Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉለአገራችን ችግሮች መፍቻ የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ

ለአገራችን ችግሮች መፍቻ የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

አገር ከሌለ ሰው የለም፣ ሰው ከሌለ አገር ከንቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ሁሉንም አስተካክሎ በልኩ እንዲኖር አድርጎ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ከእንስሳት መለየቱ መልካም ቢሆንም፣ ራሱን ብቻ ማስቀደም በማብዛቱ ዓለምን እየበጠበጠ ነው፡፡ ጦርነትን ፈጠረ፣ እርስ በርሱ ተጋደለ፡፡ ነገር ግን የሰውን ዘር ማጥፋት ባለመቻሉ በአምላክ ፈቃድ አቅመ ቢሱም ባለጉልበቱም ለተወሰነ ጊዜ ሲፍጨረጨሩ ይኖራሉ፡፡ ያ የሚዋትቱለት፣ የሚባዙኑለት፣ የሚጥረበረቡለትና የሚንገበገቡለት የምድር ሀብት ይቀርና ወደ የማይቀርበት ዘለዓለማዊ ቤታቸው በተወሰነላቸው ጊዜ ይጓዛሉ፡፡ በሥራቸው ደግሞ ደጉም በደግነቱ ክፉውም በክፋቱ ሲወሱ ይኖራሉ።

ይህ እንግዲህ የእኛ ደካሞች የሰው ልጆች ጉዞ መሆኑ ነው።                                                        ሰው ባለበት ዘመን ጥሩ ሠርቶ ማለፍ ለወገኑ፣ ለአገሩና ለተተኪው ትውልድ መልካም ሥራ ሠርቶ ማለፍ የተፈጥሮ ግዴታ መሆኑን ተገንዝበን ድርሻችን (ድርሻዬ) ምን ይሆን ብለን፣ ተስፋ ሳንቆርጥ በትዕግሥትና በመልካም አስተውሎት የምንችለውን አድርገን ማለፍ የተፈጥሮ ግዴታ መሆኑን ተገንዝበን ለጥሩ ብንሠለፍ፣ ያለምንም ተፅዕኖ ሁሉንም አሳክተንና ውጤት አሳይተን ለማለፍ ሰፊ ዕድል ነው ያለን።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለብዙ ንብረት ባለቤቶች ባለው ላይ እንጨምራለን ብለው ሲውተረትሩ እንደወጡ የቀሩ ብዙ ናቸው። ተስፋ ሳይቆርጡ ተግተው በመሥራታቸው ወደዱም ጠሉ የሚያስተዳድሩት ወገን ስላለ፣ ሥራቸው ፍሬያማ ቁምነገር አሳይቷል ማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ ለሌላው አያስቡም ቢባሉም፣ ወደውም ሆነ ሳይወዱ ሥራቸው መልካም ውጤት ሳያሳይ አይቀርረም፡፡ ምክንያቱም ለሚቀጥሩትና ለሚያስተዳድሩት ሰው የሚከፍሉት ደመወዝ፣ የሚያሰጡት የሕክምና አገልግሎት፣ የተቀጣሪው ልጆች ሳይቸገሩ ለመማር መብቃትና የነገ ሰዎች ለመሆን መብቃታቸው ሀብታሙ በዋለው ውለታ ስለሚሆን ነው።

ባለሀብቱ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የግለኝነት ተግባር ቢታይበትም፣ ተግቶ በመሥራቱ አስተዋፅኦ ማድረጉ ሊያስመሠግነው ይገባልና። ዛሬ ይህንን ያነሳሁበት ዋናው ዓላማ በጋራ የመሥራትንና አገርን የማልማትን ተገቢ መንገድ ለማስያዝ ተባብረን ብንነሳ ከሚል ዕሳቤ ነው።

ሁሉም ፀጋ የሞላትና የተረፋት ኢትዮጵያ ልጆቿ ተርበው፣ ተጠምተው፣ ታርዘውና መግቢያ አጥተው መንከራተት ይገባቸዋል ወይ ብዬ ራሴን ስጠይቅ ኃፍረት ይሰማኝና መልስ አጥቼ እቸገራለሁ። ‹‹አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ›› የሚለውንም የአበው ምሳሌ እያስታወስኩ እገረማለሁ።

ምክንያቱስ ብትሉኝ እኔ ከቤት ቤት ሳማርጥ፣ ከምግብ ምግብ ሳቀያይር፣ የልብስ ዓይነት ስለዋውጥ፣ ቆንጆና ዘመናዊ መኪና ሌላው ሲነዳ ሳይ እኔ ለምን ይህ መኪና አልኖረኝም ብዬ ለፉክክር ሲዳዳኝ፣ የዘለቀ፣ የገብረ ማርያም፣ የኢብሳና የተወልደ ልጆች አሜሪካ ስለሄዱ የእኔ ልጅ ለምን አይሄድም ብዬ በሌሎች ቀንቼ የምይዘውንና የምጨብጠውን ሳጣ፣ አንዱ ወገኔ ደግሞ እባክህን አንዴ የምጎርሳትን የዳቦ መግዣ መፅውተኝ ሲለኝ፣ ሕፃን ልጅ አዝላ ለልጄ ወተት ሳይሆን ዳቦ መግዣ ስጠኝ እያለች ስትለምን ማየቱ ከሚያሳፍረንና ከሚያሳዝነን ሌላ ምን ይመጣብናል?

ለዚህ መሠረታዊ ችግር መድኃኒቱ መተሳሰብ፣ መነጋገር፣ መተማመንና ጥርጣሬን ከእዕምሮ ጨርሶ አጥፍቶ በቁርጠኝነትና በኅብረት ለልማት በየችሎታችን መነሳሳት ናቸው። አንዳንዶቻችን እኛ ድርሻችንን ሠርተን ጊዜያችንን አሳልፈናል፣ በቅቶናል፣ ከአሁን ወዲያ ራሳችንን እያስደሰትን መኖር ነው የምንሻው የምን ልንኖር እንችላለን። ይህ ደግሞ በቃን፣ ሠልጥነናል፣ ለምተናል፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪና በጠቅላላው በሳይንስ ተራቀን ዓለምን ገዝተናልና ከአሁን ወዲያ የእነዚያን የገዛናቸውን የባሮቻችንን አካሄድ ቁጭ ብለን እንመልከት፣ እንሳለቅባቸው ብለው ከሚዛበቱብን ለየት ብለን ለጋራ ጥቅማችን እንነሳ፡፡

የሠለጠንን ባዮችን ፌዝ ወደ ራሳቸው መልሰንና ራሳችንን በመቻል እነሱን ወደ ማስናቁ ደረጃ የምንችልበትን ሁኔታ የመፍጠር ግዴታችንን ለመወጣት ሠርቼ፣ አገልግዬ፣ ውጤት አሳይቼ እዚህ ደርሼያለሁና በቃኝ ለማለት የሚቻል ሁኔታ ውስጥ አይደለንም ያለነው፡፡ ግማሽ ጎናችን ተራቁቶ፣ ግማሽ ጎናችን አጊጦ መታየትን ሳይሆን ለቀሪው ወገናችን ጋሻና መከታ፣ ከዚያም አልፎ መመኪያ በመሆን የእነሱን የፍጅት አጀንዳ እናስቁም፡፡ ከዚህ በፊት ያየነውን ልምድ ወደ ራሳችን በመለወጥ በሕይወት እስካለን ድረስ መሞከር እንጂ፣ ቁጭ ብለን ጊዜዬን ጭርሼያለሁ፣ አሁን የማረፊያ ጊዜዬ ነው ማለት አይቻልም፡፡

እስትፋሳችን እስካለች ድረስ በቁርጠኝነት ለወገናችን፣ ለአገራችንና ለመጪው ትውልድ ጠቃሚ ተግባር ማበርከት እንጂ፣ የማረፊያችን ጊዜ የሚቆመው ነፍስና ሥጋችን ሲለያዩ ብቻ መሆኑን ተገንዝበን በምንችለው ሁሉ ተባብረን አገራችንን ወደፊት እናራምድ፡፡ የእያንዳንዳችን ፍላጎትና ግዴታም ጭምር መሆን ስላለበትም ነቅተን በጋራ እንቁም ነው ሐሳቤና መልዕክቴ።  

ለመሆኑ እስካሁን ምን ተሠራና ነው እኔ በበኩሌ የሚገባኝን ድርሻ ተወጥቻለሁ ብለን በቃን የምንለው? በወጣትነታችን ጊዜ የሠራነው ለራሳችን መተዳደሪያ፣ ሕይወትን መለማመጃ አገልግሎትና ከነባሩ ለመማር የተሯሯጥንበት እንጂ እንደ እነ ሐኪም ወርቅነህና እንደ መላኩ በያን የሰው አገር ተምረን መጥተን የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ ሆነን ግልጋሎት አልሰጠንም፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተማሩልን፣ ለአገር ለወገን ተስፋ ናችሁ ብለው ባዘጋጁት ዕድል ተምረንና ደርሰን አገርን ለማገልገል የተማረው ወጣት በተነሳሳበት፣ በወኔ ተገፋፍቶ ለአገሩ ሊሠራ በተውተረተረበት ዘመን አገራችን ጉድ ሆነች፡፡

እነዚያ የማይተኙልን የጥቁር ጠላቶች ባዘጋጁት ወጥመድ የተጠመዱ በጣት የማይቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን የታሪካዊ ጠላቶቻችንን መልዕክት እንደ ወረደ ተቀብለው መጥተው ባሠራጩት መርዝ አገራችን ተበከለች፡፡ እነሆ ከዚያ መከራና ቀውስ ለመውጣት በተቸገርንበት ጊዜ የጡረታም ሆነ የማረፊያችን ጊዜ ስላልሆነ፣ በሉ የምንችለውን እያስተማርንና በልማት ዘርፍ እየመራን ወገናችንን እንርዳ፡፡ ሁሉም ነገር የሞላትን ውድ አገራችንን ወደ ሥልጣኔ መንገድ እንምራት።                                                                  

የጠላቶቻን ሐሳብና ምኞት ይህችን ኩሩና ነባር አገር ከማልማት ይልቅ ወደኋላ እንድታሽቆለቁል ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ አሳሳቢ ሴራ ተጠናክረንና ተባብረን መነሳት እንጂ የምን ማረፍ? በአገራችን ጉዳዮች በቅጡ አለመነጋገራችን ዋጋ እንድንከፍል ስላደረገን በተቻለ መጠን በምንችለው ሁሉ እንተባበር፡፡ መጪውን ትውልድ ሥራ አስተምረን ለመልካም ውጤት የማብቃት ግዴታ አለብንና ተባብረን እንነሳ ስል የአነሳሳችንንም ዘዴ በመጠቆም ነው።

እንደምታውቁት ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀኃብት ከአፍሪካ አንደኛ በዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዓለም አቀፍ ጥናት ያስረዳል፡፡ ታዲያ እንደ አንደኛነታች ውጤታማ ነን ወይስ ከንቱ ውዳሴ? ሁላችንም የምናውቀው ስለሆነ እንለፈው። ግን ማለፍ ብቻ ሳይሆን መላ እንምታበት፡፡

በዓለም ላይ የቁም እንስሳት፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ገበያ የደራው ከእኛ ይልቅ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ይቀርብ ይሆን? ይህንንም ለአንባቢያን ልተውና ወደ የሚቀጥለው ሐሳቤ ተሻጋግሬ የምኞት ጉዞዬን ላመላክታችሁ፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ የንድ በግ ዋጋ ስንት ነው? የአንድ በግ ሥጋ በኪሎ 6.09  ዶላር ነው፡፡

የአንድ ዶሮ ዋጋ ስንት ነው? አንድ ኪሎ ግራም የዶሮ ሥጋ 3.45 ዶላር፡፡ ይህንን በሚሊዮን ዶሮች በሳምንት አባዙትና የዓመቱን ሥሌት ድረሱበት፡፡ የአንድ ዕንቁላል ዋጋ ስንት ነው? 30 ዕንቁላሎች 21.75 ዶላር ሲሆኑ ይህንንም በተመሳሳይ እዩልኝ፡፡ የበሬ ሥጋ በኪሎ ስንት ነው?  አንድ ኪሎ ግራም 3.43 ዶላር መሆኑን ግንዛቤ ያዙና ኢኮኖሚስቶች ማብራሪያውን ይስጡን፡፡                      

ሰላጣ ወይም ጎመን (አትክልት) በኪሎ 0.87 ዶላር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለምሳሌ ሙዝ በኪሎ ከ17.00 ዶላር በላይ ሲሆን፣ ለገበያ ፍለጋና ዝግጅት እኔ አለሁላችሁ፡፡ ፓፓያ፣ አፕልና የመሳሰሉት በኪሎ ከ11.00 ዶላር በላይ መሸጥ ይቻላል፣ ይህም አሁን ያለበት የጊዜው ዋጋ ነው። 

ይህ በብዙ ዕቅድ ተጠንቶ በዶሮ ዕርባታ ከ20 እስከ 40 ድርጅቶችን በማቋቋም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዕንቁላልና ዶሮ በማርባትና በማባዛት ወጣቱን ብናሰማራ፣ ከሥራ አጥነት ወደ ሠራተኛ እጥረት ልንደርስ እንችላለን፡፡

በርካታ ድርጅቶችን በከብት ማደለብ ሥራ ብናስገባና በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት በየፈርጁ ማሰማራት ይቻላል፡፡ በምግብ ዘይት ዘርፍም ቢሆን ሀብታም ሆነው ዓለምን ከሚያንቀጠቅጡ ተራ መሠለፍ አያቅተንም፡፡ በርካታ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ስንችል የውጭ ምንዛሪ ችግር የሚባል ነገር በደጃችንም አያልፍም፡፡ መተባበርንና ለጋራ አገር እጅ ለእጅ ተያይዞ መነሳሳትን ከልብ ይዘን፣ የመለያየትን አባዜ አስወግደን ለአገርና ለወገን ተግተን በተደራጀና በተባበረ ሁኔታ ብንነሳ ማንም እንደማይቀድመን ላረጋግጥ እወዳለሁ። 

ነባር አርቢ ማኅበረሰቦች በተቻለ መጠን በማበረታትና መሬት፣ የባንክ ብድርና ሌሎች ድጋፎን በማድረግና የውጭ ዕርዳታም በማስተባበር ከፍተኛ ርብርቦሽ ተደርጎ ከሦስትና ከአራት ሚሊዮን የማያንሱ ዕንቁላሎች፣ ዶሮዎች፣ በጎችና የሥጋ ከብቶችን ባለማቋረጥ በየሳምንቱ ለሳዑዲና ለሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ መላክ ይቻላል፡፡

በመቀጠል እንደ ቡና፣ ሰሊጥና ተመሳሳይ ምርቶችን በነበረበት ሁኔታ ሳይሆን ዘመናዊ አሠራሮችን በመጠቀም በጋራ ብንሠራባቸው አገራችን ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ችግርም ሆነ፣ የወገኖቻችንን ሥራ አጥነት በፍጥነት በመቅረፍ በየበረሃው የሚያልቀውን ወጣት በመታደግ ወደ ታላቅ አገርነት እናመራለን፡፡ ይህንን ሐሳብ በትንሹ ሳይሆን በስፋት በማጥናትና በማቀድ ወደ ሥራ ለመግባት የበኩላችንን እንድንወጣ ሳሳስብ፣ የገበያውን ሁኔታ በተመለከተ አጠቃላይ ኃላፊነቱን ለመውሰድ ዝግጁ መሆኔን እየገለጽኩ ነው።

ከፊታችን የሚገጥሙንን ችግሮች በሚከተለው መልክ እንቋቋማለን፡፡ መሬትን በተመለከተ ይህ ዕሳቤ ለግል ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን የመሻሻል ዘመቻ በመሆኑ፣

  1. 1. መንግሥት በግንባር ቀደምትነት በጉዳዩ ገብቶ አዎንታ ውሳኔ ሰጥቶ ድርጅቱን ለማቋቋም ሙሉ ድጋፍና የመጀመሪያውንም ሥራ ለማስጀመር የመርዳት ኃላፊነት አለበት፡፡
  2. 2. ወገን ባለሀብቶች ከልባቸው በመነሳሳት የዚህ የተቀደሰ ሐሳብ ተከፋዮችና አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
  3. 3. በጉቦም ሆነ በደጅ ጥናት ጊዜ እንዳይባክን መንግሥት ጥብቅና ሕጋዊ የሆነ ቋሚ ሥርዓት ማበጀት ይኖርበታል፡፡
  4. 4. የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቅድሚያ በመስጠት ተባባሪ መሆን አለበት እላለሁ፡፡
  5. 5. ሁሉም ዜጋ ሌት ተቀን የራሴ ነው ብሎ መነሳሳትና ለውጤት ኅብረት ማጎልበት አለበት።

በመጨረሻም ነባሩን የቡና ገበያ ለማሻሻል ገበሬዎችን በዘመናዊ አሠራር ማራመድና ማበረታታት፣ ቡናችን ለብሌንዲንግ የማሻሻጫ ቅመም እንዲሆን ከሚገበያይ ይልቅ፣ ራሳችን የገበያው መሪ ለመሆን ቅድሚያውን መውሰድ አለብን፡፡ ለዚህም ለውድድሩ በሚያበቃን ሁኔታ የቡና ምርትን ለማብዛትና ተወዳዳሪ ሆነን ለማሸነፍ መነሳሳት እነ ኑግንመ ሰሊጥንና በአጠቃላይ ሌሎች ምርቶችን በሚገባ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀትን ጨምረን የአገራችንን ችግር መቅረፍ ስለምንችል በዚህ ጉዳይ ተባብረን እንነሳ፡፡

መንግሥት አያሠራም የሚለውን ምክንያት በኅብረት እንሞክርና ካልሆነ ያኔ የተባለው አያሠሩም የሚለውን ይዘን እንተማማ እንጂ፣ ገና ለገና በይሆናል ተሸብበን ጊዜያችንን አናጥፋ።

ይህ ጉዳይ ለግል መጠቀሚያ ከሆነ መንግሥት አይሆንም ቢል ምንም አያከራክርም። የእኛ ዕርምጃ ግን ወገንን፣ አገርንና መጪውንም ትውልድ መስመር የሚያስይዝ መንገድ ከፋች በመሆኑ፣ መንግሥት ይህንን አይደግፍም ብዬ አላስብም፡፡ በሚገባ ይደግፋል ያበረታታል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

ከአዘጋጁ ጸሐፊው ከዚህ ቀደም የሕይወት ታሪካቸውን የሚዘክር ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...