Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየዓድዋ ድል በዓል ባለቤትነት ለመከላከያ ሚኒስቴር መሰጠቱ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ

የዓድዋ ድል በዓል ባለቤትነት ለመከላከያ ሚኒስቴር መሰጠቱ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ኃላፊነትና ባለቤትነት የተሰጠው የመከላከያ ሚኒስቴር በፓርላማ ጥያቄ ተነሳበት፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሕዝብ በዓላትንና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ን በሚመለከት ከአስረጂዎች ጋር ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት ሲደረግ የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች የዓድዋ ድል በዓል ባለቤትነት ለመከላከያ ሚኒስቴር በመሰጠቱ ጥያቄ አንስተዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች የዓድዋ በዓል ነፃነት፣ እኩልነትና አብሮነት የታየበት በመሆኑ፣ ማኅበራዊ አንድነትን በማጠናከር የጋራ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ፣ በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች የሚከበር በመሆኑ፣ በዓሉን የማስተባበር ሥራ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዓድዋን የሚያስተባብረው የመከላከያ ተቋም የተሰጠው የማስተባበር ኃላፊነት እንዲወስድ በሚል እንጂ ብቻውን የሚያከብር ተቋም ለማድረግ አለመሆኑን በማስታወስ፣ አከባበሩም በአገር ደረጃ የሚመለከታቸውና መላው ሕዝብ የሚያከብሩት ነው ሲሉ፣ የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም ፀጥታን ከማስከበር አንፃር ለመከላከያ ሚኒስቴር መሰጠቱን የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊዎችም ተናግረዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊዎችና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የዓድዋ በዓል ለመከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠበትን ምክንያት በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡

በወቅቱ የነበሩት አርበኞች ባህላዊ አለባበሶችን፣ እንደ ቀረርቶና ሽለላ ያሉ ባህላዊ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማስዝገብ ኃላፊነት ሊኖረው የሚገባው የባህልና ስፖርት  ሚኒስቴር ሆኖ ሳለ፣ የማስተባበር ኃላፊነቱ የተሰጠው ለመከላከያ መሆኑ በድጋሚ መታየት የሚገባው መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ጥበብና የፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልመሃዲ አስረድተዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር ቢያስተባብረው ምናልባት የባህል እሴቱን ጠልቆ ማየት ስለሚከብደው፣ ፀጥታን ቢያስከብር ባህላዊ እሴትን የማስቀጠል ኃላፊነትን ደግሞ ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መሰጠት ወ/ሮ ነፊሳ አሳስበዋል፡፡

ለመከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠበት ሌላኛው ምክንያት፣ ዓድዋ የማነው የሚለው ጉዳይ ውዝግብ እየፈጠረ ነው በሚል ማብራሪያ የተሰጠበት መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ ነፊሳ፣ ለ126 ዓመታት በሰላማዊ መንገድ ሲከበር የቆየውን በዓል ባለፉት ሁለት ዓመታት ውዝግብ በመፍጠር ዜጎች እንዲጣሉ ያደረጉት አስፈጻሚዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ከሁለቱ ዓመታት ውጪ የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ከከተማ ባለፈ በእግር ጉዞ እስከ ዓድዋ ድረስ በመሄድ በሰላም በማክበር ዜጎች ያቆዩትን ባህል፣ በተለያዩ ግለሰቦች የአፈጻጸም ክፍተት ምክንያት ችግር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ታሪክን ለትውልድ ለማሸጋገር ችግር ከመፈጠሩ በፊት፣ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተነጠቀው ኃላፊነት በድጋሚ እንዲታይ ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ የአዋጁ መነሻ በፍትሕ ሚኒስቴርና በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የተያዘ ቢሆንም፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመፅደቁ በፊት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያለውን ግብዓት ማካተትና ምክንያቱን መግለጽ ነበረበት ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሳማኝ ሆኖ ከተገኘ በዓሉ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ባለቤት ሊከናወን እንደሚችል፣ እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስቴር ከባህልም አኳያ ማስፈጸም ከቻለ ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል ብለዋል፡፡

‹‹ነገር ግን ወደ ቀጣይ ሒደት ከመሄዱ በፊት የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ ተወያይተውበት ለቀጣይ ቀጠሮ ተስተካክሎ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ደግሞ መናበብ አለባችሁ፤›› ሲሉ ወ/ሮ ወርቀሰሙ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የሴቶች ቀንና የሰንደቅ ዓላማ ቀን ያልተካተቱበት ምክንያት ተጠይቋል፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠናቀቅ ዳይሬክተር ጄኔራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጠገነኝ ትርፌ፣ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ያልተካተተበት ምክንያት የራሱ አዋጅ ያለ መሆኑን፣ የሴቶች ቀን ደግሞ የአገሪቱን ባህልና ወግ ያንፀባርቃል ተብሎ ያልታሰበና ቀኑን ሕጋዊ ዕውቅና በመስጠት እንዲከበር ማድረግ አስፋላጊነቱም በጥናት ስላልተለየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ነገር ግን ቋሚ ኮሚቴውም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጁ መካተት እንዳለበት ካመኑበት፣ ቀኑን ለማካተት ቀላል ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ በበኩላቸው፣ የሴቶችና የሰንደቅ ዓላማ ቀን ቢታሰቡም፣ ዓለም አቀፍ ቀን ነው በሚል ብቻ መታለፍ የለባቸውም ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ወርቀሰሙ አክለውም ረቂቅ አዋጁ የሕዝብን ጥቅም በማስከበር ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል ሆኖ መውጣት እንዳለበት ጠቁመው፣ በቀጣይም በሚኖሩት ውይይቶች በተሰጠው አስተያየት መሠረት መካተት ያለባቸውን ጉዳዮች አካቶ በግልጽ ማቅረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው፣ የአዋጁን አስፈላጊነት በሚመለከት ሲያስረዱ፣ አዋጁ ለረዥም ጊዜ የቆየ በመሆኑ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሆንና ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ በዓላትን በአግባቡ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ እንዲሁም የአከባበር ሁኔታዎችን በግልጽ ለማስቀመጥ በማስፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል። 

በውይይቱ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎቸ ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...