Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አስጎብኚ ድርጅቶች ለጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኙ እንደገና ተመዝገቡ መባላቸውን ተቃወሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሲያቀርቧቸው የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ እንደገና ‹‹ተመዝገቡ›› መባሉ፣ ተገቢ እንዳልሆነ አስጎብኚ ድርጅቶች አስታወቁ፡፡

ቀደም ሲል አስጎብኚ ድርጅቶች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥባቸው የቱሪዝም ሚኒስቴር ዳግም ምዝገባ እንዲካሄድ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን፣ የታላቁ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ገልጿል፡፡

አስጎብኚ ድርጅቶች ለጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኙ እንደገና ተመዝገቡ መባላቸውን ተቃወሙ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ዳንኤል ተስፋዬ የታላቁ የኢትዮጵያ
አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት

ላለፉት አምስት ዓመታት ድርጅቶቹ ያልከፈሉትን ውዝፍ የግብር ዕዳ መክፈል እንዲችሉ፣ የብድር አገልግሎት ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት የተቀመጡለት መሥፈርቶች ሊስተካከሉ እንደሚገባ ጥያቄ አቅርበን በሒደት ላይ ባለንበት ወቅት፣ እንደገና ምዝገባ እንድናካሂድ መጠየቃችን አግባብ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አንድ የአስጎብኚ ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት የሚችለው ቢያንስ አንድ ተሽከርካሪ ሲኖረው ነው የሚለው መሥፈርት እንዲቀር ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ውይይት እየተደረገበት ያለ ቢሆንም፣ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት እንደገና ምዝገባ መጀመር ዘርፉ ያለበትን ችግር ካለማገናዘብ የመጣ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ 

ምንም እንኳን አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች እየተገነቡ ቢሆንም፣ የፀጥታ ችግሩና የድርጅቶቹ አቅም ማነስ ዘርፉ እንዳያንሰራራ እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ ጦርነቶችና ግጭቶች ምክንያት፣ የቱሪስቶች ፍሰት መቀነሱን እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ቦታዎች የፀጥታ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች ሥራቸውን እስከማቆም መድረሳቸውን፣ የአብዛኞቹ አስጎብኚ ድርጅቶች ባለቤቶች በመዝጋት ከአገር መውጣታቸውን አክለዋል፡፡

እንደገና ምዝገባ የሚካሄድበት ፎርም ላይ የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስፈልጉ መሥፈርቶች ዝርዝሮች ቢካተቱበትም፣ የግድ መሟላት አለባቸው ተብሎ አለመገለጹን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሆኖም በፎርሙ ላይ እንደ መሥፈርት ተቀመጠ ማለት የቱሪዝም ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥበት አሠራር የተቀየረ ነገር አለመኖሩን አመላካች ነው ሲሉ አስጎብኚዎች ያስረዳሉ፡፡

ሚኒስቴሩ ለማኅበሩ የላከውና ሪፖርተር የተመለከተው ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ ድርጅቶቹ ዓመታዊ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀታቸውን በተቀመጠው አሠራር መሠረት ባለማደሳቸው፣ እንዲሁም በአገሪቱ የሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች አሁናዊ ሁኔታን ለመረዳት የእንደገና ምዝገባው እንዳስፈለገ ይገልጻል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሌንሳ መኮንን የመረጃ ማጥራት ሥራዎች በየጊዜው እንደሚከናወኑ ገልጸው፣ እንደገና ምዝገባ ያስፈለገው ሥራ ላይ ያሉ ድርጅቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

ለብቃት ማረጋገጫ የተቀመጡ መሥፈርቶችን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ድርጅቶቹ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ እንደገና ምዝገባ ማካሄዱ ለምን አስፈለገ ተብሎ ለወ/ሮ ሌንሳ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ከዚህ ቀደም ሚኒስቴሩ ያስቀመጣቸው አሠራሮች እስካልተቀየሩ ድረስ፣ አሠራሮቹን ተከትሎ መሄድ አስፈላጊ ነው በማለት ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትር ደኤታዋ አክለውም፣ ‹‹ድርጅቶች በሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ወደፊትም ይከናወናሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ሚኒስቴሩ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ያቆማል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ለብቃት ማረጋገጫነት የተቀመጡ መሥፈርቶች አሁንም ይቀጥላሉ ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ድርጅቶቹ በበኩላቸው የብቃት ማረጋገጫ መሥፈርቶቹ ላይ ያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ እንደገና የምዝገባ ሒደት መከናወኑ ለጥያቄዎቻቸው ትኩረት ካለመስጠት የመጣ ነው በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የኮቪድ ወረርሽኝ ሲከሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ በአሁኑ ጊዜ እያንሰራራ ቢገኝም፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ የቀጠሉ ግጭቶች ፈተና መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በርካታ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች በሚገኙበት የትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲገታ ቢደረግም፣ በክልሉ ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ግን አሁንም ድረስ በሚፈለገው ልክ ውጤት እያስገኘ አለመሆኑን ከክልሉ የሚወጡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በሌላ በኩል በአማራ ክልል እየተካሄድ ያለው ጦርነት ከክልሉ አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ላለው የቱሪዝም ዘርፍ መቀዛቀዝ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስጎብኚዎች ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች