Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአጣዬ ከተማ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውና በርካቶች መቁሰላቸው ተነገረ

በአጣዬ ከተማ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውና በርካቶች መቁሰላቸው ተነገረ

ቀን:

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በምትገኘውና በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ እየሆነች ባለችው አጣዬ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

ግጭቱ የተጀመረው በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና በአጣዬ ከተማ ዋሳኝ በሚገኙ  ነጌሶ፣ ኤፍራታ፣ ግድም ወረዳና ጀዎሃ በተባሉ አካባቢዎች መሆኑን፣ ግጭቱ ሲባባስም በአጣዬ ከተማ በሰዎችና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን፣ የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ተመስገን ተስፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል በሁለቱ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ምልክቶች ይታዩ እንደነበር የተናገሩት ከንቲባው፣ ‹‹ከየካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አካባቢ ወደ ከተማው ጥሰው በገቡ የሸኔ ታጣቂ ቡድንና አባሪዎች በከተማዋ ዕምብርት ላይ ጥቃት ከፍተው ከፍተኛ የሆነ ውድመት ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ምንም እንኳን ባደረግነው ግምገማ ግጭቱ የተፈጠረው በሰላሙ ወቅት አብሮ ገበያ በሚገበያየው ሕዝብ መካከል ሳይሆን፣ ከተማዋን ለማጥፋት የፈለገ ቡድን ወይም ሸኔ ተብሎ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን ነው ብለን የወሰድን ቢሆንም፣ ኅብረተሰቡ ግን ከቡድኑ ጋር አንዳንድ ነዋሪዎች በማበር ወግተውናል ነው የሚሉት፤›› ሲሉ አቶ ተመስገን አስረድተዋል፡፡

‹‹ሸኔም ሆነ ኅብረተሰቡ ከተማን ከማቃጠል ሊታቀቡ ይገባል፣ አብሮ የኖረ ሕዝብም ቢሆን መለያየት የለበትም፡፡ በአመራር ደረጃ ያሉ አካላት በትኩረት ሊሠሩበት ይገባል፤›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ስለግጭቱ አጀማመር ሲያስረዱ፣ ‹‹በከተማዋ በስተ ምሥራቅ በኩል ከበው ሲቀጠቅጡን እኛም አትምቱን አታቃጥሉን ብለን ምላሽ እንሰጣለን፣ እነሱም ይተኩሳሉ፡፡ በአካባቢው የመከላከያ ኃይል ቢኖርም እነሱ አልፈው ገብተው ሲያጠቁን አፋጣኝ ዕርምጃ አልወሰደም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹እናንተ እውነተኛ ጠባቂ ከሆናችሁ ወሰን ጥሰው ገብተው ጥቃት ሲፈጽሙብን ለምን ዝም ትላላችሁ? እኛም የእነሱን ወሰን አልፈን ከሄድን ለምን አትመቱንም?›› በማለት ከመከላከያ ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ መነጋገራቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪው፣ ይሁን እንጂ ችግሩ ሊቀረፍ ባለመቻሉ እንደገና በቅርቡ ከመከላከያ ጋር በተደረገ ስብሰባ ከተማውን እናድነዋለን ካላችሁ አድኑት፡፡ ከሞት ካላስጣላችሁን ግን በሕግ አምላክ ውጡልን፣ እኛ ከእናንተ ጋር ፀብ  የለንም፣ ወደ እናንተ አንተኩስም፣ እኛን ለማዳን የሚመጣ ኃይል ካለ እናንተን በመርዳት አብረን እንሞታለን፤›› ብለው መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ቀድመን እንደተናገርነውም ጥቃት የሚፈጽሙብን ታጣቂ ቡድን ወደ ከተማዋ ገብቶ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ሲያደርስ የደረሰልን የለም፤›› በማለት የተናገሩት ነዋሪው፣ አሁንም ቢሆን በከተማዋ ዙሪያ ባሉ ተራሮች ላይ ሆኖ ቡድኑ ወደ ከተማዋ በመተኮስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ደብረ ብርሃንና ወደ ቅርብ አካባቢዎች መሰደዳቸውን ጠቅሰው፣ መውጣት ያልቻሉት ደግሞ በረሃብ እየተቆሉ ይገኛሉ ሲሉ አክለዋል፡፡

ምንም ዓይነት ንብረት አልተቃጠለም ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ነገር ግን የሱቅ ዕቃዎችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች ላይ ዘረፋ መካሄዱንና ወጣቶች መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡ 

‹‹ከልዩ ዞኑ የመጡ እኩይ ዓላማን ያነገቡ በርካታ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች በመንግሥት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ሸኔ ጋር በመሆን ኅብረተሰቡ ባልጠበቀበትና ባልተዘጋጀበት ወቅት፣ ወደ ከተማዋ ሰብረው በመግባት ከፍተኛ ጥቃት ፈጽመውብናል፤›› በማለት የተናገረው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ነው፡፡

ኅብረተሰቡም ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ በራሱ በመደራጅት ጥቃት አድራሾችን ከከተማው ማስወጣት መቻሉን አስተያየት ሰጪው አክሏል፡፡

የከተማዋ አንዳንድ አመራሮችም በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ስለነበር ግጭቱን ለማሰቆምና ጥቃት አድራሾችን ለማስወጣት አስቸጋሪ እንደነበር የተናገረው ወጣቱ፣ መረጃው እስከ ተጠናቀረበት ድረስም ቀደም ሲል የመከላከያ ሠራዊት ምሽግ በነበረ ከከተማዋ አቅራቢያ በሚገኝ ተራራ ላይ በመሆን ታጣቂ ቡድኑ ወደ ከተማዋ ብሬንና ስናይፐር እየተኮሰ ጥቃት በመፈጸም ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡

‹‹የገባው ኃይል በጣም ብዙ ስለሆነ እንጂ መከላከያ በሁለቱም በኩል ለማረጋጋት ሞከሯል፤›› ያሉት የአጣዬ ከንቲባ አቶ ተመስገን፣ ነገር ግን የገባው ኃይል በጣም ብዙ ስለሆነ ምናልባት ከአቅሙ በላይ ካልሆነ በቀር የሚችለውን ሁሉ አድርጓል ብለዋል፡፡

ከግጭቱ በኋላ መከላከያ ወደ ከተማዋ መግባቱን ተናግረው፣ ነገር ግን ኅብረተሰቡን መመለስ እንዳልቻለና ያሉትም በሥጋት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አካባቢው የሥጋት ቀጣና በመሆኑ በቀጣይ መንግሥት በቂ ኃይል በመመደብ፣ በጥፋተኞች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምላሽና ማብራሪያ ለማግኘት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ እንዲሁም የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊና የኦሮሚያ ልዩ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሸን መምርያ ኃላፊን ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ስልካቸውን እያነሱ በመዝጋታቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...