Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ቡድን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የደረሰውን ጉዳት መመርመር ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የደረሰው ችግር የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን ኢንሳ አስታውቋል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሞኑን ገጥሞት በነበረውን ችግር ተንተርሶ የተፈጸመው ምዝበራ ላይ ጥልቅ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፣ በምዝበራው የተሳተፉ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ግፊት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡ 

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ባንኩ ያጋጠመውን ችግር መነሻው ምንም ይሁን ምን በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ የሚያስፈልግ መሆኑ ታምኖበት እየተጣራ ነው፡፡ አጠቃላይ የደረሰውንም ጉዳት በተመለለከተ ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉበት ቡድን ተቋቁሞ የኦዲት ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ባንኩ የደረሰበትን ጉዳትና አጠቃላይ የተመዘበረውን የገንዘብ መጠን ለማወቅ ሪፖርተር የባንኩ የሥራ ኃላፊዎችን የጠየቀ ቢሆንም፣ ይህንን መረጃ አሁን ይፋ ማድረግ በምርመራ ላይ ችግር ስለሚፈጥር መግለጽ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል። ከተመዘበረው ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ እንደተመለሰ ለቀረበላቸው ጥያቄም በምርመራው ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል ተመሳሳይ ምክንያት በማቅረብ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሆኖም በዚህ ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ የቀጠለና በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦች ሁሉ [እስከ ትናንት] ድረስ የጊዜ ገደብ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልመለሱ በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ እየተደራጀ ስለመሆኑ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ባንኩ ባስተላለፈው ይፋዊ መረጃው ደግሞ በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦች ያላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ እየመለሱ መሆኑ በጎ ዕርምጃ መሆኑን ገልጾ፣ እስከ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ተመላሽ ካላደረጉ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ምሥል ጭምር ሊያወጣ የሚችልና በፍትሐ ብሔር ሕግ ጭምር ክስ መሥርቶ ገንዘቡን የሚያስመልስ መሆኑን አስታውቋል፡፡  

ባንኩ በገጠመው ችግር ዙሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መግለጫ እየሰጡበት ሲሆን፣ በተለይ ሁሉንም የአገሪቱ ባንኮች በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ባወጣው መግለጫ፣ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት ጠንከር ያለ አቋም ይዟል፡፡ 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ተገን በማድረግ ተመዝብሯል ያለውን የሕዝብ ገንዘብ ማስመለስ ብቻ ሳይሆን፣ የሕግ ተጠያቂነት መኖር ይገባዋል የሚል አቋም ያንፀባረቀው ማኅበሩ በድርጊቱ ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመግለጫው አካትቷል፡፡ ‹‹የተፈጠረውን ችግር ተገን በማድረግ፣ በባንኩ፣ ደንበኞችና በማኅበረሰባችን ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት ላይ እየተደረገ ባለው ሕጋዊ የማጣራት ሥራ ሊሠራ ይገባል፤›› ያለው የማኅበሩ መግለጫ፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ወደ ሕግ በማቅረብ በቂ፣ ተመጣጣኝና አስተማሪ የሆነ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡ ዕርምጃው እንዲወሰድ በማድረግ ረገድም ‹‹ሁላችንም አባል ባንኮች አስፈላጊውን ድጋፍ በሚጠበቅብን ልክ ለሕግና ጉዳዩ ለሚመለከተው ተባባሪ አካላት ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን፤›› በማለት የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና በፈጣን ተለዋዋጭ ዓውድ ውስጥ እየለፈ የሚገኘው ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት ተግዳሮቶች አንዱ አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ በማዘመን ወይም የተሻለ ቀልጣፋ በማድረግ ሒደት ውስጥ የሚገጥሙ ዕንከኖች ዋነኘቹ ናቸው፤›› ያለው መግለጫ፣ እነዚህ ዕንከኖች በዓለም ላይ ስምና ዝናቸው ከፍተኛ በሆኑ ታላላቅ ተቋማት ላይ ሳይቀር በሥራ ላይ አጋጣሚ ወይም ክፉ ሐሳብ ባላቸው ሰዎች ታቅደው ሊከሰቱ እንደሚችልም ጠቅሷል፡፡  

የማኅበሩ አባል ከሆኑት ባንኮች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እ.ኤ.አ. ማርች 15 ቀን 2024 አገልግሎት እየሰጠበት የሚገኘው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት ለማዘመን በነበረው ሒደት ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የተከሰተውን የአሠራር ሥርዓት መዛነፍ እንደ ዕድል በመጠቀም የተፈጸመውን ድርጊት ኮንኗል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመበትን መንገድ ባብራራበት የመግለጫው ክፍል፣ የባንኩ ደንበኞች የሆኑ ግለሰቦች በባንክ ሒሳባቸው ውስጥ የሌላቸውን ወይም ካላቸው ተቀማጭ ገንዘብ በላይ የኤቴኢምና የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም ገንዘብ በጥሬ ብር ማውጣቱንም ገልጿል፡፡ እንዲሁም ከባንኩ የሒሳብ ቋት ውስጥ ወደ ሌሎች ባንኮች ሒሳብ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲዘዋወር በማድረግ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት መንቀሳቀሳቸውን አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መላው ባንኮች ርብርብ በማድረግ ችግሩን በመቆጣጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመነሻው እስከ መፍትሔው ድረስ ሙሉ አቅሙን በመጠቀም ተቋርጦ የነበረውን የባንክ አገልግሎት ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ የዘወትር አገልግሎቱን እንዲሰጥ ማድረግ ተችሏልም ብሏል፡፡ በባንኩ ደንበኞች ሒሳብ ላይ በዚህ አጋጣሚ አንዳችም የገጠመ ጉዳትና ችግር የሌለ መሆኑ ተረጋግጦ ደንበኞች የዘወትር አገልግሎት ከባንኩ ማግኘት እንደጀመሩ የሚገልጸው የማኅበሩ መግለጫ፣ ይህ አጋጣሚ ግን ለማኅበሩ አሳሳቢ ያለውን ጉዳይ አመላክቶ ስለማለፉም ጠቁሟል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ ሲያብራራም፣ ‹‹በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ላይ ችግር በተፈጠረበት ቅፅበት የነበረውን ክፍተት እንዴት እንዳገኙ ለጊዜው ባልተረጋገጠ ሁኔታ መረጃ የደረሳቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሌሊቱን በሙሉ በመደዋወልና ያልተገባ ተግባር መፈጸማቸውን ነው፡፡ በዚያ ሌሊት መረጃው የደረሳቸው ተማሪዎች  ከአውቶማቲክ ገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ገንዘብ በመውሰድ ልዩ ልዩ ገንዘብ መክፈያና ማስተላለፊያ ማዕቀፎችን በመጠቀም የራሳቸውን ያልሆነውንና በሒሳባቸው ውስጥ ያልነበረን ገንዘብ ከመዝረፋቸውም በተጨማሪ፣ የተፈጸመውን ምዝበራ እንደ በጎ ተግባር ሁሉ፣ በሁሉም ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በጀብድ መልክ ሲዘዋወር መመልከታቸው ከፍተኛ ሐዘን እንዳሳደረበት ማኅበሩ ገልጿል፡፡  

‹‹የማኅበራችን አባል ተቋማትን ጨምሮ የነገዋን ኢትዮጵያ ተረክበው በየሚሠለጥኑበት የሙያ ዘርፍ የኅብረተሰባችንን ኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ተስፋ ተጥሎባቸው ከማኅበረሰቡ በተሰበሰበ አንጡራ ገንዘብ በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወደ ከፍተኛ ተቋማት (ዩኒቨርሲቲ) የተላኩ አፍላ ወጣቶች፣ ኢትዮጵያዊ ከሆነው ነባር እምነትና ባህል ባፈነገጠ ሥነ ምግባር ላይ ወድቀው መገኘታቸው ልብ የሚሰብርና አገራችን ካሉባት ጊዜያዊ ችግሮች በላይ የሚያሳስብ አሳዛኝ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል፤›› በማለትም የማኅበሩን ሐሳብ አንፀባርቋል፡፡

ይህንን ብዙዎች ያዘኑበትንና በማንም በኩል ተቀባይነት የሌለው ፀያፍ ድርጊትና የድርጊቱ ፈጻሚና ተባባሪ የሆኑትን አካላት ሁሉ ማኅበሩ በፅኑ የሚያወግዘውና ይህንን ፀያፍ ድርጊት መላው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ እነዚህን መሰል ወጣቶች በተመሳሳይ ውድቀት ውስጥ እንዳይገኙ ለመከላከል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ትኩረት ሰጥተው እንዲፈጽሙ አሳስቧል፡፡ 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የማኅበሩ ከፍተኛ አመራር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት እንዳይደገም ከተፈለገ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱ ላይ ጥቃት ደርሷል በሚል የደረሰውን መረጃ መሠረት በማድረግ ፍተሻ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል፡፡

መረጃው ለአስተዳደሩ ከደሰበት ሰዓት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን ባደረጉት የሳይበር ደኅንነት ፍተሻ ሲደረግ መቆየቱን፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት ሐሚድ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ በተካሄደው ፍተሻ የተገኘው ውጤት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረው የሲስተም ችግር ምንም ዓይነት የሳይበር ጥቃት ያለመሆኑን ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ግን በጥልቀት ትንተና በመስጠት የለዩ መሆኑን ያከሉት ዳይሬክተሯ፣ በምርመራ መለየት የቻሉትም ባንኩ ካደረገው የሞባይል ባንኪንግ ስሪት ማሻሻያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

‹‹ይህ የስሪት ማሻሻያ ግን ሥርዓቱን ሳይጠብቅ ምናልባትም የፕሮግራሚንግ ቅደም ተከተሉን ሳይጠብቅ የተከናወነ በመሆኑ የተፈጠረ ችግር ነው›› በማለትም ችግሩ የተፈጠረበትን ምክንያት በምርመራቸው ሊያረጋግጡ ስለመቻላቸው አመልክተዋል፡፡

ስለሆነም ባንኩ ከውጭ የተቃጣ ጥቃት ያልደረሰበት ሲሆን ነገር ግን የባንኩን የውስጥ ጉዳዮች በተጨማሪነት የማጣራት ሥራ በጋራ ከባንኩ ጋር እየተሠራ ስለመሆኑም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ምርመራው ሲጠናቀቅ የባንኩ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚገኘውን ውጤት ሪፖርት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ሒደት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁናዊ ቁመናውን ለማየት ስለመቻላቸው በመጥቀስም ባንኩ በራሱ ከባቢ የሴኩዩሪት ጥበቃና ደኅንነት ያለው እንዲሁም የ24 ሰዓት ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ማለት ከውጭ ያለውን የተፈቀደለትን ዩዘር አካውንት ወይም ሎጊን ተጠቅሞ ሊደርስ የሚችል ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት እንደሚቻልም ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች