Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዳሰሳዊው ጥናት ከ15 በመቶ በላይ የኅብረተሰብ ክፍል የመስማት ችግር እንዳለበት አመለከተ

ዳሰሳዊው ጥናት ከ15 በመቶ በላይ የኅብረተሰብ ክፍል የመስማት ችግር እንዳለበት አመለከተ

ቀን:

ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በተወሰደ ዳሰሳዊ ጥናት 15.8 ከመቶ ያህሉ የመስማት ችግር ያለባቸው ሆነው መገኘታቸውን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ አገሮች ከሚስተዋሉት የጆሮና የመስማት እክሎች መካከል 60 ከመቶ የሚሆነው በሕክምና መዳን ይችላል የሚለውን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ተከትሎ፣ የ12 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት የሆነው አገር አቀፍ የመስማት ዳሰሳ ጥናት ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ በጥናቱ የታቀፉት በሁሉም የዕድሜ ክልልና ፆታ የሚገኙ 3000 ቤተሰቦች ናቸው፡፡

ከቤተሰቦቹም መካከል 60 ከመቶ የሚሆኑት የገጠር፣ ቀሪዎቹ 40 ከመቶ ያህሉ ደግሞ የከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን፣ ጥናቱም የተከናወነው ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ መሆኑን ጥናቱ ይፋ ሲደረግ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሰሞኑን ጥናቱ ይፋ ሲደረግ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የጆሮ፣ የአፍንጫና የጉሮሮ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት አለነ መሸሻ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አገር አቀፍ የመስማት ዳሰሳ ጥናቱ በኢትዮጵያ በዓይነቱ አዲስና የመጀመሪያ ነው፡፡ የጥናቱ ውጤትም ለጤና ሚኒስቴርና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት ቀርቧል፡፡

እንደ አለነ (ዶ/ር)፣ ጥናቱ የተካሄደው ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ነው፡፡ በዚህም በመኖሪያ አካባቢያቸው ከስድስት ወራት በላይ የኖሩ 3,000 ቤተሰቦች ተሳትፈዋል፡፡

ጥናቱ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች መካከል በምሥራቅ ኢትዮጵያ የታየው የመስማት ችግር በእጅጉ የከፋ ሆኖ እንደተገኘ፣ ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማወቅ የሚያስችል ሌላ ጥናት ማከናወን እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ዓይነቱ የዳሰሳ ጥናት በስተቀር ከአሁን በፊት ምን ያህል ሰዎች ናቸው የመስማት ችግር ያለባቸው? በሚለው ዙሪያ ጥናት እንዳልተካሄደ ሲሠራበት የቆየውም የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ላይ ባስቀመጠው መረጃ መሠረተ መሆኑን አለነ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡  

ጥናቱ ለሕክምና አገልግሎት ከሚያበረክተው መረጃ ባሻገር፣ የስፔሻሊቲ ትምህርት ለሚከታተሉ ተማሪዎች ትልቅ አንድምታ እንዳለው፣ ፖሊሲ ለሚያወጡና ለሚተገብሩ አካላትም ጥሩ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የጆሮና የመስማት ችግር በርካታ ጫናዎችን እንደሚያስከትል፣ ከጫናዎቹም ከመካከል ችግሩ ባለባቸው ሕፃናት የትምህርት አቀባበል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ችግሩ በልጅነት ካልታከመ በአዋቂነት ወይም በጎልማሳነት ዕድሜ የከፋና ሥር የሰደደ እንደሚሆን አስረድተዋል

የመስማት ችግር ካለባቸው አዋቂዎች መካከል ብዙዎቹ ሥራ እንደማያገኙ፣ ቢያገኙም በትንሽ ደመወዝ ለመሥራት እንደሚገደዱና ይህም ሆኖ የተግባቦት ችግር እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የአንገት በላይ ቀዶ ሐኪምና በሲቢኤም የጆሮ ጤናና የመስማት እንክብካቤ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ብሥራት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ጆሮን ከተለያዩ የድምፅና የምት አደጋዎች መጠበቅና መከላከል አስፈላጊ እንደሆነ መክረዋል፡፡

ዘመኑ ያፈራቸውን የማዳመጫ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም እየተለመደ የመጣ ቢሆንም፣ አዘውትሮ መጠቀምና ለረዥም ጊዜ ጆሮን ለከፍተኛ ድምፅ እንዲጋለጥ ማድረግ የመስማት ችግርን ሊያስከትል እንደሚችል አክለዋል፡፡

የሕክምና ኮሌጁ ፕሮቮስት ሲሳይ ሥርጉ (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ ኮሌጁ ባለፉት አምስት ዓመታት ከሲቢኤም ጋር በመተባበር በጆሮና መስማት ጤና ክብካቤ ዙሪያ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናወን ቆይቷል፡፡

ከተከናወኑት ተግባራትም መካከል ጆሮና የመስማት ጤና ክብካቤ ላይ የሚሠሩ ጤና ባለሙያዎችን ማሠልጠንና የጆሮና መስማት ጤናን የሚያሻሽሉ ቀዶ ሕክምናዎችን ማከናወን እንደሚገኝበት አስረድተዋል፡፡

የመስማት ችግር ያለባቸውን ልየታ የተሠራ ሲሆን፣ የመስሚያ መሣሪያዎችን በመስጠት ረገድ የተቀናጀና የጎላ ተሳትፎ መደረጉንም አክለዋል፡፡

የአንገት በላይ ስፔሻሊስቶች፣ ሐኪሞችና የሠለጠኑ ነርሶች በመረጃ መሰብሰብ ሥራው የተሳተፉ ሲሆን፣ ጥናቱም የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መመርያ መሠረት የተከናወነ ነው፡፡

የዳሰሳ ጥናት ፕሮጀክቱ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅና ‹‹ሲቢኤም›› ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በመተባር አከናውነውታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...