Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ አየር መንገድን አክሲዮን ድርሻ ለሶማሌላንድ ለማቅረብ የወጣ መመርያም ሆነ አቅጣጫ እንደሌለ...

የኢትዮጵያ አየር መንገድን አክሲዮን ድርሻ ለሶማሌላንድ ለማቅረብ የወጣ መመርያም ሆነ አቅጣጫ እንደሌለ ተገለጸ

ቀን:

ከሶማሌላንድ የባህር በር ለማግኘት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ መጠኑ ያልተገለጸ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የአክሲዮን ድርሻ ሊሰጥ ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ፣ የተላለፈ መመርያም ሆነ መንግሥታዊ አቅጣጫ እንደሌለና በሐሳብ ደረጃ ብቻ የተያዘ መሆኑ ታወቀ።

መንግሥት የአገሪቱን ጥቅሞች በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው በሚል የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት የወደብ ባለቤትነት ጉዳይ፣ የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው የተባለለትን የመግባቢያ ስምምነት ታኅሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ መፈራረማቸው ይታወሳል።

ሁለቱ የስምምነቱ አካላት ውሉን መፈጸማቸውን ይፋ ያደረጉት የመግባቢያ ሰነድ ቃል በቃል ምን እንደሚል ለሕዝብ በይፋ ግልጽ ባይደረግም፣ ከፊርማው በኋላ በወጡ መግለጫዎችና ሪፖርቶች ግን ሁለት ጉዳዮች ጎልተው ሲወጡ ተስተውለዋል። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከእነዚህ ሁለት መላምቶች በአንዱ ኢትዮጵያ ለምትቀበለው የባህር በር ምላሽ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአገርነት ዕውቅና ላልተሰጣት ሶማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና ልትሰጥ ትችላለች የሚለው ተቀዳሚው ሲሆን፣ ተከታዩ ደግሞ ሶማሌላንድ በአፍሪካ ተቀዳሚ ትርፋማ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የአክሲዮን ድርሻ ልትወስድ ትችላለች የሚል እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሪፖርተር ታማኝ ምንጭ ስለሁኔታው ሲያስረዱ ‹‹የራስ ገዝ ሶማሌላንድና የኢትዮጵያ መንግሥት ከሁለት ወር ተኩል በፊት የመግባቢያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። እዚያ ስምምነት ላይ መንግሥት እንደ አንድ የስምምነት አካል የተባለው በሶማሌላንድ በኩል ‹‹ከፈለጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአክሲዮን ድርሻ ሊወስዱ ይችላሉ›› የሚል ስምምነት እንደሆነ ነው የተረዳነው፡፡ ይህ በሐሳብ ደረጃ ያለ ነው እንጂ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ድረስ የደረሰው ወይም በዚህ ረገድ የመጣ መመርያ የለም። የተረጋገጠ ነገርም አላየንምና በሐሳብ ደረጃ ያለ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል። 

የአየር መንገዱ ምንጭ አክለው በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሶማሌላንድ የአክሲዮን ድርሻ መስጠቱን በተመለከተ ዝርዝሩን መናገር የሚቻል ነገር እንደሌለ ነው። 

በዋናነት ግን የሪፖርተር ምንጭ፣ ‹‹ወደፊት ተወስኖ ከመጣ በአየር መንገዱ ላይ እንዴት ነው ሊሆን የሚችለው የሚለውን ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው። ግን እስካሁን ድረስ ለአየር መንገድ ከመንግሥት የተሰጠ ምንም ዓይነት መመርያ፣ ምንም ዓይነት አቅጣጫ የለም፤›› ሲሉ አብራርተዋል። 

ሪፖርተር ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት የአየር መንገዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውን፣ አየር መንገዱ በአጠቃላይ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያወጣ የተደረገ ወይም እየተደረገ ያለ ጥናት ካለ እንዲያሳውቁ የተጠየቀ ቢሆንም፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ አለመሆኑን ተናግረዋል። 

ሶማሌላንድ ከሶማሊያ ውጪ የሆነች ራስ ገዝ መሆኗን ያወጀችው እ.ኤ.አ. በ1991 ነበር። ሶማሌላንድ የራሷ የፖለቲካ ሥርዓት አቋቁማ መደበኛ የምርጫ ሒደት እያካሄደች፣ የራሷ የፖሊስ ኃይልና የመገበያያ ገንዘብ ስትጠቀምም ቆይታለች። 

ባለፉት አሥርት ዓመታት በቋሚነት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎች ከመፈለግ አኳያ፣ ኢትዮጵያ ላይ በሰፊው ስትንተራስ ከቆየችው ሶማሊያ በተነፃፃሪ፣ ሶማሌላንድ ተገልላ የቆየች ብትሆንም በየትኛውም ውጫዊ ወገን የአገርነት ዕውቅና ተሰጥቷት አያውቅም።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...