Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ሰሞኑን የገጠሙኝን ጉዳዮች በሁለት ከፍዬ አቀርባለሁ፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ሳምንት በሲስተሙ ላይ በተከሰተ የማይታወቅ ጉዳይ ምክንያት የደረሰበት ዝርፊያ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄዱ መጠነ ሰፊ የማፍረስ ዘመቻዎች ነዋሪዎች እየደረሰባቸው ያለው እንግልት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጦርነት እየተካሄደ ባለበት የአማራ ክልልና የተለያዩ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች በዜጎች ላይ ጉዳቶች እየደረሱ ነው፡፡ ከልካይ የሌለባቸው የሚመስሉ አጋቾች ከአዲስ አበባ ውጪ ዜጎችን አግተው ከሚጠይቁት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ባለሀብቶች እየተደወለላቸው በሚሊዮኖች እንዲከፍሉ የሚያስፈራሩ ሰዎች እንዳሉም እየሰማን ነው፡፡ እኔ ግን ለጊዜው ከላይ ያነሳኋቸው ጉዳዮች ላይ ላተኩር፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊት ገጠመው በተባለ ‹‹ችግር›› ምክንያት፣ በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኤቲኤምና በገንዘብ ማስተላለፊያ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ እንደተወሰደበት ሰምተናል፡፡ ባንኩ የሰጠው ምክንያትም ሆነ የብሔራዊ ባንክ መግለጫ ለእኔ በሚገባ ባይገባኝም፣ አንድ የተገነዘብኩት ጉዳይ ግን እንዳለ መናገር አለብኝ፡፡ ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም ሆነ ሌላ ድርጅት በዲጂታል ሲስተሙ ላይ ለውጥ ወይም ማሻሻያ ሲያደርግ፣ በሙከራ ፕሮጀክት አማካይነት ሥራውን አጠናቆ ለማስጀመር ወደ ዋናው የሥራ ቋቱ መሄድ የለበትም፡፡ ሲስተሙ ላይ ከመጫኑ በፊት በተለያዩ ዲስትሪክቶችና ኤሪያዎች ሙከራው መጠናቀቅ ነበረበት፡፡

በተለያዩ አገሮች በባንኮችም ሆነ በሌሎች የፋይናንስ ድርጅቶች ላይ የዲጂታል ዝርፊያ መፈጸሙ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዝርፊያ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያም ሆነ በአፍሪካ ውስጥ አጋጥሞ ያውቃል፡፡ ከዓመታት በፊት በጎረቤት ኬንያ በተለይ ዴይሊ ኔሽንና ዘ ስታንዳርድ የሚባሉ ጋዜጦች የፊት ገጾች በእንዲህ ዓይነት ዝርፊያዎች የተጨናነቁ ነበሩ፡፡ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ የዝርፊያ ተዋንያን እንደነበሩ የተለያዩ ዘገባዎች መውጣታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ዘገባ ሲወጣ ግን የሚመለከታቸው የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎችም ሆኑ የፖሊስ ኃላፊዎች፣ በግልጽ ያጋጠመውን ችግር በማስታወቅ ለጥንቃቄ የሚረዱ ማሳሰቢያዎችን ይሰጡ ነበር፡፡ እኛ ዘንድ ግን እንዲህ ዓይነቱ ድፍረት ስለሌለ ብዙ ነገሮች ይሸፋፈናሉ፡፡ ማጣራት ተደርጎ ለሕዝብ ይገለጻል ተብሎም በዚያው ጭልጥ ብሎ መቅረት የተለመደ ነው፡፡ አሁንም ሕዝብ የማወቅ መብት ስላለው ችግሮች በይፋ ይነገሩና መፍትሔ ይፈለግ እላለሁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ችግሮች ሲያጋጥም ማድበስበስ የሚጠቅመው ለዘራፊዎች ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በዘለለም አገርና መንግሥትን መለየት ላቃታቸው አይረቤዎች አጉል ዘለፋና ትችት መጋለጥንም ያስከትላል፡፡ የሰሞኑን የባንኩን ችግር ውስጥ መግባት አስመልክቶ ሲተላለፉ ከነበሩ አይረቤ ምልልሶች መገንዘብ የቻልኩት፣ አገር ምን ያህል በማይረቡ ግለሰቦች ምክንያት መከራ ውስጥ መውደቋን ነው፡፡ መንግሥትን መጥላት ሌላ አገርን መውደድ ሌላ መሆን ሲገባው፣ የአገር ሀብት በሆነው ንግድ ባንክ ላይ እንዲህ ዓይነት ጥላቻና ክፋት ማሳየት ነውረኝነት ካልሆነ በስተቀር ለእኔ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ በሌላ በኩል መንግሥተም ቢሆን ለትችትና ለዘለፋ ከሚያጋልጡት የማይረቡ ድርጊቶች ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ሁልጊዜ ችግር ባጋጠመ ቁጥር መተሻሸት ያስጠላል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሰሞነኛ የማፍረስ ዘመቻ ስመለስ በበኩሌ ከከተማዋ መለወጥ ጋር ምንም ዓይነት ጠብ የለኝም፡፡ በዚህ ጉዳይ ግን የመንግሥት ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚለዋወጧቸው ስድቦችና ዘለፋዎች ለማንም አይጠቅሙም፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ፍላጎት የሚመጥን ገጽታ ያስፈልጋታል፡፡ እንደ ኒውዮርክና ጄኔቭ ዓለም አቀፍ መናኸሪያ ስለሆነች፣ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል በኖረችበት ትቀጥል ማለት አይቻልም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ስሟ ካልተዋበች ነገ ተነገ ወዲያ ተጫራቾች መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ መቀመጫነቷ ካበቃ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሁሉም ኤጀንሲዎች፣ እነሱን ተከትለው የመጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሙሉ አብረው ይኮበልላሉ፡፡ ይህንን ለማወቅ የኑክሌር ሳይንቲስት መሆን አስፈላጊ አይደለም፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ስትቀየር ግን የነዋሪዎቿ ፍላጎት፣ ጥቅም፣ ደኅንነትና የወደፊት ራዕይ ጭምር ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ለከተማዋ መለወጥ አበክረን እየሠራን ነው ሲሉ፣ ሥልጣናቸው በሕዝብ ነፃ ፈቃድ የተሰጠ መሆኑን በመገንዘብ የነዋሪዎችን ይሁንታ ማግኘት ነበረባቸው፡፡ ነዋሪዎች ለከተማዋ መንገድ ኮሪደሮችም ሆነ ለወንዝ ዳርቻ ልማት ሲባል እንዲነሱ ሲደረጉ፣ የገቢ ምንጮቻቸው የሆኑ ሥራዎቻቸውም ሆኑ የመኖሪያዎቻቸው ጉዳይ በቅጡ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የተወሰኑ ወገኖች በንፅፅር የተሻሉ መኖሪያዎች ማግኘታቸው በመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲስተጋባ፣ ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑ ያላለቁ ኮንዶሚኒየሞች የተሰጧቸው ነዋሪዎች ጉዳይ ችላ መባል የለበትም፡፡ ከዕለት ኑሮዋቸው የተፈናቀሉ ዜጎችም ጉዳይ እንዲሁ፡፡

ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች ከበርካታ አገራቸውን ከሚወዱ ዜጎች ጋር የተጋራኋቸው ነጥቦች ሲሆኑ፣ አይረቤ የሆኑ አልፎ ሂያጅ ተራ ወሬዎችን ግን እዚህ ማምጣት አልፈለግኩም፡፡ ምክንያቱም የተጣለላቸውን አጀንዳ ብቻ እያመነዠኩ የአገሪቱን ውሎና አዳር መተንተን የሚፈልጉ ግለሰቦች ለእኔ ሰሞነኛ ጉዳይ ፋይዳ ስለሌላቸው ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ከአርባ ዓመታት በላይ ከጀማሪ ኤክስፐርትነት እስከ መምርያ ኃላፊነት ያገለገሉ ከትምህርቱም፣ ከልምዱም፣ ከዕድሜም ሆነ በአካባቢያቸው ከሚሰጣቸው ከበሬታ አንፃር ልጥቀሳቸው ያልኳቸው የ76 ዓመት አዛውንት እንዲህ አሉኝ፡፡ ‹‹አገራችን ከጣሊያን ወረራ በኋላ የጀመረችውን የዕድገት ጉዞ በሥርዓት ብታስቀጥል ኖሮ ዛሬ የእነ ደቡብ ኮሪያ አቻ እንሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ፊውዳሎች፣ ከዚያ ቀጥሎ ደም ፍላታም አብዮተኞች፣ በኋላ ደግሞ ፅንፈኛ ብሔርተኞች እያተራመሷት እዚህ ደርሰናል፡፡ ከእነዚህ ጥቅመ ቢስ ቅርቃሮች ውስጥ በመውጣት የጋራ አማካይ መፍጠር ከቻልን ተስፋ ይኖራል፡፡ ካልሆነ ግን ከጥፋት አዙሪት ውስጥ አንወጣም…›› ነበር ያሉኝ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

(ዘሪሁን ሸለሞ፣ ከብሔረ ጽጌ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...