Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሒሳብ ባለሙያዎች የሚዘጋጁ ሪፖርቶች አኅጉራዊ ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ማኑዋል ሊፀድቅ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአካውንቲንግ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የሚዘጋጁ የሒሳብ ሪፖርቶች በሁሉም የአፍሪካ አገሮች ተቀባይነት እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም የአኅጉሪቱ ባለሙያዎችም ከአንድ አገር ወደ ሌላው ተዘዋውረው መሥራት የሚያስችል የአሠራር ማኑዋል ሊጸድቅ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ በዝግጅት ላይ የነበረው ማኑዋል የጥራት ማረጋገጫ አሠራር ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተውጣጡ፣ የአካውንቲንግና የኦዲቲንግ ተቆጣጣሪዎችና ባለሙያዎች እየተገመገመና ለመፅደቅ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከፓን አፍሪካ የአካውንታንቶች ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ያዘጋጁትና ከማክሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በራዲሰን ብሎ ሆቴል ለአራት ቀናት እየተካሄደ ባለ የምክክር መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ የመድረኩ ዋነኛ ግብ የጥራት ማረጋገጫ አሠራሩ ላይ ተወያይቶ ማፅደቅ ነው፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታና የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ሰብሳቢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የምክክር መድረኩ በአጠቃላይ በአካውንቲንግና በኦዲት የሥራ ሒደት ላይ የጥራት ችግሮችን ማስተካከል ላይ ያተኩራል፡፡ የሚፀድቀው የአሠራር ማኑዋል ትልቁ ትኩረት ‹‹የሒሳብ ሠራተኞችም ሆኑ ኦዲተሮች የሚያወጡት ሪፖርት እውነተኛ፣ የሚታመንና በየትኛውም የዓለም ክፍል ቢኬድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርግ›› እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሚመክሩበትና የሚያፀድቁት ይህ የአሠራር ማኑዋል፣ ‹‹ድንበር ሳይገድበው የአፍሪካ አገሮችን የሚያገለግል›› ሆኖ እንደሚወጣ፣ ይህም ገቢ የማሰባሰብን አቅም እንደሚያሳድግና ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት ወደ አገር እንዲመጣ እንደሚያደርግም እዮብ (ዶ/ር) ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል፡፡

የአካውንቲንግና የኦዲት ሥራ በአገሮች የሚኖረው የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት መሠረት ስለመሆኑ በመድረኩ የተሳተፉ ባለሙያዎች አብራርተዋል፡፡ ተቋማትና ግለሰቦች መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ፣ መንግሥትም ግብር የሚሰበስብበት መሠረት፣ እንዲሁም ባንኮችም ብድር ለመስጠት የሚጠቀሙት በዋነኛነት የፋይናንስ ሪፖርቶችን ነው ብለዋል፡፡

ይህንን አሠራር ለማዘመንና በአካውንቲንግና በኦዲቲንግ ሥራ ላይ የሚታየውን የጥራት ችግር ለመቅረፍ፣ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት የቦርዱ ኃላፊዎች፣ በአኅጉር ደረጃ አንድ ዓይነት ሥርዓት እንዲኖር በማሰብ ማኑዋሉን ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቦርዱ የፌዴሬሽኑ አባል ከሆነ አራት ዓመታት መቆጠሩም ተገልጿል፡፡

የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሒክመት አብደላ፣ ኢትዮጵያ የፈረመችውና አባል የሆነችበት የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት በአባል አገሮች መካከል የባለሙያዎች ነፃ እንቅስቃሴን በመደንገጉ፣ ‹‹አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ኦዲተር ሌላ አገር ሄዶ መሥራት እንዲችልና ሌላ አገር ያለው ደግሞ ኢትዮጵያ መጥቶ መሥራት እንዲችል›› እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የባለሙያዎች ዕውቀትና አሠራር አንድ ዓይነት መሆን አለባቸው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

አሁን ባለው አሠራር መሠረት የአካውንቲንግ ሥራን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ሄዶ መሥራት እንደማይቻል፣ ማኑዋሉ ከወጣ በኋላ ግን ባለሙያዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው እንዲሠሩ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡ ይህም ቁጥጥሩ ምን ይምሰል የሚለውን ባለሙያዎቹ ተነጋግረውበት እንደሚያፀድቁ ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች