Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበረመዳን ፆም የሕዝበ ሙስሊሙ አገርን የመታደግ ትጋት

በረመዳን ፆም የሕዝበ ሙስሊሙ አገርን የመታደግ ትጋት

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ዘንድሮ በ1,445ኛው የተቀደሰው የረመዳን ወር የሙስሊሞች ፆም ውስጥ እንገኛለን (በዓመታት መሀል የሚያጋጥመው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ዓብይ ፆምም በተመሳሳይ ቀን ገብቶ እየተካሄደ መሆኑንም ልብ ይሏል)፡፡ በሙስሊሞች አቆጣጠር ረመዳን የዓመቱ ዘጠነኛ ወር ነው። ፆሙ የሚጀምረው የረመዳን ወር በገባበት በመጀመሪያው ቀን ነው። ቀኑ በየዓመቱ ሊለያይ የሚችል ቢሆንም፡፡

በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ትልቁ ለአገርና ለሰው ፍቅር የሚፀለይበትና የሚፆምበት ብሎም ነዋየ ፍቅር ተራ የዓለም ተግባር መሆኑ በተግባር የሚታይበት ይህ ፆም፣ የሚቆየው ከ29 እስከ 30 ቀናት ድረስ ብቻ ነው፡፡ እንደ ጨረቃ አወጣጥ በአንድ ቀን ወደ ፊት ወይም ወደ ኋላ ሊሆን ይችላል። ከጥንተ ጥንት ጀምሮ በሁሉም ሕዝቦች ዘንድ ወር የሚቆጠረው በጨረቃ ማግሥት መውጣት ነው ፀሐይ (ሸምስ) ደግሞ የሰዓት መቁጠሪያ ናት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በእርግጥ የወሩ መጠሪያ ብዙ አይራራቅም። ዓረቦች ረመዳን ይሉታል በፋርስ (ፐርሺያ) ረማዛን፣ በኡርዱ ራምዛን በቱርክ ራማዛን፣ በኢንዶኔዥያ ቸዋሳአ ይባላል፣ ይህ ብርቱ የፆም ወር። ሙስሊሞች ሁሉ ወሩን በተመሳሳይ ሥነ ሥርዓትና ሃይማኖታዊ ደንብ መሠረት ያከብሩታል። ዋነኛ ይዘቱ ፆም (በዓረብኛ ሶም) ዘካና ሰደቃ (አሥራት/ችሮታ ለደሆች መስጠት ሲሆን የምሽት ረጅም ፀሎትና ስግደት (ተራዊህ)፣ ቁርአን መቅራት (ማንበብ) ከሁሉም ዓይነት መጥፎ ድርጊትና ንግግር መራቅ ዋነኞቹ ናቸው።

በእኛ አገር ሁኔታ ያለውን ነገር ስንመለከት በመዲናችን አዲስ አበባና ዋና ዋና ከተሞች ትልልቅ ቢዝነስ የሚያከናውኑ ሙስሊም ወገኖቻችን እንደ መሆናቸው፣ በረመዳን ፆም ከገበያ ውጪ ወይም ሥራቸውን በእጅጉ ቀንሰው ነው የሚታዩት፡፡ በዚህም ምክንያት የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ፀጥ እረጭ ነው የሚለው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ልጅ አዋቂ፣ ደሃ ሀብታም ሳይባል ሁሉም ፆምና ፀሎት ላይ እንደ ማተኮሩ በአገር ሰላም እንዲወርድ፣ ችግርና መከራ እንዲወገድ ብሎም አገር እንዲረጋጋ መትጋትና የአቅምን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህ ፆም ጠዋት ጎህ ከመቅደዱ በፊት ጀምሮ እስከ ፀሐይ ግባት ድረስ ምንም ዓነት ምግብ እንደማይበላ ሁሉ፣ ፆመው መፍቻ ያጡ ወገኖችን አስቦ መደገፍም የእምነቱ ኃላፊነት ነው። ወደ ሆድ የሚገቡ ነገሮች በሙሉ የተከለከሉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በሙስሊሞች ዘንድ ፆም ከፈጣሪ በርካታ ትሩፋቶችን የሚያስገኝ ትልቅ ተግባርም ነው፡፡ የረመዳን ፆም ደግሞ ትሩፋቱ እጥፍ ድርብ መሆኑ ይታመናል። ሰላት (ስግደት) ማብዛትና ቁርዓንን አብዝቶ መቅራት (ማንበብ) የረመዳን ወር ዋነኛ ተልዕኮዎች የሆኑትም ለዚሁ ነው (እዚህ ላይ የሃይማኖቱ አባቶች በአገር ሰላም እንዲወርድ መንግሥትና ተፋላሚ ኃይሎችን መምከርም ሆነ መገሰፅ ይኖርባቸዋል)፡፡

የረመዳን ወር ለሰው ልጅ ሁሉ መመርያ የሆነ ታላቁ መጽሐፍ ቁርዓን (ቀርዓን አል ከሪም) በተቀደሰችው ለይለተል ቀድር ዕለት ከፈጣሪ ለነብዩ መሐመድ (ሰዕወ) በመልአኩ ጂብሪል (ገብርኤል) አማካይነት የተወረደበት ወር መሆኑን የእምነቱ አስተምህሮት ያስረዳል። በተከታታይ ለ23 ዓመታት ከፈጣሪ እየተወረደ የተሰባሰበው ይህ ታላቅ መጽሐፍ አንዳችም የመልዕክቱ ይዘት ሳይዛባና ሳይፋለስ፣ ይዘቱንና ጥራቱን ጠብቆ እስካሁኑ ዘመን ድረስ የዘለቀና ወደፊትም (ኢንሽ አላህ) በአላህ ጥበቃ የሚዘልቅ ፈጣሪ ቀደም ሲል ለሌሎች ቅዱሳን መልዕክተኞች ያወረደውን መጽሐፍት አረጋጋጭ የሆነ (ኪታቡል በይና) ነው።

ታዲያ ይህን ታላቅ የእምነቱ መመርያ አማኞች መተግበራቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ ለአገር ሰላምና ለወገን ጥቅም ብሎም ለዓለም መረጋጋት ያውሉት ዘንድ የተጠበቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም እንደ ቀደምቱ ቱፊት ሁሉ ለአገር ሰላምና ልማት አስተዋጿቸውን ከማበርከት ባሻገር ዘር፣ እምነትና ቀለም ሳይለዩ ወገናቸውን መርዳት፣ የተቸገሩን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ በአማኞቹ ውስጥ ተደብቀው በማይበጅ የጥፋትም ይባል የውንብድና ሥራ ውስጥ የተሰማሩትን መገሰፅ እንደሌላው የእምንት ተከታይም የሚጠበቅባቸው አገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡

አሁን አሁን ቀነስ ያለ ቢመስልም በታላቁ እስልምና ውስጥ የተደነገጉ ሕግጋትና ሃይማኖታዊ እሴቶች በተስፈንጣሪና ጠርዘኛ፣ ብሎም ጽንፈኛ አስተሳሰብ እያጦዙና እየተመዘዙ በመተርጎም ለራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት የሚጠቀሙ አካላትን ማስቆም ለጋራ አገር የሚበጅ ይሆናል፡፡ የአገራችን ሕዝብ እስላም ክርስቲያን ሳይባባል ሁሉም ተሳስቦና ተከባብሮ መኖሩ የማይካድ ቢሆንም፣ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን የሕዝብ እያስመሰሉ ለማባላት የሚጫረውን እሳት ማጥፋት ያለበትም ይኼው አማኝ ኅብረተሰብ ነው፡፡

ቅዱስ ቁርዓኑን በራሱ ይዘትና በትክክለኛ ትርጓሜው ስናየው በይዘቱና በግልጽነቱ አንዳችም የሚያጠራጥር ነገር የለበትም (ላ ረይበ ፊሂ ሁደን ሊል ሙተቂን)፡፡ ቁርዓን በ30 ክፍሎች (ጁዝ) በ114 ሱራ (ምዕራፍ) በ6,219 መልዕክቶች (አያ) የተቀናጀ ነው፡፡ የአያዎቹ (መልዕክቶቹ) ቁጥር በአንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ የትምህርት ማዕከላት የሚለያይበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ (በአንድ ወቅት የቦረናው ሼህ ዝቢር እንደገለጹልኝ)

ኩፋዎች (Kufa) 6,239

ባስራዎች (Basra) 6,204

ሶሪያ (Syria) 6,225

መካ (Makka) 6,219

መዲና (Madina) 6,211

መውላና መሐመድ ዓሊ የተባሉ የሃይማኖት ሊቅ (The Relegion of Islam) በተባለ መጽሐፋቸው የአያዎች ቁጥር 6,240 ሲሆን፣ ቢስሚላህ ሲጨመርበት 6,353 ይሆናል ያሉበት ሁኔታም አለ። ይህ ማለት በአንዱ ቁርዓን ውስጥ ያለው መልዕክት በሙሉ በሌሎች ቁርአኖችም ሁሉ ውስጥ አለ። የቁጥሮቹን ልዩነት ያመጣው አንዳንድ መልዕክቶች (አያዎች) በአንዱ ቁርዓን ውስጥ እንደ አንድ ሲቆጠሩ፣ በሌላው ውስጥ ደግሞ እንደ ሁለት በመቆጠራቸው ብቻ ነው እንጂ ይዘታቸውም ሆነ ቅደም ተከተላቸው ሁሉም አንድ ነው።

በረመዳን የፆም ወር አብዝቶ የሚነበበው (የሚቀራው) ቁርዓን ይሁን እንጂ፣ ሱና (Sunnah) እና ሀዲስ (Hadith) የሚባሉ ቅዱስና መጻሕፍትም አሉ። ደረጃቸው ከቁርዓን እጅግ በጣም ዝቅ ያለ ነው። ሱና የሚባለው የነብዩን (ሰዐወ) ድርጊታቸውንና ንግግራቸውን በአንድ ላይ የያዘ ሲሆን፣ ሀዲስ የሚባለው ደግሞ ንግግራቸውን ብቻ የያዘ ነው። ስለዚህ ሱና የሚባለው ትልቁ (Set) ሲሆን፣ ሀዲስ ደግሞ ትንሹ (Subset) ይሆናል ማለት ነው። ሱናውና ሀዲሱ በዋናነት ከነብዩ (ሰዐወ) ድርጊትና ንግግር ላይ የተመሠረተ (AL-Sunnan al-Nabawiyya) ነው፡፡

ከነብዩ ሕልፈት በኋላ የሙስሊሙን ሕዝብ (ኡማ-Umma) ለድልና ለዕድገት ያበቁትን የነብዩ እጅና የትግል ጊዜ ጓዶች የነበሩትን አራቱን ጥበበኛና መልካም መሪዎችም የአላህ ባሮች (al-Kulafa al Rashidun) ‹‹The Wise and Sagaciou Caliphs›› የሚባሉት፣ ማለትም አቡበከር ሲዲቅ (በ634 አልፈዋል) ዑመር ከታብ (በ644 አልፈዋል) ዑስማን ኢብኑ አፋን (በ656 አልፈዋል) እና ዓሊ አብዱል መጣሊብ (በ661 አልፈዋል) ነበሩ፡፡

ሙስሊሞች በሙሉ በእነዚህ በአራቱ ጥበበኛና ፃድቅ መሪዎች ላይ ጠንካራ እምነት ፍቅርና አክብሮት ስላላቸው ከነብዩ (ሰዐወ) በተጨማሪ፣ የእነሱንም አሠራር በማገናዘቢያነት ይጠቀማሉ። ቁርዓን ይቀድማል ሱና ይከተላል፣ ሀዲስ ይለጥቃል የሚባለውም ለዚሁ ነው። የሱና መጽሐፍት በበርካታ ጸሐፊዎች የተጠናቀሩ ቢሆንም፣ በትክክለኛነታቸው ተመርጠው ዕውቅና ያገኙት ስድስት ናቸው።

እስልምና ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሃይማኖቶች ከምድራዊ ይልቅ ሰላማዊ ሕይወትን እንድናልም የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እናም በምድር ስንኖር ተባብረን፣ ተስማምተንና ተፋቅረን መኖር ብቻ ሳይሆን አንዳችን ለሌላችን መኖር አስፈላጊ የምንሆንበትን ሥራ፣ ፈጠራና ሥልጣኔ ማምጣት የሚጠበቅብን ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው ሥልጣኔው እንደ የአካባቢውና የማኅበረሰቡ የተለያየ ቢሆንም፣ የእስልምና እምነት ተከታዮችም በራሳቸው ሕግና ሥርዓት እየተዳደሩ ዓለምን የሚያስተናግዱበት ዕይታ አላቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በበርካታ አገሮች ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች በውስጥና በውጭ ቀውሶች ሰላም አጥተው ይኖራል፡፡ በፍልስጤም፣ በየመን፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በሶማሊያ፣ በምዕራብ አፍሪካ፣ ወዘተ እንዲህ ያሉ ፈተናዎች በአገራችን እንዳይከሰቱም ሆነ የተከሰቱት እንዲቆሙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እያደረጉ ካሉት ጥረት በላይ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሰላም የሁሉም ጉዳዮች መሠረት ነውና፡፡

ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ የሚሉት አስተሳሰቦች በርክተው የሚስተዋሉት ግን፣ ከዋናዎቹ ሕግጋት ጀርባ የራሳቸውንም ሐሳብ እየጨመሩ በሚናገሩ አንዳንድ የሃይማኖቱ መምህራን እንደሆነ ይነገራል፡፡ እስልምና ከዕውቀት፣ ከሰላምና ከብልፅግና ውጪ የቆመ ሃይማኖት እንዳልሆነ ነው የሚታወቀው። ለመረዳዳትና ለመተዛዘንም ቢሆን በእጅጉ የቀረበ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እስላም ማለት ሰላም ማለት ነው። የረመዳን ወር ደግሞ የተቀደሰና የተባረከ ቁርዓን የተገለጠበት (የተወረደበት) ምዕመናን (ሙዕሚኒን) ከዓለማዊ ነገሮች ርቀው ከምግብና ከመጠጥ፣ ከመጥፎ ድርጊትና ንግግር ተቆጥበው ለሰላምና ለፍቅር ለመቻቻል ምድርን መልካም ለማድረግ ወሩን ሙሉ በፆም፣ በፀሎትና በስግደት የሚያሳልፉበት ነው፡፡ ያለው ለሌለው የሚያቋድስበት ዘካ (አሥራት) የሚወጣበት ሰደቃ (ልግስና) አብዝቶ የሚሰጥበት ሰይጣን የሚታሰርበት በላጭ ወር ነው። ይህን ቅዱስ ወር በሰላምና በመተሳሰብ ማሳለፍ የሃይማኖቱ ግዴታ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአገራችን እስልምና አዳዲስ ትሩፋቶች እያሳየን ነው፡፡ በጎዳና ላይ አፍጥር፣ የሰፊ በዓላት አከባበርና በመተባበር ሰላምን የማስከበር ሥራ መጠናከር ያለበትና ለአገር ገጽታ ግንባታ ሊውል የሚገባውም ነው፡፡ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ውጪ ከታየ መንግሥትም ቢሆን በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ፣ በዓላቱም መንግሥታዊ ዕውቅና እንዲያገኙ እያደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚሰኝ ነው፡፡

በቀጣይም ቢሆን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና በየትኛውም መስክ ለተጎጂዎች ቆሞ መከራከርን ለማሳየት በየትኛውም ቦታና ጊዜ ነገር ቆስቋሾችን፣ ሁከት ፈጣሪዎችንና አመፅ ቀስቃሾችን መገሰፅ ያስፈልጋል፡፡ ነገሮችን እየተነጋገሩ በሰላምና በቀናነት መፍታት ሲቻል በትንሽ በትልቁ ድንጋይ ወርዋሪዎችንና አቀባዮችን፣ በሕዝብና በመንግሥት ንብረቶች ላይ ጉዳት አድራሾችን፣ የሰላማዊውን ሕዝብ ሰላም አደፍራሾችን የመቆጣጠር ተቀዳሚ ኃላፊነት የሕዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን የክርስቲያኑና የሌላውም ነው፡፡ ምክንያቱም ተጎጂዋ የጋራ አገር ነችና፡፡

እውነት ለመናገር በአሁኑ ጊዜ እስልምና ታላቅ ክብር አግኝቷል ቢባል ግነት የለውም። የእስላም ኮፍያ አድርጎ መንግሥት መሥሪያ ቤት ደጃፍ መድረስ ይከለከል የነበረበትና ሙስሊሙ እንደ ጠላት ይቆጠር የነበረባቸው እነዚያ ሥርዓቶች አልፈው፣ ዛሬ ኮፊያውን አድርጎ ዳኛ ሆኖ የሚፈርድበት ደረጃ ላይ ተደርሷል የሚሉ አማኞች አሉ። ከየትኛውም ማኅበረሰብ ባልተናነሰ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና ቢሮክራሲው ውስጥ ሚናቸው እያደገ መጥቷል፡፡

ዛሬ በመንግሥት በሬዲዮ በቴሌቪዥን ሳይቀር በተለይ የረመዳን ወር የምሽት ፀሎት (ተራዊህ ፕሮግራም ከታላቁ አንዋር መስጊድ በቀጥታ ለመላው ዓለም የሚተላለፍበት አሠራር ተዘርግቶ አይተናል። ተመስገን (አልሃምዱሊላሂ)፣ በዋና ዋና ጎዳናዎችና ቤተ መንግሥት ሳይቀር አፍጥር መፈጸሙም ትልቅ እመርታ ነው፡፡ ይህን አስጠብቆ መቀጠል የሚቻለው አገር ስትኖር ነውና ለአገር ሰላም መሥራት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡

ምንም ተባለ ምን የአገራችንን ሰላም የሚያስጠብቁ የመነጋገርና የሰላም መፍትሔዎች ይጠናከሩ እንጂ፣ ጊዜው ለእስልምናም ሆነ ለክርስትና እምነቶች በጣም የተሻለና የተመቸ ነው። በነገራችን ላይ እስልምናና ክርስትና በብዙ የእምነት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ፡-

  • ሁለቱም ሃይማኖቶች በአንድ ፈጣሪ ብቻ ያምናሉ (ሁው አሏሁ አሃድ)፣ አሃዱ አምላክ እንደ ማለት፡፡
  • ከፈጣሪ (ከአሏህ) በቀር ሌላ አምላክ አለማመን አለማሻረክ (ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አይኑርህ አታሻርክ /ላ ሸሪከአሏህ)፡፡
  • ጣዖት አለማምለክ (እስልምናም ሆነ ክርስትና በጣዖት አያምኑም)፡፡
  • ፆም (ሶም Soum) ሁለቱም እምነቶች በራሳቸው ግንዛቤና ሕግጋት መሠረት ይፆማሉ። እስልምና በፆም ጊዜ አምስቱም የስሜት ሕዋሳቶች እንዲፆሙ ያዝዛል። ክርስትናም አፍህ ይፁም፣ አይንህ ይፁም፣ እጅህ ይፁም፣ ልብህ ይፁም ይላል። ፆም በዓረብኛ ሶም (Soum) ሲባል በህንድና በፓኪስታን ሮዛ (Roza) ይባላል።
  • ስግደት (ሶላት) ሁለቱም ለፈጣሪያቸው ይሰግዳሉ። በቀን ውስጥ የሚሰግዱበት ጊዜና የስግደቱ መጠን (ብዛት) እና የአሰጋገዱ ሁኔታ ቢለያይም ለፈጣሪ መስገዳቸው የነበረ ያለና የሚኖር ነው።
  • የዕርድ ከብት ሲታረድ ሙስሊሙ ቢስሚሏህ ይላል፣ በአማርኛ በስመ አብ ማለት ነው።
  • ሁለቱም እምነቶች በሞትና በትንሳዔ ያምናሉ፣ በመሆኑም በዋና ዋና የእምነት ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ልዩነቶች የሉም።

በአጠቃላይ እንኳንስ በተቀደሰው የረመዳን ወር ቀርቶ በሌላውም መደበኛ ጊዜ ቢሆን ሙስሊሙን እርስ በራሱ የሚያናቁር፣ ሙስሊምና ሌላውን የሚያጋጭ ምንም ዓይነት ሁኔታ እንደሌለ ሁሉ ትብብራችንና መተሳሰባችን እንዲጎለብት መሥራት ተገቢ ይሆናል። ለአገር ሰላምና ደኅንነት ሲባል ለይቅር መባባልና ለዕርቅ እስልምና ታላቁን ድርሻ እነዲወጣ መነሳትም ከአማኞቹና መሪዎቻቸው ሁሉ የሚጠበቅ ነው፡፡

ከአዘጋጁ:- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...