Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በአፍሪካ ጨዋታዎች በውጤት ጎዳና

‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በአፍሪካ ጨዋታዎች በውጤት ጎዳና

ቀን:

እንደ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች 13ኛው ምዕራፍ በጋና አስተናጋጅነት መካሄድ ከጀመረ ሁለተኛው ሳምንት ላይ ደርሷል፡፡

‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በአፍሪካ ጨዋታዎች በውጤት ጎዳና | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የ800ሜ ማጣሪያን በአንደኝነት ያጠናቀቀችው ጽጌ ዱጉማ

ኢትዮጵያ ገዝፋ የምትታይበት አትሌቲክስን ጨምሮ በ29 የስፖርት ዓይነቶች የሚስተናገዱበት አኅጉራዊ ጨዋታዎች በሦስት የጋና ከተሞች (አክራ፣ ኩማሲ፣ ኬፕ ኮስት) በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

12ኛ ቀኑን ያስቆጠረው ውድድሩ ኢትዮጵያ ከሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ የገባችው በብስክሌት ግልቢያ ኪያ ጀማል ሮጎራ ሁለተኛ ሆኖ ባገኘው የብር ሜዳሊያ ሲሆን፣ ደረጃዋም 26ኛ ላይ አስቀምጧት ነበር፡፡ ኪያ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክና በአፍሪካ ጨዋታዎች በብስክሌት የወከለውና የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበረው የጀማል ሮጎራ ልጅ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአትሌቲክስ ውድድሮች መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. መጀመራቸውን ተከትሎ፣ ምሽቱን በተደረገው የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ሳሙኤል ፍሬው በአስደናቂ አሯሯጥ 8፡24፡30 በሆነ ጊዜ በአንደኛነት በመፈጸም ወርቁን አጥልቋል፡፡ ተከታትለው በ2ኛና በ3ኛነት የገቡት ኬንያውያኑ ሰሬም አሞፅ (8፡25፡77) እና ኪፕሮፕ ሲሞን (8፡26፡19) ሲሆኑ፣ 4ኛ እና 5ኛ ሆነው የፈጸሙት ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ አብርሃም ቱፋና ጃሬስ ሚልኬሳ ናቸው፡፡

በዕለቱ በተደረገውና ተከታትለው ሦስቱን ሜዳሊያዎች (ወርቅ፣ ብር፣ ነሐስ) በማሸነፍ፣ ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› የተሰኘው ብሂል ዳግም የታየው በሴቶች 5000 ሜትር ውድድር ነው፡፡

‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በአፍሪካ ጨዋታዎች በውጤት ጎዳና | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በብስክሌት ግልቢያ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ኪያ ጀማል ሮጎራ

የቡድን ሥራና ኅብረት በታየበት ውድድር ቀዳሚ ሆና የፈጸመችው መዲና ዒሳ በ15፡04፡32 በሆነ ጊዜ ሲሆን፣ ተከታትለዋት የገቡት ብርቱካን ሞላ (15፡05፡32) እና መልክናት ውዱ (15፡07፡04) ናቸው፡፡

መዲና ወርቁን ታጥልቅ እንጂ ከ17 ዓመት በፊት በአልጀርስ በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች መሠረት ደፋር 15፡02፡72 በሆነ ጊዜ በማሸነፍ የያዘችውን የጨዋታውን ክብረ ወሰን ማሻሻል አልቻለችም፡፡ የዓለም ክብረ ወሰን በጉዳፍ ፀጋይ በ14፡00፡21 መያዙ ይታወሳል፡፡

በትናንት ምሽት 2 ወርቆች፣ 1 ብር እና 1 ነሐስ ሜዳሊያዎች መገኘታቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ በደረጃ ሠንጠረዡ ወደ 14ኛ ከፍ ብላለች፡፡ በአጠቃላይ 2 ወርቅ፣ 2 ብር እና 1 ነሐስ በድምሩ 5 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡

አስቀድመን ወደ ኅትመት በመግባታችን ምክንያት ውጤቱን አልያዝንም እንጂ፣ በትናንት ምሽት በወንዶች 10,000 ሜትርና በሴቶች 800 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያ በሁለቱ ርቀቶች በሜዳሊያዎች የታጀበ ውጤት እንደምታገኝ ቅድመ ግምት መሰጠቱን በሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡

በ800 ሜትር ሴቶች የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮኗ ጽጌ ዱጉማና አስቴር አሬሬ ለወርቃዊው ድል ተጠብቀዋል፡፡

የ10,000 ሜትር  ወንዶች ፍፃሜ ተፎካካሪዎች ኃይለ ማርያም አማረ፣ ንብረት መላክና ገመቹ ዲዳ ናቸው፡፡

‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በአፍሪካ ጨዋታዎች በውጤት ጎዳና | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አረንጓዴ ጎርፍን ያስታወሱት የ5000ሜ ባለድሎቹ መዲና ዒሳ፣ ብርቱካን ሞላና መልክናት ውዱ

ሌላው የምሽቱ የፍፃሜ ውድድር የድብልቅ ዱላ ቅብብል (ሜክስድ ሪሌ) ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለፍፃሜው የደረሰችው ከምድቧ በ3፡26፡51 ሦስተኛ ወጥታ ነው፡፡ 1ኛ እና 2ኛ የወጡት ናይጄሪያ (3፡15፡23) እና ጋና (3፡23፡87) በማስመዝገብ ነው፡፡ በሁለተኛው ምድብ ተከታትለው ከ1 እስከ 3 የገቡት ቦትስዋና (3፡14፡36) ኬንያ (3፡18፡42) እና ደቡብ አፍሪካ (3፡19፡63) ናቸው፡፡  

በብስክሌት ውድድር የአገሮች ደረጃ ኢትዮጵያ በ1 ብር ሜዳሊያዎች 7ኛ ደረጃ ስትቀመጥ፣ የመጀመሪያ ደረጃውን የተቆናጠጠችው በ6 ወርቅ፣ በ2 ብርና በ15 ነሐስ ያገኘቸው ኤርትራ ናት፡፡ በአጠቃላይ አገሮች ደረጃም 8ኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡

እስከ መጋቢት 10 በነበረው አጠቃላይ ውጤት ግብፅ በ91 ወርቅ፣ 36 ብር፣ 31 ነሐስ፣ በ158 ሜዳሊያዎች ቀዳሚ ስትሆን፣ ናይጄሪያ በ27 ወርቅ፣ 21 ብር፣ 30 ነሐስ በ78 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ፣ ደቡብ አፍሪካ በ26 ወርቅ፣ 29 ብር፣ 38 ነሐስ በ93 ሜዳሊዎች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ አዘጋጇ ጋና በ9 ወርቅ፣ 22 ብር፣ 15 ነሐስ በድምሩ በ46 ሜዳሊዎች 6ኛን ይዛለች፡፡

የትናንት ምሽት፣ የተመዘገቡና ዛሬና ነገ በሚደረጉ ውድድሮች የሚገኙ ውጤቶች ከመሪዋ ግብፅ በቀር የሌሎቹን ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ደረጃ ይለውጠዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ውጤት የምትጠበቅባቸው ሐሙስ የሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ የሴቶችና የወንዶች 1500 ሜትር ማጣሪያና በማግሥቱ ፍፃሜ፣ የሴቶችና የወንዶች ግማሽ ማራቶን እንዲሁም የወንዶች 5000 ሜትር ናቸው፡፡

ዛሬ የሴቶች 20 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፣ ሦስት አትሌቶች ዓለም ታፈሰ፣ ውባለም ሽጉጤና ስንታየሁ ማስሬ፣ እንዲሁም በወንዶች 20 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ መለሰ ሙሉ፣ ምስጋና ዋቁማና ቢሰጠኝ እንዳሻው ይፎካከራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፊታችን ቅዳሜ የሚጠናቀቀውን 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎችን የአፍሪካ ኅብረት የስፖርት ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ)፣ እንዲሁም የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ማኅበር በበላይነት ያስተዳድሩታል፡፡

የመጀመሪያው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች እ.ኤ.አ. በ1965 በኮንጎ ብራዛቪል ሲጀመር ኢትዮጵያ የተካፈለች ሲሆን፣ ማሞ ወልዴ በ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...