Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየተመድ ዋና ጸሐፊ ሙስሊም ጠልነትን ያወገዙበት ንግግር አንድምታ

የተመድ ዋና ጸሐፊ ሙስሊም ጠልነትን ያወገዙበት ንግግር አንድምታ

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ እ.ኤ.አ. ማርች 15 ቀን 2024 በተመድ የጉባዔ አዳራሽ ባደረጉት ንግግር፣ የስብሰባው መሠረታዊ ዓላማ በመላው ዓለም የሚገኙ ቁጥራቸው ሁለት ቢሊዮን ያህል የሆኑ ሙስሊሞች የረመዳን ወር ማክበራቸውን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ረመዳን የመተሳሰብ፣ የመከባበርና የአንድነት ስሜት ከፍ የሚልበት፣ መተሳሰብና መደጋገፍ በብዙ አቅጣጫ የሚንፀባረቅበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሚስተር አንቶኒዮ ጉተሬስ የረመዳንን ወር ፋይዳ አስመልክተው አጠር ያለ መግቢያ ከሰጡ በኋላ፣ ‹‹ይህም ሆኖ በዓለም ላይ ለሚገኙ ብዙ ሙስሊም አገሮች የዘንድሮው ረመዳን ወር የጭንቀትና የፍርኃት ጊዜ ሆኗል። ስለሆነም ከሁሉ አስቀድሜ የረመዳን መንፈስ በተላበሰ ስሜት በጋዛና በሱዳን ያሉ ጠመንጃዎች ፀጥ እንዲሉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢስላም ጠል የሆነ ወቅታዊ አመለካከት ያሳሰባቸው አንቶኒዮ ጉተሬስ ‹‹ከዚህም በተጨማሪ፣ ዛሬ እዚህ ቦታ በተሰባሰብንበት በጣም ጠቃሚ መድረክ ላይ ሆኜ ሁሉም የዓለም፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የማኅበረሰብ መሪዎች ጦርነትና ጦርነት የሚያስከትለው ግፍ ተወግዶ ሰላምና መተባበር ይሰፍን ዘንድ የምናቀርበውን  ልመና ሰምተው ከእኛ ጋር እንዲቀላቀሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡

‹‹በዚህ ፍርኃት በሰፈነበት ዓለምና ጊዜው ስለሰላም ድምፅን ከፍ አድርጎ ማሰማት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ እንዳስታወሱት፣ በእርግጥም የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ብዙ ሙስሊሞች በምዕራቡ ዓለም ዘንድ ክብር እንደማይሰማቸው ይናገራሉ። በተለይም 52 በመቶ አሜሪካውያንና 48 በመቶ ካናዳውያን ሙስሊም ማኅበረሰቦችን አያከብሩም ይላሉ። በዚህ ረገድ የአሜሪካውን ጎላ እንጂ የጣሊያን፣ የፈረንሣይ፣ የጀርመንና የእንግሊዝ ሙስሊሞች ይስማማሉ፡፡

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም በሙስሊሙና በምዕራቡ ዓለም መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ዋና መንስዔ ሃይማኖትና ባህል በሁሉም ክልሎች ከፖለቲካ ይበልጣል። ስለኢስላሞፎቢያ በሚደረጉ ውይይቶች የሃይማኖት ልዩነቶች በሕዝብ መካከል የበለጠ ሥር የሰደዱ ናቸው በማለት ይገልጻሉ።

ጥናቶቹ በተጨማሪም፣ በአሜሪካ ፕሮግረስ ሴንተር የሚቀርቡ የተሳሳቱ መረጃዎች በአሜሪካ ውስጥ ኢስላሞፎቢያን በንቃት እንደሚያበረታቱ ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎች ኢስላሞፎቢያን በማስተዋወቅ በአጠቃላይ ሕዝብ መካከል ጭፍን ጥላቻንና አድልኦ እንዲፈጠር አሉታዊ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በእርግጥም ጭፍን ጥላቻ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ጭፍን ጥላቻ ብቻ፣ እንደ አሉታዊ ፍርድ፣ አስተያየት ወይም አመለካከት፣ የሕዝቡን አጠቃላይ ደኅንነት የሚጎዳ ነው። ጭፍን ጥላቻ ከግልጽ ድርጊቶች ጋር ተዳምሮ ወደ አድልኦ ደረጃ መውጣት ለተጎጂዎቹ አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራል የሚል ዘገባ ያቀርባሉ፡፡

መረጃዎቹ እንደሚያመለክቱት አሜሪካ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የብሔራዊ ተወካይ ናሙናዎች ሞርሞኖች፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ካቶሊኮች፣ ሙስሊሞችና አይሁዶች በአጠቃላይ፣ አብዛኛው አሜሪካውያን ለሙስሊም አሜሪካውያን ጭፍን ጥላቻ እንዳላቸው ይስማማሉ። በተለይም 66 በመቶ አይሁድ አሜሪካውያንና 60 በመቶ አሜሪካውያን በአጠቃላይ ለሙስሊም አሜሪካውያን ጭፍን ጥላቻ አላቸው ይላሉ።

ያም ሆነ ይህ አንቶኒዮ ጉተሬስ ረመዳን በመላው ዓለም ለሚገኙ ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞችን አንድ የሚያደርግ የእምነትና የአምልኮ ምሰሶ መሆኑን ጠቅሰው ‹‹ምንም እንኳን የረመዳን ወር የሚከበረው በራሳቸው በሙስሊሞች ቢሆንም፣ ኢስላም ከዚህ በታች በምዘረዝራቸው ታሪካዊ ክስተቶችና ክንዋኔዎች ምክንያት የጋራ ታሪካችን ምሰሶ መሆኑንም እናስታውስ፤›› በማለት፣ ዓረቦች ለመላው ዓለም ያበረከቱት ለዘመናት ወሳኝ የባህል፣ የፍልስፍና፣ የስኮላርሺፕና የሳይንስ ምንጭ መሆናቸው አሌ ሊባል እንደ ማይቻል እንደሚከተለው አስረድተዋል።

ሙስሊሞች የፍልስፍና፣ የስኮላርሺፕና የሳይንስ ምንጭ መሆናቸውን ምሳሌ ጠቅሰው ሲያብራሩ፣ ‹‹ታላቁ ሙስሊም ሐኪምና ፈላስፋ አቪሴና  የፕላቶና የአርስቶትል ፍልስፍናዎች ትርጓሜ በምዕራብ አውሮፓን እንዲታወቁና እንዲስፋፉ ያደረገው አስተዋጽኦ ምንጊዜም ሲታወስ የሚኖር ነው። አል ኸዋሪዝሚ በመባል የሚታወቀው ሙስሊም የሒሳብ ሊቅና የሥነ ፈለክ ተመራማሪ  ‹‹የሂንዱ ዓረብ ቁጥሮችና የአልጀብራ አባት›› ተብሎ እንደሚጠራ የታወቀ ነው። ያለ ኸዋሪዝሚ ዛሬ የምንጠቀምበት ቁጥርና የሒሳብ ሥሌት ምንጭ የሆነውን አልጀብራ ማሰብ ከቶ አይቻልም። የአመክንዮአዊ አስተሳሰብ አባት (Father of Rationalism) አቬሮይስ፣ የእሱ ወሳኝ ትችቶች ኢስላማዊና ምዕራባውያንን አስተሳሰቦችን እንዳቆራኙም ሐቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህ ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በቁጭት፣ ‹‹በእርግጥም ሙስሊሞች በየዘርፉ  በተለይም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሕክምና፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ጥበብ፣ በሙዚቃና በሥነ ሕንፃ ላደረጉት ሥፍር ቁጥር የሌለው አስተዋጽኦ ምሥጋና ሊቸራቸው በተገባ ነበር፤›› በማለት የገለጹት፡፡

ዋና ጸሐፊው ጉዳዩ ከአሳሳቢ ደረጃ መድረሱን አስመልክቶ በአፅንኦት እንደገለጹት፣ ‹‹ይህም ሁሉ ሀቅ ኖሮ የዛሬው ክስተት እስልምናንና ሙስሊሞችን ሙሉ በሙሉ የሚክድ ኢስላም ጠል (ኢስላሞፎቢያ) አመለካከት እየተንፀባረቀ ይገኛል። በእርግጥም ባለማወቅ ላይ የተመሠረተ፣ የማይካድ አስተዋጽኦን የሚወክል ፀረ ሙስሊም የጥላቻና የትምክህት ማዕበል ተከስቷል። ይህም ክፉ መቅሰፍት እያየለ በመሄድ ላይ መሆኑ በገሃድ እየታየ ነው፤›› ያሉት ጉተሬስ፣ ኢስላሞፎቢያ (እስላም ጠል አመለካከት) ወረርሽኝ ከሚንፀባረቅባቸው በርካታ ሥልቶች ውስጥም በውጭ አገር በተሰደዱ ሙስሊሞች ላይ የሚፈጸሙ በደሎች ይጠቀሳሉ። እነሱም፣

  • መዋቅራዊና ሥርዓታዊ መድልኦ፣
  • ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ መገለል፣
  • እኩል ያልሆኑ የኤሚግሬሽን ፖሊሲዎች፣
  • ያልተፈቀደ ክትትልና መገለጫ፣
  • ዜግነትን፣ ትምህርትን፣ ሥራንና ፍትሕን የማግኘት ገደቦች ናቸው፡፡

‹‹እነዚህና ሌሎች ተቋማዊ መሰናክሎች ለሰብዓዊ መብትና ክብር ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት ይጥሳሉ። እንዲሁም በየትውልድ የሚስተጋባውን የመገለል፣ የድህነትና የመብት ዕጦት አዙሪት እንዲቀጥል ያደርጋሉ። በከፋፋይ ንግግሮችና በውሸት ወሬዎች የተዛባ አስተሳሰብን በማስፋፋት፣ ማኅበረሰቡን በማጥላላትና አለመግባባትና መጠራጠርን በመፍጠር አስከፊ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች በማኅበራዊ ሙያው ጭምር በሰፊው እየተሠሩ ነው፤›› በማለት የችግሩን ጥልቀትና ስፋት አመልክተዋል፡፡

በእርግጥም ነገሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ብሪታንያዊው ፕሮፌሰር ኢምራን አዋን ባደረጉት ጥናትና ምርምር ያሳያሉ፡፡ ፕሮፌሰር አዋን የወንጀል ፕሮፌሰርና በበርሚንግሃም ሲቲ ዩኒቨርሲቲ የተግባራዊ ወንጀል ጥናት ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ናቸው። ፕሮፌሰሩ ከአሥር ዓመታት በላይ ከጥላቻ ወንጀሎች፣ ከጽንፈኝነትና ኢስላሞፎቢያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን ያካሄዱ ሲሆን፣ ጥናቶቻቸው በተለይ በብሪታንያ ውስጥ ኢስላሞፎቢያ ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች ጥልቅ ምርምርን አሳትመዋል። እሳቸው በእስላምፎቢያ ላይ ያደረጉት ጥናትም ትልቅ የፈጠራና የምርምር ፕሮጀክቶች አካልና የታላቋ ብሪታንያ የፖለቲካ መሪዎችን አቅጣጫ አመላካች ሆኖ ቆይቷል፡፡

ፕሮፌሰር አዋን የእንግሊዝ መንግሥት እንደ ኢስላሞፎቢያ ፍቺ እንዲወሰድ፣ ‹‹በሙስሊሞች ወይም ሙስሊም ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ያለው ፍርኃት፣ ጭፍን ጥላቻና ጥላቻ በማስፈራራት ወደ ቁጣ፣ ጠላትነትና አለመቻቻል የሚመራ ነው። በመስመር ላይም ሆነ ከመስመር ውጪ በሙስሊምና ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ላይ ማዋከብ፣ ማጎሳቆል፣ ማነሳሳትና ማስፈራራት። በተቋማዊ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ጠላትነት የተነሳ ወደ መዋቅራዊና ባህላዊ ዘረኝነት የሚሸጋገር የሙስሊም ማንነት ምልክቶችና ምልክቶች ላይ ያነጣጠረ ነው፤›› በማለት ኢስላሞፎቢያ የጥላቻ ወንጀል በጥላቻ፣ ወይም በግለሰብ ማንነት ላይ ባለው ጭፍን ጥላቻ የተነሳ ክስተቶችን ለመግለጽ በሰፊው ትርጉሙ የሚያገለግል ጃንጥላ ጽንሰ ሐሳብ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

‹‹በመሠረቱ ሙስሊሞችን መፍራት ጭፍን ጥላቻ ነው። ሙስሊሞችን ከመጥላትና ከመፍራት ጋር በተያያዘ ማስፈራራት፣ ማዋከብ፣ ማንገላታት፣ ማነሳሳት ወደ ቅስቀሳና ለመቻቻል የሚመራ ከመሆኑም በላይ በሙስሊም ማንነት ምልክቶችና ምልክቶች ላይ ያነጣጠረ ነው፤›› ይላሉ ፕሮፌሰር አዋን፡፡

በዩሮ ኒውስ “view@euronews.com” የተሰኘው ድረ ገጽ ለንባብ ያቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያመለክተው፣ በመላው አውሮፓ ኢስላሞፎቢያ እየተስፋፋ ነው። ድረ ገጹ እንዳሰፈረው ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ሃማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፣ በመላው ዩናይትድ ኪንግደም በ365 በመቶ ፀረ ሙስሊም የጥላቻ ድርጊቶች እየጨመሩ በመጡበት ወቅት ነው። የውጭ ዜጎች ጥላቻ በፖለቲካ ሥልጣን እርከኖች ውስጥ ከመደበኛ በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሆኖም የብሪታንያ መንግሥት የአንድነት መልዕክቶችን ከማስተዋወቅ ይልቅ በሚያቃጥሉ ንግግሮች ምላሽ ሰጥቷል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ለሌላ የሙስሊም ፓርላማ ምላሽ እንደ እስላማዊ ፎቢያ መጠቀማቸው እንደ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚጠቀስ ነው፡፡

ለአደጋ የተጋለጡት አናሳዎች ብቻ ሳይሆኑ የምዕራቡ ዓለምም ጭምርና የጋራ የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት እሴቶቻችን ናቸው ሲል ናዝ ሻህ ጽፏል። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አናሳ ብሔረሰቦችን ከጀርመን ለማባረር በአፍዲ ፓርቲ ባለሥልጣናትና በኒዮ ናዚዎች መካከል የተደረገ ሴራ ይፋ ሆኗል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊም፣ ‹‹በአንድ በኩል ሙስሊሞች ወደ ትንኮሳ እንዲያመሩ የሚያደርጉ የተንኮል ሴራዎችን እየሸረቡ ራሳቸውን ለመከላከል ሲነሱ ግልጽ የሆነ ጥቃትን ሲፈጽሙባቸው ይታያል። ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን በዓለም ዙሪያ ባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች እየተዘገበ ነው። አንዳንዶች ፀረ ሙስሊም ጥላቻንና አግላይ ፖሊሲዎችን ለፖለቲካዊ ትርፍ እያዋሉት ነው። ይህንንም አስከፊ ተግባር በስሙ ‹ጥላቻ› ብለን ልንጠራው ይገባል፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ስለሆነም የጥላቻ ንግግር አራማጆች በታሪክ ውስጥ በጣም ኃይለኛ የሆነውን ሜጋፎን አፀያፊ አስተሳሰባቸውን ለማጉላትና ለማሠራጨት ያላግባብ እየተጠቀሙበት ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ይህን አፀያፊ ተግባር በመፈጸም ግንባር ቀደም ሚናውን በመጫወት ላይ ይገኛል፤›› በማለት አውስተው፣ ‹‹24 ሰዓት ክፍት የሆኑት ድረ ገጾች ለጽንፈኛ አስተሳሰቦችና ትንኮሳዎች መፈልፈያዎች ሆነዋል። ይህ መከፋፈልን የሚያጠናክር ብቻ አይደለም። በእውነተኛ ሕይወት ላይ ብጥብጥ እንዲፈጠርም ያደርጋል፤›› ሲሉ በይፋ አሳውቀዋል፡፡

በእርግጥም “Cross Government Anti-Muslim Hatred Working Group (HCL0034)” የተሰኘ ነፃ የሆነ አጥኝ ቡድን ለታላቋ ብሪታንያ መንግሥት እንዳቀረበው በካምብሪጅ፣ በሱሴክስ፣ በርሚንግሃም፣ በሌስተር (እና ሌሎች) ዩኒቨርሲቲዎች የተደረጉ ምርምሮችም ኢስላሞፎቢያ ወይም ፀረ ሙስሊም አድሎአዊነት በሥራ ቦታ፣ በምልመላ፣ በትምህርታዊ ቦታዎች የእስልምና ጥላቻ ልምዶች በመጨመር ላይ መሆናቸውን ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ በተመሳሳይ ስለብሪቲሽ ሙስሊሞች በመገናኛ ብዙኃን የሚሰጡ አሉታዊና አድሏዊ መግለጫዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እንዳሉ መገንዘብ ተችሏል፡፡ አንዳንድ ወላጆች በሚደርስባቸው ጥላቻ ምክንያት ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት የማስወጣት አዝማሚያ እየጨመረ መምጣቱ የሚያመለክተውም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ በተለይም ከለንደን ውጪ እንደ ብራድፎርድና ሊድስ ባሉ ከተሞች ውስጥ ሙስሊም ሴቶች፣ ወጣት ሙስሊሞች፣ ጥቁር ሙስሊሞች፣ አካል ጉዳተኞች ሙስሊሞች፣ ለጥላቻ ያላቸው ተጋላጭነት በጣም ከፍተኛ መሆኑን የታላቋ ብሪታንያ መንግሥት ይገነዘባል፡፡

ውድ አንባቢያንም የሙስሊም ጥላቻን በሚመለከት የተወሰኑ አገሮች በምሳሌ ተጠቀሱ እንጂ በብዙ አገሮች ይህ ችግር በሰፊው ይስተዋላል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ ለጊዜ ግን ሐሳቤን እዚህ ላይ ልዝጋና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሚስተር አንቶኒዮ ጉተሬዝ እ.ኤ.አ. ማርች 15 ቀን 2024  በተባበሩት መንግሥታት የጉባዔ አዳራሽ ያደረጉትን የመጨረሻ የንግግር ገጽ ላቅርብላችሁ፡፡

‹‹በመጨረሻም፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን አስከፊ የዓለም ገጽታ ለመቀየር የዓለም የፖለቲካ መሪዎች ፍርኃትን ሳይሆን ማኅበራዊ ትስስርን መፍጠር አለባቸው። መንግሥታት ጥላቻና ብጥብጥ ቀስቃሽ ንግግሮችን ማውገዝና የእምነት ነፃነትን መጠበቅ አለባቸው።  ዲጂታል መድረኮች ተጠቃሚዎችን ከትንኮሳ እየጠበቁ የጥላቻ ይዘት ያላቸው አመለካከቶችን እንዳይሠራጩ መከላከል አለባቸው። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አድሎአዊነትንና የተዛባ አመለካከትን መቀነስ እንጂ ማባዛትና ማጉላት የለበትም። ጥላቻን ለመዋጋት አንድ ሆነን እንቁም። የእኩልነት፣ የክብር፣ የሰብዓዊ መብትና የመከባበር መርሆዎችን ለማስከበር የገባነውን ቃላችንን እናድስ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር እንደሠፈረው እነዚህ የጋራ ሰብዓዊነታችን የመሠረት ድንጋይ ናቸው። ልዩነትን እንደ ጥንካሬ ከመመልከት ይልቅ ርኅራኄን እናስፋፋ። ይህን አመለካከት ለማስፋፋት በማኅበራዊ ትስስር ማዕቀፍ ላይ ኢንቨስት እናድርግ። እናም በዚህ በተከበረው የረመዳን ወርና በየቀኑ ከዓለም ዙሪያ ካሉ ሙስሊሞች ጋር በአንድነት እንቁም። በአንድነት እያንዳንዱ ግለሰብ (እምነቱ ምንም ይሁን ምን) በስምምነትና በሰላም የሚኖርባቸው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰቦችን መገንባት እንችላለን። በዚህ መልካም አጋጣሚም በሃይማኖቶች መካከል ውይይትን ለማበረታታት አብረው ለሚሠሩ የሃይማኖት መሪዎችን አመሠግናለሁ። ስላዳመጣችሁኝ አመሠግናለሁ።›› ነበር ያሉት፡፡

ማስታወሻ

ይህ ጽሑፍ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ካደረጉት ንግግር ከድምፅ የተወሰደ ስለሆነ የትርጉም ክፍተት ሊኖርበት ይችላል፡፡ ሆኖም ትክክለኛውን ንግግር ከአንደበታቸው ትሰሙ ዘንድ ቪዲዮው እንድትመለከቱ አሳስባለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...