Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ደጓሹ

ቀን:

የድጉስ ሥራ በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ በተለያዩ የእምነት ተቋማት በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የድጉስ ሥራ ከብራና መጻሕፍት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጎዱ መጻሕፍትን የሚደጉሱና የሚያክሙ ተቋማትና ግለሰቦች በብዛት ባይገኙም፣ በጣት ከሚቆጠሩ የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል ኤርሚያስ ሙላቱ አንዱ ነው፡፡

አቶ ኤርሚያስ እንደሚናገረው፣ የድጉስ ሥራ ዘመናትን ያስቆጠረና ከአባቶች እየተሻገረ እዚህ ዘመን የደረሰ ጥበብ ነው፡፡ የድጉስ ሙያ፣ ጥንታዊ ወይም ዘመናዊ መጻሕፍት ለረዥም ጊዜ ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲቆዩ የማድረጊያ ዘዴና መንገድ ሆኖ ያገለግላል፡፡

መጻሕፍትን የመደጎስ ሥራ በቤት ውስጥ ሙከራ (በራሱ መጽሐፍ) እንደ ጀመረ፣ ሥራውን የተመለከቱ ጓደኞቹና የቅርብ ሰዎች የሚያደርጉለት ድጋፍና ዕገዛ ብርታት ሆኖት ሥራውን ሊገፋበትና ሊቀጥለበት ችሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ መጻሕፍቱን የሚደጉሰው ከንፁህ ቆዳ ነው፡፡ አገራችን የሚገኙ ቆዳ አምራቾች ለልብስ፣ ለጫማ፣ ለቦርሳና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚያመርቷቸውን ቆዳዎች ለሥራው የሚጠቀም ሲሆን፣ በአብዛኛው የበግና የበሬ ቆዳ ለድጉስ ሥራው የሚገለገልባቸው ናቸው፡፡

የድጉስ ሥራውን ከጀመረ አንስቶ በቁጥር የማያስታውሳቸውን መጻሕፍትን መደጎሱንና ከድጎሳ የሚገኘውም ገቢ እንደ የመጻሕፍት ዓይነት መጠንና የገጽ ብዛት የተለያየ ነው፡፡

መጻሕፍቱ በጣም የተጎዳ ከሆነ ለመደጎስ ረዥም ጊዜ የሚጠይቅና አዲስ መጽሐፍ ከሆነ ደግሞ የሚወስደው አነስተኛ ጊዜ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ኤርሚያስ፣ እነዚህ ነገሮችና የሚጠቀምባቸው ቁሳቁሶች ተደማምረው ለድጉስ በሚመጡ መጻሕፍት የዋጋ ተመን ይወጣላቸዋል፡፡

የድጉስ ሥራ በአብዛኛው በእጅ የሚሠራ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለዚህ ሥራ የሚያገለግሉ ዘመናዊ ማሽኖች በውጭ አገሮች ቢኖሩም፣ ዋጋቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ለመጠቀም የአቅም ውስንነት ተግዳሮት ሆኖታል፡፡

ሙያውን ለመልመድ የረዥም ጊዜ የቆየ ፍላጎቱ በመሆኑ፣ የዚህ ሙያ ልምድ የነበራቸውና በቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚያውቃቸውን አባቶች እንዲያስተምሩት በመጠየቅና በተጨማሪ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ ሙያውን ለማዳበር መቻሉንም ይናገራል፡፡  

እሱ እንደሚገልጸው፣ ከተቋማት ጋር በመገናኘት እስካሁን የሠራው ሥራ ባይኖርም፣ መጻሕፍት እንዲደጎስላቸው የሚሹ የተለያዩ ግለሰቦች መጻሕፍትን  በማምጣት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጥንታዊ አገሮች በርካታ ታሪክና ጥበባቸው የሚገኘው በጥንታዊ መጻሕፍት ውስጥ ስለሆነም ቀደምት የብራናና ሌሎችም መጻሕፍት እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እንደ አንድ ግለሰብ የራሱን ጥረትና አበርክቶ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡

‹‹በየገዳማቱና በየመስጊዱ እንደ ብራና ያሉና ሌሎች ጥንታዊ መጻሕፍት እንክብካቤ አጥተውና ተጎሳቁለው ስለሚገኙ፣ መንግሥት በትምህርት ደረጃ ለወጣቶች ሥልጠና እየሰጠ የሥራ መስክ ቢያደርገው አንድም መጻሕፍቱ ዕድሜያቸው ይጨምራል፣ ሁለትም ለግለሰቦች የገቢ ምንጭ ይሆናል፤›› ሲል ሐሳቡን የሚሰነዝረው ኤርምያስ፣ መንግሥት የድጉስ ሙያን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት በትምህርት ሥርዓቱ ማካተትና በተቋማት ደረጃ ትምህርቱ መስጠት ይገባዋል ይላል፡፡ በዚህ የድጉስ ሙያ ውስጥ ዓመታትን ካስቆጠሩ መጻሕፍት መካከል የሪቻርድ ፓንክረስት (Economic History of Africa)፣ የቅዱስ ያሬድ ዜማ የተጻፈበትና በ1965 ዓ.ም. የታተመ መጻሕፍና ሌሎችንም ለጊዜው የማያስታውሳቸውን ቀደምት መጻሕፍት መደጉሱን የሚናገረው ወጣቱ፣ አንድን መጽሐፍ ለመደጎስ እንደ መጽሐፉ ጉዳት እስከ አንድ ወር ጊዜ ይወስዳል፡፡

መጽሐፉ እጅግ የተጎዳ ከሆነ እያንዳንዱ ገጽ ተለቅሞ መሰፋት ይኖርበታል፡፡ የተጎዳው መጽዳት አለበት፡፡ የመተኮስ ደረጃም ሊደርስ ይችላል፡፡ ስለሆነም መጽሐፍ ለመደጎስ በቅድሚያ የመጽሐፉን ጤንነትና የጉዳት ደረጃውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የድጉስ ሥራ ለመሥራት በቅድሚያ መጽሐፉ በጥንቃቄ መገንጠል ይኖርበታል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ሊበተን የሚችልበትም አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንዴ መጽሐፉ ደህና ከሆነ እዚያው ባለበት የጎደሉ ገፆች እየተሟሉ ይሰፋል፣ ይደጎሳል፣ ከቨር ቦርድ ይሠራል፣ ከዚያም በሚፈለገው ቀለም ቆዳውን የሚለብስ ይሆናል፡፡

እንደ ባለሙያው አገላለጽ፣ የድጉስ ሥራ በኢትዮጵያ ጥንት እንደመጀመሩና ረዥም ዕድሜ እንደማስቆጠሩ አንፃር ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ በርካታ ዕድሜ ጠገብ መጻሕፍት በአያያዝና በአጠቃቀም ጉድለት እየተበላሹ ይገኛሉ፡፡ አያሌ ጥበቦችን፣ ዕውቀቶችንና ታሪኮችን የያዙና ከትውልድ ትውልድ ሊሻገሩ የሚገባቸው እነኚህ ጥንታዊ መጻሕፍት ተጠብቀው እንዲኖሩ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ለሙያው ዕውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

እንደ ባለሙያው፣ መንግሥት የዱጉስ ባለሙያዎችን መደገፍ አለበት፡፡ ለሥራው የሚያገለግሉና በአገር ውስጥ የማይመረቱ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ሙያተኞች ሙያቸውን የሚያጎለብቱበት አጫጭር ሥልጠናዎችን በማዘጋጀትና እንዲሁም ሌሎችንም አስፈላጊ ዕገዛዎች በማድረግ ባለሙያዎች ከዘርፉ እንዳይወጡ ማበረታታት ይኖርበታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...