ብለው ዕቃውን መኪና ላይ ለመጫን ስላቃታቸው ሲናደዱና ለቅሶ ሲተናነቃቸው ተመልክተናል፡፡ ባለቤታቸውም አካል ጉዳተኛ በመሆናቻው የሚሆነውን ነገር በቁጭት ነበር የሚመለከቱት።

በፈረሰባቸው ቤት ምትክ ሀና ፉሪ በተባለ ቦታ በጋራ መኖሪያ ሕንፃ መኖሪያ  ቤት እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ወይዘሮዋ፣ በዕጣ የደረሳቸው ቤት አምስተኛው ወለል ላይ በመሆኑ ለችግር መጋለጣቸውን ይገልጻሉ፡፡

አካል ጉዳተኛን ያላገናዘበና በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የአካል ጉዳተኞች መብት ያላከበረ ነው በሚል፣ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ሁሉ ቢያሳውቁም፣ ገና ሰሚ እንዳላገኙ አክለዋል፡፡

የኖሩበትን ሠፈር ጥሎ ወደማያውቁት አካባቢ መሄድ ስሜትን ይጎዳል የሚሉት ወ/ሮ መቅደላዊት፣ የኖሩበት ማኅበራዊ እሴት ሊጠፋ ይችላል ሲሉም ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ተወልደው ያደጉበትን፣ ክፉና ደጉን ያሳለፉበትን፣ በሐዘናቸው ያለቀሱበትን፣ በደስታቸው የጨፈሩበት፣ ሠፈራቸውን ዳግም ድርሽ ላይሉ ተሰናብተው ለመውጣት  የሞት የሽረት ጉዳይ ሆኖባቸዋል።

ፒያሳ እንኳንስ ተወልዶ ላደገባት በእንግድነት እግር ጥሎት ያለፈ ያገደመባት ትዝታን አስቋጥራ የምትሸኝ ባለ ብዙ ታሪክ ናት።

ብዙ አርቲስቶች ስለፒያሳ ገጥመው አንጎራጉረውላታል፣ ‹‹አፈረሱት አሉ መሀል አራዳን ያለ አባት ያለ እናት ያሳደገንን›› በማለትም ተነግሮላታል፡፡

በፈረሰባቸው ምትክ ቤት የተሰጣችው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ሰባት ስምንት ቤተሰብ  ይዘው ሜዳ ላይ የወደቁ በርካታ ቤተሰቦች እንደሚገኙ መታዘብ ተችሏል፡፡

‹‹መንግሥት ዋሽቶናል ‹ማንንም ቢሆን ምትክ ቤት ሳንሰጥ አውጥተን አንጥልም›  ብሎ ከእነቤተሰቦቻችን ሜዳ ላይ ጥሎናል፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን ለሪፖርተር አቅርበዋል፡፡

ለመውለድ ሳምንታት የሚቀራቸው እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞችና በሕመም ላይ ያሉ ነዋሪዎች የቤት ኪራይ በማጣት ዛሬም በፈራረሰው ቤታቸው ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ወርደው ችግራቸውን ሊፈቱና በአግባቡ ሊረዷቸው ፈቃደኛ ስላልሆኑ፣ ከተማ አስተዳደሩ በአካል ተገኝቶ ቃል በገባው መሠረት ችግራቸውን እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...