Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊገዳሙ የወጠነው ከ500 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚፈጅ የሆስፒታልና ተያያዥ ግንባታ

ገዳሙ የወጠነው ከ500 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚፈጅ የሆስፒታልና ተያያዥ ግንባታ

ቀን:

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሥር ምሰው ቅጠል በጥሰው ፈዋሽ መድኃኒትን መቀመም ቢችሉም፣ ‹‹የጓሮ ፀበል የቁርበት መንከሪያ ይሆናል›› እንደሚባለው ሆኖ ሙያቸው ብዙም ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል።

ቤተ ክርስቲያኗም፣ አማኞቿንም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ከፀበልና ሌሎች መንፈሳዊ ከሆኑ ተግባራት በዘለለ፣ በዘመናዊ ሕክምናው ያላት እንቅስቃሴ ብዙም አይደለም።

በተለይ ደግሞ ከከተማ ርቀው የሚገኙ መነኮሳት በአቅራቢያቸው የሕክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለመኖሩ፣ በቀላሉ ታክመው መዳን ሲችሉ በሕመም ሲሰቃዩና ሲሞቱ ይስተዋላል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በ1993 ዓ.ም. የተመሠረተው  የመካነ ሕይወት ጮቢ በአታ ለማርያም አንድነት ገዳም፣ የገዳማውያንን የጤና ችግር ከመቅረፍ አልፎ የአካባቢውን ኅብረተሰብ እንዲሁም በገንዘብ እጥረት መታከም አቅቷቸው በየአካባቢው ወድቀው የሚገኙ ሕሙማንን በነፃ የሚያክም ሪፈራል ሆስፒታል ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል።

ገዳሙ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዱግዳ ቦራ ወረዳ በሃርቦ አቡኖ ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን፣ 81 ሔክታር መሬት ይሸፍናል።

በቆሞስ አባ ተክለ ሥላሴ ገብረ ሕይወትና በመንፈሳዊ ልጆቻቸው እንደተመሠረተ የሚነገረው የአንድነት ገዳሙ፣ ላለፉት ሁለት አሠርታት ለሌሎች ገዳማትና ተቋማት ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸው ተነግሯል።

ከተሠሩ ሥራዎች ባሻገር በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ለተነገረለት ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ፣ ከአካባቢው አስተዳደር 350 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ መረከቡንና የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን፣ የገዳሙ አስተዳዳሪዎች ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

‹‹ገዳማት የልማትና የበረከት ምንጭ መሆን አለባቸው፣ ገዳም ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ምዕመናን በምንም ዓይነት መልኩ መቸገር የለባቸውም፤›› ሲሉ የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ሥላሴ ተናግረዋል።

ገዳማውያን ለብዙ ዘመናት በሕክምና ዕጦት ሲሰቃዩ መቆየታቸውን ያነሱት አባ ተክለ ሥላሴ፣ በገዳሙ ሊገነባ የታሰበው ሆስፒታል በውስጡ ያሉ ገዳማውያንና የአካባቢውን ነዋሪ እንዲሁም ሌሎችንም ከማስተናገዱም ባሻገር ለሌሎች ገዳማት ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ፣ ከተመላላሽ ታካሚዎች ባሻገር ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማን የሚሆኑ ከ1,000 በላይ አልጋዎች እንደሚኖሩት ታቅዷል።

ግንባታው የእምነቱ ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያንን ቀና ትብብርና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት የሆስፒታሉ ግንባታ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳንኤል አስራት (ዶ/ር) ናቸው።

ሆስፒታሉ በውስጡ ኮሌጅን ጨምሮ ጤና ጣቢያዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች ማረፊያ ሕንፃዎች፣ የባህል ሕክምና ምርምር ተቋምና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንደሚያካትት ዳንኤል (ዶ/ር) ተናግረዋል።

‹‹ሆስፒታሉ የብዙዎችን የጤና ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይገመታል፤›› ያሉት ሰብሳቢው፣ ከአገር ውጭ ሄደው ለመታከም ለልመና እጃቸውን የሚዘረጉት ግለሰቦችን የሚታደግ ከመሆኑም፣ የአገርን መልካም ገጽታንም የሚገነባ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሕክምና ተቋሙ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር አጥኝዎች ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ለጥናት ከሚወጣው ወጪ ጀምሮ ግንባታው ተጠናቆ፣ አስፈላጊ የሕክምና መሣሪያዎች ተገጥመውና ባለሙያዎች እስከሚቀጠሩበት ባለው ሒደት እስከ 545 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚጨርስ የተናገሩት የግንባታው አርክቴክቸር ክፍል ኃላፊ ሳዶር አስመሮም (ኢንጂነር) ናቸው።

‹‹ግንባታው ሲጠናቀቅም በአገራችን ብሎም በቀጣናው የማይሰጡ የሕክምና ዓይነቶችን መስጠት የሚያስችል ይሆናል፤›› ያሉት ሳዶር (ኢንጂነር)፣ ከኢትዮጵያ ተነስተው ለተሻለ ሕክምና ወደ ውጭ የሚሄዱትን ታካሚዎች ከማስቀረቱም ባሻገር፣ ከተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ተነስተው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ወደ ቱርክና የመሳሰሉት አገሮች በሪፈር የሚበሩ ታካሚዎችን በዚሁ ማስተናገድ እንደሚቻል አውስተዋል።

ለግንባታው የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት በቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሚጀመር ሲሆን፣ ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል።

ገዳሙ የወጠነውን ግዙፍ ፕሮጀክት ዕውን ማድረግ እንደሚችል ከተገደመበት ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ የሠራቸው ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች አመላካች መሆናቸው ተጠቁሟል።

በዚህም አሥር የሚሆኑ ዓበይት ተግባራት የተጠቀሱ ሲሆን፣ ከ110 በላይ የአብነት ተማሪዎችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን እንደሚያስተምርና ለ300 ተማሪዎች ከመዋለ ሕፃናት እስከ አራተኛ ክፍል በነፃና በዝቅተኛ ክፍያ እንደሚያስተምር በመግለጫው ተመልክቷል።

44 ዲያሜትር ስፋትና የስምንት ፎቅ ያህል ርዝመት ያለው ባለቅስት ቤተ መቅደስ በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ መገባደጃው ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በግብርናው መስክ ደግሞ በየዓመቱ ከ400 ኩንታል በላይ እህል በማምረት በአካባቢው ያሉ የተቸገሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንደሚረዳ ተመልክቷል።

በገዳሙ ከ20 የሚበልጡ የወተት ላሞችን በማርባትም ከሚገኝ ወተት ወላጆቻቸውን ላጡና ለተቸገሩ ሕፃናት እንደሚሰጥና በተጨማሪም ባለ አንድ ፎቅ ዘመናዊ የእናቶች ማረፊያ፣ የሕፃናት ማሳደጊያና ከ1,000 ሰው በላይ የሚይዝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በውስጡ መያዙ ተነግሯል።

ገዳሙ የራሱ የሆነ የእርሻ ትራክተር ያለው ሲሆን፣ ከሦስት መቶ ሺሕ ሌትር በላይ የሚይዝ የውኃ ገንዳ ማስገንባቱንና ለሥራ የሚሆን ተሽከርካሪ ለመግዛት ማቀዱም ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ የእህል ወፍጮ፣ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት፣ ሞተር ሳይክልና ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ገዝቶ እየሠራባቸው እንደሚገኝ የገዳሙ ኃላፊዎች አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...