Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልግእዝ እና የአብነት ትምህርትን የመታደግ ትልም

ግእዝ እና የአብነት ትምህርትን የመታደግ ትልም

ቀን:

የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ሕግ፣ ነገረ ሃይማኖት፣ ነገረ ሥራይ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ፈለክ፣ ቅኔ፣ ዜማ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ አመለካከትና ሥነ ልቦና የተላለፈው በግዕዝ ቋንቋ አማካይነት ነው፡፡

ይሁን እንጂ በተለይ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት በኢትዮጵያ ካቆጠቆጠ ወዲህ የግዕዝ ቋንቋን ወደ ጎን በመተዉ እንዲዳከምና አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አድርጎታል፡፡

ባለፉት ዓመታትም የአማራና የትግራይ ክልሎች ከዩኒቨርሲቲዎቻቸው ባለፈ የግዕዝ ቋንቋን  በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በመደበኛነት ለማስተማር አቅደው ነበር።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ እስካሁን ይኼ ነው የሚባል  አመርቂ ውጤት አልታየም። ግዕዝ አሁንም የቤተ ክህነት ቋንቋ ሆኖ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚገኙ የአብነት ተማሪዎች  እየተማሩት ይገኛል።

የአብነት ትምህርት ቤት በድንቅ ችሎታቸው የሚታወቁ የሥነ ፈለክ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ሕክምና ጠበብትንና ሌሎች የአገር ባለውለታዎችን ያስገኘ ተቋም ነው።

ነገር ግን የግዕዝ ቋንቋ መፍለቂያ እንደሆነ የሚነገርለት የአብነት ትምህርት ቤት  ትኩረት ተነፍጎት አሁንም ኋላቀር በሆነና ባልተደራጀ መንገድ እየተሰጠ በመሆኑ  የአብነት ተማሪዎችን በመደገፍ የግዕዝ ቋንቋን ለማስፋፋት ያለመ ‹‹ቁስቋም ቅድስት ማርያም መንፈሳዊ ማኅበር›› ወደ ሥራ መግባቱን ረቡዕ መጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

‹‹በእንተ ስማ ለማርያም ለእኔ ተማሪ›› በሚል መሪ ቃል ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቀው ማኅበሩ፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ከቤተ ክርስቲያን እጅ ወጥተው የተበተኑ ትውልድ አሻጋሪ መጻሕፍትን የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራ በመግለጫው ተመልክቷል።

ማኅበሩ ወጣቶችን በዕውቀትና በክህሎት ማብቃት፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን በማስከፈት፣ ገዳማትን መደገፍ፣ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ አደጋዎች ምክንያት በተለያዩ ችግሮቸ ውስጥ የሚገኙ ገዳማትንና አድባራትን መልሶ በማቋቋም የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ለሴት መነኮሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማሟላት እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት የመስጠት ሥራዎችን አካቶ እንደሚሠራ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ጥንታዊውን የአብነት ትምህርት ቤትን ይዛና ጠብቃ አሁን እስካለንበት ትውልድ ማድረስ የቻለች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

የብዙ ጥበብ መፍለቂያ የሆነው የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያገለግለው የግዕዝ ቋንቋ ጥልቅና ሰፊ ምስጢራትን የያዘ ቋንቋ ነው ያሉት የሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ናቸው።

ነገር ግን ይህ የአገር ሀብት የሆነው ቋንቋ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ብቻ ተደርጎ ከተወሰደ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ይህም ተግባር ማንነትን የዘነጋ ትውልድ ስለመኖሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

በዘመመ የሳር ጎጆ ውስጥ ለሚገኙ የአብነት ተማሪዎችና መምህራን ማረፊያ፣ የመማሪያ ጉባዔ ቤት፣ የምግብ ማብሰያ፣ የተሟላ ቤት በተለያዩ የአገሪቱ ገጠራማ ሥፍራ መሠረተ ልማትን በሟሟላት ከረሃብና እርዛት ለመከላከል እንደሚሠራ ተገልጿል።

በ20 የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚገኙ ለ1,200 ተማሪዎች የሁለት ዓመት መጻሕፍትን፣ ቀለብና አልባሳት የማሰባሰብ፣ እንዲሁም የሊቃውንት መምህራን ደሞዝ ክፍያ መፈጸም፣ በአብነት ትምህርት ቤቶች አስከፊ የሆነውን ተላላፊ በሽታ  ለመከላከል ታሳቢ መደረጉም ተነግሯል።

ለዚህም 24 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን ፕሮጀክቱ ለሁለት ዓመት እንደሚቆይ ተገልጿል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...