Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከመቅደላ የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

ከጥቂት ዓመታት በፊት ‹‹ራዕየ ዮሐንስ የዓለም መጨረሻ›› በሚል ርዕስ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ባስነበበው መጽሐፉ ገጽ 18  ላይ፣ ከመቅደላ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን መረጃ አጋርቶን ነበር፡፡

እቴጌ ምንትዋብ ራዕይ መጽሐፍን አስጽፈው ለጎንደር ደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለራሳቸውና ለልጃቸው ለኢያሱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ መስጠታቸውንና ይህም መጽሐፍ በመቅደላው ወረራ ጊዜ እንግሊዞች ዘርፈው ወስደው አሁንም ድረስ በብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት MSOr. 533 ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብትና ኩራት የሆኑ ቅርሶቻችንና የቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት ወደ አውሮፓ እንዲሻገሩ ምክንያት ከሆኑት መካከል የመቅደላው ጦርነት አንዱ እንደ ነበር የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎችና ሰነዶች አሉ፡፡ 

«የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ»  በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባሳተመው የጥናት መጽሐፍ፣ ግርማ ኪዳኔ የተባሉ ምሁር ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ በወቅቱ የጦርነቱን ሁኔታና የእንግሊዞቹን ዝርፊያ በማስታወሻው ላይ ያሰፈረው ‹‹የኒውዮርክ ታይምስ›› ሪፖርተር የሆነው ሄነሪ ስታሊንን ጠቅሰው የወቅቱን ዝርፊያና ውድመት እንዲህ ገልጸውታል፡-

አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ባጠፉበት ወቅት የተኩስ ድምፅ በሰሙበት አካባቢ ሁለት የአይሪሽ ዜግነት ያላቸው ወታደሮች፣ የተኩስ ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተሯሯጡ በመምጣት በሕይወትና በሞት መካከል ከነበሩት ከአፄ ቴዎድሮስ ላይ ሽጉጣቸውን፣ የጣታቸውን የወርቅ ቀለበትና የአንገታቸውን መስቀል መውሰዳቸውንና እነዚህ ወታደሮችም እኚህ በጀርባቸው የተንጋለሉት ሰው አፄ ቴዎድሮስ መሆናቸውን በጭራሽ እንዳላወቁ በመግለጽ እነዚህ ወታደሮች በአጠገባቸው የተጋደሙት ሰው አፄ ቴዎድሮስ መሆናቸውን ያወቁት ሽጉጣቸውን እያገላበጡ በማድነቅ ሲመለከቱ በጎን በኩል ከብር ተቀርጾ የተለበደውን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ ነበር፡፡ ጽሑፉም እንዲህ የሚል ነበር፡፡ 

‹‹... 1854  ለአሽከሬ ለፕላውደን የአቢሲኒያው ንጉሥ ቴዎድሮስ ላደረጉለት ቅንነት የተሞላበት ደግነት ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ ከታላቋ ብሪታንያና አየር ላንድ ንግሥት ቪክቶሪያ የተላከ ስጦታ፡፡››

የአፄ ቴዎድሮስ መሞት ከተሰማ በኋላ የእንግሊዝ ወታደሮች በቀጥታ የተሰማሩት ወደ ዝርፊያ ነበር፡፡ ‹‹ይህ ደግሞ በወቅቱ በጣም የተለመደ ነበር›› ይላሉ ሪታ ፓንክረስት በጥናታዊ ጽሑፎቻቸው፤ «The Capture of Maqdala was followed by an evening of looting in the best tradition of the British army at that time»  እና ‹‹The Maqdala Library of Tewodros ›› በሚል ባቀረቡት አንድ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ ከ350 በላይ የሚሆኑ የብራና መጻሕፍት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና ክርስትና ሃይማኖቷን በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት በሚል ወደ አውሮፓ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መጻሕፍት ውስጥ እጅግ የተዋቡና በልዩ ሁናቴ የተጠረዙ የብራና መጻሕፍትን ለንግሥት ቪክቶሪያ በስጦታ መልክ ተሰጥቷቸው ዊንድሶር ካስል በተባለ በንግሥቲቱ ልዩ ቤተ መጻሕፍት በክብር እንደተቀመጠና እነዚህ ብርቅ ስብስቦች ለማየት ልዩ የሆነ የንግሥቷ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ ሪታ ፓንክረስት ጽፈዋል፡፡

ይህን የመቅደላውን የእንግሊዞቹን ዝርፊያ አቶ ግርማ ኪዳኔ ከላይ በጠቀስነው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ከእንግሊዝ ወታደሮች ከመቅደላ በጨረታ የገዛውን በርካታ ቅርሶች በመጫን ወደ አውሮፓ ስላሻገረው የኒዮርክ ታይምሱ ሪፖርተር ሄነሪ ስታሊን ሲያብራሩም፡-

ስታሊን ከእንግሊዝ ወታደሮችና ሹማምንት በጨረታ የገዛውን በርካታ ቅርሶች በአምስት አጋሰስ ጭኖ ከመቅደላ ወደ ሰንዓፌ ከዚያም ወደ ዙላ ከምትባለው የቀይ ባሕራችን ጠረፍ ደረሰ፡፡ ከዚያም አምስት በቅሎዎች ላይ ጭነው ያመጣቸውን ቅርሶች በሣጥን አስገብቶ ካሸጋቸው በኋላ በቅሎቹን ሽጦአቸው በማግስቱ «ትራንስፖርት እስቲመር ኢንጂን» ተብላ በምትጠራው አነስተኛ መርከብ እርሱና የአፄ ቴዎድሮስን አራት ዘውዶች ለንግሥት ቪክቶሪያ እንዲያደርስ ከተወከለው ከኮሎኔል ሚልወርድ ጋር በመሆን በስዊዝ ካናል በኩል አድርገው ቅርሶቻችን ከአገር እንዲወጡ አደረገ፡፡

በተጨማሪም የእንግሊዝ ጦር አዝማች የነበረው ጄኔራል ናፒየር በርካታ ቅርሶችን በመዝረፍና በጨረታ በመሸጥ፣ እንዲሁም እጅግ ውድ የሆኑትን ቅርሶችን የግሉ ንብረት በማድረግና በመጨረሻም መቅደላንና አፄ ቴዎድሮስ የተቀበሩበትን የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያንን ሳይቀር በእሳት በማጋየት የጦርነቱን ፍጻሜ እንዳበሰረ ጽፈዋል፡፡

የአፄ ቴዎድሮስ እስረኛና ምርኮኞች ከነበሩት እንግሊዛውያን ሚሲዮናውያን መካከል አንዱ ስለተፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊትና ዝርፊያ የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርተር የሆነው ስታሊን በወቅቱ የታዘበውን ሲገልጽ፡- 

‹‹…በጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው ከነበሩት ከአቡነ ሰላማ መቃብር ድረስ በመሄድ አስክሬናቸውን ከመቃብሩ በማውጣት ከአልማዝ የተሠራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበረ ነው…›› ሲል በሐዘኔታ የታዘበውን በመጽሐፉ አስፍሮታል፡፡

አቶ ግርማ ኪዳኔም በጥናት ወረቀታቸው እንደገለጹት፣ የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሠራ አክሊልና የቁርባን ጽዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ የሆነው ሆልምስ በአራት እንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበርና በኋላም እነዚህን ቅርሶች ሪቻርድ ሆልምስ ከኮሎኔል ፍሬዘር፣ ከኮሎኔል ሚልወርድና ከኮሎኔል ካሜሩን ጋር በመመሳጠር « አቢሲኒያን ፈንድ ኮሚቴ»  በሚል ስም ለብሪትሽ ሙዚየም በሁለት ሺሕ የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲሸጥላቸው እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 1868  አቅርበውት እንደነበር የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች በዋቢነት በመጥቀስ ጽፈዋል፡፡

በመቅደላ ወረራ ወቅትና በተለያዩ ጊዜያት ወደ አውሮፓና የተለያዩ ዓለማት የወጡ ታሪካዊና ብርቅዬ ቅርሶቻችንን በማስመለስ ረገድ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፣ እየተደረጉም ነው፡፡ በአንድ ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ እነዚህን በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የተወሰዱትን ቅርሶች ለማስመለስ የተቋቋመ አፍሮሜት (AFROMET)  የተባለ ማኅበር ነበር፡፡ ይህ ማኅበር በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት በመቅደላ ጦርነት ተዘርፈው ከሄዱት ታሪካዊ ቅርሶቻችን መካከልም፣ የአፄ ቴዎድሮስን መዝሙረ ዳዊት፣ የአንገታቸው ክታብ፣ ጎራዴያቸውንና ሌሎችንም ውድና ብርቅዬ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶቻችንን በማስመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ መዘክር ለሕዝብ ዕይታ ቀርበው እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡

በወቅቱም አፍሮሜነ የተባለውን ማኅበር በበላይነት ይመሩ የነበሩት፣ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ባለቤታቸው ሪታ ፓንክረሰት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር (ሶፊ)  አባላት፣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ምሁራንና በቅርስ ዙሪያ ከሚሠሩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ እንደ ዩኔስኮ ካሉ ድርጅቶች ጋር እያደረጉት ባለው ጥረት ትልቅ ሥራን ሠርተዋል፡፡

በአሁን ወቅትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በታሪክ፣ በባህልና በቅርስ ዙሪያ በሚሠሩ ኢትዮጵያውያንና የውጪ አገር ምሁራንና ተቆርቋሪዎች አማካይነት እየተደረገ ያለው ጥረት ለፍሬ እንደሚበቃ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ሒደትም ወደፊትም በእንግሊዝና በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ በርካታ ቅርሶቻችን እንዲመለሱልን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እነዚህ ቅርሶች የጋራ ሀብቶቻችንና ኩራታችን ናቸውና ድምፃችንን በአንድነት ልናሰማ ይገባናል እላለሁ፡፡

 ሰላም ለኢትዮጵያ!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles