Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከዕቅዱ አስቀድሞ መመሥረቻ ካፒታሉን ማሰባሰብ የቻለው የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበር

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበርን ለማቋቋም ከተካሄዱ የአክሲዮን ሽያጮች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማግኘቱ (መሰብሰብ መቻሉ) ተጠቆመ፡፡

የኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ ከመዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ የ30 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ግዥ ለመፈጸም የሚያስችለውን ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ማረጋገጥ እንደተቻለው፣ እስካሁን በተካሄደው የአክሲዮኖች ሽያጭ ኩባንያውን ለማቋቋም ያስፈልጋል ከተባለው ገንዘብ በላይ ካፒታል መሰብሰብ መቻሉ ታውቋል፡፡ የኩባንያው መመሥረቻ ካፒታል እስከ 1.2 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ እ.ኤ.አ. ማርች 29 ቀን 2024 ኩባንያው የአክሲዮን ሽያጩን የሚዘጋ ሲሆን፣ ቀነ ገደቡ ከመድረሱ በፊት ከሚፈለገው በላይ ካፒታል መሰብሰብ መቻሉን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን ኢስማኤል (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ የ30 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ግዥ የፈጸመውን ኅብረት ኢንሹራንስ ጨምሮ እስካሁን ከ30 በላይ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች የቢዝነስ ድርጅቶች የኩባንያው ባለቤት ለመሆን የሚያስችላቸውን የተለያየ መጠን ያላቸው አክሲዮን ግዥዎች ፈጽመዋል፡፡

እንደ ጥላሁን (ዶ/ር) ገለጻ፣ በአሁኑ የመዋዕለ ንዋይ ገበያ የአክሲዮን ማኅበር በዋናነት ባለአክሲዮን እንዲሆኑ የሚፈለጉት የፋይናንስ ተቋማት በመሆናቻው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተሳትፏቸው እየጨመረ ተቋማት የአክሲዮን ግዥዎች እየፈጸሙ ነውም ተብሏል፡፡

ይህም አክሲዮን ኩባንያው በፋይናንስ ተቋማት መሸፈን አለበት ተብሎ በዕቅድ ተይዞ የነበረውን መጠን ያህል የአክሲዮን ግዥ ፈጽመዋል ማለት እንደሚቻልም ጠቅሰዋል፡፡ የአክሲዮን ሽያጩ ሊጠናቀቅ ከአራት ቀን ያልበለጠ ጊዜ ብቻ የቀረው ቢሆንም፣ እስካሁን ካፒታል በማሰባሰብ ረገድ የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን የኩባንያውን ምሥረታ በቶሎ ዕውን ለማድረግ ያስችላል፡፡

በአክሲዮን ኩባንያው ዕቅድ መሠረት ከሚያስፈልገው የመመሥረቻ ካፒታል 25 በመቶው በመንግሥት የሚሸፈን ሲሆን፣ 50 በመቶው ደግሞ በፋይናንስ ተቋማት መሸፈን እንዳለበት ታሳቢ ተደርጎ ሲሠራ እንደነበር ታውቋል፡፡ ቀሪው ድርሻ በሌሎች የቢዝነስ ተቋማትና የውጭ የኩባንያዎች ሊይዙት ይችላል ተብሎ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡

በመንግሥት፣ በፋይናንስ ተቋማትና በሌሎች የቢዝነስ ድርጅቶች መያዝ አለበት ተብሎ በተያዘው የባለቤትነት ድርሻ መጠን ልክ አክሲዮኖች መሸጣቸውን የጠቆሙት ጥላሁን (ዶ/ር)፣ የውጭ ኩባንያዎችን የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ግን ለጊዜው ሊሳኩ አለመቻላቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

የአክሲዮኑ ሽያጭ አስከሚጠናቀቅበት ዕለት ድረስ ግን የውጭ ኩባንያዎች የሚጠበቁ ሲሆን፣ እነርሱ መጡም አልመጡም አሁን በተሰባሰበው ካፒታል፣ አክሲዮኖችን በገዙት ኩባንያዎች መሥራች አባልነት የኩባንያው ምሥረታ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እስካሁን በዚህ ኩባንያ ውስጥ አክሲዮን እየገዙ ያሉት በአብላጫው ባንኮች ሲሆኑ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም በአክሲዮን ግዥ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ኅብረት ኢንሹራንስ የ30 ሚሊዮን ብር አክሲዮን በመግዛት ቀዳሚ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ከኅብረት ኢንሹራንስ ሌላ ዘመን ኢንሹራንስ የ20 ሚሊዮን ብር አክሲዮን መግዛቱ ታውቋል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ ከካፒታል ገበያ መፈጠር ጋር በተያያዘ የተለየ ታሪክ እንዳለው የጠቀሱት የኅብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሠረት በዛብህ፣ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲፈጠር ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ፣ በኢንሹራንስ ኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ያለማቋረጥ የካፒታል ገበያ መፈጠር አለበት የሚለው ሐሳብ ሲያካትቱ መቆየታቸውን በአስረጂነት ገልጸዋል፡፡

የካፒታል ገበያ መፈጠር አስፈላጊነት የሚገልጸውን መልዕክት ከኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ እንዲወጣ የተደረገው፣ የካፒታል ገበያ ሕግ መውጣቱ እንደተረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ፣ ኩባንያቸው ለካፒታል ገበያ መፈጠር ሲያደርግ የነበረውን ግፊት አስረድተዋል፡፡ በዕለቱ ከመዋዕለ ንዋይ ገበያ ኩባንያ ላይ አክሲዮን የገዙት በአጠቃላይ በአገር ደረጃ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ እንደሆነ ወ/ሮ መሠረት አብራርተዋል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ በዕለቱ አክሲዮን ግዥ ስምምነት ፊርማው ይካሄድ እንጂ የአክሲዮን ግዥውን ለመፈጸም ውሳኔ ያሳለፈው ቀደም ብሎ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ከኢንሹራንስ አገልግሎት ባሻገር በአዋጭ ኢንቨስትመንት ላይ የመሰማራት የዳበረ ልምድ ያለው ኩባንያ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበር ላይ የመሥራች ባለአክሲዮንነት ድርሻን ለመግዛት በጥናት ላይ በመመርኮዝ ወስኗል›› ያሉት ወ/ሮ መሠረት፣ ኅብረት ኢንሹራንስ ከማንኛውም የኢንዱስትሪ ባለድርሻ በላይ በግንባር ቀደምትነት ሲሠራበት ነበር ብለዋል፡፡ ለዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የመዋዕለ ንዋይ ገበያ እንዲቋቋም በተገኘው መድረክ ሁሉ ሐሳብ ከማቅረብ ባሻገር፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሕግ አርቃቂ አካላት የማማከር (አድቮኬሲ) ሥራ በመሥራት ሲታገል መቆየቱንም ያወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ይኼው ጥረታቸው ዕውን ሆኖ በማየታቸውና የዚህ ታሪክ አካልና መሥራች ባለድርሻ በመሆናችው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው ‹‹ታሪካዊነትንና ዘመናዊነትን አጣምሮ በያዘው ኩባንያችን ላይ ኅብረት ኢንሹራንስ የመሥራችነት ድርሻን መያዙ እጅግ ያስደሰተን ሲሆን፣ የኅብረት ውሳኔ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ የተወሰነ ውሳኔ አድርገን እንወስደዋለን›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበር ኩባንያ ዙሪያ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያም እስካሁን አክሲዮን በገዙ ኩባንያዎች የሰበሰበው አክሲዮን መጠን ልክ ምሥረታውን ቢያደርግም፣ ከምሥረታው በኋላም ያልተካተቱ የፋይናንስ ተቋማት ባለአክሲዮን የሚሆኑበት ዕድል እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ኩባንያው ለሚያስፈልገው ሥራ በቂ የሆነ ካፒታል መሰብሰብ መቻሉን የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከምሥረታው በፊት እየተካሄዱ ያሉ ዝግጅቶችም ኩባንያውን በቶሎ ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችለው ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የሠራተኞች ቅጥርና ለሥራው የሚያስፈልገው ቴክኖሎጂ ግዥዎች እየተፈጸሙና የቢሮ ማደራጀት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ጥላሁን (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

አዲሱ ቢሮውም የቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሕንፃ ሲሆን፣ ምናልባትም በቀጣይ ሳምንት በዚህ ሕንፃ ውስጥ ተዛውሮ ሥራውን የሚጀምር ስለመሆኑ ከጥላሁን (ዶ/ር) ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከካፒታል ገበያ መፈጠር ጋር በተያያዘ ወ/ሮ መሠረት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ ‹‹የካፒታል ገበያ በጣም ስንጠብቀውና ስንፈልገው የነበረ ስለነበር በጣም ደስ ብሎናል›› ያሉት በተለይ የካፒታል ገበያ ሥራ ላይ ወሳኝ ጉዳይ የአይቲ ሲስተም በመሆኑ እዚህ አካባቢ ችግር እንዳይኖር ጠንክሮ መሥራት የሚጠይቅ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ገበያው አዲስ ከመሆኑ አንፃር የሰው ኃይል ላይ በጣም ሰፊ ክፍተት ስላለ፣ በዚህ ላይም የመዋዕለ ነዋይ ገበያ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ኩባንያው አሳካዋለሁ ብሎ የተነሳውን ዕቅድ ያሳካል የሚለውን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በዕለቱ ከኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አክሲዮን በመግዛት ተጠቃሽ የሆነው ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር፣ የመድን ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል ቀዳሚ ከሆኑት የግል የመድን ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ከ29 ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን በ2016 የሒሳብ ዓመት አጋማሽ የኩባንየው አጠቃላይ የሀብት መጠኑ አራት ቢሊዮን ብር የተሻገረ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የተከፈለ ካፒታል መጠኑንም 1.1 ቢሊዮን ብር በላይ በማድረሱ በኢንሹራንስ ዘርፍ የተከፈለ ካፒታላቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካደረሱ ሦስት ኩባንያዎች መካከል አንዱ ለመሆን አስችሎታል፡፡

ኅብረት ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት ከግብር በፊት 391 ሚሊዮን ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ በኅብረት ባንክ፣ በኢትዮጵያ የጠለፋ ዋስትና ድርጅት፣ እንዲሁም በተለያዩ ትርፋማ በሆኑ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያለው መሆኑም ታውቋል፡፡ ኩባንያው በጠቅላላው 68 ቅርንጫፎችና አገናኝ ቢሮዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች አሉት፡፡

በቅርቡ ይፋዊ ምሥረታውን ያደርግል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ አክሲዮን ማኅበር፣ በካፒታል ገበያ ድንጋጌ አንቀጽ 31 (ቁጥር 1248/2021) መሠረት በግልና መንግሥታዊ ሽርክና ፈቃዱን ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በማግኘት የተመሠረተ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው የሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ግብይትን የሚያካሂድና የራሱ ተቆጣጣሪ አካል የሆነ በማዕከላዊነትም ግብይትን ለማሳለጥ እንዲሁም ከአክሲዮን፣ ከቋሚ ገቢና የገንዘብ ግብይት ጋር በተያያዘ በተሳለጠ መንገድ አገልግሎት ለመስጠት የሚሠራ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች