Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከድቅድቅ ጨለማ ለማምለጥ አዲስ የሉላዊ ማኅበራዊ ዕድገት አጀንዳን መቅረፅ ምሥረታ

ከድቅድቅ ጨለማ ለማምለጥ አዲስ የሉላዊ ማኅበራዊ ዕድገት አጀንዳን መቅረፅ ምሥረታ

ቀን:

በባሕሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)

ይህ በርዕሱ የተመለከተው ሐሳብ እ.ኤ.አ በ2014 በፓሪስ ከተማ የተመሠረተው የዓለም አቀፍ ማኅበራዊ ዕድገት ፓነል (International Panel on Social Progress, -IPSP) አንግቦ የተነሳውን ዓላማ ያመላክታል፡፡ ምኅፃረ ቃሉ ከበይነ መንግሥታቱ የአየር ንብረት ለውጥ ፓነል (Intergovernmental Panel on Climate Change, IPCC) ጋራ ከመመሳሰሉ የተነሳም፣ የዚያ ዝነኛ ተቋም ማኅበራዊ ዘርፍ ተብሎም ይጠቀሳል፡፡ ተቋሙ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፣ ከሦስት መቶ በላይ ደራስያን የተሳተፉበትን የመጀመሪያውን ሪፖርት የሃያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን ኅብረተሰብ መተለም (Rethinking Societies for the 21st Century) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2018 ለኅትመት አብቅቷል፡፡

ፓነሉ በአስተባባሪ ካውንስል የሚመራ ሲሆን፣ የአማካሪዎች ቦርድና የክብር አባላት ኮሚቴም አለው፡፡ 74 አባላት ካሉትና የመጀመሪያ ስብሰባውን እ.ኤ.አ. በመስከረም 2016 ዓ.ም. በፓሪስ ካደረገው የአማካሪዎች ቦርድ መካከል ስድስቱ ከአፍሪካ አገሮች ሲሆኑ፣ ከእነሱም ውስጥ እኔም እገኝበታለሁ፡፡ ለፓነሉ ዓላማ መሳካትም የሚከተሉት ታዋቂ ግለሰቦች ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል፡፡ የኖቬል ተሸላሚው ኢኮኖሚስቱና ፈላስፋው አማርትያ ሴን፣ ሌላው የኖቬል ተሸላሚ የባንግላዴሹ የማይክሮ ፋይናንስ ፋና ወጊ ሙሐመድ ዩኑስ፣ የቀድሞ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔስና በዩኔስኮ የማኅበራዊና ሥነ ሰብዕ ሳይንስ ረዳት ዋና ዳይሬክተር ጋብርኤላ ራሞስ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ተግዳሮቱ

ዓለም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአካባቢ አየር መዛባት፣ ማኅበራዊ ኢፍትሐዊነት፣ የዴሞክራሲ ማሽቆልቆል፣ ቀውስ አዘል ቴክኖሎጂና የሉላዊ ትብብር ዕጦት እየተፈተነች ትገኛለች፡፡ በቅርቡ የተከሰቱት ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች፣ ጦርነቶችና የአየር ጠባይ መዘበራረቅ ማኅበረዊ ትስስርንና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በብርቱ ፈትነዋል፡፡ ከዚያም አልፎ እስካሁን የተከተልናቸው የልማት ሥልቶች ያለባቸውን ክፍተት በግልጽ አሳይተዋል፡፡

በፓነሉ ሥር የተሰባሰብነው ምሁራንና የኅብረተሰብ ተዋናዮች ከከባቢዊና አገራዊ ዓውድ ባሻገር፣ የእነዚህን ተግዳሮቶች ተወራራሽነት መገንዘብ እንዳለብን እናምናለን፡፡ ይህ ለችግሮቹ ሁነኛ መፍትሔዎችን ለመሻትና በሚከሰቱት መልካም አጋጣሚዎችም ለመጠቀም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

የማኅበራዊ ዕድገት ትርክት በፓነሉ ዕይታ

ከሁሉ በፊት ለምንመኘው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ራዕይ ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህ ራዕይ የሚከተሉትን የሚያካትት ይሆናል፡፡ ከሁሉ በፊት ገበያውንና ኮርፖሬሽኖችንን በመግራት አካታች የሆነና ኃላፊነት የሚሰማው ኢኮኖሚ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለአካባባዊ ሁኔታዎች ሥርዓት ሲበጅላቸውና ሰፊና ሕዝባዊ ዓላማ እንዲላበሱ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ በተጨማሪም አሳታፊ የሆነ ዴሞክራሲን መገንባትና የተሻለ የመረጃ ሥርዓትን መዘርጋት ይሻል፡፡ ሉላዊ ተግዳሮትን ለመቋቋም ብዝኃ ሕይወትን መንከባከብና ቴክኖሎጂን ለበጎ ውጤት ማዋል ይጠይቃል፡፡

ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ዕድገት ፓነል እ.ኤ.አ. በ2018 ባወጣው ሪፖርት አማካይነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዘላቂ የዕድገት ግቦች (Sustainable Development Goals) ለማሳካት የሚያግዝ አቅጣጫ በማስቀመጡ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝቷል፡፡ በእኩልነት፣ በነፃነት፣ በተሳትፎና በአካታችነት እሴቶች ላይ የተመሠረቱ ተቋማትና ለውጦችን ያካተተ የዕድገት ራዕይ ለዓለም አበርክቷል፡፡

የተሻለ ኅብረተሰብ ለመፍጠር አዲስ እመርታ

የተሻለ ኅብረተሰብን ለመፍጠር የተለያዩ የተናጠል ዕርምጃዎች በመንግሥትም፣ በሲቪል ማኅበረሰብም ደረጃ ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በሲቪል ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተዋንያን ለዚህ አጀንዳ መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል፣ ከእነሱም ብዙ መማር እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ቋሚ ችግሮች በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ይህንን ድክመት ስንወጣ ነው ለማኅበራዊ ዕድገት ማነቆ የሆኑትን ማኅበራዊ፣ አካባቢያዊና አስተዳደራዊ መሰናክሎች ማለፍ የምንችለው፡፡ የፓነሉ የ2024 – 2027 አዲስ የሥራ ዕቅድም እንዲህ ያሉትን ጥምረቶች በመገንባት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የወደፊት አቅጣጫ

ፓነሉ እ.ኤ.አ. በ2023 ብዙ አባላት ያሉበትን የአማካሪዎች ቦርድ የመጀመሪያ ስብሰባ በማካሄድ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ ሳይንሳዊ ሚዛናዊነትና ነፃነት መለያው እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ተከታይ ሥራው ወደ ብዙኃን ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመውረድ፣ እንቅስቃሴውን ስፋት መስጠትና የበለጠ ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ ከሳይንስም ከልምድም ድንበር ዘለልና በይነ ዲሲፕሊናዊ ዕውቀት በመቅሰም የብዝኃ ተዋንያን መስተጋብርን ለመረዳት ይጥራል፡፡ በዚህ ረገድ ለደቡቡ የዓለም ክፍልና ውክልና ለተነሱ ድምፆች የተለየ ትኩረት ይሰጣል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2024 ጀምሮ ፓነሉ ለውጥ አምጪዎችን ለማገዝና የሽግግሩን ሒደት ለማሳለጥ አዳዲስ ሥልቶችንና ዘዴዎችን ሥራ ላይ ያውላል፡፡ በሚከተሉት መንገዶች የማኅበራዊ ዕድገት አጀንዳን ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራል፡፡

 • ነባሮቹ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማት ያለባቸውን መሠረታዊ ድክመቶች ለመቅረፍ ማሻሻያዎች መቀየስ፣
 • የለውጥ ሐሳቦችን በማበረታታት ለማኅበራዊ ዕድገት ያለውን ዕምቅ ችሎታ ማጎልበት፣
 • የተዛቡ የኃይል ሚዛኖችን በማቃናትና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን በማጎልበት የጋራ ውሳኔዎችን ቅቡልነት ማጠናከር፣
 • ሉላዊ ደኅንነትንና ኅብረትን በማበረታታት ግጭትን ማስወገድ፣
 • ከተፈጥሮ ህዋሳን ጋር ያለንን ግንኙነት በውል በመረዳት የሕይወትን ውስብስብና ዳይናሚክ የሆነ መስተጋብር ማክበር፡፡

ፓነሉ የለውጥ አራማጆች እንዲገናኙና ጥምረት እንዲፈጥሩ የሚያግዝ የጋራ የዕውቀት ማዕከል ይፈጥራል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከሚቀጥለው ሰኔ ወር ጀምሮ የለውጥ ዕርምጃዎችና ፕሮጀክቶች የሚከማቹበት የዓለም አቀፍ ማኅበራዊ ዕድገት መድረክ (International Platform for Social Progress) የተሰኘ የበይነ መረብ ማዕከል ሥራ ላይ ያውላል፡፡ ይህም ፓነሉ የማኅበራዊ ዕድገት አጀንዳውን ለማራመድ አጋዥ የሆኑትን ኃይሎች ነቅሶ ለማውጣት ይረዳዋል፡፡ የሚገኙት ግብዓቶችም በማኅበራዊ ዕድገት ዙሪያ የሚደረጉትን ክርክሮች በማስፋት፣ መንግሥታትና የንግድ ተቋማት ዓላማቸውን ከማኅበራዊ ዕድገት አጀንዳ ጋር እንዲያጣጥሙ ጫና ለመፍጠር ያግዘዋል፡፡

በፓነሉ ጥረት እንዴት መሳተፍ ይቻላል?

በዚህ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ብዙ ዕድሎችና አማራጮች አሉ፡፡ ተሳትፎውም ፈርጀ ብዙ ይሆናል፡፡ ከአነስተኛ ማኅበረሰቦች እስከ ግዙፍ የግንኙነት መረቦች፣ ሲቪል ማኅበረሰቡና ትልልቅ ኮርፖሬሽኖች፣ ከከተማ አስተዳደሮች እስከ ድንበር ዘለል ድርጅቶች፣ ከትምህርት ማዕከሎች እስከ መደበኛና ሶሻል ሚዲያ፡፡ ቴክኖሎጂ ዕውቀትን በማሸጋገርና ለውጥ አምጪዎችን በማስተሳሰር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ፓነሉ በሚከተሉት ዘርፎች የሥራ እንቅስቃሴ ለማድረግ ውጥን አውጥቷል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም አግባብነት አላቸው ብለው በሚያምኑት መስኮች መሳተፍ የሚፈልጉ ንድፈ ሐሳባቸውን (ፕሮፖዛል) ማቅረብ ይችላሉ፡፡

 • ከማኅበራዊ ተግዳሮቶች ጀርባ ያሉትን የሲስተም መስተጋብርና የኃይል አሠላለፍ ነቅሶ ማውጣት፣
 • በዚህ የሶሻል ሚዲያና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘመን የመረጃ ሲስተሙን ለሕዝብ በሚጠቅም መንገድ ማደራጀት፣
 • የአካባቢ ጥበቃ ሕግ (Environmental Rule of Law) የሚከበርበትን ሥልት መቀየስ፣
 • የመንግሥትና የግሉ ሴክተር ተግባራት ማኅበራዊ ዕድገትን በሚያጎለብት መንገድ እንዲከናወኑ ማድረግና
 • ሉላዊ ዜግነትን ለማስረፅ ሉላዊ ትብብርን ማጠናከር፡፡
 • የፓነሉ ተግባር ግዙፍ የሆነውን ያህል ፋታ የማይሰጥም ነው፡፡ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ብዙ ዕድሎች አሉ፣ ሳይረፍድ እንጠቀምባቸው፡፡

ለተጨማሪ መረጃ የፓነሉን ድረ ገጽ https://www.ipsp.org/ መመልከት ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የታሪክ ጸሐፊ፣ ተመራማሪ፣ መምህርና የፓነሉ አማካሪ ቦርድ አባል ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bahru.zewde@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...