Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹በማኅበረሰቡም ሆነ በመንግሥት ባለሥልጣናት የኪነ ጥበቡ ዘርፍ እጅግ ትኩረት ያጣ ነው›› ...

‹‹በማኅበረሰቡም ሆነ በመንግሥት ባለሥልጣናት የኪነ ጥበቡ ዘርፍ እጅግ ትኩረት ያጣ ነው›› አቶ አበረ አዳሙ፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት

ቀን:

ከስድስት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው  ደራስያን የተሰባሰቡበት አንጋፋ ተቋም የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ነው። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ዘመነ መንግሥት በ1952 ዓ.ም. ሲቋቋም መጠሪያ ስሙ የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር ነበር። ከ2010 ዓ.ም . ወርኃ መጋቢት ጀምሮ ከስድስት ዓመት በላይ ማኅበሩን እየመሩ ያሉት አቶ አበረ አዳሙ ናቸው። ስለማኅበሩ እንቅስቃሴና ስላጋጠመው ፈተና እንዲሁም ስለወደፊት ዕቅዱ ከየማነ ብርሃኑ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

ሪፖርተርየኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት ምን ተግባራትን በመከወን ላይ ይገኛል?

አቶ አበረ፡- ማኅበሩ የአባላቱን መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ ሰፋ ያለ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ አዕምሮው በመልካም ነገር እንዲቀረፅ በማድረግ በኩል በርካታ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ‹‹ብሌን ኪነ ጥበባዊ የሰላም ምሽት›› በየወሩ እናካሂድ ነበር፡፡ የንባብ ባህልን ለማዳበር ሰኔ 30 የንባብ ቀን ተብሎ እንዲታወጅና በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኝ፣ መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበን ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ግን አዋጅም ሆነ ሌሎች ነገሮች ሳያስፈልጉ ማኅበሩ በራሱ ማድረግ ይችላል የሚል ፈቃድ ስለሰጠን በዚህ ላይ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ‹‹ህያው የጥበብ ጉዞ›› በሚል መርሐ ግብር በየክልሉ በመሄድ የወጣቶችን የሥነ ጽሐፍ ስሜት በማነቃቃት ረገድ የማይናቅ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ አሁን ላይ በአገር ላይ ባለው የሰላም ችግር ምክንያት ይህንን ፕሮግራም ለማስቀጠል አልቻልንም፡፡ ማኅበራችን መንግሥት በሰጠው 3,000 ካሬ ሜትር ቦታ ሕንፃ ለመገንባትና የአፍሪካን ደራስያን መቀመጫ አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን የማድረግ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ የሕንፃችንን ሥራ አስጀምረናል፡፡ ይህ እንደ ትልቅ ስኬትና ድል የሚቆጠር ነው፡፡ በየጊዜው ለወጣቶች የሥነ ጽሑፍ ሥልጠናም እንሰጣለን፡፡ አሁን ላይ ወደ ዘጠነኛ ዙር ደርሰናል፡፡ ሥልጠናውም የረዥምና የአጭር ልብ ወለድ አጻጻፍ፣ የግጥም፣ የፊልምና ቴአትር ስክሪፕት አጻጻፍን በተመለከተ ሲሆን፣ በታዋቂ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንንና በደራስያን የሚሰጥ ነው፡፡ በቀጣይ ሕንፃችን ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ሥልጠናውን ከክረምት ባሻገር ረዘም ላለ ጊዜ የሚሰጥ ነው የሚሆነው፡፡ የሕንፃው ፕሮጀክት ከሚያካትታቸው አንዱ ቤተ መጻሕፍት ነው፡፡ ስለሆነም ለማኅበረሰቡ በቀጣይ ይህንን በሰፊው የምናመቻች ይሆናል፡፡ በወጣቱ ትውልድ ዙሪያ በአሁኑ ወቅት የሥነ ምግባር ችግሮች ይታያሉ፡፡ የትምህርት ጥራቱም እጀግ አጠያያቂ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ወደ ጤናማ መንገድ እንዲመጡ ማኅበራችን አበክሮ ይሠራል፡፡ ወጣቶች በዕውቀትና በሥነ ምግባር የታነፁ፣ አስተሳሰባቸው ጤናማ የሆነ፣ ወገን፣ ቋንቋ፣ ጎሳና ሃይማኖት እየለዩ የማይቧደኑ ይሆኑ ዘንድ አዕምሮ ላይ መሥራት አለብን ብለን አምነን እየሠራን እንገኛለን፡፡     

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተርየሕንፃ ግንባታውን በምን ያህል ገንዘብ ነው የምታከናውኑት? የገንዘቡስ ምንጭ ምንድነው? 

አቶ አበረ፡- ገቢው ከአባላት በሚሰበሰብ 30 ብር መዋጮ ነው፡፡ ማኅበሩም የሚተዳደረው በዚሁ ነው፡፡ ሕንፃው በ100 ሚሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን፣ ባለ ሰባት ወለል ነው፡፡ በደራሲ (በአባላት) መዋጮ ማንም ድጋፍ ሳይሰጥህ መገንባት ከባድ ቢሆንም እኛ ግን ጀምረነዋል፡፡ የወጣቶች ማዕከላት፣ የስፖርት ማዕከላትና የመሳሰሉ እየተባሉ በየቦታው የሚገነቡ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በድርሰትና በኪነ ጥበብ ዙሪያ ግን እዚህ ቦታ ይህ ተሠርቷል የሚባል አንዳች ነገር አላየሁም፡፡ በእርግጥ ‹አብርሆት› ላይብረሪ ተገንብቷል፡፡ ይህ ለንባብ አፍቃሪው ትልቅ ድል ነው፡፡ እንደ አገር የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች የሚቀርቡባቸው ቦታዎች ውስን ናቸው፡፡ በንጉሡ ጊዜ ከተሠሩ አዳራሾች ውጪ ሌላ ግንባታዎች እስካሁን የሉም፡፡ ሀገር ፍቅር፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ አምባሳደር፣ ራስ ቴአትር (እሱም ከፈረሰ ስንት ጊዜው ነው) ሌላ ቲአትር ቤቶች የሉንም፡፡ በማኅበረሰቡም ሆነ በመንግሥት ባለሥልጣናት የኪነ ጥበቡ ዘርፍ እጅግ ትኩረት ያጣ ነው፡፡  እናም ይህ ነገር እልባት እንዲያገኝና የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በአገር ደረጃ ቦታ እንዲሰጠው ጥረት በማድረግ ላይ ነን፡፡ 

ሪፖርተርየኢትዮጵያ የደራስያን ማኅበር አጀማመር፣  ማኅበሩ ምን ያህል አባላት እንዳሉት ቢገልጹልን 

አቶ አበረ፡- የኢትዮጵያ ደራስያን  ማኅበር የተጀመረው ‹‹የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር›› ተብሎ እንደ ዕቁብ ነው፡፡ እነ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት፣ አቤ ጉበኛ፣ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅንና ሌሎች በርካታ ደራስያን መጻሕፍትን ለማሳተም በዕቁብ መልክ የተጀመረና የካቲት 12 ቀን 1952 ዓ.ም. የተመሠረተ አንጋፋ ማኅበር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን  ማኅበር ሰመራ፣ መቀለ፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሐዋሳ፣ ሐረሪና የመሳሰሉ ቦታዎች ቅርጫፎች አሉት፡፡ የቅርንጫፍ አባላቱን ሳይጨምር በአሁኑ ወቅት ወደ 2,500 አካባቢ የሚደርሱ ደራስያን አባላት ያሉት ነው፡፡ የማኅበሩን ኃላፊነትም ከመጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተረክቤ እስካሁን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡  

ሪፖርተርጸሐፍት (ደራስያን ) እንዲወጡ በማድረግ በኩል የኢትዮጵያ ደራስያን  ማኅበር እያደረገ ያለው ድጋፍና ዕገዛ ምን ይመስላል? ከኅትመት ዋጋ መናር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን በመፍታት በኩልስ ምን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው?

አቶ አበረ፡- በአገር ደረጃ ጸሐፊያን እንዲወጡ በሁለት መንገድ እናደርጋለን፡፡ አንደኛው አማተር ጸሐፊያን ትክክለኛ መስመራቸውን እንዲይዙ ሥልጠና መስጠት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ረቂቅ ያላቸውን ሰዎች በማወዳደር የተሻለ ሥራ ያላቸው በተዘዋዋሪ ሒሳብ (ሪቮልቪንግ ፈንድ) ሥራቸውን እንዲያሳትሙ በማድረግ ላይ ነን፡፡ በዚህ መንገድ እስካሁን 16 መጻሕፍትን አሳትመናል፡፡ ሌላው ለጀማሪ ደራሲዎች ነፃ የአርትኦት ድጋፍ መስጠት ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል የተቋቋመ ኮሚቴ አለ፡፡ ወረቀትን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወረቀት ዋጋ ተወዷል፡፡ ‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› እንዲሉ፣ በእኛ አገር ደግሞ ከድህነቱና ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ የወረቀት ዋጋ እጅግ የናረ ሆኗል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት መንግሥትን ‹‹ግብር ቀንሱ፣ እንዲህ አድርጉ›› ምናምን እያለን አንጮህ ነበር፡፡ አሁን ግን የወረቀት ዋጋ ውድነት እየባሰ መጥቷል፡፡ የወረቀት ዋጋን ያስወደደው የአምራቾች ቁጥር እየቀነሰ መምጣት ነው፡፡ ወቅቱ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው እያዘነበለ በመምጣቱ የኅትመት ሚዲያው በተለይ በእኛ አገር ትኩረት እንዲያጣ ሆኗል፡፡ ስለሆነም የወረቀት ዋጋ ንረት አንደኛው ምክንያት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው መዘመን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የመጽሐፍ አንባቢው ቁጥር እየቀነሰ መምጣትና ነጋዴዎችም ከዚህ ዘርፍ መውጣታቸው ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ በተደጋጋሚ ጊዜያት ለመንግሥት አቤት እያልን እንገኛለን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕዝባችን የሆድ ረሃብተኛ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ረሃብተኛ እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡ ዘይት፣ ስንዴ፣ ወዘተ የመሳሰሉ የምግብ ፍጆታዎች ድጎማ ተደርጎላቸው ወደ አገር እንደሚገቡ ሁሉ፣ ወረቀት ላይም ድጎማ ተደርጎ እንዲገባ በየመገናኛ ብዙኃኑ ስንጮህ ቆይተናል፡፡ አሁንም ከመጮህ አልታቀብንም፡፡ ወጣቶችን ለመቅረፅ ዕውቀት ላይ መሥራት ይገባናል፡፡ ዕውቀት ላይ ለመሥራት ደግሞ መጻሕፍት መታተም ይኖርባቸዋል፡፡ መጻሕፍት ያለ ችግር በገፍ እንዲታተም የወረቀት ዋጋ በእኛ አቅም ሊገዛ የሚችል መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴርና ባህል ሚኒስቴር ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የሐዲስ ዓለማየሁን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የተባለ መጽሐፍ ‹‹ትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር›› ይባል የነበረ ተቋም ነው ያሳተመው፡፡ ስለሆነም አሁንም ትምህርት ሚኒስቴር ለማኅበረሰቡ የሚመጥን፣ በይዘቱ ጥሩ የሆነ፣ የወጣቱን ሥነ ምግባር በመልካም ሊቀርፅ የሚችል መጽሐፍ አይቶና መዝኖ ማሳተም የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡ ባህል ሚኒስቴርም ‹‹ንባብ›› ባህል እንዲሆን መሥራት ቢችል እንደ አገር በወጣቶች ዙሪያ በጎ የሆኑ ለውጦች ይመጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለሆነም የሚያነብና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ሆነ ትምህርት ሚኒስቴር  ከማኅበራችን ተቀራርበው በጥምረት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡          

ሪፖርተርበአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የሥነ ጽሐፍ ዕድገት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ አበረ፡- ወረቀት እየተወደደ፣ አንባቢ እየጠፋ ዕድገቱ ምን ሊሆን ነው? አደጋ ላይ ነው ያለው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቁጥር ደረጃ ብዙ መጻሕፍት በተለይም የግጥም መድበል እየታተመ ነው፡፡ ጥራቱን ያየን እንደሆነ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ በእርግጥ ጥሩ ጥሩ ደራስያንንም አሉ፡፡ የዚያኑ ያህልም ገለባው የሚበዛ ብዙ ነው፡፡ በደርግ ዘመን አንድ መጽሐፍ ይታተም የነበረው 30 እና 40 ሺሕ ቅጂ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው የሰው ቁጥር ደግሞ ከ40 ሚሊዮን የሚበልጥ አልነበረም፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ማንበብ የሚችለው ውስን ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ከ120 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ባለበትና ማንበብ የሚችለው ሰው ቁጥር ቢጨመርበት ከምንም በላይ ደግሞ፣ በመንግሥት ደረጃ ብቻ ከ50 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙበት አገር፣ አንድ መጽሐፍ በሚሊዮን ቅጂ መታተም ነበረበት፡፡ ነገር ግን አሁን እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በዚህ አገር ትልቁ የሚታተመው ቅጂ በቁጥር ከአምስት ሺሕ አይበልጥም፡፡ ከዚህም ያነሰ አምስት መቶና ሦስት መቶ ቅጂ የሚያሳትሙም ደራሲዎች ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ ድርሰቶቻቸው አይሸጡላቸውም፡፡ ይህ የደራሲውን መንፈስ እጅግ የሚጎዳ ነው፡፡ መጻሕፍቱ የማይሸጡበትን ምክንያት ያየን እንደሆነም አንድም የሚታተመው መጻሕፍት ጥራት የለውም (አልፎ አልፎ ጥራት ያለው ነገር የሚጽፉ ደራሲዎች እንዳሉ ሆነው)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የወረቀት ዋጋ በመወደዱ የተነሳ የመጽሐፍ ዋጋ ከፍ በማለቱ ነው፡፡ እንደ አገር የማንበብ ልማዳችንም ደካማ ነው፡፡ ስለሆነም የወረቀት መወደድ፣ የንባብ ልምድ አለመኖርና የመጻሕፍት ጥራት መውረድ በሥነ ጽሐፍ ዕድገታችን ላይ የራሳቸውን ጥላ እያጠሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚጽፉ በርካታ ደራስያን አሉ፡፡ እነኚህን ጸሐፍት በሚቻለው ልክ ማገዝ ብንችል የወረቀት ዋጋ ቢስተካከል፣ የአንባቢውንም ቁጥር መጨመር ብንችል ነገ ከአገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ሊቸራቸው የሚችሉ ደራሲዎች ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡  

ሪፖርተርማኅበራችሁ አንባቢ ትውልድ ለማፍራት የመጻሕፍት ባንክ ለማቋቋም ያደረገው ጥረት ካለ ቢገልጹልኝ?

አቶ አበረ፡- ማኅበራችን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት 5,100 መጻሕፍት ለግሷል፡፡ ለተለያዩ ተቋማትም በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ግዴታችን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን  ማኅበር ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥነ ጽሐፉ እንዲዳብርና የደራሲዎች መብትና ጥቅም እንዲከበር ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን በንባብ የተገነባ ትውልድ እንዲኖረን በማሰብ የዜግነት ድርሻችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን፡፡ በትምህርት ቤት ደረጃ የንባብ ባህል እንዲዳብር ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍ ስንለግስ የቆየን ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ መጻሕፍት ቤት አቋቁመን ለሕዝብ በነፃ የማስነበብ ዕቅድ ይዘን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...