Sunday, April 21, 2024

የፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራ ሊፈጥረው የሚችለው የፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ ልዩነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሰላም ጥረት ገና ሲጀመር ጀምሮና ወደ ፕሪቶሪያ ስምምነትም ሲገባ አርቆ አሳቢ ወገኖች ሒደቶቹ ሁሉንም ወገን አቃፊ እንዲሆኑ ሲወተውቱ ነበር፡፡ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ሁሉም ኃይሎች የሚያነሱት የየራሳቸው ጥያቄ መኖሩን በመጥቀስ፣ ይህ ጥያቄያቸው በተቻለ መጠን በተመጣጣኝ ሁኔታ የሚስተናገድበት መንገድ እንዲመቻች ውትወታ ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡ ጦርነቱ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይወሰን በአፋርና በአማራ ክልሎችም የተስፋፋ በመሆኑ ሕወሓትና የፌዴራል መንግሥቱ ወደ ድርድሩ ሜዳ ይዘውት የሚመጡት የመደራደሪያ ነጥብ ብቻ ሳይሆን፣ በጦርነቱ ተጎጂ ሆነው የቆዩ ሌሎች ክልሎችም የሚያነሷቸው ጥያቄ በመድረኩ ቦታ እንዲያገኙ ሐሳብ የሰነዘሩ ነበሩ፡፡

ወደ ድርድሩ ሜዳ ሁለቱ ወገኖች ሲገቡ በተለይ በመንግሥት ወገን የአማራንና የአፋርን ክልል ጉዳዮች ማንሳት የሚችሉ ተወካዮች ቢመደቡ የተሻለ እንደሚሆን ጭምር የጠቆሙ አልጠፉም፡፡ ይህ ሁሉ ታልፎ የፕሪቶረያ ስምምነት ተደረገ፡፡ ከዚህ ወዲህ ደግሞ የስምምነቱ ሰነድ በያዛቸው የመግባቢያ ነጥቦች የተለያዩ ሐሳቦች ይነሱባቸው ጀመር፡፡ ለአብነትም በሕገ መንግሥታዊ አግባብ የሚል አንቀጽ በስምምነቱ ቢገባም፣ አጨቃጫቂ ቦታዎች እንዴት ሊፈቱ ነው የሚለው አሁንም ድረስ ማወዛገቡን ቀጥሏል፡፡  

ተፈናቃዮችን የመልሶ ማስፈር ሥራ፣ ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ጉዳይ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ውይይት ጉዳዮች በምን መንገድ ሊመሩ ነው የሚሉና ሌሎችም ጉዳዮች ከስምምነቱ መፈረምም ወዲህ የመከራከሪያ ነጥብ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ በጦርነቱ ለደረሱ ውድመቶች የመልሶ ግንባታ፣ የጥገናና የካሳ ጉዳይ በቂ መልስ አላገኘም እየተባለ መነገሩ በቀጠለበት ወቅት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈጸመ አንድ ዓመት የተቆጠረ ቢሆንም፣ የስምምነቱ አተገባበር የፈጠረው ሒደት አለመግባባት ግን አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከሰሞኑ ይህንኑ የስምምነት ትግበራ ሒደት በተመለከተ የአፍሪካ ኅብረት በጠራው የመገምገሚያ መድረክ ላይ በብዙ መንገዶች ስምምነቱ ፍሬ ያፈራ ቢሆንም፣ ገና ብዙ የትግበራ ምዕራፍ እንደሚቀረው መግለጹ አይዘነጋም፡፡

የፖለቲካ ውይይት፣ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ፣ ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ የማቋቋም የመሳሰሉ ወሳኝ የስምምነቱ ጉዳዮች ገና አለመነካታቸውን ነው የኅብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት የመገምገሚያ ስብሰባውን አስታከው የተናገሩት፡፡ 

የፕቲቶሪያ ስምምነት በተለይ ለአጨቃጫቂ ቦታዎች መልስ በመስጠቱ ሒደት ፈተና እንደገጠመው በሰፊው ይነገራል፡፡ የስምምነት ሰነዱ አጨቃጫቂ ጉዳዮች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዕልባት ይሰጣቸዋል ቢልም፣ በትግራይና በፌዴራል መንግሥቱ፣ እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልል መካከል ለዚህ የስምምነት አንቀጽ የሚሰጡ ፍቺዎች ፍጹም ሲቃረኑ ይታያል፡፡

የአጨቃጫቂ ቦታዎች ዕልባት አሰጣጥ ጉዳይን በተመለከተ ከውጭ ሆነው ጉዳዩን እንዳኝ የሚሉና በፕሪቶሪያው ድርድር ወቅት ተሳታፊ የነበሩ እንደ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካን የመሳሰሉ ኃይሎችም ቢሆኑ የሚያነሱት ሐሳብ በአወዛጋቢነት ነው የሚጠቀሰው፡፡

አንዳንዶች ይህ ሁኔታ ለትግራይ ክልል መንግሥት የበለጠ ጫና ለመፍጠር መደፋፈር እንደሰጠው ቢናገሩም፣ ሌሎች ግን በብዙ አስገዳጅ መነሻ ምክንያቶች የተነሳ ነው የትግራይ ክልል የአጨቃጫቂ ቦታዎች ጉዳይ በቶሎ ዕልባት እንዲሰጠው ግፊት እያደረገ ያለው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ሕወሓት የአፍሪካ ኅብረቱን የፕሪቶሪያ ስምምነት ግምገማ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ አለመተግበር፣ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ሕዝቡ እምነት እንዲያጣ ሊያደርገው እንደሚችል ሥጋቱን ገልጿል፡፡ ጦርነቱ ቢቆምም በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢ በኤርትራና በአማራ ኃይሎች እጅ ሥር መሆኑን በመጥቀስ፣ የትግራይ ክልል ሙሉ ግዛት እንዲመለስ ጠይቋል፡፡ የትግራይ ክልልን ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችና ኮሪደሮች አሁንም ድረስ ዝግ መሆናቸውን በማስታወስ፣ በዚህ ላይ አስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካ ውይይት መጀመር እንዳለበትና ከበጀት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችም መልስ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የስምምነቱ በርካታ የትግበራ ምዕራፎች ገና ብዙ እንደሚቀራቸው ያስታወቀው ሕወሓት የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ምሉዕ የሚሆነው የፌዴራል መንግሥቱ ለሰላም ስምምነቱ መተግበር ያለውን ቁርጠኝነት ሲያረጋግጥ ነው ይላል፡፡

ከዚህ ቀደምም ቢሆን አንዴ በሕወሓት ሌላ ጊዜ ደግሞ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስም በሚወጡ መግለጫዎች፣ በፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አተገባበር ሒደት ላይ የትግራይ ክልል የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሲስተጋቡ ታይቷል፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ውስን በሆኑ አጋጣሚዎች መልስ የሰጠው የፌዴራል መንግሥቱ በተለይ በኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር በኩል ባወጣቸው መግለጫዎቹ የሰላም ስምምነቱ ምሉዕ ሆኖ ላለመተግበሩ ዋናው እንቅፋት ራሱ የትግራይ ክልል እንደሆነ ሲያሳውቅ ቆይቷል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በእነዚህ በተደጋጋሚ የሰላም ስምምነቱን አተገባበር በተመለከቱ መግለጫዎቹ የትግራይ ክልልን ሲወቅስ ቆይቷል፡፡ ክልሉ ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ ወታደሮቹን በካምፕ አስፍሮ እየቀለበ ነው ሲል ለሒደቱ ዝግጁ አለመሆኑን ተችቷል፡፡ በአጨቃጫቂ ቦታዎችን በተመለከተ በስምምነቱ መሠረት ቦታዎቹ በሕገ መንግሥቱ እስኪፈቱ፣ በፌዴራል ኃይሎች እጅ እንደሚቆይ መገለጹን በመጥቀስ ትግራይ ክልል ካልተቆጣጠርኩ ማለቱን ሲተችም ነበር፡፡

የፌዴራል መንግሥት የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ደጋግሞ ቢጠቅስም፣ በሰላም ስምምነቱ ትግበራ ብዙ ውጤታማ ሥራዎችን ስለመሥራቱ በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን መጠገን፣ ቴሌኮም ማስጀመር፣ ባንክ ማስከፈት፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን መልሶ ሥራ ማስጀመርና የመሳሰሉት በከፍተኛ ርብርብ የተሳኩ ሥራዎች ስለመሆናቸው ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ አጨቃጫቂ ቦታዎችን ወይም የኤርትራና የአማራ ክልል ኃይሎችን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ አልሰጠም በሚል በተደጋጋሚ ሲተች ቆይቷል፡፡

ለአብነት ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለፓርላማ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ አጨቃጫቂ የወሰን ጉዳዮችን በተመለከተ አማራ ክልል ጉዳዮችን ባነሱበት አጋጣሚ ተናግረው ነበር፡፡ የአጨቃጫቂ ቦታዎች መፈታት ጉዳይ ከትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል በተካሄደ ጥናትም ሕዝቡ ደጋግሞ እንደሚያነሳው ዓብይ (ዶ/ር) አውስተዋል፡፡ ይህን በሚመለከት መንግሥታቸው የያዘውን አቋም ሲገልጹም፣ ‹‹ከግጭት በራቀ ሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መንግሥት ይፈልጋል፤›› ነበር ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥታዊ መንገድና በሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈታ ማብራሪያ የሰጡበት ይህ ጉዳይ፣ ከዚያም ወዲህም በተደጋጋሚ ጥያቄ እየተነሳበት ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ሁለቱንም ክልሎች የሚያስማማ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሆነ የችግር አፈታት ዘዴ ይኖረው ይሆን ወይ የሚለው ጥያቄ እስካሁን መልስ ያገኘ አይመስልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት የሚከተላቸው መንገዶች አንዱን አስከፍቶ ሌላውን የሚያስደስት ከሆነ፣ የፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ ልዩነቶችን እንደሚያስከትል ከወዲሁ እየተሠጋ ነው፡፡

መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአጨቃጫቂ ቦታዎችን ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ያለው አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እንደማያስችል ምክንያት ያቀርባል፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ በማስፈር በእነዚህ ቦታዎች ከሕዝቡ የተወከለ አስተዳደር በመመሥረት ለሕዝበ ውሳኔው አመቺ ጊዜ ሲፈጠር፣ በዚሁ አግባብ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚል መፍትሔ ሲያቀርብም እየተደመጠ ነው፡፡  

በአማራ ክልል በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ በይፋ ሊጠቀስ የሚችል አቋም በቅርብ ጊዜ ባያንፀባረቅም፣ ከ15 ቀናት በፊት በባህር ዳር በተደረገው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የመካከለኛና የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ ይኼው ጉዳይ ከአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች አንዱ ተብሎ ተነስቷል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለዘመናት የታገለላቸውና መስዋዕትነት ሲከፍልባቸው የቆዩ እንደ የማንነትና የወሰን ጥያቄ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የስሁት ትርክቶች እርማት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና የመሳሰሉ ጥያቄዎች እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ቢሆኑም ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚታገል የፓርቲው ስብሰባ በአቋም መግለጫው አንፀባርቆ ነበር፡፡

አማራ ክልል አሁን በሚገኝበት የፖለቲካ ተክለ ቁመናም ሆነ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ፣ በአጨቃጫቂ የወሰን ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ውይይት ለማድረግና ለመደራደር የሚያስችል የፖለቲካዊ ጥንካሬ አለው ወይ የሚለው እያነጋገረ ነው፡፡ 

በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት የሰሜኑን ጦርነት ቢያስቆምም፣ የሁሉንም ተፋላሚ ኃይሎች ፍላጎት ያማከለ ነበር የሚለውን የሚጠራጠሩ በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ስምምነት በስተኋላ ለተፈጠሩና አሁንም ድረስ በአማራ ክልል ተፋፍመው ለቀጠሉ ግጭቶች መንስዔ መሆኑን የሚያወሱም አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ ባለበት ደግሞ የስምምነቱ በተጨባጭ ሙሉ ለሙሉ በተግባር መተርጎም አለመቻሉ ሌላ ዓይነት ቀውስ እንዳይፈጥር የሚሠጉ ብዙ ናቸው፡፡

ሕወሓትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያነሱት የታጠቁ ኃይሎች ከአጨቃጫቂ ቦታዎች ወጥተው የትግራይ ክልል ወሰን ወደ ቀደመ ቦታው ይመለስ የሚለው ግፊት፣ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደረ ይመስላል፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ በተግባር ካልዋለ በሚል ጫና ሥር የሚቀርበው ጥያቄ ደግሞ፣ የአደራዳሪዎችን በተለይም የምዕራባዊያኑን ድጋፍ ያገኘ ነው የሚመስለው፡፡

በሌላ ወገን የአጨቃጫቂ ቦታዎች ወይም የወሰን ማስከበር ጥያቄያችን በሕገ መንግሥታዊ አግባብ መልስ ያግኝ የሚለው የአማራ ክልል መንግሥት ግፊት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ የወልቃይትና የራያ ማንነት ጥያቄን አንግበው የተነሱ ኃይሎች የክልሉን መንግሥት ጥያቄ በአዎንታዊ ጎን ይመለከቱታል ቢባልም፣ ፋኖ ነን በሚሉ ወገኖች ግን ይህ አይንፀባረቅም ነው የሚባለው፡፡ በፋኖ ወገን በኩል አቋም ከሚያንፀባርቁ ኃይሎች እንደሚደመጠው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚመለሰው መንግሥትን በነፍጥ ትግል በማስገደድ ወይም በማሸነፍ ብቻ ነው የሚል ኃይለ ቃል ነው ደጋግሞ ሲነገር የሚሰማው፡፡   

በቅርቡ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው በትግርኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ መንግሥት አጨቃጫቂ ቦታዎችን በተመለከተ የሚነሱ ውዝግቦችን ለመቋጨት የሚከተለውን ስትራቴጂ አብራርተው ነበር፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማስፈር አንዱ ሲሆን በእነዚህ ቦታዎች ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረት ደግሞ ቀጣዩ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ሁኔታው አመቺ በሆነ ወቅት የሕዝበ ውሳኔ እንደሚደረግ ነበር የተናገሩት፡፡

ይህ መንግሥት ያወጣው የመፍትሔ ዕቅድ ግን ሁሉንም የሚያግባባ ውጤት ያመጣል ወይ የሚለው ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት አለመተግበር በተለይም የአጨቃጫቂ ቦታዎች ጉዳይ ዕልባት አለማግኘት ደግሞ ሌላ ተያያዥ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል የሚል ሐሳብን እየፈጠረ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ችግር አለመፈታቱ የኃይል አሠላለፍ ለውጥን፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዳያስከትልና ወደ ሌላ ዙር ግጭት እንዳያመራ እየተፈራ ነው፡፡

ከሰሞኑ የወጣው የአሜሪካ ኢንተለጀንስ ኮሙዩኒቲ የሥጋት ትንተና እ.ኤ.አ. የ2024 ሪፖርት (The 2024 Annual Threat Assessment of the U.S. Intelligence Community) በኢትዮጵያ ለተጨማሪ ቀውስ መነሻ ይሆናሉ የሚላቸውን ጉዳዮች መዘርዘሩ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ቀውስ መኖሩን፣ በብሔርና በፖለቲካ ልዩነት መገፋፋትና ውጥረት መስፈኑን በማያያዝ ትኩስ ግጭቶች በየቦታው መኖራቸውን ይገልጻል፡፡ እነዚህ ግጭቶች በጎረቤት ሱዳን ካለው ቀውስ ጋር ሊያያዙ የሚችሉበት ዕድል መኖሩንም ያመለክታል፡፡ እነዚህን ችግሮች በቅጡ መፍታት ካልተቻለና ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ ደግሞ አገሪቱ ወደ የማያባራ ችግር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ነው የሚገምተው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ በባህር በር ጉዳይ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት ውጥረት ገና አለመብረዱ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ኤርትራ በትግራይ ክልል ውስጥ የተወሰኑ ቦታዎችን ተቆጣጥራለች የሚለው ስሞታ ደግሞ የትግራይ ክልልና የፌዴራል መንግሥትን ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ ኤርትራ የራሴን እንጂ የኢትዮጵያን መሬት አልያዝኩም የሚል አቋም ስታራምድ ቆይታለች፡፡ ሆኖም ከኤርትራ ጋር የተያያዘው ችግር ገና ያልተቋጨ ሲሆን፣ ኤርትራ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ ሊፈጥሩ ከሚችሉ ወገኖች ተርታ ትቀመጣለች፡፡ በሌላ በኩል በፋኖና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል እየተጠናከረ የቀጠለው ውጊያ ለተጨማሪ የኃይል አሠላለፍ በር እንደሚከፍት ይገመታል፡፡ ሕወሓትም ሆኑ የኤርትራ ኃይሎች ይህ ውጊያ በቀጠለ ቁጥር ሊኖራቸው የሚችለው አቋም ሊለዋወጥ እንደሚችል ነው በርካታ ተንታኞች መላምት እየሰጡ የሚገኘው፡፡ የሱዳን ውጊያና በውጊያው ተካፋይ የሆኑ ተፋላሚ ኃይሎች ድንበር ተሻግሮ በአማራ ክልል በሚካሄደው ውጊያ ሊኖራቸው የሚችለው ተፅዕኖም ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -