Wednesday, April 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

እኛም ታሪክ አለን

በሽብሩ ተድላ (ኢመረተስ ፕሮፌሰር)

(በግራጭ ታሪክ ከጦርነት መለስ ጉዞ ላይ በዳባት ከተሰረቀ በኋላ ያለው ጽሑፍ ልብ ወለድ ነው፡፡ ልብ ወለዱ ትርክት በ”አይታሊክስ” (Italics) ነው የተጻፈው)፡፡

የዚህች ጽሑፍ መነሻ እንስሳት ለሰው ልጅ የሚያበረክቱትን አገልግሎት ማውሳት ሲሆን፣ እግረ መንገዱን የቤት እንስሳትንም ታሪክ ለማጣቀስ ታስቦ ነው የተዘጋጀው፡፡ እንስሳት የራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው፡፡ ከዚያም አንፃር የእንስሳቱ ባለቤቶች ስለአገልጋይ እንስሳዎቻቸው የነበሩዋቸው አስተያየቶች የእንስሳት የታሪክ አካል ስለሆነ፣ የባለቤቶቻቸውን አስተያየትም ያካትታል፡፡ ጽሑፉ በአቶ ሀዲስ አለማየሁ በቅሎ፣ በ”ግራጭ” ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ እንዲሁም የበቅሎ እናት ዝርያ ፈረስም ይወሳል፡፡ የሚተረክለት ፈረስም ዝነኛው የደጃች ብሩ ጎሹ ፈረስ፣ “ዳምጠው” ነው፡፡

የዱር እንስሳትን የቤት እንስሳት ማድረግ

በመሠረቱ የዱር እንስሳት የነበሩ፣ የሰው ልጅ አላምዶ የቤት እንስሳት ያደረጋቸው፣ በተፈጥሮዋቸው ለመልመድ የሚችሉትን ብቻ ነው ይባላል፡፡ ይህም ማለት ለመላመድ የሚያበቃቸውን ባህሪ የሚያመቻቸው፣ “የበራሂ” (Genetic) ቅድመ ሁኔታ አለ፣ ማለት የህያው የዘር ማስተላለፊያ ሥርዓት አካል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ያም ከሥረ መሠረቱ፣ ተፈጥሮ ለማዳ እንዲሆኑ የሚያስችሉ በራሂዎችን አበርክታላቸዋለች እንደ ማለት ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ማስረጃ ውሻ ነው፡፡ ውሻ ምንም ግንኙነት ባልነበሩዋቸው የተራራቁ ቦታዎች (በተለያዩ የዓለም ክፍሎች) ለማላመድ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በእስያና ሌሎች አካባቢዎች፡፡ ይህም ውሻ የመልመድ ቅድመ ሁኔታን በተፈጥሮ ተጎናፅፎ እንደነበረ ያመለክታል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ፣ ሁሉም ቦታ የመላመድ ዕድሉ የመነመነ ይሆን እንደነበረ መገመት አያዳግትም፡፡

የሰው ልጅ የሚያላምዳቸውን እንስሳት ሲመርጥ፣ የተለያዩ የእንስሳት ባህሪያትን አጢኖ፣ ፈትሾ ነው ለማላመድ የሚሞክር፡፡ መሥፈርቶቹም ብዙ ናቸው፣ ዋና ዋናዎች እነሆ፡፡

አንደኛ እንስሳው በአጭር ዘመን (አንፃራዊ/ ከሰው ዕድሜ አንፃር ታይቶ) መራባት መቻል እንዲሁም በቶሎ ለማደግ የሚችል መሆን አለበት፡፡ ግን መልመድ የሚችል እንስሳ ሁሉ የቤት እንስሳት አባላት አይደረጉም፡፡ ስለሆነም፣ ለምሳሌ ለመራባት ብዙ ጊዜ የሚወስድበትን የዝሆንን ዝርያ ማላመድ እንጂ የቤት እንስሳት አባል ማድረግ ያዳግታል፡፡

ሁለተኛ እንስሳው በውስን አካባቢ መራባት መቻል አለበት፣ ለመራባት ሰፊ ቦታ የሚሻ እንስሳን (ምሳሌ ፓንዳ፣ አቦሸማኔ) የቤት እንስሳ ማድረግ ያዳግታል፡፡ አቦሸማኔን (የድመት አስተኔ/ዘመድ) ለማራባት ያስቸግራል፣ ምክንያቱም አቅመ መጠን የደረሱ ሴትና ወንድ አቦሸማኔዎች ወሲባዊ ግንኙነት ሲያደርጉ በይፋ አይደለም፣ ሰወር ያለ ቦታ ሆነው ነው፡፡ ይህን ዓይነት ሥፍራ ሰው በሚኖርበት አካባቢ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፡፡

ሦስተኛ እንስሳቱ በመንጋነት (አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው) መሰማራት የሚችሉ መሆን አለባቸው (ያንን ዓይነት ባህሪ እንዲኖራቸው ያሻል)፡፡ መንጋው በአንድ አካባቢ ቢሰማራም፣ ያንን አካባቢ ከሌሎች የእንስሳት መንጋዎች ጋር ለመጋራት የሚችል (መጋራቱ በጊዜ ሊለያይ ይችላል) መሆን አለበት፡፡ ይህም መንጋው የእኛ መሰማሪያ ብቻ የሚለው አካባቢ የለውም፣ የመሰማሪያ ቦታዎችን ሌሎች መንጋዎች ሊሰማሩባቸው ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የሚላመዱት የእንስሳቱ መንጋዎች፣ ምግብ የማግኛ ቦታዎቻቸውን ከሌሎች መንጋዎች ጋር መጋራት የሚያስችል ባህሪ እንዲኖራቸው ያሻል፡፡

አራተኛ  የእንስሳቱ ኅብረት (ግንኙነት) በሥርዓት የተደነገገ (አውራና ተራ፣ አለቃና ምንዝር፣ ወዘተ.) ያለው እንዲሆን ይመረጣል፡፡ ይህን ዓይነት ሥርዓት በፈረስ መንጋ፣ በቀንድ ከብት መንጋ፣ እንዲሁም ሌሎች ለማዳ እንስሳዎች ላይ የሚታይ ባህሪ ነው፡፡

አምስተኛ  እንስሳቱ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ቢበሉ፣ እንዲሁም የምግብ ዓይነቶችን  ከሰው ጋር ባይጋሩ ይመረጣል (ሰው የማይበላውን ምሳሌ ሳር በል ቢሆኑ)፡፡ ምግብ ከሰው ጋር የሚጋሩ እንስሳትን ለምሳሌ ሥጋ በሎችን አላምዶ የቤት እንስሳት አባል ማድረግ ለኪሳራ ይዳርጋል፡፡

ስድስተኛ ለማላመድ የሚመረጡት እንስሳት ጠባየ መልካም፣ ገራም (የተረጋጉ)፣ በቀላሉ ሰው ሊቆጣጠራቸው የሚችል መሆን አለባቸው፡፡ እንስሳቱ ጀርጃሮች፣ ቀዥቃዦች፣ ከሆኑ፣ እነሱን ዓይነት እንስሳት በመኖሪያ ሠፈር አካባቢ ማላመድ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ዚብራ (Zebra) አንድ መጥፎ ጠባይ አለው፤ ሰው ሲጠጋው፣ የተጠጋውን ሰው ገላ አመች ቦታ ላይ ነክሶ አልለቅም ይላል፣ አንዳንዴም ይራገጣል፡፡ ይህን ዓይነት እንስሳ ማላመድ ያዳግታል፡፡

በቅሎ፣ ፈረስና አህያ የቤት እንስሳት አባላት የሆኑበት ዘመን

የአህያ ዝርያ የቤት እንስሳ የተደረገው ከአምስት ሺሕ ዓመት ገደማ በፊት፣ ቦታውም ግብፅ/ሜሶፖታምያ አካባቢ እንደነበረ ይገመታል፡፡ በዘመናችን አርባ አንድ ሚሊዮን ገደማ አህዮች እንዳሉ፣ በብዛትም ቻይና (አሥራ አንድ ሚሊዮን ገደማ)፣ ከዚያም ፓኪስታንና ኢትዮጵያ (በተመሳሳይ ደረጃ) በእያንዳንዳቸው ስምንት ሚሊዮን ገደማ አህዮች እንዳሉ ይገመታል፡፡

ፈረስ የቤት እንስሳ የተደረገው ከሦስት ሺሕ ዓመት በፊት በኢሮእስያ አካባቢ እንደነበረ፣ ብሎም በዓለም ዙሪያ ስድሳ ሚሊዮን ገደማ ፈረስ እንዳለ ይገመታል፡፡ ፈረስ በብዛት የሚገኘው አሜሪካ (10.6 ሚሊዮን) ሲሆን በአውሮፓ፣ በእስያ እንዲሁም በአፍሪካ በዚያ ያሉ ፈረሶች አሉ፡፡

በቅሎ አሁን ቱርክ በመባል ከሚታወቀው አካባቢ ከክርስቶስ ልደት በፊት ሦስት ሺሕ ዓመት ገደማ ነበር የቤት እንስሳት አባል የተደረገው፡፡ በዓለም ዙሪያ ወደ አሥር ሚሊዮን የሚጠጉ በቅሎዎች አሉ፡፡ ከእነሱም በብዛት የሚገኙት ማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ ሲሆን፣ አፍሪካና እስያ መለስተኛ ቁጥር ያሉዋቸው በቅሎዎች አሉ፡፡ በአንደኛ ደረጃ በሜክሲኮ፣ ከዚያም በቅደም ተከተል በቻይና፣ በብራዚልና በኢትዮጵያ ነው በቅሎዎች የሚገኙት፡፡

አህያና ፈረስ በወሲባዊ ግንኙነት በቅሎን መውለድ የጀመሩት ከሰባት ሺሕ ዓመት በፊት እንደነበረ ይገመታል፡፡ ያም ሁለቱም (ፈረስም አህያም) ገና የቤት እንስሳት አባሎች ከመሆናቸው በፊት መሆኑ ነው፡፡ በቅሎ ከሴት ፈረስ (ባዝራ) እና ከወንድ አህያ (አለሌ) ነው የምትወለድ፡፡ ከወንድ ፈረስና ከሴት አህያ የምትወለድ ሌላ ዝርያ አለች፣ የእንግሊዝኛ ስሟም “ሂኒ” (Hinny) ነው፡፡

በቅሎ በቁመት ከአባቱ ከአህያ ዘር ይልቃል፣ በጥንካሬው ከእናቱ ዘር ከፈረስ ይልቃል፡፡ ፍጥነቱ ግን ከእናቱ ዘር ፍጥነት መለስ ያለ ነው፡፡ የበቅሎ ቆዳ ከፈረስ ዘር ቆዳ ስለሚወፍር፣ ለዕቃ መጫኛነት (መጋዣነት) ተመራጭ ነው፡፡ ከበድ ያለ ጭነትም ለመሸከም የሚመረጥ በቅሎ ነው፡፡

በቅሎ በመሠረቱ መሃን ናት

በቅሎ እንደ መሃን ነው የምትቆጠር፣ መሃን የሆነችው ከእናቷ ከፈረስ 64 ሃብለ በራሂ (Chromosomes)፣ ከአባትዋ ከአህያ 62 ሃብለ በራሂ ስለምትወርስ፣ ይህ ሁኔታ ዝርያ ለመተካት የሚያስፈልገውን ተፈጥሯዊ ሥርዓት ስለሚያፋልስ በቅሎ በመሠረቱ ዘር አታፈራም፣ መሃን ናት፡፡

ሆኖም ሴት በቅሎ፣ ከወንድ አህያ ወይም ፈረስ ጋር በመገናኘት፣ በጣም ውስን በሆኑ ጊዜያት ልጅ ማፍራቷ ተመዝግቧል፡፡ በመጀመሪያ በቅሎ 450 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ልጅ ወልዳ እንደነበረ ሲመዘገብ፣ ከዚያ ወዲህም እንደ ጎርጎሪዮስ ዘመን አቆጣጠር ከ1527 አስከ 2002 በቅሎ ስድሳ ገደማ ውርንጭሎች እንደወለደች ተምዝግቧል፡፡ በቅርብ ጊዜም በሞሮኮ (2002) እና በሜክሲኮ (2007) ውርንጭሎች እንደወለደች ይፋ ተደርጓል፡፡

የቤት እንስሳትን መሰንጋት

በዓለም ዙሪያ፣ ኢትዮጵያንም ያካትታል፣ የቀንድ ከብትና የጋማ ከብት መሰንጋት የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን፣ “ሰንጋ” የሚለው ቃል ከቀንድ ከብት ጋር (ከበሬ ጋር) እየተቆራኘ መጥቷል፣ በፊት ቃሉ በብዛት ከፈረስ ጋር የተዛመደ ነበር፡፡ ወንድ የኮርቻ በቅሎዎች በብዛት የተኮላሹ (የተሰነጉ) ናቸው፡፡ የሚኮላሹበትም ዋና ምክንያት ለተፈለገው ተግባር አላስፈላጊ የሆነውን የተባእትነት ባህሪ ለመቀነስ፣ ከተቻለም ለማስወገድ፣ ብሎም ገራምና ሰላማዊ የኮርቻ ከብት ለማግኘት ነው፡፡ መኮላሸት የወንድ እንስሳዎችን ተንኳሽነት፣ አስቸጋሪነት ባህሪይ ይገታል፡፡ ለዚሁ ተግባር ሲባል “ግራጭም” ተኮላሽቶ ነበር፣ እንዲሁም “ዳምጠው”፡፡

ለበቅሎና ለፈረስ ረዘም ያለ ትረካ ሲቀርብላቸው፣ አህያን አጣቃሽ ብዙ ትረካ በአካባቢያችን አልተመዘገበም፡፡ የአህያ ዝርያንም የሚያኮራ፣ ከተራ ታሪክ የላቀ፣ ከእምነት ጋር የተቆራኘ ታሪክ አለ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ በማርቆስ ወንጌል እንደተወሳው፣ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ፣ ሕዝቡ በሆታና በእልልታ ነበር የተቀበለው፡፡ ይህ ለአህያ ዘር ሁሉ፣ የታሪክ ማጣቀሻ፣ የኩራት መቀስቀሻ፣ የማንነት መታወቂያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ፈረስ በጦር ሜዳ ተሳታፊነቱ በጣም ይኩራራል፡፡ ጀግኖችም የሚጠሩት፣ የሚታወቁት  በፈረሶቻቸው ስሞች ነው፣ “አባ ታጠቅ ካሳ”፣ “አባ በዝብዝ ካሳ”፣ “አባ ዳኘው”፣ “አባ ጤና” (ምነው በሽንኩርቴ፣ ባታክልቴ ላይ? ኢያሱ አባ ጤና አይዳኝሽም ወይ? የተባለለት)፣ “አባ ጠቅል፣ “አባ መላ”፣ “አባ ኮስትር”፣ “አባ መቻል” እየተባሉ፡፡ ሆኖም በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የተነሱት ፎቶግራፎች እንሚያመለክቱት፣ የሕዝብ መሪዎች/ ነገሥታት በቅሎ ላይ ሆነው፣ እንጅ በፈረስ ጀርባ ተሳፍረው አይደለም፡፡ መሪዎች ለጦርነት ሲዘምቱም ቢሆን፣ እስከ ጦር ግንባር ድረስ በበቅሎ ተጉዘው፣ በመፋለሚያ ቦታው ላይ ነበር በፈረስ ጀርባ ላይ ሆነው ጦርነቱን የሚቀላቀሉት፡፡ 

የግራጭ ዕጣ ፈንታ

አቶ ሀዲስ አለማየሁ “ትዝታ” በምትባለዋ ውብ መጽሐፋቸው ስለ በቅሎአቸው ስለ “ግራጭ”  የተረኩት ከጣሊያን ወረራ ጋር ተዛምዶ ነበር፡፡ አቶ ሀዲስ አለማየሁ በጦርነቱ መሰናዶ ጊዜ ሲዘጋጁ፣ “የኮርቻ በቅሎ ፊቱንም ነበረኝ፡፡ ለድንኳኖቻችንና ለስንቅ መጫኛ የሚሆኑ አንድ በቅሎ አጋሰስ እና አንድ ስናር አህያ ገዛሁ” ይላሉ፡፡

በጦርነቱ ዋዜማ ወደ ሽሬ ግንባር ጉዞ እንደተጀመረ፣ ጉዞው ላይ፣ ዳባት ሲደርሱ ችግር ተከሰተ፡፡ ዳባት ከጎንደር 50 ኪሎሜትር ወደ ሰሜን፣ ጎንደርን ከደባርቅ ከሚያገናኘው መንገድ ላይ ያለች ከተማ ናት፡፡ በጣልያን ወረራ ዘመን ያ መንገድ አልነበረም፣ ሆኖም በጦርነቱ ዘመን ዳባት ላይ አንድ መለስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያ ነበረ፡፡ የጣሊያን ወረራ እንደ ተጀመረ፣ ከሽሬ ጦርነት በፊት፣ የራስ እምሩ ጦር እዚያ አካባቢ ሰፍሮ ስለነበር፣ አይሮፕላኖች  ለቀናት እየተመላለሱ ዳባት ላይ ቦምብ አዘነቡ፡፡

ዳባት በቦምብ መጋየት መንስዔ፣ አይሮፕላን “እርባና ቢስ ናት” ብሎ ደብረ ማርቆስ ላይ የሰበከውን ተማሪ ሀዲስ አለማየሁን ሊፋለም፣ ልጅ ዳኛቸው ተሰማ ከጅሎ ነበር፡፡ ልጅ ዳኛቸው ተሰማ ቁመቱ ዘለግ ያለ ጠጉረ ለዛ፣ ሽንጥና ወገቡ ሎጋ የነበረ፣ ጠመንጃ የያዙ ጋሻ ጃግሬዎች አስከትሎ ሀዲስ አለማየሁን ሊፋለም መጥቶ እንደ ነበር ሀዲስ አለማየሁ ያወሳሉ፡፡ “ያ ተማሪ የት አለ”? እያለ፡፡ ልጅ ዳኛቸው ተማሪውን ሀዲስን ፍለጋ፣ ፊታውራሪ ዳምጠው ተሰማ እና ሀዲስ አለማየሁ ወደነበሩቡት ወደ ሀዲስ አለማየሁ ድንኳን መጥቶ ነበር፡፡

ከዚያም ፊታውራሪ ዳምጠው ተሰማ ተቆጥተው፣ በዱላ አስፈራርተው ሊከሰት የነበረውን ጠብ አበረዱት፡፡ ፊታውራሪ ዳኛቸው ተሰማም አካባቢውን ለቆ ወጣ፡፡ ፊታውራሪ ዳምጠው ተሰማ የጦሩ የበላይ መሪ ለነበሩት ለራስ እምሩ የቅርብ አማካሪ ነበሩ፡፡ በጠላት ወረራ ዘመንም እሳቸውና ወንድማቸው ፊታውራሪ አስፋው ተሰማ የታወቁ አርበኞች ነበሩ፡፡ በመጨረሻም የፋሺስት ጦር የእሳቸውን ና የወንድማቸውን ራስ ቆርጦ ላልገበሩለት የጎጃም አርበኞች ማስፈራሪያ አድርጎት ነበር፡፡

ዳባት ላይ በአይሮፐላን ድብደባ በተደረገ ሌሊት፣ ልጅ ገሠሠ በለው፣ የበለው ተክለ ሃይማኖት ልጅ፣ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የልጅ ልጅ፣ ሌሊት ከግብራበሮቹ ጋር ሆኖ ፈረጠጠ፡፡ የዳባት በአውሮፕላን መደብደብ ለልጅ ገሠሠ በለው በጦርነቱ ዋዜማ ከጦር ሜዳ የመኮብለል ምክንያት ሆነው፡፡ ልጅ ገሠሠ በለው እና ጭፍሮቹ፣ ልጅ ዳኛቸው ተሰማን ጨምሮ፣ ከአካባቢው ተሰውረው ወደ አገራቸው ወደ ጎጃም ተመለሱ፡፡ በበነጋው በጉዞ ላይ ይህ ወሬ  ሲወጋ ግራጭ ሰምቶ ነበር፡፡

እነ ልጅ ገሠሠ በለው ከጦርነት ሽሽተው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በሁዋላም አላረፉም፣ መንግሥት እንቆጣጠራለን በለው የቀሰቀሱት ጦርነትን ለማኮላሸት፣ የዙፋን ጠባቂው የራስ ካሳ ኃይሉ ጦር ከሰላሌ በደጃች ተስፉ መሪነት ወደ ጎጃም ዘምቶ ነበር፡፡ ልጅ ገሠሠ በለው  ያስከተለውን የገበሬ ጦር ብቸና ጊዮርጊስ አጠገብ፣ የቀጋን ከምትባል ቦታ አስፈጅቶ፣ እንደለመደው እሱ ከቦታው  ተሰወረ፡፡ ከዚም ይባስ ብሎ በጣሊያን ወረራ ዘመንም ለጣሊያን ገባሪ፣  ሹም ሆኖ ነበር፡፡

ያደገበት አከባባቢ ወግ አጥባቂ፣ በዘር ላይ የተመሠረተ ሥልጣን የሚጎናጸፉበት አካባቢ ስለነበር፣ ግራጭ ወሬ ጠገብ ሆኖ፣ እሱም የራሱን የዘር ማንዘር ሀረግ፣ በአሳዳሪዎቹ መጠን ለመገንዘብ በቅቶ ነበር፡፡  ግራጭ ምንም ከቤተ መንግሥት መጥቶ፣ ለዘመናት ሥርዓቱን ነቃፊ ከሆነ ተማሪ እጅ ቢወድቅም፣ ከዚያ ለአጭር ጊዜ የመጫኛ ነካሽ፣ ታታሪ ነጋዴ አጋሰስ ቢደረግም፣ የዘር ወጉን አልረሳም ነበር፡፡

ግራጭ ከንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ማለፊያ ኮርቻ በቅሎዎች አንዱ የሆነ፣ በወርቅ ድግድግ መረሻት የሚያጌጥ፣ ባለ ማእረግ በቅሎ ነበር፡፡ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ልጅ፣ ወይዘሮ ንግሥት ተክለ ሃይማኖት፣ አዲስ አበባ ብዙ ቆይተው ወደ አገራቸው ወደ ጎጃም ሲመለሱ፣ ንግሥተ ነገሥታት  ዘውዲቱ ምኒልክ ከሸለሙዋቸው የክብር ሽልማቶች መሃከል አንዱ የጭን በቅሎዋቸው ግራጭ ነበር፡፡ ሁዋላ ወይዘሮ ንግሥት ተክለ ሃይማኖት የዳሞት ግዛታቸው ወኪል ለነበሩት፣ የዳንግላ ተወላጅ ለሆኑት ሹማቸው፣ ለቀኛዝማች ሙሉነህ ቦጋለ ግራጭን ሸለሙዋቸው፡፡ ሀዲስ አለማየሁ ዳንግላ በነበሩበት ጊዜ በቅሎውን ከቀኛዝማች ሙሉነህ ገዙት፡፡ “ቀኛዝማች በቅሎውን ለኔ ሸጡልኝ”፣ ይላሉ አቶ ሀዲስ አለማየሁ፡፡

የወይዘሮ ንግሥት ተክለ ሃይማኖት እናት፣ ወይዘሮ ላቀች ገብረመድኅን፣ የጎበዜ ገብረመድኅን (በኋላ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ) እህት ናቸው፡፡ እንዲሁም ራስ ካሳ ኃይሉ ያጎታቸው የኃይሉ ገብረ መድኅን ልጅ  ነበሩ፡፡ ስለሆነም ወይዘሮ ንግሥት ከላስታ፣ እና ከጎጃም የገዥው መደብ ይወለዱ ነበር፡፡ ከሸዋ የገዥ መደብ ጋርም በራስ ካሳ ኃይሉ በኩል ዝምድና ነበራቸው፡፡ የወይዘሮ ንግሥት ባል፣ የአገው ምድሩ ባላባት ራስ መስፍን ደረሶ ነበሩ፣ ወይዘሮ ንግሥት የደጃች አድማሱ መስፍን እና የፊታውራሪ ካሳ መስፍን እናትም  ነበሩ፡፡

ልጅ ዳኛቸው ተሰማ “ያ ተመሪ” ባላቸው ከሀዲስ አለማየሁ ጋር ግራጭ ሽሬ ዘምቶ፣ በተከዜ በረሃ ከደረሰው የመርዝ ዝናብ ተርፎ፣ በሽሽት በመልስ ጉዞ ዳባት ደርሶ ነበር፡፡ ግን ምን ይሆናል ዳባት ላይ ከጦርነት ስቃይ መልስ የደከሙ አርበኞች፤ አንድ ሌሊት እንቅልፍ እንደጣላቸው፣ ግራጭን እና ሌላ አንድ አጋሳስ ሌቦች ወሰዱዋቸው፡፡ ሀዲስ አለማየሁና ጓደኛቸው ጠዋት በቅሎዎችን ፍለጋ ቢሰማሩም ሊያገኙዋቸው አልቻሉም፡፡

ሌቦቹ ከጥቂት ቀናት በኋላ በቅሎዎችን ለነጋዴዎች ሸጡላቸው፣ ሰጋሩ ግራጭም ተራ የነጋዴ አጋሰስ ለመሆን ተዳረገ፡፡ ከጥቂት ወራት በሁዋላ በመተማ መንገድ ግራጭን ጭነው ይነዱ የነበሩ ነጋዴዎችን ሽፍታ አገታቸው፡፡ ከነጋዴዎቹም ጥቂቶቹ የታጠቁ ስለነበሩ፣ ተኩስ ከፈቱ፡፡ በግርግር የተጫኑት አጋሰሶች ደንብረው በየፊናቸው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ጋልበው ከአካባቢው ተሰወሩ፡፡

ግራጭም ረዣዥም ዛፎች ወደ ነበሩበት አካባቢ ከገባ በሁዋላ፣ በዛፎች በተሸፈነው አካባቢ  ያለማቋረጥ ከነጭነቱ ሲጋልብ ቆይቶ፣ ከብቶች ተሠማርተውባቸው ወደ ነበረ ገላጣ ቦታ ደረሰ፡፡ በአካባቢ የነበሩ ጎረምሶች፣ ግራጭን አረጋግተው ያዙት፡፡ ከዚያም ጎረምሶቹ ጭነቱን አራግፈው ተሸክመው ከአካባቢው ተሰወሩ፡፡ ግራጭም ጭነቱ ተራግፎለት ሌጣ ሆኖ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከዚያም በሁዋላ ሌሎች ጎረምሶች ሊይዙት ሞክረው ነበር፡ ሆኖም ደጋግሞ ከመያዝ አምልጦ በዝግታ መንገዱን እንደቀጠለ፣ ቀኑን ሙሉ ሲጉዋዝ ስላለፈበት የሕይወት ጉዞው ነበር የሚያሰላስል፡፡

አሳዳሪው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በነበሩበት ዘመን፣ ገፈራ እየተመረጠ ይቀርብለት ነበር፡፡ ገብስ፣ ባቄላ እናም ሌላም ጥራጥሬ እንደ ልብ በሰፊው ነበር የሚቀርብለት፡፡ በወይዘሮ ንግሥት ተክለ ሃይማኖት ቤትም ተመሳሳይ ምግብ ይቀርብለት ነበር፡፡ ቀኛዝማች ሙሉነህ ቦጋለ ቤት፣ ያው ሥራ ይበዛበት ነበር እንጅ፣ የምግብ ችግር አልደረሰበትም፡፡ የተማሪው የሀዲስ አለማየሁ አገልጋይ በነበረበትም ወቅት፣ ምርጫው ውስን ይሁን እንጅ፣ ምግብ እንደልብ ያገኝ ነበር፣ እዚያ ቤት ብዙ ጊዜውንም የሚያሳልፈው በዕረፍት ላይ ነበር፡፡

በመጨረሻ የነጋዴ ጭነት ማጓጓዣ አጋሰስ ሲሆን ግን፣ ሁኔታው ተቀየረ፡፡ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ከሚያሳድደው ነጋዴ እጅ ከወደቀ በሁዋላ ግን፣ ረሃብም ድካምም ደጋግሞ አጥቅቶታል፡፡ የነጋዴ አጋሰስ በነበረበት ወራት ከሳምንት ውስጥ ከአንድ ቀን ያለፈ ዕረፍት ኖሮት አያውቅም ነበር፡፡ ሌሎቹ ጌቶቹና እመቤቶቹ ቤት ግን በሥራ ከሚሠማራባቸው ቀኖች፣ በዕረፍት የሚያሳልፋቸው ይበልጡ ነበር፡፡

የነጋዴ መጋዣ በነበረበት የችግር ዘመኑ ሰሞን ግራጭ አንደ ትዝ ያለው ትረካ ነበር፡፡ አንድ ባለፀጋ አንድ ሰንጋ ፈረስ፣ አንድ ሰጋር በቅሎ አስጭነው በጉዞ ላይ ነበሩ፡፡ ፈረሱ ለሜዳ ጉዞ፣ በቅሎይቱ ደግሞ፣ ለዳገት ወይም ድንጋይ፣ ቅርቅፍት ለበዛበት አካባቢ ጉዞ ነበር የምታገለግል፡፡ ባለ ፀጋው እንደ ሁኔታው፣ አንድ ጊዜ በፈረስ ጀርባ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በበቅሎ ላይ ሆነው ነበር የሚጉዋዙት፡፡

በዚያ ጉዞ ላይ፣ የባለፀጋው ፈረስ፣ የፈረስ ቀሚስ ለብሶ፣ በጌጥ ያሸበረቀ ኮርቻ ተጭኖ፣ አንድ ጋሻ ጃግሬ ሲጎትተው፣ ጌቶቹ በበቅሎ ላይ ሆነው አንድ ዳገት እየወጡ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ ሌላ የጌቶች ጋሻ ጃግሬ፣ አንድ ዲሞትፈር ጠበንጃ በትከሻው ተሸክሞ፣ ሰማኒያ ጥይት ገደማ የያዘ ዝናር ታጥቆ፣ ሌላ ቁሳቁስ በከረጢት መሳይ አንግቦ፣ እያላበው ዳገት በእግሩ ሲወጣ፣ ለፈረስ ጎታች ባልንጀራው፣ “አሁንስ ፈረስ ባደረገኝ” ብሎ ሲያወጋው (ምንም ሳይሸከም ዳገት ሊወጣ ተመኝቶ) ጉዋደኛው፣ “አንተ ፈረስ ብትሆን ኖሮ፣ የነጋዴ መጋዣ ነበር የምትሆን፣ ይህ ገጣባ እድልህ አይለቅህም ነበር”፣ አለው ይባላል፡፡ ግራጭ ፈገግ እያለ “ሁለቱን መሆን ይቻላል” አለ በልቡ፣ በደህና ጊዜ የጌታ ፈረስ፣ ቀን ሲጥል የነጋዴ መጋዣ፣ አጋሰስ፣ መሆን፡፡

ቀኑ እየመሸ ሄዶ ሌሊት ሲሰፍን፣ ግራጭ አንድ ትልቅ ዛፍ ስር ተጠልሎ ለማደር ወሰነ፣ ሆኖም ከሩቅ ጅብ ሲጮህ ሰምቶ ሥጋት ውስጥ ገባ፡፡ ጅብ የጋማ ከብቶች ተፈጥሮአዊ ጠላት እንደሆነ ግራጭ በደመነፍስ ያውቃል፡፡ ብዙም ሳይቆይ የፈራው አልቀረም፣ ዓይኖቹ እያበሩ አንድ ጅብ እሱ ወደ አለባት ቦታ ሱክ ሱክ ኢያለ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ ጅቡ ከአጠገቡ ሲደርስ፣ የአባቱ ዘመዶች እንደሚያደርጉት፣ ግራጭ ፊቱን ወደ ጅቡ አዙሮ፣ በፊት እግሮቹ ኮቴዎች፣ ጅቡን መከላከል ጀመረ፡፡

ሌላ ጅብ ከሁዋላው ተጠግቶ ኖሮ፣ ሲነክሰው ግራጭ በሽሽት ሩጫ ጀመረ፡፡ ጅቦችም ተከትለውት መሮጥ ጀመሩ፡፡ ግራጭ ውስን ርቀት እንደሮጠ፣  ከቀናት በፊት ይዞት የነበረው የሳል በሽታ ተቀስቅሶበት፣ ሮጦ ከጅቦቹ ለማምለጥ ተሳነው፡፡ ጅቦችም የኋላ እግሩን ሥጋ ደጋግመው፣ ሲቦጭቁት ተሰማው፡፡ ከሆድ ዕቃው አካባቢ፣ በተደጋጋሚ ነከሱት፡፡ ከተነከሰባቸው አካባቢዎች፣ በጠቅላላ የህዋላ የአካል ክፍሉና ከሆድ ዕቃው አካባቢ፣ ደም በጣም መንዠርዠር እንደጀመረ፣ ግራጭ ራሱን ስቶ፣ መቆም ተስኖት ወደቀ፡፡

ጅቦች ሲቀራመቱት ስሜት አልባ ሆነ፣ በመጨረሻም የታየው በሕይወት ያሳለፈው ጊዜ ነበር፣ ጦርነቱንም ቃኜው፣ የወይዘሮ ንግሥት ወንድም፣ የበለው ተክለ ሃይማኖት ልጅ፣ ገሠሠ በለው ከጦር ሜዳ በመሸሹ ታዝቦት፣ አፍሮበትም እንደ ነበረ ትዝ አለው፡፡ ያም ሆኖ በጣም ውል ብሎ የታየው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በክብር፣ በአሽከራቸው አማካይነት፣ እሱን ለወይዘሮ ንግሥት ተከለ ሃይማኖት ሲሸልሙ ነበር፡፡ በሽልማቱ ሽር ጉድ ወቅት፣ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረም ለሱ ለግራጭ ነበር፡፡ በዚያች ቀቢፀ ሰዓት አጠቃላይ የመልካም ጊዜ ትዝታ ነበር ጎልቶ የታወሰው፣ መልካም አስደሳች ቅጽበት፡፡

በበነጋታው፣ ረፋድ ላይ፣ በቅሎ ፍለጋ ተሰማርተው የነበሩ ነጋዴዎች፣ ግራጭን ሳይሆን በፈርስ እና በደም የተበከለ አካባቢ፣ ጆፌ አሞራዎች የሚጋግጡት አጥንት ነበር ያገኙት፡፡ በብዛት ያልተጎዳው የራስ ቅሉ አካባቢ ነበር፣ ያም ሆኖ አንድ ጆፌ አሞራ የግራጭን የግራ ዓይን በማንቁሩ በመጎርጎር ላይ ነበር፣ ሌላኛው ዓይኑ የነበረበት ቀፎው ብቻ ነበር የሚታይ፡፡

ግራጭ ለማመን የሚያዳግት ጥንካሬውን/ ጉልበቱን ንቁ ባህርይ እና አልበገሬ ባይነትን ከአባቱ ከአህያ ነበር የወረሰ፡፡ የስፖርተኛነትና በጥድፊያ ከአደጋ የማምለጥን ባህርይን እና ውበት ግን የተጎናፀፈው ከእናቱ ነበር፡፡ በቅሎ የቤት እንስሳ አባል ሆኖ ሲኖርም አስተዳደሩ ቤተሰባዊ አስተዳደር መሰል ነበር፡፡

ተማሪው ሀዲስ አለማየሁ ስለ በቅሎዋቸው ስለ ግራጭ ሲያወሱ፣ እንዲህ ይላሉ፣ “በዘመቻው ካየሁዋቸው በቅሎዎች ሁሉ፣ አፌን ሞልቼ ግራጭን የመሰለ አልነበረም እላለሁ፡፡ በትልቅነቱ ከሩቅ ለሚያየው ፈረስ እንጂ በቅሎ አይመስልም ነበር፡፡ ዕድሜው እየገፋ በመሄዱ፣ ጠጉሩ ጨርሶ በመንጣቱ፣ ከግራጫነቱ ወደ ዳለቻነት ቢለወጥም፣ በድሮ መልኩ ተንተርሰን ግራጭ ነበር የምንለው፡፡ ግራጭ በሙያው ሆነ ባመሉ ልዩ ነበር፡፡ ገና ተጭኖ ወደሚቀመጥበት ሰው ሲቀርብ፣ አንገቱን ሰበር፤ ጆሮዎቹን እንደተደገነ ጣምራ ቀስት ወደ ፊቱ ቅስር፣ ጫራውን ነስነስ አድርጎ፣ ሠልፉን አሳምሮ ይቆይና፣ ከተቀመጡበት በሁዋላ ሲሰግር፣ ቆሞ ስግርያውን እየተመለከተ ሳያደንቅ የሚሄድ አላፊ መንገደኛ አልነበረም” ይላሉ ሀዲስ አለማየሁ፡፡

ተማሪ ሀዲስ ከዚም ቀጠል አድርገው፣ “አንድ ቀን ተቀምጨበት እያስገረኩት ስሄድ፣ አንድ እግሩ ሳር ለብሶ በማይታይ ጉድጉዋድ ላይ ቆሞ እስከ ጉልበቱ ጠለቀና ወደ ፊት ደፋ ሲል፣ እኔ ተወርውሬ ከፊቱ ወደቅሁ፡፡ እንዲያ እንደወደቅሁ ዘወር ብዬ ከሁዋላየ ግራጭ ሲፈራገጥ ዓይቼ፣ በላየ ላይ እንዳይወድቅብኝ ፈርቼ ነበር፡፡ ነገር ግን እሱ እንደምንም እየተስገመገመ እግሩን ከገባበት ጉድጉዋድ  አውጥቶ፣ እኔን አልፎ ከሄደ በሁዋላ፣ የተጎዳ ጉልበቴን እያሻሸሁ በወደቅሁበት እንደተቀመጥሁ፣ ግራጭ ከሄደበት ተመልሶ መጥቶ ሲያሸተኝ ቆየና ባጠገቤ ቆመ፡፡ ተመሳሳይ ድርጊት ከዚያን ዕለት በፊትም ፈጽሞ እንደነበር ሰምቼ ነበር” አሉ፡፡

“ዳምጠው” የብሩ አገልጋይ

ደጃች ብሩ ለካሳ ኃይሉ (በሁዋላ አፄ ቴዎድሮስ) አልገበርም ብሎ፣ ካሳ ኃይሉ እሱን በሚያባርርበት ወቅት፣ ደጃች ብሩ ሶማ አምባ ላይ መሽጎ ነበር (ዓባይ ቆላ አጠገብ ብቸና አካባቢ)፡፡ ካሳ ኃይሉ፣ ታች ሆኖ የሶማን አምባ አሻቅቦ እየተመለከተ፣ ለደጃች ብሩ አንድ መልዕክት ልኮ ነበር ይባላል፡፡ የደጃች ብሩን የፈረስ ስም “ዳምጠውን” ተመኝቶት “የፈረስዎን ስም  ለእኔ ይስጡኝ፣ አልያ ለኔ ፈረስ ስም ያውጡለት” ብሎ ለደጃች ብሩ መልዕክት ልኮ ነበር ይባላል፡፡ ብሩም “የእኔን ፈረስ የዳምጠውን ስም ላንተ አልሰጥም፣ ያንተን ፈረስ ተንጓለል በለው” ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡

ብሩ ጎሹና ካሳ ኃይሉ በአንድ ላይ ደጃች ጎሹ ቤት ይኖሩ ነበር፣ ብሩ አባቱ ቤት፣ ካሳ ኃይሉ  ጥገኛ ሆኖ፡፡ ከአሳዳሪያቸው ከደጃች ጎሹ ቅርበት ሲታይ የበላይ እና የበታች ሆነው ነበር የሚኖሩ፡፡ ያ ስለነበረ ነበር ካሳ ኃይሉ ብሩን አንቱ ብሎ ሲጠራ፣ ብሩ ካሳን አንተ ብሎ የሚመልስለት፡፡

በዘመነ መሳፍንት መቁዋጫ የአካባቢው ዝነኛ ፈረስ የደጃች ብሩ ጎሹ ፈረስ “ዳምጠው” ነበር፡፡ ደጃች ብሩ ለወዳጁ ለሚካኤል አባዲ ስለ “ዳምጠው” ጉብዝና ብሎም አሟሟት ብዙ አውግቶት ነበር፣ ከወጉ የተቀነጨበ እነሆ፡፡ “ጠላቶቻችን በፈረስ እያባረሩን ሳለ፣ አንድ የተወረወረ ጦር ጭኔን ጠበሰቀኝ፣ ሌላው ፈረሴን ዳምጠውን ጭራው መጋጠሚያ ላይ ወጋው፡፡…….ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዳምጠው ደከም ማለቱ ተሰማኝና፣ እሱን ለጥቅስ መርዕድ (የጦር አዝማች) ሰጥቼ.፣ እኔ የሱን ፈረስ ተቀመጥኩ፡፡…ጥቅስ መርዕድ እንደ አንበሳ ተዋጋ፣ ግን ዳምጠው ከራሱ ላይ ተመትቶ ቆሰለበት”፡፡.

“…. ዓባይን ተሻግረን አገራችን ጎጃም ከገባን በኋላ፣ ታማኙ ፈረሴ መሄድ እምቢ አለ፡፡ ትንሽ ቆየና ሞተ፡፡ ከመሞቱ በፊት.አንገቱን ቀና አደረገና በአፍንጫው አየሩን አፈሰው፡፡ ከዚያ መላ ሰውነቱ ተንዘፈዘፈና ዘፍ ብሎ በጎኑ ወደቀ፡፡ ያንን የሚያምር አንገቱን አሸዋው ላይ ዘፍ አደረገና እህህህህሀ አለ በረዥሙ፡፡ እንደዚያ እጥፍ ዘርጋ ይሉ የነበሩ ቅልጥሞቹ፣ ድርቅ አሉ፡፡ ወታደሮቼ እያለቀሱ ዙሪያውን ከበው ቆሙ፡፡ እኔማ አንጀቴ ሲላወስ ይሰማኛል፡፡ ወይኔ ብሩ እስከወዲያኛ እሱን የመሰለ ፈረስ የማገኝ አይመስለኝም፡፡ … ነጠላዬን አልብሼ ልቀብረው ፈለግሁ፣ ሰዎቼ ግን ተው አሉኝና አዚያው እወደቀበት ቦታ አሳረፍነው” ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡

ከዚያም ደጃች ብሩ ቀጠል አድርጎ “… በሰይፋችን፣ በሾተል እና ጦር ጫር ጫር አድርገን የቀበርንበት ቦታ በዓይኔ ውል ብሎ ይታየኛል፡፡ የዱር አራዊት እንዳይቀራመቱት ብለን የቻልነውን ያህል አፈር እና ድንጋይ ከቆለልነበት በኋላ ሄድን፡፡ … ዳምጠው ያረፈበት ቦታ ቱል ከሚባል ዓባይ ገባር የሆነ ወንዝ አጠገብ ነው፡፡ ያም አካባቢ አንበሳ፣ ጎሽና ዝሆን ብቻ የሚረመሰመስበት አካባቢ ነው” አለ ደጃች ብሩ፡፡

ደጃች ብሩ ትንሽ ሲተክዝ ቆይቶ ወጉን ቀጠለ “.. ምሽት ላይ ካረፍንበት መንደር ያገኘናቸውን ባላገሮች፣ ወንዙ በክረምት ሞልቶ ዳምጠውን የቀበርንበትን ቦታ እንዳይጠራርገው፤ ወንዙ ለክረምት የተሠራለትን ግድብ በደምብ እንዲያጠናክሩ፣ ከዚያም አራት ጦሮች በመቃብሩ በዙሪያ እንዲተክሉ አዘዝኳቸው”፡፡  ደጃች ብሩ ዙሪያውን ከቃኜ በኋላ ወጉን ቀጠል አድርጎ፣ “… መቼም ሚካኤል ትረዳኛለህ፣ ልክ ዘመድ ሲሞትብኝ እንደማደርገው ሁሉ፣ ጡሩምባ እየተነፋ፣ ታምቡር እየተመታ፣  ቄሶች እንደ ፍትሃት እየወረቡ ዳምጠው ቢቀበር ደስ ይለኝ ነበር፡፡… ነጋሪት ቢጎሰምለት፣ አልቃሽ ቆሞ ቢያለቅስለት በተደሰትኩ ነበር፡፡ እኔ ብሩ ለዳምጠው ቀብር መልስ ግብር ባበላለትስ ኖሮ፣ በሱ ስምስ ግብር ለማብላት ምን ይጎድለዋል”፡፡  ሚካኤል አለ ደጃች ብሩ፣ “ከቱሉ ወንዝ ዳርቻ ዳምጠው ደክሞት ሲቆም፣ ብታየው ታዝን ነበር፡፡ ጆሮዎቹ ቅልስ ብለው ወደ ጋማው ተኝተዋል፡፡ አፍንጫውና ከንፈሮቹ ጭምድድ ብለው፣ ዓይኖቹ ደፍርሰው፣ ጋማው ተዝለፍልፎ፣ አንገቱን ደፍቶ ነበር የቆመው ” አለ ብሩ፡፡

“… በየጦር ሜዳው ያለ ከፈን ተዘርረው እንደቀሩት እንደምወዳቸው ብዙ ጓደኞቼ  ዳምጠውንም ሜዳ ላይ ጥለነው ሄድን፡፡ … አሁን ድረሰ ማጅራቱ ላይ የሚዘናፈለው ጋማውን፣ ስንቱ ቦታ አብረውኝ የሮጡትን እግሮቹን (ሚካኤል ክንፍ እንጅ እግር አትበላቸው) ሳስብ አዝናለሁ” አለ ደጃች ብሩ ስለፈረሱ ሞት ለወዳጁ ለሚካኤል አባዲ ሲያወጋ፡፡

ከዚያም ቀጠል አድርጎ፣ “… አፍ ቢኖረው ዳምጠው የሚናገረውን አውቃለሁ፡፡ ‹እኔ ዳምጠው ወታደር ነኝ፣ ወታደር ሆኜ በጦር ሜዳ ተገኝቼ እንደ አውሎ ነፋስ እየበረርኩ ጎራውን ዞሬ ጌቶችን አድርሻለሁ፡፡ ግንባራችን ታጥፎ ብንመለስ ጌታዬን ሽምጥ እየጋለብሁ ከእሳት አውጥቻለሁ፡፡  ጠላት ሲያባርረን ብንቆስልም ጌታዬን ብሩን ይዜ በርሬያለሁ፡፡ ጠላትም ራሴን አግኝቶ አይደሰትም፡፡ ሞትን በሩጫ ቀድሜው ይኽው እዚህ ደርሻለሁ፡፡ አሁን ባገሬ መሬት ደክሞኝ ቆሜ ሞትን እጠብቀዋለሁ› ነበር የሚል፤›› አለ፣ ደጃች ብሩ፡፡

ሰጋሩ ግራጭ በመተማ ቆላ ጫካ ውስጥ፣ ጅብ ሲቀራመተው፣ ዝነኛው ዳምጠው ግን በክብር ተቀበረ፣ ለጦረኝነቱ ምልክትም አራት ታሪካዊ ጦሮች በመቃብሩ አራቱ ማእዘን ላይ እንዲተከሉ ተደረገ፡፡ ይህን ይመስላል የጋማ ከብቶች ዕጣ ፈንታ፡፡

ከአዘጋጁ፡-ሐፊው  ሽብሩ  ተድላ  (ፒኤችዲ)  የአዲስ  አበባ  ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ኢመረተስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን አሳትመዋል፡፡ ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል ማኅበራዊና ሰብዓዊ (ሶሺያል ኤንድ ሂዩማኒስት) ጉዳዮችን  በጥልቀት ያቀረቡበት  ከጉሬዛም ማርያም እስከ  አዲስ አበባ  የሕይወት ጉዞ እና ትዝታዬ፣ የህያው ፈለግ፣ ከየት ወደ የት፣ ወረርሽኝ ይገኙበታል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው shibrut@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles