Monday, April 15, 2024

ያልተቋጩ የድንበር ውዝግቦችና የሉዓላዊነት ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የተለየ ፖለቲካዊ ድባብና የአንድነት ስሜት በኢትዮጵያ የተፈጠረበት እንደነበር በርካቶች ያስታውሳሉ፡፡ በ‹‹አሸው አንበሳው››፣ ‹‹በልበለው ጀግናዬ በለው››፣ ‹‹አፋር አለበሎ››፣ ወዘተ በሚሉ ሙዚቃዎች ታጅበው የሚቀርቡ የግዛው ዳኜ ሰበር ዜናዎችን ዛሬም በርካቶች ያስታውሷቸዋል፡፡ የባድመ ግንባር ድል፣ የእገላ ምሽግ መሰበር፣ የዛላምበሳ ግንባር ገድል፣ ከየግንባሩ ይሰሙ የነበሩ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ድሎች በመላው ኢትዮጵያ ሕዝቡ በየአደባባዩ እየወጣ በአገር ፍቅር ስሜት የሚጨፍርባቸው ዘገባዎች ነበሩ፡፡

ለጦሩ ከየክልሎች የሚያስደንቅ ድጋፍ ሲቀርብ የታየበት የጦርነት ወቅት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት የቆመችበት ወቅት እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በአደገኛ ቦዘኔነት ወንጀል ስም ሲሳደድ የቆየው ከየከተማው የዘመተ ወጣት በየግንባሩ ታላቅ መስዋዕትነት ከፍሎ አገር ያኮራበት ነበር ይባላል፡፡ በድሉ ማግሥት በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በጦርነቱ የተሰው ጀግኖች በተሸለሙበት ወቅት በጦርነቱ ‹‹እኔ ፈንጂው ላይ ልንከባለል እናንተ ተራምዳችሁ አገሬን ከወራሪ ኃይል ነፃ አውጡ፤›› ብለው ለጓዶቻቸው ቀድመው የሚሰው ጀግኖችን ማዋለዱ፣ በጉልህ ሲነገር መሰማቱን ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡

ይህ ሁሉ መስዋዕትነትና የአገር ፍቅር ስሜት ይንፀባረቅ የነበረው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ በኤርትራ ድንበሯ ተወረረ የግፍ ጥቃትም ተፈጸመባት በሚል ቅስቀሳ ነበር ሁሉም አገሩን ለማዳን በጋራ የተመመው፡፡ ይህ መስዋዕትነት ተከፍሎ የተገኘው ወታደራዊ ድል ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክ በመድገም ድሉን በዘለቄታው አገሪቱ እንደምታረጋግጥ የተጠራጠረ ብዙም አልነበረም፡፡

የአልጀርስ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ የአጨቃጫቂ ድንበሮች ጉዳይ ይግባኝ በሌለው በኔዘርላንዱ የሄግ ፍርድ ቤት እንዲዳኝ ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር አካል የሆኑ መሬቶች ለኤርትራ ተላልፈው ተሰጥተዋል የሚለው ወሬ ቀድሞ በበርካቶች ዘንድ ቢሰማም፣ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን (አምባሳደር) በሄጉ ውሳኔ ለኢትዮጵያ ድል መገኘቱን የሚያበስር መግለጫ ተሰጠ፡፡ ይህ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ከተፈጠረው ቅሬታ እኩል ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የድጋፍ ደስታ ለመግለጽ አደባባይ ወጥተው የታየበትን አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር፡፡

የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በስተኋላ በፓርላማ ቀርበው ‹‹ከበጣም መጥፎ መጥፎን መቀበል›› የሚል ገለጻን ስለድንበሩ ጉዳይ እስኪሰጡ ጊዜ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ድንበር አካል የሆኑ መሬቶች ለኤርትራ ተሰጥተዋል የሚለውን ጉዳይ መንግሥት በከፊል እንኳ ለማመን ፈቃደኝነት አጥቶ መቆየቱ ይነገራል፡፡ የድንበር ማካለል ኮሚሽን ተቋቁሞ በአካባቢው ‹‹UNMEE›› (United Nation Mission in Ethiopia and Eritrea) የተባለ ሰላም ማስከበር ኃይል እንዲሰፍር ተደረገ፡፡ ለስምንት ዓመታት የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ቆየ፡፡ ሆኖም የድንበር ማካለሉ (መሬት ላይ ችካል መቸከሉና ወሰን ማስመሩ) በተግባር ሳይተረጎም ቀረ፡፡

በ1969 ዓ.ም. ሕወሓት ትግል ላይ በነበረ ጊዜ ጀበሀ የተባለው የኤርትራ ሸማቂ ቡድን ባድመን ተቆጣጥሮ እንደነበር፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የሕወሓት ታጋይ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት የዛሬ አራት ዓመት ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹እኛ በጊዜው ትንሽ ስንሆን ጀበሀ ግን ትልቅ ኃይል ነበረው፡፡ ጉዳዩን ለማጤን እኔ አንድ ልዑክ ይዤ ወደ እነሱ ተላኩኝ፡፡ ከባድመ እንዲወጡም ጠየቅን፡፡ የኤርትራ ነው ብለው ሞገቱ፡፡ ተስማምተን ቦታው በነበረበት አስተዳደር ወሰን እንዲቀጥል ወሰንን፡፡ በዚህም አካባቢው ብዙ ኤርትራዊ ቢኖርበትም፣ በትግራይ አስተዳደር ወሰን ሥር መሆኑ ስለተረጋገጠ ጀበሀዎቹ ለቀው ወጡ፤›› ሲሉ ታሪክ አጣቅሰው ሁለቱን አገሮች ወደ ጦርነት ስለከተተው መሬት ተርከዋል፡፡

ሜጀር ጄኔራል አበበ እንደተናገሩት ከትግል በኋላም ቢሆን የአጨቃጫቂ መሬቶች ጉዳይን በጋራ ኮሚቴ በሰላም ለመፍታት ተከታታይ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኤርትራ መንግሥት በሒደት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለራሱ ጥቅም ለማዋል መጣጣር በመጀመሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግንኙነታችን መርህ የተከተለ ይሁን ብሎ እንደተቃወመ ያወሳሉ፡፡ ‹‹ይህን ጊዜ በሰላም ተይዞ የቆየውን የድንበር ጉዳይ በወረራ ለማስፈጸም ተነሳ፤›› በማለት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት አነሳስን ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነቱ ትልቅ ድል እንዳስመዘገበች የሚናገሩት ሜጀር ጄኔራል አበበ፣ ሆኖም በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ከአገራቸው ይልቅ የኤርትራን ጥቅም የሚያስቀድሙ አመራሮች በመብዛታቸው፣ በአልጀርሱ ስምምነት መዘዝ ኢትዮጵያ ተጎጂ እንደሆነች ተናግረዋል፡፡

የሕወሓት መሥራችና አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ አሥራት በበኩላቸው፣ ከኤርትራ ጋር ኢትዮጵያ ገጥማው የነበረውን የድንበር ውዝግብን አፈታት ሒደት ‹‹ከመጠን በላይ ተንበርካኪነት የተንፀባረቀበት ፖሊሲን የተከተለ›› እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከሦስት ወር በፊት በአንድ ሚዲያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበር ውዝግብ አፈታት በተለይ በአልጀርስ ስምምነት የተፈጸመው ስህተት ኢትዮጵያን እስከ ዛሬም የሚከተል ችግር ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

‹‹የኤርትራ ሉዓላዊነት ከተነካ ለእነሱ ቆመን እንዋጋለን የሚሉ እንደ አቶ ስብሀት ነጋና መለስ ዜናዊ ያሉ፣ ከአገራቸው ጥቅም ይልቅ ለኤርትራ የወገኑ አመራሮች ናቸው የተሳሳተውን ዓለም አቀፍ የድንበር ውሳኔ የተቀበሉት፤›› ብለዋል፡፡ በአቶ ገብሩ እምነት ሕወሓት አሁንም ቢሆን አንዳንድ አመራሮቹ እንዲህ ካለው ለኤርትራ ያጋደለ አመለካከት አልጠሩም፡፡

በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጦርነቱን በግንባር ከመሩ አዛዦች አንዱ የነበሩትና አሁን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል አመራር የሆኑት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ የፆረናን ምሽግ ሰብረን እንደ ተሰነይ ያሉ የኤርትራ ግዛቶችን እየተቆጣጠርን ወደ ደጋው ለመሻገር ስንቃረብ ጦርነት መቀጠል የማንችልበት ሁኔታ ተፈጠረ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ የዛሬ አራት ዓመት ከአንድ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹ኤርትራ ትግራይ ላይ ዳግም ጥቃት ትከፍታለች ብዬ አላስብም፣ ብትከፍትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝም ይላል ብዬ አላስብም፤›› በማለት ነበር በሁለቱ አገሮች መካከል ዕልባት ሳያገኝ ስለቀጠለው ጉርብትና ግምገማቸውን ያቀረቡት፡፡

ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ይህን ቢሉም እንደ ቀድሞ አጋሮቻቸው ሜጀር ጄኔራል አበበ እንዲሁም አቶ ገብሩ ሁሉ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ይገባኛል ጉዳይ ከአልጀርስ ስምምነትና ከሄግ ፍርድ ቤት ያልተሳካ አያያዝ ጋር በተገናኘ ውስብስብ ችግር ውስጥ መግባቱን ተናግረው ነበር፡፡

የቀድሞ ባለሥልጣናት ይህን ቢሉም ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ከኤርትራ ጋር የተፈረመውና ለ16 ዓመታት ሳይተገበር የቆየውን የድንበር ስምምነት እንደሚቀበለው አስታውቋል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ውሳኔው፣ ‹‹በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም የተሳሰሩትን ለሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሠራ መሆኑን ለመግለጽ ይፈልጋል፤›› ሲል ነበር በይፋ ያስታወቀው፡፡

ኢሕአዴግ ከዚያ ቀደም በቅድመ ሁኔታ ተቀብዬዋለሁ ሲለው የቆየውን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ ተቀበልኩት ማለቱ በጊዜው ትልቅ ገረሜታ ፈጥሮ ነበር፡፡ አሁን ያለው መንግሥትም ይህን መሠረት በማድረግ ከኤርትራ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የድንበር ውዝግብ እንደሚፈታ ደጋግሞ አስታውቋል፡፡ ይህ ጉዳይ ግን በበርካታ ልሂቃን ዘንድ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከትግራይ ክልል የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ የትግራይ ክልል አካል የሆኑ መሬቶችን ይዟል የሚለው ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር፡፡

ለዚህ መልስ የሰጡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከፌዴራልና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተውጣጣ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኮሚቴው ቦታዎቹን ሄዶ እንዲመለከት ታዟል፡፡ ከአልጀርሱ ስምምነት ውጪ በሆነ መንገድ የተያዙ መሬቶች ካሉ ሪፖርቱ ሲመጣ በጋራ የምናይ ይሆናል፡፡ ማንም የማንንም ቦታ በኃይል ይዞ ለዘለዓለም መኖር አይችልም፡፡ ዳግም እንዳንዋጋ፣ ዳግም ግጭት እንዳይፈጠር ትርፍ ነገር የተኬደ ካለ አይተን ቦታውን ለይተን በንግግር መልክ ለማበጀት እንችላለን፤›› በማለት ነበር የተነሳውን ጥያቄ በተቋቋመ አጣሪ ኮሚቴ መልስ ለመስጠት ሥራ መጀመሩን ያስታወቁት፡፡

ከኤርትራ ጋር ብቻ ሳይሆን የድንበር ውዝግብ ከሱዳን ጋር በተገናኘም በቅርብ ዓመታት ሲነሳ ነው የቆየው፡፡ የትግራይ ጦርነት እንደተጀመረ ሱዳን አጋጣሚውን ተገን በማድረግ ድንበር ተሻግራ አልፋሽቃ የተባለውን ለም የእርሻ መሬት የሚገኝበትን አካባቢ ተቆጣጥራለች መባሉ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሲፈጥር የቆየ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ለረጅም ዓመታት በጋራ የድንበር ኮሚቴ ሲሸመገል የቆየው የኢትዮ ሱዳን ድንበር ውዝግብ ዘላቂ መፍትሔ አልተሰጠውም፡፡ በአካባቢው በየጊዜው የሚፈጠረው መለስተኛ ግጭትና የመሬት ወረራ አንዱ ከሌላው ጋር የሚወነጃጀልበት ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን ዓመታዊ ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ሱዳን በኃይል የያዘችውን የኢትዮጵያ መሬት ለቃ እንድትወታ አሳስበው ነበር፡፡ ‹‹ሱዳን በኃይል የያዘችውን መሬት በማንኛውም መመዘኛ የኢትዮጵያ ግዛት በመሆኑ ይመለሳል፤›› ሲሉ ቃል ገብተውም ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በሱዳን ተወሯል የሚባለው የኢትዮጵያ መሬት ጉዳይ እስካሁንም በተጨባጭ ስለመመለሱ ከመንግሥት ወገን ማረጋገጫ ሲሰጥ አልታየም፡፡

ከአንድ ወር ቀደም ብሎ የታተመው ‹‹ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿ፣ የትብብርና የውዝግብ አዙሪት›› በሚል ርዕስ የቀረበው መጽሐፍ፣ ኢትዮጵያና በዙሪያዋ ካሉ አገሮች ጋር ያላትን በመልካምነትና በመጥፎነት የሚጠቀስ ጉርብትና በሰፊው ፈትሾታል፡፡ በታዋዊው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ምሁር በለጠ በላቸው (ዶ/ር) የቀረበው ይህ መጽሐፍ ከኤርትራ ጀምሮ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከጂቡቲ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሌላንድ ጋር ኢትዮጵያ ያላትን የቅርብና የሩቅ ወዳጅነትና የድንበር ክርክር በተናጠል ለማቅረብ ይሞክራል፡፡

ከሱዳን ጋር (ደቡብና ሰሜን ሱዳን አንድ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን) ኢትዮጵያ ያላትን የድንበር ውዝግብ በተመለከተ ባሰፈሩበት ግርጌ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የነበራት ግንኙነት በአመዛኙ በድንበር ውዝግቦች ተፅዕኖ ሲወሰን መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከ2011 ዓ.ም. በኋላ የጋራ ድንበሩን ጉዳይ በተመለከተ በሱዳን በኩል ተጋፊነት የሚታይባቸው ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያን አንፃራዊ መዳከም በማስተዋል የቀደሙ መግባባቶችን በጣሰ ሁኔታ በመሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ (Status Quo) የመቀየር አዝማሚያ ይታያል፤›› ሲሉ ባለሙያው ጽፈዋል፡፡

ለዚህ የሱዳኖች አዝማሚያ ኢትዮጵያ የሰጠቻቸውን ምላሾች ሲያነሱ ደግሞ ከቀደመው ጊዜ አካሄዶቿ ያልተለየ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከብሔራዊ ስሜት ባሻገር ከሱዳን ጋር ስላለው የጋራ ድንበር ውዝግብ በቂ ግንዛቤ የለም፡፡ ሕጋዊ ካርታዎች ሳይቀሩ የሚያመላክቱት የሻለቃ ግዌይን መስመር መሆኑ እምብዛም ሲያስጨንቅ አይስተዋልም፡፡ ይልቁንም ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር በግለሰቦችና በቡድኖች ከተያዘው የእርሻ ይዞታ ጋር ሲቆራኝ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ይህ ችግር ከኤርትራ ጋር ያለው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ከተስተናገደበት መንገድ እምብዛም አይለይም፤›› በማለት ነበር የሱዳንን ድንበር ውዝግብ አብነት በማድረግ ተመሳሳይ የድንበር ችግሮችን ለመግለጽ የሞከሩት፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ ጋር ብቻ ሳይሆን ብዙም ከማትወዛገባት ከኬንያም ጋር ቢሆን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ያላት አገር ስለመሆኑ በበርካታ ምሁራን ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ኢለሚ ትሪያንግል በሚባለው ቦታ ኬንያና ኢትዮጵያ ገና ያልፈቱት የድንበር ጥያቄ እንዳለ ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያ የተለዋወጡ መንግሥታት አገሪቱ በዙሪያዋ ካሉ ጎረቤት አገሮች ጋር የሚያወዛግቧት የድንበር መሬቶችን በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት ሲፈተኑ መቆየታቸው በጉልህ ይወሳል፡፡ የውስጥ መዳከምና ወጥነት ያለው በመርህ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ መከተል አለመቻል፣ ችግሮቹ በቅብብሎሽ ዘመናትን አልፈው ወደዛሬ እንዲሻገሩ ማድረጉ በትልቅ ችግርነት ይገለጻል፡፡

‹‹በአፍሪካ አርቲፊሻል ድንበር ነው ያለው፡፡ ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩት አርቲፊሻል ድንበር እንጂ የከለለው መላው ምሥራቅ አፍሪካ አንድ መሆን የሚችል ክፍለ አኅጉር ነው፤›› የሚል ዝንባሌ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የነበረው የአሁኑ መንግሥት በተከታታይ ከኤርትራ፣ እንዲሁም ከሱዳን ድንበር በኩል የገጠሙት ችግሮች ሐሳቡን ሳያስቀይሩት እንደማይቀር ነው በብዙዎች የሚገመተው፡፡ አሁን ያለው መንግሥት በቅብብሎሽ የወረሳቸውንና አገሪቱን ለተደጋጋሚ ቀውስ ሲያጋልጡ የቆዩ የድንበርና የሉዓላዊነት ችግሮችን በምን መንገድ ነው በዘላቂነት እልባት የሚሰጠው የሚለው ጥያቄ ግን የሚቀጥል ይመስላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -