Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ፕሮጀክቶች ማኅበረሰቡን ታሳቢ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

የመንግሥት ፕሮጀክቶች ማኅበረሰቡን ታሳቢ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

ቀን:

የመንግሥት ፕሮጀክቶች ማኅበረሰቡን ታሳቢ ሊያደርጉ እንደሚገባ ለመልሶ ማልማት የተነሱ የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች አሳሰቡ፡፡

መንግሥት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች የማኅበረሰቡን አቅምና ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ ሊሆን ይገባል ሲሉ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ለመልሶ ማልማት የተነሱ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለረዥም ዓመታት በአካባቢው ነዋሪ የነበሩና ለልማት እንዲነሱ የተደረጉ ነዋሪዎች፣ ውሳኔው ተፈጻሚ ሲደረግ የማኅበረሰቡን አቅምና ፍላጎት ማዕከል ያደረገ እንዳልሆነ ተናግረው፣ የተሰጠው ጊዜም አጭር መሆኑን አክለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳና አራት ኪሎ አካባቢ ለመልሶ ማልማትና ለኮሪደር ልማት የአካባቢው ነዋሪዎችን በማስነሳት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

በመልሶ ማልማት ሥራው ምክንያት ከነበሩበት ሥፍራ እንዲነሱ የተደረጉ ነዋሪዎች ላለፉት 35 ዓመታት በአካባቢው መቆየታቸውን ገልጸው፣ ለልማት ተብሎ እንዲነሱ ሲደረግ፣ ከእነሱ ጋር በቂ ውይይት አለመደረጉንና በድንገት ተግባራዊ መደረጉ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

ቤታቸው የፈረሰባቸውና የመክፈል አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ከ150 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር ቅድሚያ ክፍያ በመክፈል፣ ለሃያ ዓመታት ያህል በየወሩ ከአምስት ሺሕ እስከ ስድስት ሺሕ ብር እየከፈሉ የሚኖሩበት የኮንዶሚኒየም ዕጣ እንደ ወጣላቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለኮንዶሚኒየም ቆጥበው ዕጣ ለሚወጣላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተግባራዊ ሲደረግ በነበረው አሠራር መሠረት ተግባራዊ የተደረገ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የኮንዶሚኒየም ዕጣ የወጣላቸው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ የደረሷቸው ቤቶች በርና መስኮቶቹ ያልተገጠሙላቸው ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ቀሪ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ስለሚቀሯቸው ችግሩን የከፋ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዕጣ ደርሶን የተረከብነው ቤት ውኃና መብራት የሌለው፣ በርና መስኮቶቹም ገና ያልተገጠሙ በመሆናቸው መግባት አልቻልንም፡፡ የሚከራይ ቤት ስንፈልግም ልጆች ይዘን ቤት ማግኘት አልቻልንም፤›› ሲሉ ከተነሺዎቹ መካከል አንድ ነዋሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ቤት የማፍረሱ ሒደት ከመጀመሩ በፊት 150 ሺሕ ብር የካሳ ክፍያ እንደሚሰጠን ተነግሮን የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን 50 ሺሕ ብር ብቻ ውሰዱ ተብለናል፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ዓመቱ ባለመጠናቀቁ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በምትክነት ወደ ተሰጣቸው ቤት ለመግባት የልጆቻቸው የትምህርት ሁኔታ እንዳሳሰባቸውም አስረድተዋል፡፡ 

በሌላ በኩል የንግድ ፈቃድ በማውጣት ይሠሩበት ለነበረ ቦታ ተለዋጭ እንደሚሰጣቸው ከከተማ አስተዳደሩ ተገልጾላቸው የነበረ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት የመሥሪያ ቦታ እስካሁን እንዳልተሰጣቸው ከፒያሳ የተነሱ በአነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡

የኮንዶሚኒየም ዕጣ የደረሳቸው 1,100 ያህል ነዋሪዎች ቤቶቹ እንደ መብራት፣ ውኃ፣ በርና መስኮት የሌላቸው መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን ቢገልጹም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ቤቶቹ መሠረታዊ አገልግሎቶች ሁሉ የተሟሉላቸው ናቸው ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ 

ከንቲባዋ የቀበሌ ቤት የመረጡ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከነበሩበት አካባቢ ሳይርቁ፣ ከበላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን ጋር በጋራ በመሆን ባስገነቧቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣዎችን እንዲያወጡ በማድረግ ቤቶቹ መተላለፋቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...