Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሳለፈው ዱብ ዕዳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ በመጥፎ የሚታወስ ምሽት ነበር፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ባለው የባንክ አገልግሎት ዘመን በቢሊዮኖች የሚገመት ምዝበሩ በኢትዮጵያ ባንኮች ላይ የተፈጸመበት ጊዜ የለም፡፡ 

መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽት ሦስት ሰዓት እስከ ንጋት ድረስ የአገሪቱ ትልቁ ባንክ የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያጋጠመው ክስተት አስደንጋጭ ከመሆኑ ባለፈ ከባንክ ሥራ ጋር በተገናኘ ከፍተኛው ምዝበራ የተፈጸመበት መሆኑን በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ድርጊቱ በፍጹም ያልተጠበቀና ይሆናል ተብሎም ያልተገመተ ነበር፡፡ በዚያች ምሽት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገጠመው የገንዘብ ምዝበራና በዚህ ያልተገባ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉት በሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸው ነው፡፡ ባንኩ በዲጂታል የባንክ አገልግሎቱ ሥርዓት ላይ ያጋጠመውን መፋለስን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በዚያች ምሽት ያልተገባቸውን ገንዘብ ከባንኩ የኤቲኤም ማሽኖች ሲያወጡና የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን በመጠቀም በርከት ያለ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ የነበሩት አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መሆናቸው ሁኔታውን የበለጠ አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሰጡት ማብራሪያ፣ ባንኩ በዚያች ምሽት በገጠመው የሲስተም ችግር ምክንያት በሕገወጥ መንገድ የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ባያሳውቁም፣ ችግሩ ከተፈጠረበት መጋቢት 6 ቀን ሌሊት አንስቶ እስከ ንጋት ድረስ 490 ሺሕ የገንዘብ ማውጣትና ማስተላለፍ መፈጸሙን ጠቁመዋል።

በተፈጠረው ክፍተት ባልተገባ መንገድ የተዘዋወረው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ሊሆን የሚችል ቢሆንም ባንኩ የሚገለጽን ያህል አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ ባንኩ የሚሰጠውን የዲጂታል ባንክ አገልግሎት የሚጠቀሙት ደምበኞቹ ብዛት 32 ሚሊዮን መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ብቻ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ብቻ አሥር ትሪሊዮን ብር በላይ መንቀሳቀሱን ጠቁመዋል። ይህም በቀን ሲሰላ ከ41 ቢሊዮን ብር በላይ በመሆኑ በመጋቢት ሰባት ምሽትም በሕገወጥ መንገድ የተዘዋወረው ገንዘብ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ያመላክታል። ከሰሞኑ ባንኩ የገጠመው ችግር ከታወቀበት ምሽት ጀምሮ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተቋማት በማግስቱም ወደ ሁለት ሺሕ የሚሆኑት የባንኩ ቅርንጫፎች ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉም ያልተለመደ ተብሏል፡፡ 

ባንኩ በታሪኩ ለረዥም ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ የሆነው በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል በተባለው የምዝበራ ተግባር ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመቀነስ ሲባል የተወሰደ ዕርምጃዎች መሆኑን ባንኩ አሳውቋል፡፡ ይህ ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሁሉ መሪ ዜና እስከመሆን የደረሰው አፀያፊ ተግባር መንስዔ መነጋገሪያነቱ የቀጠለ ሲሆን ጉዳዩ ይመለከታቸዋል በተባሉ አካላት ምርመራ እንዲረግበት አስገድዷል፡፡ 

ይህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት የገንዘብ ምዝበራ ተግባር በመጀመርያ ሲባል እንደበረው የሳይበር ጥቃት የተፈጠረ አልነበረም፡፡ በአገሪቱ በተደጋጋሚ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከሚደረግባቸው የኢትዮጵያ ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ቢሆንም የሰሞኑ ችግር ግን ከዚህ ጋር የተያያዘ አለመሆኑንም አቶ አቤ አረጋግጠዋል፡፡ 

የችግሩ መንስዔ በራሱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ተፈጠረ በተባለ ክፍተት የሆነ ነው፡፡ አቶ አቤ ሳኖ እንዳስረዱትም በዚያች ምሽት ባንኩ የገጠመውና በተለያዩ መዝባሪዎች ላልተገባ ተግባር ሊጋለጥ የቻለው አንድ የሒሳብ ማስታረቅ ቅልጥፍና እንዲያመጣ ታስቦ የተሠራ የሲስተም ማሻሻያ ሲተገበር ስህተት በመፈጠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለሌቦቹ ደግሞ በዚህ ቀዳዳ ስለመጠቀማቸው አውስተዋል፡፡ 

በዚያ ምሽት ስለሆነው ነገርም ሲያስረዱ አንድ ትራንዛክሽን ከተቋረጠና ግቡ ካልደረሰ ከደንበኛ ሒሳብ ማስቀረት፣ ወይም የአገልግሎት ክፍያዎችን ቆርጦ ዋናውን መመለስና የመሳሰሉ ክፍተቶች አልፎ አልፎ እንደነበር በማስታወስ ነው፡፡ 

እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ሲሠሩ የነበሩ ሥራዎች በማንዋል የሚሠሩ ነበሩም ብለዋል፡፡ ይህንን የሚሠራው የባንኩ ባለሙያዎች ቡድን ቀኑን ሙሉ የተፈጸመውን ግብይት ጠዋት ገብተው ፈትሸው በማንዋል ወደ ቦታው መልሰው ያስተካክሉታል፡፡ ይህንን አሠራር በማንዋል ከማድረግ በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተቋረጠው አገልግሎት ወዲያው እንዲፈጸም መደረግ አለበት ተብሎ የተሠራው ሲስተም ግን እክል በመፍጠሩ ችግሩ እንደተፈጠረ ያስረዳሉ፡፡ 

ለተሻለ አገልግሎት ተብሎ የተተገበረው ሲስተም በትክክል የሚሠራ ስለመሆኑ በሚገባው አካል ቀርቦ የተረጋገጠ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ነገር ግን በትግበራው ሒደት ስህተት ተፈጠረ፣ የጎደለች ኮድ ነበረች በዚያች ምክንያት የተተገበረው የሒሳብ ማስታረቅ ሥራ የሌላውንም ትራንዛክሽን መረጃ እንዲጠፋ በማድረጉ ችግሩ ተፈጠረ፤›› ብለዋል። ይህ ስህተት በዚያ ሌሊት የተፈጸመው ግብይቶችን ሁሉ ግብይቱ ከተደረገ በኋላ ወይም ገንዘቡ ከተላለፈ በኋላ እንዳልወሰደ ቆጥሮ አካውንቱ ውስጥ ብሩን እንዲመልስ አድርጓል፡፡ 

ይህ ችግር በዋናነት የተፈጠረው ወደ ዋሌት ገንዘብ የሚያስተላልፈው ሲስተም ላይ መሆኑን የሚያመለክተው የፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ይኼ የውስጥ ትግበራ ችግር ነውም ብለውታል፡፡ ሆኖም ችግሩ እንዴት ተከሰተ? ለምን ተከሰተ መከሰት የሚችል ነው ወይ? ጉዳዩ ወዴት ይደርሳል የሚሉ ጥያቄዎች ግን አሁን ባለው ደረጃ መልሶ የሚያገኙና ቀጣይ የምርመራ ሒደቶች የሚፈቷቸው ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡ የምርመራው ግን ብዙ ሥራዎች የሚጠይቅ ነውም ተብሏል፡፡ የሚሠሩ ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ 

ይህ ማብራሪያ ችግሩ የውስጥ ችግር መሆኑን አመላክቷል፡፡ የተፈጠረውን ችግር ለማወቅም ጊዜ የወሰደ ከመሆኑም በላይ ችግሩን ማወቅ የተቻለው ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ባንኩ ሠራተኞች መሆኑ ደግሞ ብዥታ ፈጥሯል፡፡ ማዕከል ላይ ያሉ ሰዎች ይህ መረጃ እስኪደርሳቸው ድረስ አላወቁም፡፡ አቶ አቤ እንደገለጹትም ችግሩ እንዴት ታወቀ? ለሚለው ጥያቄ አቶ አቤ በየዕለቱ ብዙ የግብይት እንቅስቃሴ ስላለ በቀላሉ መጠርጠር አይቻልም፡፡ ትራንዛክሽን ሞኒተር የሚያደርግ ቡድን አለ፡፡ ሞኒተር የሚያደርገው ቡድን ግን በዚያን ወቅት ወዲያው ይህንን ችግር ማየት አለመቻሉንና ግብይቶቹ ጤናማ ግብይት አድርጎ ነበር የወሰደው ብለዋል፡፡ 

ነገር ግን በክልል ዲስትሪክት ላይ ያሉ ሠራተኞች ባልተለመደ ሁኔታ በተለይ ተማሪዎች ከኤትኤም ተሯሩጠው ገንዘብ ሲያወጡ በማየታቸው በሌሊት ወደ ማዕከል በመደወላቸው ነው ችግሩ ሊታወቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ይህንን መረጃ ይዘው ከእኩለ ሌሊት በኋላ የባንኩ የአይቲ ማኔጅመንት አባላት ገብተው የችግሩን መንስዔ በትክክል በቶሎ ማየት ባይቻልም የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ 

በወቅቱ የነበረውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ጤናማ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሌላውን ሲስተም ማቆምን ሁሉ የሚጠይቅ በመሆኑ የተጠረው ሁኔታ እንደየመጠን የባንኩ የአይቲ አመራሮችም ሲቢኢ ብር አካባቢ ችግሩ አለ በማለት አገልግሎቱን ሊቋረጥ ችሏል፡፡ ይህም በመሆኑ ሥጋቱ ሊቀንስ ቢችልም ግብይቱ ግን መቀጠሉን አረጋገጡ፡፡ በዚያ ክፍተት ገንዘብ ሲያስተላልፉ የነበሩት ቀደም ብለው ገንዘብ በማስተላለፋቸው ገንዘቡን እንዳያወጡ ቀጣይ ዕርምጃ በማስፈለጉ የሞባይል ባንክና የኤትኤም አገልግሎት ተቋረጠ፡፡ ከዚያም የቅርንጫፍ አገልግሎቶችን አቋረጡ፡፡ በመጨረሻም ቅዳሜ ጠዋት ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ 

አገልግሎቱ የተቋረጠው ግን የተቋረጠው ሲስተሙ ላይ በተፈጠረ ችግር ሳይሆን የተፈጠረው ችግር ጉዳት እንዳያደርስ ቀድሞ እንዲህ ያለው ዕርምጃ በማስፈለጉ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ ዋነኛ መንስዔ የታወቀው ከትናንት በስቲያ ሰኞ መሆኑንም ከአቶ አቤ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ችግር ፈጠረች የተባለችው ፕሮግራም ከሲስተም ስትወጣ የነበረው ችግር የተስተካከለና ባንኩ ወደ ሙሉ ሥራው ሊገባ ችሏል፡፡ ሆኖም ይህቺ የተጨመረችው ፕሮግራም ለምን ችግር አስከተለች የሚለው ጉዳይ ግን ገና መልስ የሚፈልግ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አቶ አቤም ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥናት የሚጠይቅ ነው በማለት ገልጸውታል፡፡ 

ባንኩ የገጠመውን ችግር ለማስተካከል ከወሰዳቸው ከዚህ ዕርምጃዎች ባሻገር በምሽቱ በሕገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የተላለፉ ከ490 ሺሕ እንዳይንቀሳቀሱ ማሳገድ ችሏል፡፡ ይህም ዕገዳ ሁሉንም የአገሪቷ ባንኮች በሚያስተሳስረውና ክፍያዎችን በሚያሳልጠው ኢትስዊች በኩል የተከናወነ ነው፡፡ 

ይህ የሆነበት ምክንያት የተላለፉ ገንዘቦችን ወደ ቅርንጫፍ ሄደው እንዳይወጡ ለማድረግ እንደነበር ታውቋል፡፡ 

በዚያ ሌሊት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ግብይት የተደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከእነዚህ ግብይቶች ውስጥ ጤናማ ግብይቶች ያሉ ቢሆንም ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ በዚያ ሌሊት የተደረጉ ግብይቶች ሁሉ ሊታገዱ ችለዋል፡፡ ይህም አሁንም ድረስ የማጣራት ሥራው ያላለቀ በመሆኑ ጤነኛ ግብይት ያላቸውን ደንበኞች ገንዘብ እንዳያንቀሳቅሱ አድርጓል፡፡ 

በዕለቱ የተደረጉትን ግብይቶች ለማጣራት በተሠራው ሥራ ብዙዎች በተለይም በዩኒቨርሲቲ አካባቢ ያሉ ተማሪዎች ከሦስትና አራት ጊዜ በላይ ግብይት ማካሄዳቸው ታውቋል፡፡ እስካሁን በተደረጉ የማጣራት ሥራዎች አንድ ሰው ከ189 በላይ ግብይት የፈጸመ ወይም በተደጋጋሚ ገንዘብ ያዘዋወረ ስለመኖሩ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ 

ይህ የትራንዛክሽን ቁጥሩ ቀላል የሚባል አይደለም ያሉት አቶ አቤ ይህንን ሁሉ ትራንዛክሽን እንዳይንቀሳቀሱ የተደረገውም በዚያ ሌሊት የተደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን በሙሉ የሚያግድ ሶፍትዌር በልፅጎ በመከናወኑ እንጂ 490 ሺሕ ትራንዛክሽን በማንዋል የማጣራት ሥራው ይደረግ ቢባል በሳምንትም አያልቅም ነበር ብለዋል፡፡ በተደረገው ማጣራት ችግር ያለበትንና ጤነኛውን ለመለየት ሥራ ተሠርቶ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ተለይቶ ለፍትሕ አካላት ሪፖርት መደረጉም ታውቋል፡፡ ከአሁኑ ወቅትም በሕገወጥ ግብይቱ የተሳተፉት በተለይ ተማሪዎች በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሠረት ብሩን እየመለሱ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ያልተጠበቀ ነበር የተባለውን ምዝበራ ማን ፈጸመው የሚለውን ለመለየት የተሠራው ሥራና የተገኘው ውጤት ግን አስደንጋጭ ነበር ተብሏል፡፡ በልየታ ሥራው  በተፈጠረው ክፍተት ተጠቅሞ ከፍተኛውን የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ያደረጉት እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ መሆናቸውን ማረጋገጥ የተቻለው ወዲያው እንደነበርም አቶ አቤ ገልጸዋል፡፡ 

አቶ አቤ በዚህ አሳዛኝ ባሉት ተማሪዎች ተግባር ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በድርጊቱ በአብዛኛው የተሳተፉ ተማሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ሥራ ይዘው ወደፊት አገር ይረከባሉ፣ የነገው የአገር ባለቤት ይሆናሉ የተባሉት ተማሪዎች የስርቆቱ ዋነኛ ተዋንያን ተማሪዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ክፍተቱ ስለመፈጠሩ መረጃውን እንዴት አገኙት የሚለው ጥያቄ እስካሁን መልስ ያላገኘና መረጃው ከባንኩ ሾልከው ከሆነ? የሚል ጥያቄዎች በብዙዎች ዘንድ የጫረ ቢሆንም አቶ አቤ በዚህ ድርጊት በብዛት ተማሪዎች ሊሳተፉ የቻሉት በተፈጠረው ክፍተት ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሳተፉ በሶሻል ሚዲያ መረጃ በመቀባበል ጭምር የፈጸሙት ነው ይላሉ፡፡ 

‹‹ይህ ያለመታደል ነው›› ያሉት አቶ አቤ በድርጊቱ የተሰማቸውን ስሜት ለማጉላት ‹‹በሌላው አገር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለይ የአይቲና የሳይበር ዕውቀት ያላቸው ተማሪዎች ትልልቅ የተባሉ ተቋማትን በጥሰው ይገባሉ፡፡ ሲስተሙን በጥሰው ገብተው ግን አይሰርቁም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የውጭዎቹ ተማሪዎች ሲስተማቸው እንዲህ ያለ ክፍተት ስላለው ዝጉት ብለው ለተቋሙ ያሳውቃሉ እንጂ የሚፈጥሩት ጉዳት የለም፡፡ የእኛ አገር ተማሪዎች ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ራሳቸውን ከባንካቸው ጋር ያስተዋወቁት በስርቆት መሆኑን በቁጭት ገልጸዋል፡፡ 

‹‹ባለፈው ዓመት 12 ሺሕ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የቀጠሩ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አቤ እነዚህ ወዴት እንደምናደርጋቸው አናውቅም›› በማለትም በሁኔታው እጅግ ማዘናቸውንም አክለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ባንኩ ከገጠመው ጉዳት በላይ ያመማቸውም የአገር ተተኪ ትውልድ በስርቆቱ ላይ መሳተፉ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በዚህ ያህል ደረጃ ሊደፍሩ የቻሉት ባንኩ ላይ ሳይበር ጥቃት ደርሷል በሚልና ይህም የተንቀሳቀሰው ገንዘብ አይታወቅም ከሚል የተሳሳተ ዕሳቤ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ግብይቱ በተጸመባቸው አካባቢ ላሉ ዩኒቨርሲቲዎች ስም ዝርዝር እየሰጠ በመሆኑ በዚሁ መሠረት እየመለሱ ነው፡፡ ባንኩ የመጀመርያ ዕርምጃ ያደረገው ገንዘብ የወሰዱት ከመለሱ ወደ ክስ አንሄድም የማይመልሱ ከሆነ ግን በሕግ ይጠየቃሉም ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገጠመውን ችግር በተመለከተ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብሌን ጊዜ ወርቅ በበኩላቸው፣ ድርጊቱን እንደ ባለድርሻ አካል በቅርበት ሲሠሩት መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹መሰል ሁኔታዎች በተለያዩ አገሮች ሊከሰት ይችላል፤›› ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ በተለያዩ ተቋማትም እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወደፊትም ሊያጋጥም እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህ ቴክኒካል ውስጣዊ መንስዔ ያላቸው ጉዳዮች ይቅርና ከዚህም ከባድ ያሉ ጉዳዮች ሊያጋጥሙ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ የተለያዩ ልምዶች የሚያሳዩ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ትልቁ ነገር ተቋማት ሁኔታውን በወቅቱ በፍጥነት ተረድቶ በቁጥጥር ሥር የማዋል ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ከዚህ አኳያ የእኛ አገር ባንኮች ሁሉም በሚባል ደረጃ የሚከተሏቸው የፋይናንሻል ቴክኖሎጂዎች ጥብቅ የውስጥ ክትትል ሥርዓት ያላቸው፣ አለፍ ሲልም በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትም ጭምር በመታገዝ ሁሌም ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚሠራ በመሆኑ ብዙም ሥጋት እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡ 

‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሰሞኑን በተፈጠረው ሁኔታ ፈጥኖ ችግሩን በቁጥጥር ሥር ማድረጉን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ በዚህም ምክንያት ሊደርስ ይችል የነበረውን ጉዳት አስቀድሞ በመቆጣጠር በጣም ኢንሲፊጋንት የሆነ ደንበኞች ጥቅም ላይ ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

እንደ ፋይናንስ አገልግሎት ደግሞ መሰል አጋጣሚዎችን የመቆጣጠር፣ የመከታተል፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት ደኅንነትና ጤናማነት የማረጋገጥ ሕጋዊ ተልዕኮ እንዳለው ተቋሙ ይህንን ክስተት ተከትሎ ከባንኩና ከሌሎች አካላት ጋር ሲሠራ እንደነበርም ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገሪቱ ግዙፍ ባንክ እንደመሆኑ መጠን በአገሪቱ  ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ድርሻ ያለው የሕዝብ ባንክ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ዳይሬክተሩ ችግሩ አሁን ላይ አነስተኛና በባንኩ ደንበኞች ላይ የተከሰተ ጉዳት ባይኖርም፣ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን በጥብቅ መቆጣጠርና አጥፊዎችን የመለየት ቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው ዕርምጃዎችን ጭምር ማየት እንደሚያስፈልገን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ከባንኩ ጋር በመሆን የመለየት ሥራ እንደተሠራውና ተማሪዎችም ሆኑ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በገዛ ፈቃዳቸው ያላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ እየመለሱ ነው፡፡ አሁንም የወሰዱትን እንዲመልሱ የሚያደርግ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የመለየት ሥራ ጎን ለጎን እየተሠራም ነው፡፡ 

በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ሁሉ በመጀመሪያ በፈቃደኝነት እንዲመልስ አሳስበው፣ የማይመልሱ ላይ ደግሞ ምርመራ ተደርጎ በሕግ ይጠየቃሉ፣ ውጤቱንም ለሕዝብ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ 

በሰሞኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግር የተንቀሳቀሰውን የገንዘብ መጠን በትክክል ለመግለጽ ግን እርሳቸውም አልቻሉም ይህ ምርመራው ሲያልቅ የሚታወቅ በመሆኑ እናሳውቃለን በሚል ገልጸውታል፡፡ አቶ አቤም መጠኑን ለማወቅ ምርመራው ማለቅ እንዳለበት ግን ከባንኩ አቅም አንፃር መጠኑ እጅግ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ 

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክስተት ጋር በተያያዘ ችግሩ የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን አቶ አቤ ማረጋገጫ ቢሰጡም፣ ኢትዮጵያ ከሚያጋጥሟት የሳይበር ጥቃት ውስጥ ብልጫ ያለውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የሚፈጸም መሆኑን ግን አስታውሰዋል፡፡ 

‹‹በኢትዮጵያ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ በሳይበር ብዙ ጥቃቶች ይደርሳሉ፤›› ያሉት አቶ አቤ፣ ሕዝብ ብዙ ጊዜ የሚያውቀው ጦርነት ጠመንጃ ይዞ የሚመጣውን ብቻ ነው፡፡ ጦርነት በተለያየ አቅጣጫ የሚመጣ ሲሆን፣ አንዱ በኢኮኖሚ አውታሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ማድረስ ነው ብለዋል፡፡ ኢንሳ ብዙ ጊዜ ደረሰ ብሎ ከሚገልጻቸው የሳይበር ጥቃቶች ከሚደርስባቸው ተቋማት መካከል በመጀመሪያ ተርታ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነውም ብለዋል፡፡  

‹‹ይህ የመንግሥት ተቋም የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ መሠረት በመሆኑ፣ የንግድ ባንክ ሥራ ማስቆም ሌሎችም ባንኮች ቆሙ ማለት ነው፣ መሥራት አይችሉም፤›› ያሉት አቶ አቤ፣ አንድ ላይ ተሳስረው ነውና ኦፕሬት የሚያደርጉት የፋይናንስ ዘርፉን ሁሉ እንደሚቆም በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁልጊዜ የጥቃት ማዕከል ነው፡፡ 

በተለይ በኢትዮጵያ ላይ ጥላቻ ያላቸው አገሮች ጥቃቶች ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ጥቃቶች ግን አንዳቸውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳይበር ሴኪውሪቲ በጥሶ መግባት የቻለ ያለ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ሙከራ ቢያደርጉ ከውጭ የመጣ ጥቃት የለም፡፡ የሰሞኑ ችግርም ግን ከሳይበር ጥቃት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡  

‹‹ስለዚህ ማንም የሳይበር ሴኪውሪቲ አልፎ በመግባት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲስተም መንካት የቻለ እስከዛሬ የለም፤›› ብለዋል፡፡  ነገር ግን ወደፊት አይመጣም ማለት እንዳልሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ቴክኖሎጂ በማንኛውም ሰዓት ሊመጣ የሚችል ስለመሆኑ ግን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን በውጭ ጥቃት ወደ ውስጥ ገብቶ የነካና የቀየረ ኃይል የሌለና የባንካቸው የሴኪውሪቱ ደኅንነት እጅግ በጣም የተሻሉ ከሚባሉት ምድብ ውስጥ የሚመደብ ነው ብለዋል፡፡ እስካሁን በዚህ ድክመት ባንኩ ላይ የገጠመ ያለመኖሩን በየቀኑ ግን ጥቃቶች ይመጣሉ፣ ይከሽፋሉ፣ ይመለሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጉልበት ሲኖራቸው አገራችን ኢትዌይ ላይ እንዲዘጋልን እንጠይቃለን፡፡ በራሳችን ለመከላከል የሚከብዱን ተደጋጋሚ ጥቃቶች አሉ፡፡ ሲከብድ ኢትዮ ቴሌኮም ላይ እንዲዘሠጋ ኢንሳ የሚጠይቁበት ጊዜ እንዳለም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

ስለዚህ ባንኩ የሳይበር ጥቃት ያልደረሰበት፣ የሳይበር ሥጋት ብዙ የሌለበት፣ ጠንካራ የሳይበር ሴኪውሪቲ ሥርዓት ያለው መሆኑን በማስገንዘብ የሰሞኑ ችግር የመጣው ‹‹አንዲት›› ያሏት የአገልግሎት ማሻሻያ ሲስተም ዓርብ ማታ ላይ መተግበሯ የፈጠረችው መዛባት እንደሆነች ገልጸው አሁን ላይ ግን ችግር የፈጠረችዋ ሲስተም በመውጣቷ አገልግሎቱ ያለችግር ቀጥሏል ብለዋል፡፡ 

ገንዘብ የማስመለሱ ሥራ ግን የሚቀጥል ሲሆን የችግሩ መነሻ ቢታወቅም ለምን ይህ ሆነ የሚለው ጉዳይ ግን የምርመራ ውጤቱ የሚመልሰው ነው ተብሏል፡፡ 

ባንኩ ላይ የደረሰው ጉዳት ባንኩ ካለው አቅምና ሀብት አንፃር ሲታይ እጅግ በጣም አነስተኛ ሊባል የሚችል በመሆኑ የደረሰ የጎላ ተፅዕኖ ያለመኖሩም በፕሬዚዳንቱ ተብራርቷል፡፡ 

ከሁሉም በላይ ደግሞ ተፈጠረ የተባለው ችግር ከባንኩ ደንበኞች ሒሳብ ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌለው ደንበኞች ሥጋት አለባቸው ተብሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስምንት ወራት ከአሥር ትሪሊዮን ብር በላይ በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ገንዘብ አንቀሳቅሷል፡፡ ይህም ከጠቅላላው የገንዘብ እንቅስቃሴ 73 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል፡፡ በቀን ከራት ሚሊዮን በላይ ግብይት የሚፈጸም ሲሆን፣ የዲጂታል ደንበኞቹም 32 ሚሊዮን ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች