Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተጎጋ የሲሚንቶ ፋብሪካን 49 በመቶ ድርሻ ለውጭ አገር ኩባንያዎች ለመሸጥ ዕቅድ መያዙ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ምዕራብ አቅጣጫ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የተጎጋ ሲሚንቶ ፋብሪካን በ17.2 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ከባንኮች ብድር ማግኘት ካልተቻለ፣ 49 በመቶ አክሲዮኑን ለውጭ ኩባንያዎች ለመሸጥ ዕቅድ መያዙን የፋብሪካው የቦርድ ሰብሳቢ አስታወቁ፡፡

የትግራይ ክልል የንግድ ዘርፍ ማኅበራትና የፋብሪካው የቦርድ አመራር ፕሬዚዳንት (ሰብሳቢ) አቶ አሸናፊ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በትግራይ ክልል ተጎጋ አካባቢ ለመገንባት የታሰበውን የሲሚንቶ ፋብሪካ ዕውን ለማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሦስት ቢሊዮን ብር ከአክሲዮን ሽያጭ መሰብሰብ ተችሏል፡፡

በተጎጋ ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ ከ25 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች እንዳሉት የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ አንድ አክሲዮን በመቶ ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ጦርነት ከመፈጠሩ በፊት የሲሚንቶ ፋብሪካውን ለመገንባት ጅምር ሥራዎች እንደነበሩ አስታውሰው፣ የአክሲዮን ሽያጭ ዋጋው በዝቶብናል ላሉ ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች፣ ለአርሶ አደሮችና ለሌሎች ተቋማት ሃምሳ ሺሕ ብር ከፍለው ቀሪውን 50 በመቶ ከባንክ ብድር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ በተከናወነው የአክሲዮን ሽያጭ ላይ የተሳተፉት ሰዎች መካከለኛ ገቢ ያላቸው መሆናቸውን፣ ነገር ግን ከተያዘው መጋቢት ወር ጀምሮ ባለሀብቶች አክሲዮን እንዲገዙ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የተጎጋ የሲሚንቶ ፋብሪካ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በቀን አሥር ሺሕ ቶን የማምረት አቅም እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ ‹‹በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ የታሰበውን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ ከተቻለ፣ ጎን ለጎን የማሽነሪ ግዥ ጨረታዎች ለማውጣት፣ ጥረት ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ከዘጠኝ ወራት በኋላ የሚጀመር መሆኑንና 190 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በመጪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ ፋብሪካው የሚያርፍበት ሥፍራ ጠረጋ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

የተጎጋ የሲሚንቶ ፋብሪካ በ17.2 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ መሆኑን፣ ለግንባታው የሚሆን ብድር ከባንኮች ለማግኘት 5.2 ቢሊዮን ብር ወይም 30 በመቶ ለባንኮች ማስገባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ለሲሚንቶ የሚሆኑ ግብዓቶች እዚያው አካባቢ እንደሚገኙ፣ በአሁኑ ወቅት ባንኮች ብድር መስጠት ፍላጎት እያሳዩ ባለመሆናቸው 49 በመቶ አክሲዮን ለውጭ ኩባንያዎች ለመሸጥ ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባንኮች ብድር የሚያመቻቹበት አጋጣሚ ከተፈጠረ፣ የፋብሪካው ግንባታ ሙሉ ለሙሉ የሚከናወነው አክሲዮን በገዙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካው ተገንብቶ ከተጠናቀቀ ለአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖው፣ የሲሚንቶ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የአክሲዮን ሽያጩን በፍጥነት በማከናወን ወደ ግንባታ ለመግባት እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን አክለዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች