Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኦቲዝም ተጠቂዎችን የማብቃት ፈተና

የኦቲዝም ተጠቂዎችን የማብቃት ፈተና

ቀን:

ወ/ሮ ሃና አብርሃም ከኦቲዝም ጋር የምትኖረዋ የታዳጊ ሳሮን ቢንያም ወላጅ እናት ናቸው፡፡ ከኦቲዝም ጋር የምትኖረውን ልጃቸውን ቤት ማስቀመጥ ባይፈልጉም፣ በርካታ አስገዳጅ ሁኔታዎች ገጥሟቸው ነበር፡፡ በተለይ ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች የሚመጥን ትምህርት የሚሰጥና ራሱን የቻለ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖሩ ፈትኗቸዋል፡፡

በግልና በመንግሥት የትምህርት ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ የኦቲዝም ማዕከላት ልጃቸውን ለማስመዝገብና ለማስተማር ያደረጉት ጥረት እጅግ አድካሚና ተስፋ አስቆራጭም ነበር፡፡

በኦቲዝም ዙሪያ የሚሠሩ አንዳንድ ማዕከላት የሚቀበሏቸው ልጆች ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች መሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከአሥር እስከ 20 ሺሕ ብር ክፍያ መጠየቃቸውና የተጠየቀውን ለመክፈል አቅማቸው ባለመቻሉ፣ ልጃቸው ለ12 ዓመታት ያህል ትምህርት ሳታገኝ እንድትቆይ ምክንያት ሆኗል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ወ/ሮ ሃና ምሉዕ ፋውንዴሽን ሲመሠረት ግን ልጃቸው የትምህርትና በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት ችላለች፡፡ ከኦቲዝም ጋር የምትኖረው ታዳጊ ሳሮን፣ ወደ ማዕከሉ ከመግባቷ በፊት ዳይፐር ትጠቀም እንደነበር የሚያስታውሱት እናቷ፣ በማዕከሉ በሚሰጠው የቴራፒ አገልግሎት አሁን ላይ ዳይፐር መጠቀም አቁማለች፡፡

‹‹ብዙ ማስታወስ የማልፈልጋቸው መከራዎችን በልጄ ምክንያት ዓይቻለሁ፣ ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይግባውና በማዕከሉ በሚሰጣት ትምህርትና ድጋፍ በልጄ ሕይወት ውስጥ ለውጦችና መሻሻሎችን ዓይቻለሁ፤›› ይላሉ፡፡

እንደ ወ/ሮ ሃና፣ ልጃቸው ቀደም ሲል ከሰዎች ጋር የመግባባት ችግር ነበረባት፡፡ አሁን ላይ በተሻለ ደረጃ የመግባባትና የመረዳት አቅሟ ጨምሯል፡፡ ትምህርት ቤት ስትሄድም ደስተኛ ነች፡፡

ማዕከሉ ልጃቸውን በነፃ ተቀብሎ እያስተማረላቸውና እየደገፈላቸው ይገኛል፡፡ መምህራኑም ከልጆቹ አዕምሮ ጋር የተጣጣመ ትምህርት በመስጠት፣ የመገንዘብ አቅማቸውን እንዲያዳብሩ ከፍ ያለ ዕገዛ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ወ/ሮ አገሬ በላይ፣ የሕፃን ቤተማርያም ግርማይ ወላጅ እናት ናቸው፡፡ ሕፃን ቤተ ማርያም ከኦቲዝም ጋር የሚኖር ሲሆን፣ በምሉዕ ፋውንዴሽን ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡

ወ/ሮ አገሬ እንደሚናገሩት፣ ልጃቸው በማዕከሉ የቴራፒ አገልግሎትና ትምህርት በማግኘቱ የማስተዋል ደረጃው ከፍ ብሏል፡፡ የታዘዘውንም ሰምቶ መፈጸም ጀምሯል፡፡ የንግግር፣ ነገሮችን ለይቶ የማወቅና የመገንዘብ ክህሎቱም አድጓል፡፡ ይህ በልጃቸው የመጣው ጉልህ ለውጥ በማዕከሉ ድጋፍና ዕገዛ ነው፡፡

ማዕከሉ ነፃ የትምህርት ዕድል ከሰጣቸው ልጆች መካከል አንዱ የእሳቸው ልጅ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ አገሬ፣ ማዕከሉ እንደ እኔ ልጃቸውን ከፍለው የማስተማርና የማቆየት አቅም የሌላቸውን ወላጆች በመደገፍና ዕንባቸውንም በማበስ ታላቅ ሥራ ሠርቷል ይላሉ፡፡ 

ኦቲዝም የአንድን ልጅ የአዕምሮ ዕድገት፣ የማገናዘብ ችሎታ፣ የመማር አቅም፣ የባህሪና የስሜት አገላለጽ፣ የተግባቦት፣ የቋንቋ፣ የንግግርና የማኅበራዊ ክህሎት የሚጎዳ ነው፡፡

የስሜት ዕድገት፣ ስሜትን የማቀናጀትና አጠቃላይ ራስን የመርዳት ክህሎትን በተለያየ መጠን የሚያዛባና የሚጎዳ የጤና እክል መሆኑም በወ/ሮ መዓዛ መንክር በ2013 ዓ.ም. የተጻፈው ‹‹ሁሉም በአንድ ተግባር ተኮር የሕክምና መጽሐፍ›› ይገልጻል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ዮናስ ባህረ ጥበብ 2010 ዓ.ም. ‹‹ዓይኔን ተመልከተኝ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ እንደገለጹትም፣ የኦቲዝም አዕምሮ ዕድገት መዛባት መንስዔ በውል ባይታወቅም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ እንደሚችል የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል የዘር ተወራራሽነት፣ በእርግዝና ወቅት ያጋጠመ ሕመም፣ በወሊድ ወቅት በሕፃኑ ላይ የደረሱ ጉዳቶች፣ በኢንፌክሽንና በመርዛማ ነገሮች መጠቃት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በኦቲዝም ጥላ ሥር የሚኖሩ ልጆች ላይ ጎልተው ከሚታዩ ምልክቶች መካከል፣ የቋንቋና የተግባቦት ውስንነት፣ የማኅበራዊ ግንኙነት እክል፣ ያልተለመደና ድግግሞሽ የበዛበት ባህሪ ማሳየት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ዶ/ር ዮናስ ይገልጻሉ፡፡ 

ነኸሚያ የኦቲዝም ማዕከል በድረ ገጹ እንዳሠፈረው፣ በኢትዮጵያ ከ600 በላይ ልጆች ከኦቲዝምና ከተመሳሳይ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነቶች ጋር ይኖራሉ፡፡ ሆኖም እነዚህን ልጆች ለማስተማር፣ ለማሠልጠን፣ ለማብቃትም ሆነ ሙሉ ሕክምና ለመስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ ለእነሱ የሚሆኑ ማዕከላት ጥቂት ናቸው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱም ከማስተማር ጀምሮ ምዘና እስከመስጠት ድረስ የማይችሉትን ውስብሰብ የሒሳብ ሥሌቶችን ጨምሮ፣ ሌሎች ትምህርቶችን ከሌላው ተጨማሪ እኩል እንደሚሩ የሚያደርግ ነው፡፡ 

በአገራችን በኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ልጆችን በመደገፍ፣ በማገዝና በመንከባከብ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መካከል አንዱ ምሉዕ ፋውንዴሽን ነው፡፡

የምሉዕ ፋውንዴሽን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግሥት ኃይሉ እንደሚናገሩት፣ ድርጅታቸው የተቋቋመው የተቀናጀ ማኅበረሰብ ተፈጥሮ የማየት ራዕይን ሰንቆ በኦቲዝምና በሌሎች ልዩ ፍላጎት ባላቸው ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ዙሪያ ለመሥራት በ2013 ዓ.ም. ነው፡፡

ለድርጅቱ መቋቋም ምክንያት የሆናቸው የመጀመሪያ ልጃቸው የኦቲዝም ተጠቂ መሆኑ ነው፡፡ እሱን ለመደገፍና ለመርዳት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሌሎች ተመሳሳይ ችግር ያሉባቸውን ልጆችና ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ለ34 ልጆች የቴራፒ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በዕውቀትና በሥነ ልቦና ለማብቃትም ይሠራል፡፡ ማዕከሉ በሥልጠና መርሐ ግብሩ፣ ከሁለት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ወላጆች፣ ተንከባካቢዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሕፃናት ማሳደጊያዎች፣ በሆስፒታሎችና በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ባለሙያዎች በዕውቀት የተደገፈ ሥልጠና መስጠቱንም ወ/ሮ ትዕግሥት ይናገራሉ፡፡

በማዕከሉ ቤተ መጻሕፍት፣ ለሁሉም የዕድሜ ክልል የሚያስጠቅም ከሦስት ሺሕ በላይ መጻሕፍት ያሉ ሲሆን፣ የቤተ መጻሕፍት አባልነትን ከአረንጓዴ ልማትና አካባቢን ከማሰዋብ ሥራዎች ጋር በማቀናጀት እየሠራ እንደሚገኝም ወ/ሮ ትዕግሥት ገልጸዋል፡፡

ሥራ አስኪያጇ እንደሚናገሩት፣ የምሉዕ የተቀናጀ የቴራፒ ማዕከል ከሦስት እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ልጆች ተቀብሎ በሦስት ፈረቃ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የጠዋቱ ፈረቃ ለስምንትና ዘጠኝ ዓመታት ቤት ውስጥ ተቀምጠው ትምህርትና ቴራፒ አግኝተው የማያውቁ ልጆች የሚስተናገዱበት ሲሆን፣ ሁለተኛውና የከሰዓቱ ፕሮግራም ትምህርት ቤት የገቡና ዕገዛ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህም አፍ ያልፈቱ፣ ትምህርት የመቀበልና የባህሪ ችግር ያሉባቸውን ያካትታል፡፡ ሦስተኛው ፈረቃ ሐሙስና ቅዳሜ የሚሰጠው የቴራፒ አገልግሎት ጥቂት ዕገዛ ለሚሹ ልጆች ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ማዕከሉ በቀጣይ ከ12 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ልጆች የመቀበል ዕቅድ እንዳለው የሚናገሩት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ቴራፒ ወስደውና ሠልጥነው የጨረሱ ልጆች ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው እንዲማሩ የማብቃትና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ አክለዋል፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴርና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት የሚሠሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ማዕከሉን ተመሳሳይ ችግር ላለባቸው ልጆች ተደራሽ ለማድረግና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ፣ ለመንግሥት የቦታ ጥያቄ ማቅረባቸውንና ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

በማዕከሉ የፕሮግራም አስተባባሪና የካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ባለሙያ ወ/ሪት ትሁት ግርማ እንደምትገልጸው፣ ማዕከሉ ለልጆች የቴራፒ አገልግሎት የሚሰጡ ስምንት ኮሪደሮች አሉት፡፡

እነዚህ ኮሪደሮች ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ደረጃ በደረጃ ነገሮችን ማከናወን የሚለማመዱባቸው ክፍሎች ናቸው፡፡

በማዕከሉ ለሚገኙ ልጆች ድጋፍና እንክብካቤ የሚያደርጉ በልዩ ፍላጎት የሠለጠኑ መምህራን፣ ማኅበራዊ ባለሙያዎች የሥነ ልቦና ባለሙያ (ሶሻል ወርከሮችና) ሳይኮሎጂስቶች መኖራቸውን የምትናገረው ወ/ሪት ትሁት፣ በኦቲዝም ጥላ ሥር የሚኖሩ ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍና ዕገዛ ካገኙ እንደ ማንኛውም ሰው ውጤታማ መሆን ይቻላሉ ብላለች፡፡

የኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 2 ቀን የሚከበር ሲሆን፣ ዘንድሮም ‹‹የማብቃት ታሪኮች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ዘለቄታዊ የልማት ግቦች ከኦቲዝም ግንዛቤ ጋር በማጣጣም የተገኙ ድሎች›› በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል፡፡

ምሉዕ ፋውንዴሽንም ‹‹እራት በምክንያት›› በሚል መርሐ ግብር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ዕለቱን ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑን ሰምተናል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...