Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደብረ ብርሃን በካምፕ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ዕርዳታ በመቋረጡ ወደ ቀን ሥራ እየተሰማሩ ነው...

በደብረ ብርሃን በካምፕ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ዕርዳታ በመቋረጡ ወደ ቀን ሥራ እየተሰማሩ ነው ተባለ

ቀን:

ከተለያ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናዮች ከመንግሥትና ከተለያዩ በጎ አድራጎት ማኅበራት ይደረግ የነበረው ድጋፍ በመቋረጡ ወደ ቀን ሥራ መግባታቸው ተገለጸ፡፡

ከአራት ዓመታት በላይ በመጠለያ ካምፕ ለነበሩት ተፈናቃዮቹ በመንግሥት ይሰጥ የነበረው ዕርዳታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከተቋረጠ ከሦስት ወር በላይ ማለፉን ለደኅንነቱ በመሥጋት ‹‹ስሜ እንዳይተቀስ›› ያሉ አስተባባሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የመድኃኒትና የተለያየ አልባሳትን ጨምረው የምግብ አቅርቦት ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል የሚል መረጀ ከሰሙ በኋላና በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን ከፍተኛ የሆነ ሥጋት እየፈጠረ በመምጣቱ ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ በማቋረጣቸው ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቀደም ሲል የፌዴራል መንግሥትና የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተወካዮች በተገኙበት ተፈናቃዮቹን ‹‹አካባቢያችሁ ከፀጥታ ሥጋት ነፃ ስለሆነ መመለስ ይኖርባችኋል›› ተብለው የተመለሱ ቢሆንም፣ የተሻሻለ ነገር ባለመኖሩ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ እየተመለሱ መሆኑም ተገልጿል፡፡

‹‹ስም ዝርዝራችሁ ከካምፕ ስለወጣ አንቀበልም›› እየተባሉ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ በመጀመሪያም ተገደው አንዳንዶችም በፀጥታ ኃይል ድብደባ ተፈጽሞባቸው እንደሄዱ አስተባባሪው አስታውሰዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ከመሄዳቸው በፊት አካባቢውን የሚያጠና ኮሚቴ ተልኮ እንደነበርና  ከኮሚቴዎቹ አንዱ እንደነበሩ የገለጹት አስተባባሪው፣ በወቅቱ ተፈናቃዮችን  ወደ ቦታቸው ሊመልስ የሚያስችል ሁኔታ እንዳልነበር ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሪፖርት አቅርበው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት እንዲሄዱ በመፈለጉ ብቻ በግዴታ ተገፋፍተው እንዲሄዱ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹ወደ ቤታችሁ እንመልሳችሁና አርሳችሁ ትበላላችሁ፤ ወደ ቀደመው ኑሯችሁ ትመለሳላችሁ፣ ብለው ወስደው ሜዳ ላይ ጥለውን ነው የከረሙት›› ሲሉ የተናገሩት  ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡

ቀድሞ ይኖሩበት ወደነበረው ምሥራቅ ወለጋ ዞን ቢሎቦሾ ወረዳ ተመልሰው እንደነበር የተናገሩት አስተያየት ሰጪው፣ ወደ ቤታቸው እንደሚገቡ የተነገራችው  ቢሆንም በቦታው ሲደርሱ በክልሉ ልዩ ኃይል ከሚጠበቅ ካፕ ገብተው በቤተሰብ 15 ኪሎ ሩዝ እየተሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራትም ሆነ ወደ ወንዝ ወርደው ልብሳቸውን ማጠብ፣ ወደ ገበያ በመሄድ የሚያስፈልጋቸውን ዕቃ መግዛት እንዲሁም ሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳልቻሉ አስተያየት ሰጪው ገልጸዋል፡፡

እሑድ መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሎቦሾ ወረዳ ጨሪጃርሶ በተባለች ቀበሌ  አቶ ካሳ ደርበው የተባሉ ግለሰብ፣ ከካምፕ ወጥተው ጥለውት የከረሙትን ቤታቸውን  ለማየት ሄደው ተደብድበው መገደላቸውን ተናግረውል፡፡

‹‹ሥልጣኑ የፌዴራል መንግሥቱና የክልሉ በመሆኑ እንጂ ሰላም ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ወደመጣችሁበት ሂዱ አንልም ነበር›› ያሉት የተፈናቃዮች ካምፕ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አንተነህ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው፡፡

ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ሥራ ውጤታማ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ አንተነህ፣ ሄደው የነበሩት እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡

ዘገባው እስተጠናቀረበት ድረስ 11 አባወራዎች ወደ ካምፕ መመለሳቸውን ተናግረው፣ ነገር ግን አጥጋቢ የሆነ ድጋፍ አለመኖሩን አክለዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ከሰሜን ሸዋ ዞንና ከኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሸን ምላሽ ለማግኘት ሪፖርተር ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...