Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትእኛና ዙሪያችን

እኛና ዙሪያችን

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

የካቲት 66 ሆይ! ተስፋ እንዳለን እንዳወጋሁሽ ሁሉ ጉድ በይልኝ የሚያሰኝም ትዝብት አለኝ፡፡

1) ዛሬ አምባገነን አራጆችን ጥዬ ዴሞክራሲን አቋቁማለሁ የሚል አመፅና የብረት ትግል የሚያስፈራበት ዘመን ሆኗል፡፡ ትግል እንመራለን በሚሉት ልሂቃን ዘንድ የብልህነት መሰለብ፣ ለሕዝብ የሚቆረቆር ልብ ማጣትና የውጭ ጣልቃ ገቦች ተቀፅላ መሆን ሁሉም ሥፍራ የተባዛ ሕመም መስሏል፡፡ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣… የውስጥ ትግልና የውጭ ጣልቃ ገብነት ተቧክቶ አገረ መንግሥታት ፈርሰው ወይም የአንድ ትጥቅ ቡድን ያህል ተኮማትረው ሕዝቦች በሥርዓት አልባነት ሲዖል ሲቆጥሩ ታይቷል፣ እየታየም ነው፡፡ በቅርቡም፣ አገረ-መንግሥትነት በሌላቸው ፍልስጤሞች ውስጥ ከፊል መንግሥትነትንም ነፃ አውጪነትንም ደርቦ የያዘው ሐማስ በጫረው ‹‹የታጋይነት›› ጥቃት የእስራኤል-አሜሪካን ልክ ያጣ ወታደራዊ ቅጣት ቀስቅሶ፣ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ መሠረተ ልማቶችና የኑሮ አውታራት ፈራርሰው የብዙ ፍልስጤማውያን ሞት ረክሶ መጠለያ፣ ምግብና ሕክምና የማግኘት ነገርም ነፍስ አድን ምፅዋት በመቀበል ደረጃ ወርዶ ለማየት በቃን፡፡ ለሰብዓዊ መብት በመቆርቆር በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንና የጦር ወንጀሎችን አምርሮ በመቃወም ረገድ፣ ዓለማችን ሐዘን ልብስ ከለበሰች ውላ አድራለች፡፡ አሁኑ ፍልስጤሞች ላይ እየደረሰ ላለው ውርጅብኝ፣ ዓለማችን በሰጠው አሳፋሪ ምላሽ እንደታየውም ለሰው ልጆች ሰቆቃ የሚጮህ ድምፅ ከምዕራብ አገሮች ሸሽቶ፣ በመካከለኛ ምሥራቅ ውስጥም ጠንካራ ተገን አጥቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ዋና ቢሮውን ከፍቷል፡፡ ፍልስጤሞችም ከመካከለኛው ምሥራቅ የዘር ዘመዶቻችን ይበልጥ ደቡብ አፍሪካ የግፍ ተፋራጃችን ሆነችልን ባዮች ሆነዋል፡፡ በፍልስጤሞች ላይ እየተካሄደ ያለውን ግፍ መቋቋም ያቃተውም የአሜሪካ ወታደር፣ ‹‹ለሰው ልጆች የሚቆም ከእኔ በላይ ላሳር›› ስትል በኖረችው አገሩ ውስጥ ራሱን በእሳት ሲያቃጥል ታየ፡፡ የታሪክ አሳዛኝ ስላቅ!!

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ታሪክ የዛሬውን ዓለማችንን የምታሽሟጥጥበት ስላቋ በዝቷል፤ ሠልቷል፡፡ የምዕራባውያን የዛሬ የስደተኛ አቀባበል ለሰው ልጅ ችግር መጠጊያ በመሆን የሚለካ ሳይሆን በፖለቲካ ጥቅም፣ አብሮ በሚሰደድ የገንዘብና የሠለጠነ ሙያ ጥቅም የሚለካ መሆኑን ታሪክ ኩልል አድርጋ አሳይታናለች፡፡ የዓለማችን ችግሮች መላ ያጡበት ጊዜ መሆኑን ለመናገርም፣ ታሪክ ስደትን እየተጠቀመችበት ነው፡፡ ስደት በተሻለ ሕይወት ፍለጋና በነፍስ ማዳን ሽሽት አኅጉር ያቋርጣል፡፡ ኢትዮጵያን ምሳሌ ብናደርግ፣ ከኢትዮጵያ በተለያየ አቅጣጫ የሚዘምቱ ስደተኞች በሚያቆራርጡበት አገርም ሆነ በሸሹበት ሥፍራ ከአገራቸው የከፋ ኑሮና ቀውስ ገጥሟቸው እንደገና የ‹አድኑን!› ጨኸት አስምተው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው በአንድ በኩል ሲወጡ፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ብትሻለን ብለው ከጎረቤት አገር ወደ ኢትዮጵያ ሌሎች ይመጣሉ፡፡ የስደተኛ ፍልሰቱ ሶሪያውያንንና የመናውያንን ኢትዮጵያ ድረስ አምጥቷል፡፡ ታሪክ እያሳየችን ያለችው፣ ስደት አዙሪታም የሰቆቃ ሽሽት መሆኑን ብቻ አይደለም፡፡ ስደት፣ እጅግ አትራፊና ጨካኝ የሆነ አኅጉር አቋራጭ የንግድ መረብም ነው፡፡ ልዩ ልዩ ባርነት የሚካሄድበት፣ ለሆድ ዕቃ ብልት ንግድ ሰው እንደ ፍሪዳ የሚሸረከትበት፣ ለውጭ ምንዛሪ መጠጣ ሰው እየተጋዘ የሚቀጠቀጥበት ሲዖልም ነው ስደት፡፡

ስደትና ግፍ ተገናኝተው ሀብት ማፍሪያ መረባዊ ‹‹ኩባንያ›› እንደፈጠሩ ሁሉ፣ በሕዝብ ስም የሚደረግ ትግል ስለመዝቀጡም ታሪክ በምፀታዊ ሽሙጥ እየተናገረች ነው፡፡ የየመን ሕዝብ የለውጥ ትግል ወደ ሱኒና ሺዓ ግጥሚያ ተንሸራቶና በአካባቢው ጉልበት አለን በሚሉ ተቀናቃኝ አገሮችና በኃያላን ጣልቃ ገብነት ተጠልፎ የመን የምድር ሲዖል በሆነችበት ታሪክ ውስጥ አንዱ ቀንደኛ ተሳታፊ የነበረው የሁቲዎች ቡድን፣ ከጥፋት መማርንና የየመንን ሕዝብ መከራ ማቅለልን ሳያውቅበት፣ አሁን ደግሞ የፍልስጤሞችን ሰቆቃ ለማስቆም የሚታገል ‹‹ወገኛ›› ሆኖ ቀይ ባህር ላይ ሮኬትና ሚሳይል እየተኮሰ የእነ አሜሪካ ጥቃት የመን ውስጥ እንዲገባ አደረገ፡፡ የሁቲዎችና የሂዝቡላዎች ደጋፊ የሆነችው ኢራንም የመን የገባው የአሜሪካ ቅጣት ኢራን ተሻግሮ ገሃነም ሊፈጥር የሚችልበት ዕድል እየበሰለ መሆኑ አልገለጥ ብሏት፣ ፊር ፊር ማለቷን ቀጥላለች፡፡ በሌላ አገር ሕዝብን የሚጠብስ ገሃነምን እታገላለሁ እያሉ ያው ገሃነም ወደ ራስ አገር እንዲሻገር መልፋት ምን ይባላል! እንዲህ ያለ ማሰቢያ ራስ የሌለው ታጋይነት ሁሉም ሥፍራ አለ የሚያሰኝ ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል፡፡

እዚሁ በኢትዮጵያ ቤታችን ውስጥ በአንድ ጊዜ ሁለት አገሮች ላይ ተኩስ የከፈተና በአራት ግንባሮች ጦርነት ያካሄደም ማሰቢያ ራስ አጥቶ አንገቱን ሸምቀቆ ውስጥ የከተተ ‹‹ታጋይነት››ም ዓይተናል፡፡ በአገራችንና በዙሪያችንም የፖለቲካ ልሂቅ ካብ-አይገቤነትና አጥፊነት ተባዝቷል፡፡ ከአምባገነን አዛዥ ናዛዥነትም አልፈው መጨፍጨፍ የለምዱ ገዥዎች ላይ ሕዝብ እንዲያምፅ መቀስቀስ አስፈሪ አደጋ ከመሆኑ ይባስ ብሎ፣ ከአምባገነነኞች ጋር የተሸማገለ የጥገና ለውጥ ማምጣት እንኳ ብርቅና ከባድ ሆኗል፡፡ እናም የለውጥ ነገር በዙሪያችን እንደምናስተውለው ሲመጣ ይምጣ እስከ ማለት ድረስ መላ ቸግሮታል፡፡ ሙልጭልጭነት፣ ውለታ አያውቅ ወመኔነት፣ ለገዛ አገር መረጋጋትና ግስጋሴ አለመጣር፣ ከዚያ አልፎ የገዛ አገር ጥቅምን ማጥቃት፣ ለራስ ነፍስ ሲሉ የገዛ አገር ሕዝብን ‹ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ› ሁኔታ ውስጥ መክተት፣ የኢትዮጵያን ግስጋሴና መረጋጋት መቀናቀን፣ የገዛ አገርን ጥቅም መቀናቀን መሆኑን አለማስተዋል፣ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢያችን መታወቂያ ለመሆን የሚሻሙ — ከመሸማትም የሚተጋገዙ — ነገሮች እየመሰሉ ነው፡፡

2) የኢትዮጵያ ለውጥ ብሩህ ሆኖ በተጀመረበት ጊዜ አካባቢ፣ ባስገመገመ የሕዝብ ብሶትና የለውጥ ፍላጎት ላይ ተንጠላጥሎ በሱዳን የተካሄደው ወታደራዊ ግልበጣ፣ የሱዳን ሕዝብ ለውጥ መታነቂያ ጠንቅ ሊሆን የመቻሉ ነገር ሱዳን ውስጥ የነበረውን የሶቆቃ ታሪክ ላወቀ አስተዋይ ፖለቲከኛ ሥውር አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያው መሪ ሸምጋይነት ተጨምሮበት የተፋጠጡት የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ገልባጮችና የሱዳን የለውጥ እንቅስቃሴ ተቀራርበው፣ በሽግግር መንግሥትነት መቀናጀት መቻላቸው ጥሩ ተስፋ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ የሱዳን ሕዝብ የለውጥ ፍላጎት፣ በዴሞክራሲ ላይ በቀላሉ የማይሸነገል ጥንካሬ ማሳየቱና በጅምላ ጭፍጨፋና በጦር ወንጀል የተጨማለቁት የሱዳን ወታደራዊ መኳንንት እንደምን ይኳኳኑ ይሆን የሚለው ጥያቄ ከባድ ነበር፡፡ ከዚህ ከባድ ጥያቄ አኳያ፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ የመቻሉ ነገር፣ የፖለቲካ ብልህነትን እጅግ የሚፈትን እንቆቅልሽ ነበር፡፡ እንደተፈራውም ጊዜያዊው የሽግግር ምክር ቤቱ ተንጦ፣ ሲቪሉ ተሳትፎውን አጥቶና የወታደራዊ ወንጀለኞች መፈናገጫ ሆኖ ሱዳን ካርቱም ለሁለት ጄኔራሎች ወታደራዊ መቧቀሻነት ተዳረገች፡፡ ሁለቱም ጄኔራሎች የዳርፉር ሰቆቃ ባለታሪኮች ናቸው፡፡ መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በጃንጃዊድ ሚሊሺያነት ያደገ ነው፡፡ የፈጥኖ ደራሽ ጦርም የተደራጀው የጃንጃዊድ ሚሊሺያን መሠረት አድርጎ ነበር፡፡ ይህንን የጭፍጨፋ ጦር ያደራጁትና ከርቀት ይመሩት የነበሩትም የኡማር አል በሽር መንግሥትና የመደበኛ ጦር ከፍተኛ አዛዦቹ ነበሩ፡፡ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ራሱ የዳርፉር አካባቢ አዣዥም ነበር፡፡ እናም የአል በሽርን መንግሥት ገልብጦ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጉዳይ፣ ወንጀለኛውን አል በሽር በማስወገድ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ መንገድ ከመጥረግ ይበልጥ፣ አል በሽርን ሰውቶ ከተጠያቂነት የማምለጥ ሩጫ ነበር፡፡

የካርቱም ሰማይ ቦምብ እየጣለች የካርቱም ከተማዋን ያፈራረሰችውና የብዙ ሺዎችን ነፍስ በልታ ሚሊዮኖችን የውስጥ ስደተኛና ድንበር ተሻጋሪ ስደተኛ ያደረገችው፣ የውጭ ሰይጣን ገብቶባት አልነበረም፡፡ ይህ ሁሉ ቀውስ እስኪፈጠር ድረስ ጄኔራሎቹ ለጋላጋይ ያስቸገሩትበት ሚስጥርም እንቆቅልሽ አይደለም፡፡ የዕርቅና የግልግል ሽምግልና ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅና አዲስ አበባ ቢል መላ አልገኝ ያለው (አንዱ ጄኔራል ጉልበት ተሰምቶት እንቢ ሲል ሌላው ለዕርቅ እሺ የሚለው፣ እሺ ባዩ እንቢ ባይ ሲሆን፣ እንቢ ባይ የነበረው ለግልግል እሺ ባይ የሚሆነው) ግብግቡ፣ አንዱ ወንጀለኛ ሌላውን አወራርዶ ራሱን ለማትረፍ የሚካሄድ ስለሆነ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ማለቂያ ያጣ ግብግባቸው ዕድሜያቸው ረዝሟል፡፡ የጠቅላላ ምርጫ ነገርና የለውጥ ነገር ተረስቶ፣ የሱዳን ሕዝብ ሁነኛ ተቀዳሚ ጥያቄ የነፍስ ጉዳይ (የሰቆቃው ማብቃት) ብቻ ሆኗል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ቀልቡ የተያዘው ምዕራቡ ዓለም፣ ሱዳንን ከናካቴው ዘንግቷታል፡፡ ለማስታረቅ መጀመሪያ ላይ ታች ያለችው አሜሪካ አሁን የሱዳን ነገር ለአፍ ያህል እንኳ አንሶባታል፡፡ በዳርፉር አካባቢ በአሁኑ ውጊያ ጊዜ ስለተካሄደ ጅምላ ጭፍጭፋ (ምናልባትም ከእነ ነፍስ የመቅበር ግፍን ያዘለ) በ‹ሲኤንኤን› ለአመል የተለቀቀ መረጃ አላት፡፡ ግን ይህንን ከረዥም ጊዜ በፊት የጀመረ ግፍ ለማስቆም ዓለም ስላለበት ኃላፊነት ያሳሰበችበት ጥረት ቢጤ እንኳ የለም፡፡ የሱዳን ተፋላሚ ጄኔራሎች አሁን ባሉበት ሁኔታ፣ አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሱዳን ሉዓላዊ ሥልጣን ወኪል አድርጎ ራሱን ቆጥሮ፣ በተናጠል እያናገሩ ለማስታረቅ የሞከሩ ጎረቤቶችን፣ ‹‹በሱዳን የውስጥ ጉዳይ የገቡ ጠላቶች›› ባይ ሆኗል፡፡ እዚህ ዕብሪት ውስጥ እስከ ቆየ ድረስም ሱዳን የግብፅ በጥባጭነት መሣሪያ ለመሆን ተጋልጣ ትቆያለች፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር በሶማሌላንድ ጠረፍ ምድር የንግድ ወደብና የወታደራዊ መቀመጫ ሠፈር በኪራይ የማግኘት መግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ የይፋ ዜና በሆነ ጊዜ፣ ሶማሊያ ያሳየችው ባህሪይም (ኢትዮጵያን በመሬቷ የመጣች ‹‹ወራሪ›› ብላ በቁጣ መንበልበሏ)፣ በሶማሊያ ሉዓላዊ አስተዳደር ሥር ያለ መሬት ላይ ኢትዮጵያ እጇን የሰደደች ያህል አስገራሚ ነበር፡፡ የሶማሊያ አገርነት ከጣሊያን ሶማሌላንድና ከፈረንሣይ ሶማሌላንድ ውህደት የተገኘና የ30 ዓመት ባለ ዕድሜ አገርነት እንደሆነ፣ ሶማሌላንድ ነፃ አገርነቷን ያወጀችው ከዚያድ ባሬ ጋር ሶማሊያ ተንኮታኩታ የሥርዓተ አልባነትና የጦር አበጋዞች መፈንጫ በሆነችበት ጊዜ እንደነበር፣ ሶማሊያ ከፈረሰች (ሶማሌላንድ ነፃ አገርነቷን ካወጀች) ሰላሳ ዓመታት እንደሞላት፣ የሶማሊያም ከሥርዓት አልባነትና ከአሸባሪዎች ሜዳነት የመውጣት ትግል 30 ዓመት እንደፈጀ፣ ዛሬም ‹‹ፌዳራላዊ›› መንግሥት ብትፈጥርም የአሜሪካ ፀረ ሽብር ዕገዛ ሳይለያትና ከአፍሪካ ውስን አገሮች የተውጣጣ ጦር እየደማላት እንደቆየች (በዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ ውለታ አሁን ድረስ ጉልህ እንደሆነ) የመንግሥቷ መሪ የሚያውቅም አልመሰለ፡፡ በመሪዋና በአንዳንድ ሊሂቃኖቿ አኳኋን እንዳስተዋልነው፣ ሶማሊያ በአልሸባብ እንደገና መስፋፋት ስታስፈራራ፣ አይዞሽ አለሁልሽ ካለቻት ግብፅ ጋር ምክር ስታበዛ፣ የግብፅ እርካብና መሣሪያ ወደ መሆን የሚወስድ ድጥን እንደማትፈራው፣ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት ከመቃጣት አንስቶ ከአልሸባብ አሸባሪነት ጋር እስከ መሞዳሞድ ድረስ ህሊና ልታጣ ስለመቻሏ ራሷን አስገምታለች፡፡ በአንዳንድ ሚዲያ እንደታየው ከ‹ተማሩ› ሶማሊያውያን በኩል የሚታየው የስሜታዊ ውርጭት አጫፋሪ መሆን፣ የሶማሊያን ተመልሶ መሰባሰብ የማይጠቅም መሆኑን አለመረዳት፣ የሶማሊዎች የስብስብ ሁነኛውና ዕውናዊው መንገድም የቀጣናዊ ትስስር ጎዳና መሆኑን አለማስተዋል፣ የሶማሊያን አካሄድ ከማቃናት አኳያ ትልቅ ትራጀዲ ነው፡፡ የሶማሊያ ለመሽቆልቆል ቅርብ መሆንና በውጭ ኃይሎች የሚታገዙት የሱዳን ጄኔራሎች ውጊያ በሱዳን የፈጠረው ቀውስ አንድ ላይ ሲዛመድ የአፍሪካ ቀንድን ከአሁኑ ይበልጥ ትርምሳም ለማድረግ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይሆንም፡፡

3) ለቀጣናችን ቀውስ አባባሽነት ምንጭ የሚሆኑት ሁለቱ ብቻ አይደሉም፡፡ ኤርትራ በጋራ ጥቅም ወደብ የማልማት ጥያቄ ላቀረበችው ኢትዮጵያ ቀዝቃዛ ምላሽ መስጠቷና ከሶማሊያና ከግብፅ ጋር ሰበር ሰካ ማለቷ፣ የገዛ ሕዝቧን ወርቃማ የልማት ዕድል እንቢኝ ከማለትም በላይ፣ ወርቃማውን ዕድል ለማክሸፍ የምትደፍርም አስመስሎባታል፡፡ ኤርትራ ይህንን ወርቃማ ዕድል ረግጣ፣ ከግብፅና ከአሁኑ የሶማሊያ አደገኛ ውርጭት ጋር ወዳጅ ሆና ለሶማሊያ ዘራፍ ባይነት ወታደር አሠልጥኖ መመገብን ገቢዋ አድርጋ ብትይዝ፣ ለራሷም ለቀጣናውም የማይበጅ ጥፋት ውስጥ መግባት ይሆንባታል፡፡ አብሮ መልማትን መሠረት ያደረገውን የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ፣ የጦርነት ጎሳሚነት አድርገው የሚሥሉና ኢትዮጵያን ‹‹ተስፋፊ፣ ለራሷም ያልሆነች በመፍረስ አፋፍ ላይ የምትገኝ›› የሚሉ አፈ ሰፊ፣ ግን ኦናዎች ወይም እውነታን የካዱ ‹‹ልሂቃን›› ከዘመዶቻችን ከኤርትራ ልጆች መሃል (በፈረንጅ አገር ካሉ) መስማትም በኤርትራ-ኢትዮጵያ ግስጋሴ ላይ የመጣ መርዶን የመረዳት ያህል ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የሶማሌላንድን መግባቢያ ሰነድ፣ ከኤርትራ ህዳሴ አኳያ መባነኛ አድርጎ ከመውሰድ ፋንታ ጭራሽ መሳለቂያ ማድረግ ጤና ማጣት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ ጊዜ በተወሰነ ደረጃ ተላውሳለች፡፡ ከኢሕአዴግ በኋላ የመጣው ለውጥ የተጠራቀሙ ችግሮች የተከፋፈቱበት የፈተና ጊዜ ቢሆንም፣ ውድ ኪሳራ ያስከፈለ ጦርነት የተካሄደበት ቢሆንም፣ አሁንም ገና ያልተገባደዱ የሰላም ጣጣዎች ቢኖሩትም፣ ኢትዮጵያ ከእሳት ውስጥ ይበልጥ ጠንክራ ወጥታለች፡፡ በልማት እየፈጠነች የልሂቃኗን ንቁ ተሳተፎ እያሻሻለች፣ የወጣቶቿን የተሽመደመደ ልሂቅነት በማደስ እያቃናች፣ የወደቀ የትምህርት ሥርዓቷንም አዲስ መሠረት እያስያዘች ትገኛለች፡፡ በዚህ ሁሉ ፈርጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የለውጥ እርግብግቢት ተቀስቅሶ፣ ኤርትራ በ1983 ዓ.ም. የነፃነት ባንዲራ የተሰቀለበት ጊዜ ላይ ተገትራ የቀረች፣ የዴሞክራሲን ሽታ የማታውቅ፣ የተለያየ ሐሳብ የማንሸራሸር ልምምድ ምድረ በዳ የሆነች፣ ‹‹የነፃነት›› መሪው ኢሳያስና ኤርትራነት አንድ የሆኑባት፣ በስለላ የተገነዘች አገር መሆኗን አለማስተዋል እያዩ አለማየት ነው፡፡ እነ አስመራና ምፅዋ እርጅናን በቁማቸው የሚቆጥሩ የጣሊያን ጊዜ አሮጌ ሥነ ሕንፃዎችና ቁስቁሶች የሚጎበኙባቸው ሙዚየማዊ ከተሞች ሆነው መቅረታቸውን፣ የኤሌክትሪክና የውኃ መሠረተ ልማት የሌላቸው መሆናቸውን፣ ማታ ከፀሐይ ብርሃን በሚሞላ ባትሪ ብርሃን ካላገኙ በቀር በጨለማ መዋጣቸውን፣ ካረጁ ግንባታዎች ባሻገር የደርግ ጊዜ ጦርነት ውጤት የሆኑ የሕንፃ ፍርስራሾች (በተለይ በምፅዋ) ዛሬም እንደ ቅርስ ዕቃ መገተራቸውን አለማስተዋል እያለሁ የለሁም እንደማለት ነው፡፡ በተከተረ ሕይወት ውስጥ ኑሮን ለማሸነፍ በሚፍጨረጨሩት የኤርትራ ተሬዎች አካባቢ ያለውን በቀን አንዴ በልቶ መዋል እንግዳ ያልሆነበትን የኑሮ ማነስ አስተውሎ አለመነካት ከዕድገት አልባነት ጋር ሽርክና ከመያዝ አይለይም፡፡ አስተውሎ በዝምታ ውስጥ ቢብሰለሰሉትም ፋይዳ የለውም፡፡ በኤርትራውያን የኑሮ ድቀት ተነክቶ በዙሪያችን ከታዩ የለውጥ ክሽፈቶች ተምሮ፣ በኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ውስጥ የታየውን የፍስፍስ ልምድ ሸሽቶ፣ በለዘበ መቀራረብና መግባባት የኤርትራ ህዳሴ የሚወለድበትን ፋና ለማብራት አለመቻል፣ አገርንና ሕዝብን ተስፋ የለሽ አድርጎ ከመተው አይሻልም፡፡

እርግጥ ነው ከተለያየ አቅጣጫ ልናገኝ ከምንችለው መረጃ እንደምንረዳው፣ የኤርትራ ልሂቅ በተለያዩ ችግሮች የተቆራረሰ ነው፡፡ በኤርትራ አገረ-መንግሥት የሙያና የአገልግሎት አውታራት ውስጥ የተሰማራው ልሂቅ፣ እንደ ተራው ሕዝብ መናፍስት-አከል በሆነ የስላላ ሥውር አውታር የተገነዘና በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሳይቀር መንግሥትንና ኢሳያስን ለማማት እየሠጋ የሚኖር ነው፡፡ ከጊዜ ጊዜ በጥራትና በተቋማት ዕድገት እየከረከሰ ከሄደውና ውትድርና ከተጫነው የኤርትራ ትምህርት የሚገኘው ወጣት ስደትን ከማሰላሰል ውጪ የአገሩን ህዳሴ ለማውጠንጠን ልሂቃዊ አቅምም ነፃ ትንፋሽም እንደሌለውም ግልጽ ነው፡፡

በገፍ ‹‹ተማረ›› እየተባለ ከሚወጣውና በኤርትራ ውስጥ ቆይቶም ሆነ ተሰድዶ ለጉርሱ ከሚፍጨረጨረው ትምህርት ቀመስ ባሻገር፣ በውጭ የሚገኙትን ዘለግ ያሉ ልሂቃንን ለይተን ብንመለከት አንደበትና ህሊናን ያፈኑ ችግሮች አሉባቸው፡፡

የኤርትራን የነፃነት ትግልና ድል በደፈናው በማወደስና በባለድልነት ኩራት ውስጥ መኖርን ብዙዎቹ ዘንድ እናገኛለን፡፡ የተጋድሎ ታሪካቸው ላይ የሂስ አፍን ማሳረፍም ለብዙዎቹ ከነውርና ከክህደት የሚቆጠር ነው፡፡ ይህንን ጥቅል አቋም የሚጋሩት ሊሂቃን ግን በኢሳያስ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት ተሰናጥረው ይገኛሉ፡፡ ተቃዋሚዎቹ ኢሳያስን አምባገነን ከማለታቸው በቀር፣ ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥ ጠላትነት የሚመለከተው ዓይናቸው እንዳለ ነውና ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ጉድኝት የሚሆን ሥፍራ ልባቸው ውስጥ የለም፡፡ መጎዳኘት ወደ ሌላ ‹‹ባርነት›› መሄድ ሆኖ ፀጉራቸውን ያቆመዋል፡፡ የሚገርመው የዚህ ዓይነቱን አቋም በመያዝ አንዳንድ ሥፍራ ላይ ብሰው የሚታዩት ‹‹ባለው የኤርትራ መንግሥት ተሳድደናል…›› በሚል አቤቱታ ጥገኝነት አግኝተው ዜግነት የቀየሩና ኤርትራ መግባት ዛሬ የማይፈቀድላቸው ናቸው፡፡

የእነዚህኞቹ ቆሞ ቀርነት የሌለባቸው (ኤርትራ ልማትና ለውጥ የቸገራት አገር መሆኗን ካስተዋሉ በኋላ የተቀየሩና የሚብከነከኑ) ተበራክተው ብናገኝም፣ እነዚህም በተለያዩ ምክንያቶች የተሸበቡ ናቸው፡፡ 

  • ኤርትራ ውስጥ ቤትና ቤተሰብ ያላቸው፣ የዜግነት ግዴታቸውን አሟልተው በውጭ የሚኖሩ ቢሆኑም፣ ከጊዜ ጊዜ ቤተሰባቸውን ኤርትራ ሄደው የሚያዩ፣ ባለው የኤርትራ መንግሥት ጥቁር ነጥብ እንዳይያዝባቸው በመሥጋት የለውጥ ነገርን ማንሳት ፍርኃት ይሆንባቸዋል፡፡
  • ከኤርትራ አፈና አምልጠን መጣን በሚል ትርክት ጥገኛነትና የውጭ ዜግነት ያገኙትና ለውጥ ካልመጣ ወደ ኤርትራ የመግባት ዕድል የሌላቸው፣ የኢሳያስን መንግሥት ለመቃወም ባይፈሩም፣ የመፍትሔ መላ ማጣት አንዱ ችግራቸው ነው፡፡
  • በኤርትራ አለማደግ ከሚያዝኑት መሃል፣ ሐዘናቸው ኢሳያስ አፈወርቅን የነፃነት ምልክት አድርጎ ከማየት ጋር ተጣብቆ ፍዝ ያደረጋቸውም አሉ፡፡
  • በኤርትራ አለማደግ ከማዘን አልፈው ኤርትራ የነፃነት ባንዲራዋን እንደያዘች ከኢትዮጵያ ጋር መጎዳኘት እንደሚያዋጣት፣ የኢኮኖሚ መዋሃድ እስከፈጠሩ ድረስ ይበልጥ የሚጠቀመው የኤርትራ ሕዝብ እንደሆነ፣ ለኢትዮጵያ ወደብ ማቋደስ በጣም ትንሽ ነገር እንደሆነ የገባቸው ቢኖሩም ግን ይህንን እውነት መቀበል ለነፃነት የተደረገውን ትግል ለድርድር የማቅረብ ያህል ቃር የሆነባቸው አሉ፡፡
  • ቃር ባያስቸግራቸውም፣ ስለሁለቱ አገሮች የዚህ ዓይነት ጉድኝት በይፋ መናገር፣ የ30 ዓመት የሃርነት ተጋድሎን ለሽሙጥ መዳረግ ተደርጎ ይተረጎምብኝ ይሆን በሚል ፍርኃት አንዳንዶቹ ዝምታን መርጠዋል፡፡ አንዳንዶቹም ሰሚ አናገኝም በሚል ቸለልታ ውስጥ ቦዝነዋል፡፡ መሰባሰብ ፈጥረው መፍትሔ ለመሆን እየፈለጉ የዕውቀት አቅም የገደባቸውም እንዳሉ ይሰማል፡፡
  • የኤርትራ ፓስፓርትን እንደያዙ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዘዴ የኢትዮጵያንም ፓስፓርት ይዘው በኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩት ደግሞ ኑራቸው የኢትዮጵያና የኤርትራን መተሳሳር የህልውና ጉዳይ መሆኑን ቢናገርም፣ አሁን ባሉበት ሁኔታ ‹ከሁለት ያጣ› እንዳይሆኑ ምንም ከመተንፈስ የታቀቡ ሆነዋል፡፡ እኔ ራሴም ብሆን ይህንን ሁሉ ማውራቴ፣ ‹‹ቅዱሰይ›› የሚሉኝን የኤርትራዊ እናቴን ጓዳ ለወሬ ያሰጣሁ ሆኖ ይሰቅቀኛል፡፡

የዝምታ ምክንያቶችን በዓይነቱ ስለደረደርን ዝምታን ተገቢ አናደርገውም፡፡ ይህን ያህል መዘግየት ሳያንስ ዛሬም በተለያዩ የግብዝነት ሰበቦች ተሸብቦ ለኤርትራ መፍትሔ ለመሆን አለመቻል የሕዝብ ተቆርቋሪነትና ቁጭት አለኝ ለማለት አያበቃም፡፡ የኤርትራን ሉዓላዊ አገርነት ሳያስነኩ፣ የኢሳያስ አፈወርቂን የነፃነት ትግል መሪነት ታሪክ እንዳከበሩ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተሳሰረው እንዲጠቃቀሙ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዛሬ ‹‹አምፀህ ፈንቅል! ገርስስ!…›› የሚል ሆይ ሆይታ ወደ ብርሃን ይውሰድ ወደ ጨለማ በማይታወቅበት ቀውጢያም ዘመን፣ አዋጭ ሆኖ የሚገኘውም የለውጥ መንገድ በጥገና ብልኃት ለውጥን ማበጃጀት ነው፡፡ ብዙ የኤርትራ ልጆችን አንድ ላይ ለለውጥ እንቅስቃሴ በማያያዝ ረገድ ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖራል!? ብልጠት እንዳይመስልብኝ በሚል ይሉኝታ ዛሬ ሳልናገረው የማላልፈው ሌላም ነገር አለ፡፡ የኢሳያስ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ስለኤርትራ ሰላምና ግስገሴ የምር የሚብከነከኑ ከሆነ ቢፈጥኑ ይሻላል፡፡ በዘገዩ ቁጥር፣ አሻንጉሊታቸውን ሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ የትኛውንም መንገድ ከመጠቀም ለማይመለሱት፣ ለ‹‹ሲአይኤ›› እና ለቅጥረኛ መሰሪዎች ዕድል ነው የሚሰጡት፡፡

4) ሶማሌላንድ እንደ አገር ዕውቅና ማግኘት የሚገባት ስለመሆኗ ብዙ መከራከሪያ ልታነሳ ትችል ይሆናል፡፡ እንደ ታይዋን የእናት ምድር ታሪክ ያላት የመሆን አለመሆኗም ነገር፣ የእሷ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እኛን አይመለከተንም፡፡ የሶማሊያ ሪፐብሊክ የተቋቋመችው ከቅኝነት ከመውጣት በኋላ እንደሆነ፣ ጦርነት ወዳዱ የዚያድ ባሬ መንግሥት ሶማሊያን ለመንኮታኮት እንዳበቃት፣ የአሁኗ ሶማሌላንድም የተወለደችው መንኮታኮት ካስከተለው ሥርዓተ አልባነት ውስጥ ራስን የማዳን ውጤት ሆና እንደነበር መናገርም ነውር (የሶማሊያን አንድነት መቃረን) አይሆንብንም፡፡ ምክንያቱም ይህ በእኛ ፍላጎት ውስጥ የሌለ በታሪክ የተፈጸመ ሀቅ ነውና፡፡ ሶማሌላንድ ከሥርዓተ አልባነት ላንቃ ወጥታ በአገርነት ራሷን ካቋቋመችም አንድ ትውልድ የሞላት፣ ሽብርና የውስጥ ትርምስ የማያምሳት፣ የባህር አካባቢዋን ሰላም የጠበቀችና በ‹‹ዴሞክራሲ›› የምትመራ አገር ነች፡፡ እንዲያም ሆና እስካሁን በሉዓላዊነት ዕውቅና ያላገኘች፣ ግን ከተወኑ አገሮች ጋር ከአምባሳደር ዝቅ ያለ የውጭ ግንኙነት ያላት መሆኗም እውነት ነው፡፡

ይህም ሀቅ የሁለቱን ባለጉዳዮች በራስ-ገዝም ሆነ በሌላ ቅንብር የመዛመድ ዕድል አይጣላም፡፡ ወደ አንድነት መምጣት አለመምጣት የሁለቱ ሕዝብ ፍላጎትና መስማማት ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር ያለው በጫና ‹‹የተጠበቀም›› አንድነት ሆነ፣ በጠብ የተገኘም የሉዓላዊነት ዕውቅና፣  ሰላምንና መረጋጋትን ማናጋት አለማናጋቱ ነው፡፡ የአንድ፣ ሁለትና ሦስት አገሮች ይፋ ዕውቅና ለማግኘት ተብሎ ‹‹መሬቴ/አካሌ!!›› ከሚል አገር ጋር በግጭትና በጦርነት መቋሰል ለሁለቱ ወገኖችም ሆነ ለቀጣናው አማቃቂ ነው፡፡ አንድና ሁለት ቦታ የተገኘች ስማዊ ዕውቅናን ይዞ በሰላም ዕጦት ከመራገፍ ይልቅ፣ ጣጠኛውን የዕውቅና ትግል አዘግይቶ አገርነትን በግስጋሴ ይዘት መሙላት ይበልጥ ይፈይዳል፡፡ የግስጋሴ ይዘት ብቻውን በዓለም ለመታወቅና ለመከበር ያስችላል፡፡ ተመድ ራሱ አላወቅኩም እያለ የሚያውቀው፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከብዙ አገሮች ጋር ለመዘርጋት ያስችላል፡፡ በባዶ ጥንካሬ ‹ግዛቴ ነሽ!› የሚል የዘመድ አገር ተንኳሽነትን ያሳፍራል (መሳቂያ ያደርጋል)፤ እየተናጡ ግዛት ከመቁጠር ይልቅ ተረጋግቶ መልማትን ያስተምራል፡፡

የሶማሌላንድን ሶማሊያነት በስማዊነቱ ብቻ የሙጥኝ ይዞ በጠብ እየተላፉ መኖርም ለሶማሊያ አይጠቅማትም፡፡ ወደ የምትፈልገው ባለ ይዘት አንድነት አያደርሳትም፡፡ በዚያ ላይ በፀብ ውርጭት ራሷን ትጎዳለች፤ አካባቢዋንም ታብጣለች፡፡ ሲብስም፣ እስካሁን የተለፋለት የተረጋጋ አገረ-መንግሥት የመሆን ዕድሏ የኋሊት ይመለስ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለቀጣናውና ለአኅጉሩ የባሰ ጣጣ ነው፡፡

በአጭሩ ሁለቱም የእልህና የፀብ መንገዶች ለማንም አይበጁም፡፡ ኢትዮጵያም ሶማሌላንድም ሶማሊያም በአፍሪካ ቀንድ የተሳሰረ የልማት ግስጋሴ ማዕቀፍ በኩል፣ የሶማሌ ሕዝቦች መያያዝ  (መሰባሰብ) በጋራ የሚገናኙበት ግባቸው ከሆነ፣ በዚህም ተሄደ በዚያ ‹ዞሮ ዞሮ መዝጊያው ጭራሮ› ነውና በዕውቅና ላይ ዛሬ መናቆር የዛሬን አጀንዳ የረሳ ሥራ ፈትነት ይሆንባቸዋል፡፡ የሦስቱም ባለጉዳዮችና የቀጣናው አገሮች አጀንዳ ውስጣዊና አካባቢያዊ ሰላምን እየተንከባከቡ መልማት ነው፡፡ በተለይ ሶማሊያ ከቀጣናዊ የትስስር ጉዞ በመለስ ከሶማሌላንድ ጋር የመቀናበርን ዕድል ልታቀርብ የምትችለው ተረጋግቶ መልማትን ካወቀችበት ነው፡፡ ሶማሊያ ዛሬ ባላት ያልጠናና ያልተረጋጋ አቅሟ ‹‹ዘራፍ!›› ብላ ወደ ኃይል መንገድ ብትገባ የሶማሊዎች ተያይዞ መጥፊያና የአፍሪካ ቀንድ መታመሻ ወኪል (ጣቢያ) ከመሆን በቀር፣ ሶማሌላንድን ዛሬ በግድ አካሏ ልታደርጋት አትችልም፡፡ የቀጣናው ትስስር አካል የሆነውን የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ጉድኝትም አትበጥሰውም፡፡ ከጦርነት በመለስ ‹‹ሶማሌላንድን ተነጠቅሁ ሉዓላዊ ግዛቴ ተደፈረ!›› ከሚል እኝኝ ጋር የሶማሌላንድንና  የኢትዮጵያን የጋራ ልማት ተራክቦ በአውዳሚ ሻጥሮች ማጥቃት ውስጥ ብትገባም፣ የራሷን ልማትና መረጋጋት ከማጥቃትና ከማስጠቃት በተጨማሪ፣ በቀጣናዊ የልማት ግስጋሴ በኩል የሚመጣውን የሶማሌዎች መሳባሰብ የማደናቀፍ/የማራቅ ሚና ነው የምትጫወተው፡፡

ሶማሌላንድና ኢትዮጵያም ‹‹የዕውቅና ቅድመ ሁኔታ›› የሚል ሰበብ ያገኘ የቀውስና የአሮጌ አስተሳሰብ ወኪል ተጎራብተው፣ ትስስራዊ ልማትንና የገቢ/ወጪ ንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ቢሞክሩ ብልኃት ያጣ (የፀጥታና የደኅንነት ወጪ የበዛበት) ተግባር ውስጥ መግባት ይሆንባቸዋል፡፡ ጥረታቸው እዚያው ፈላ እዚያው ሞላ ከመሆን ብዙ እንደማይርቅ መገመትም አይከብድም፡፡ መሠረተ ልማትን የሚያጠቃ ሰርጎ ገብ አሸባሪነት ምን ያህል እንደሚያከስር ማጤን በራሱ ጥንቃቄን የሚያስተምር ነው፡፡ ‹‹ዕውቅና›› ከሚባል ነገር ጋር መተሻሸት የአካባቢ ፀጥታን መደፍረስ ከመጥራቱም ባሻገር እስካሁን ባለው የይፋ ግንዛቤ መሠረት፣ የአፍሪካ መርህንና ውሳኔዎች ከማክበር ኃላፊነት ጋር የተያያዘ ሌላ መዘዝም የሚጎትት ነው፡፡ ይህንን መዘዝ አጢኖ በመጠንቀቅ ረገድም የኢትዮጵያ መንግሥት አስታዋሽ እንደማይሻ እተማመናለሁ፡፡

ስለዚህ ለሦስቱም አገሮችና ለአካባቢው የተረጋጋ ጉዞ የሚበጀው ከትስስር ጎዳና በመለስ ያለ የሶማሊያና የሶማሌላንድ መዋሃድና አለመዋሃድ የሁለቱ አገሮች ድርድር ጉዳይ (ኢትዮጵያ አፍራሽም አቀንቃኝም የማትሆንበት) መሆኑ ላይ መስማማት ነው፡፡ የአሁኑ የሶማሊያ መንግሥት በዚህ ላይ ለመስማማት አሻፈረኝ ቢል እንኳ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የሚያስሩት ውል የአፍሪካ ኅብረትን መርህ ያልጣሰ የሶማሊያን ኅብረት ያልተቃራነ (እንዲያውም የሶማሌዎችን የስብሰብ አድማስ ያሰፋ) መሆኑን በማሳየት፣ በሶማሊያ ውስጥም በአፍሪካ ኅብረትና በዓለም ውስጥ የሚበራከት ድጋፍ ማግኘት ይቻላቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...