Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እንኳን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የአገሪቱ ህልውናም እንዴት ነው ተጠብቆ የሚቀጥለው የሚለው ጉዳይ ጥያቄ እየሆነ መጥቷል›› መላኩ ተገኝ (ዶ/ር)፣ አንጋፋ ፖለቲከኛና ጸሐፊ

የአለማያ ኮሌጅ ተማሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ያኔ እነ ጥላሁን ግዛው የተገደሉበትና ለውጥ ጠያቂ ወጣቶች የታፈነ እልህና ቁጭት የሚንጣቸው ጊዜ ነበር፡፡ በጊዜው አለማያ ኮሌጅሦስተኛ ክፍለ ጦር የተወሰነ ጦር መጥቶ ግቢውን በመክበብ 15 ቀናት ተማሪዎች ሳይንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ የትግል መንፈሳቸው መነቃቃት የጀመረው እዚሁ አገር ቤት ኔዘርላንድስ ከመሄዳቸው በፊት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹እኔን የመሳሰሉ ሰዎች ወደ ውጭ የሄድነው እኮ ለመማርና ለመሥራት አይደለም፣ ተደራጅቶ አብዮታዊ ትግል ለማድረግ ይጠቅማል በሚል ነበር፤›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡ በኔዘርላንድስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሶሻል ስተዲስ የፖስት ግራጁዌት ዲፕሎማ ተምረዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ጎን ለጎን ደግሞ የኦልተርኔቲቭ ፖለቲክስ ትምህርት ተከታትለው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ሶሺዮሎጂ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) ወስደዋል፡፡ በሥራ ረገድ የፋኖስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የናይል ተፋሰስ ዲስኩር ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የነባር ሕዝቦች ጥናት ቡድን ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊቀመንበር፣ እንዲሁም በወሰን አካባቢ ሕዝቦች መብት ተሟጋች ዓለም አቀፋዊ ካውንስል አባልም በመሆን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ከተማሪዎች የፖለቲካ ንቅናቄ እስከ ኔዘርላንድስ የደረሰ የፖለቲካ ትግል አድርገዋል፡፡ መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) ‹‹ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም›› የተባለ ግለ ታሪካቸውን ያሰፈሩበት መጽሐፍ አበርክተዋል፡፡ የአብዮቱን 50 ዓመት በተመለከተ ሰፊ ጉዳዮችን ያነሱበት ዮናስ አማረ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- አብዮቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን፣ የመሬት ጥያቄን ደርግ መመለሱን፣ እንዲሁም የብሔሮችን ጥያቄ ኢሕአዴግ ፈቶታል ቢባልም አብዮቱ ያነሳቸው ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም የሚሉ አሉ፡፡ የመሬት ጥያቄ፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጥያቄ የመሳሰሉት በአብዮቱ ወቅት የተነሱ በርካታ ጉዳዮች አልተመለሱም ስለመባሉ ምን ይላሉ?

መላኩ (/)፡- በእኔ ግምት የየካቲት አብዮት እኮ ተሸንፏል፡፡ ተሸነፈ ማለት ደግሞ የተነሳበትን ዓላማ አላሳካም ማለት ነው፡፡ ከሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ጀምሮ እስከ ሴቶች መከበር ድረስ በርካታ በርካታ ጥያቄዎች ነበር ይዞ የተነሳው፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ወደ 95 በመቶ አልተመለሱም፡፡ ተድበስብሶ የመሬት አዋጅ ቢታወጅም ይህ ነው የሚባል ውጤት አላመጣም፡፡ በአጠቃላይ ስታየው ከየካቲት አብዮት በፊት ጀምሮ ሲነሱ የቆዩና በተማሪዎች ንቅናቄ፣ ቀጥሎም በአብዮቱ ጊዜ የተነሱ የዴሞክራሲና የመብት ጥያቄዎች እስከ ዛሬም ጨርሶ አልተነኩም፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የማንኛውም አብዮት ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው፣ የሥልጣን ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ካልተፈታ ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች አይፈቱም ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ የሚታየው ችግርም ይኼው ነው፡፡ ደርግ የአብዮቱን ጥያቄ አልመለሰም እንዳይባል አንዱን የመሬት ጥያቄ ብቻ ነጥሎ የመሬት አዋጅ አወጀ፡፡ የመሬት አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ጥያቄውን የመለሰ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ወታደራዊ መንግሥት ይህን ሊመልስ አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ የመሬት ጉዳይ ብዙ ምሁራን እንደሚስማሙበት በአርሶ አደሮች አብዮት እንጂ በመሬት ሪፎርም አይመለስም፡፡ ከመሬት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ብዙ ጥያቄዎች ስለሚከተሉ ነው፡፡ የመሬት ጥያቄ የመሬት ይዞታ ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የመሬት ይዞታው ምን ዓይነት ሥርዓት ውስጥ ነበር የነበረው የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ፊውዳላዊ ሥርዓት ውስጥ ነበር፡፡ ፊውዳል ሥርዓት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ብቻ ያለው አይደለም፡፡ ፖለቲካንም፣ ማኅበራዊንም፣ ባህልንም የያዘ ነው፡፡ አንዱን የመሬት የኢኮኖሚ ገጽታ ብቻ እመልሳለሁ ብትል ሌላው ነገር ሊመለስ አይችልም፡፡

አብዮቱ ያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች አልተመለሱም የሚባለው በብዙ ምክንያት ነው፡፡ አብዮቱ በመሸነፉና በኢትዮጵያ የትኛውም ጥያቄ ባለመመለሱ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር አየተባባሰ በፍጹም ወደ አልታሰቡ አቅጣጫዎች ሲሄድ ዛሬም እናያለን፡፡ ደርግ ሥልጣኑን በፍጹም የበላይነት ለብቻው ባይዝ ኖሮ፣ እንደተጠየቀው ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም ተኪዶ ቢሆን ኖሮ፣ ዴሞክራሲ ቢኖር ኖሮ፣ ሕዝብ እንደፈለገው እየተደራጀ ቢሠራና ቢካፈል ኖሮ የሕዝቦች አንድነት እየተጠናከረ ይሄድ ነበር፡፡ የብሔሮች መከፋፈልና ቁርሾ እየቀነሰ ይሄድ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ በስተኋላ ለሚመጡ መልካም ነገሮች መሠረት ይሆን ነበር፡፡ አብዮቱ በሚካሄድበት ጊዜ እኛ ከየካቲት ጀምሮ ደርግ እስከ ተቋቋመበት ሰኔ 20 ድረስ በነበሩት ወራት፣ ይካሄዱ በነበሩ ተቃውሞዎችና ሠልፎች ላይ ሕዝቡ ይጠይቃቸው የነበሩ ጉዳዮችን እያንዳንዱን ቀን በደንብ መዝግበናል፡፡ በእነዚህ ትግሎች ላይ የብሔር መብት ጥያቄ ወይም ልገንጠል የሚል አንድም ነገር አልነበረም፡፡ የየካቲት አብዮትን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታላቅ የሚያደርገው ነገር ሕዝቡ በአንድነት መነሳቱ ነው፡፡ በብሔር፣ በዘር፣ በሃይማኖት ሳይከፋፈል ጭቁኑ አንድ ላይ ተነስቶ በጨቋኝ ላይ ተቃውሞን ያነሳበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ነው የአብዮቱ መነሻ መሠረት፡፡ ደርግ ይህን በመከልከል የፖለቲካ ሒደቱን አፈነው፡፡ የዴሞክራሲ ሽግግሩ ተገደበ፡፡ በዚህ ምክንያት የተለያዩ ቡድኖች ወደ ተለያየ አቅጣጫ መሄድ ጀመሩ፡፡ ሕወሓት፣ ኦነግ፣ ኦብነግ የመሳሰሉ ተገንጣይ ቡድኖች የተቋቋሙት ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣ በወራት ውስጥ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ደርግ አላፈናፍን የሚል ዕርምጃ በመውሰዱ ነው፡፡ ደርግ መግደል ጀመረ፡፡ ሠራተኞችን፣ ተቃዋሚዎችን፣ 60 የቀድሞ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በርካቶችን ርሸና ተጀመረ፡፡ ይህ አስፈሪ የአፈና ሥርዓት በመፍጠሩ በዚህ ተገፋፍተው ወደ ጎጣችን ገብተን ብንታገል ይሻላል የሚል ምርጫ ውስጥ ብዙዎች ገብተዋል፡፡ የደርግ አካሄድ ትልቅ ጉዳት ያመጣና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕድገትን ያቀጨጨ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ደርግ ዛሬም ድረስ በአንዳንድ ወገኖች ይናፈቃል፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምም ልደታቸውን እስከ ማክበር የደረሰ አድናቆት ሲጎርፍላቸው ይታያል፡፡ ይህ ደርግ የተሻለ ነገር በማድረጉ የመጣ ነው? ወይስ ደርግ በዘመኑ የፈጸማቸውን ስህተቶች ካለመረዳት የተፈጠረ?

መላኩ (/)፡- ይህ የነበረውን ሒደት በደንብ ካለመተንተን የመጣ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ሁሉ ቀውስ ዋና ምንጭ ደርግ ነው፡፡ ብዙዎች የሚያዩት ደርግ መደንፋቱን ነው፡፡ በሶማሊያ ወረራ ወቅት በኩባና በሶቪየት ኅብረት ዕርዳታ ማሸነፉን ነው የሚያዩት፡፡ ከዚያ በመለስም በአንዳንድ ቦታዎች የወሰዳቸውን ጠንካራ ዕርምጃዎችና አንዳንድ ውሳኔዎቹን ነው የሚያዩት፡፡ ብዙ ጊዜ ከደርግ በኋላ የመጡ እንደ መለስ ዜናዊ ያሉ መሪዎች ባራመዱት ጠባብ አመለካከት በመበሳጨት፣ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለው መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ነበር የሚሻለን የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ቁንፅል የሆነ አመለካከት ብቻ ሳይሆን የነበረውን የፖለቲካ ሒደት ካለመረዳት የተፈጠረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቱ ለአብዮቱ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ መሬት ለአራሹ፣ ሕዝባዊ መንግሥት፣ ዴሞክራሲያዊ መብት፣ የሃይማኖት መብት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ የሴቶች መብትወዘተ ብለው የታገሉ የአብዮቱ ተሳታፊዎች ውድ መስዋዕትነት ከፍለዋል ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ የመጣው ውጤትና አሁንም ኢትዮጵያ የምትገኝበት ፖለቲካዊ ተክለ ቁመና ያንን ለአብዮቱ የተከፈለ መስዋዕትነት የሚመጥን ነው? ከአብዮት በኋላ በርካታ አገሮች ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር አድርገዋልና ይህን እንዴት መግለጽ ይቻላል?

መላኩ (/)፡- በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ብዙ ዓይነት አብዮቶች ተከስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ አብዮቶች ውስጥ እንደ ኢትዮጵያው አብዮት ሁሉ የተሸነፉ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ያሸነፉት በጣም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ቬትናም እያልን በቀላሉ መቁጠር እንችላለን፡፡ አብዮቶች የሚሸነፉበት ብዙ ዓይነት ምክንያት አለ፡፡ ልክ እንደ ሕግ በዚህ ነው የሚባል አንድ ዓይነት ምክንያት ሊሰጥ አይቻልም፡፡ አብዮቶቹን እያንዳንዳቸውን በምን እንደተሸነፉ በጥልቀት ገብቶ መተንተን ይጠይቃል፡፡ በሌሎች አገሮች ልክ እንደተከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት ሁሉ በኢትዮጵያ አብዮትም ጊዜ ውድ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ለምሳሌ በርማ (ሚያንማር) በሚባለው አገር የነበረው ኮሙዩኒስት ፓርቲ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ሲታገል የነበረ ድርጅት ነው፡፡ አሁን ያ ፓርቲ የለም፡፡ እንቅስቃሴውም ከስሟል፡፡ በዚህ መንገድ ከታየ በጣም ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው አብዮት የተሸነፈባቸው ብዙ አገሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የዘመናዊ ኢትዮጵያን ፖለቲካ በተለይም ከአብዮቱ ወዲህ ያለውን 50 ዓመታት ፖለቲካ እንዴት ይገልጹታል?

መላኩ (/)፡- በአንድ ቃል ወይም ሐረግ የሚገለጽ አይደለም፡፡ አብዮቱ በመጠለፉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ነው የሄደው፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ተገንጣይ የብሔር ፖለቲካ ቡድኖች የተነሱት፡፡ ከዚያም ወዲህ የመጣው ቀውስ የዚህ ተያያዥ ውጤት ነው፡፡

ሪፖርተርከአብዮቱ በኋላመጡ ኃይሎች የሕዝቡን ጥያቄ በሙሉ የብሔር ጥያቄ ብቻ ነው ወደሚል ወሰዱት ማለት ይቻላል?

መላኩ (/)፡- ሁሉም የእኔ ብቻ የሚሉትን ጥያቄ ነው ያቀረቡት፡፡ የሕወሓት ሥልጣን መያዝ ደግሞ የራስን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የብሔር ቡድኖችንም ጠቅልሎ መያዝ ይቻላል የሚል ሐሳብን አሰረፀ፡፡ ሐሳብ ሐሳብን እየወለደ በጊዜው እያደገ ነው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የተገባው፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔር ጥያቄ አብዮተኛ በሚባለውና በተማሪ እንቅስቃሴ ውስጥ አልነበረም ወይ የተነሳው?

መላኩ (/)፡- የተማሪ እንቅስቃሴ በእርግጥ የብሔር ጥያቄን አንስቷል፡፡ አንዳንዶች ታሪክን ለማጣመም በመፈለግ ዋለልኝ ብቻ የቆሰቆሰው ያደርጉታል፡፡ ሆኖም ዋለልኝ መኮንን አልነበረም የጻፈው፡፡ በቡድን የተሰባሰቡ ወጣቶች የጻፉት ሲሆን በእሱ ስም ይውጣ ስለተባለ ነው እሱ ያቀረበው፡፡ በዚያን ጊዜ ገዥው መንግሥት ዘመቻ ጀምሮ ነበር፡፡ ተማሪውንም በዘር ለመከፋፈል ዘመቻ ጀምሮ ነበር፡፡ የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች ደግሞ በዚህ ጉዳይ ጥብቆች ነበሩ፡፡ ተማሪው እንዳይከፋፈል፣ በተገንጣይነት ወይም በብሔር ፖለቲካ አክራሪነት የማይጠረጠር ሰው በስሙ ይውጣ ብለው ዋለልኝ ፈቃደኛ ስለነበር በእሱ ስም የወጣው፡፡ በዋለልኝ ስም ይውጣ እንጂ ነገርየው የእሱ ብቻ ሐሳብ አልነበረም፣ የሁሉም ተማሪ ድጋፍ ነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔር ጥያቄው በዚያ መንገድ መቅረቡ እስከ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለ ነው ይባላል፡፡ አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ አድርጎ የሚፈርጀው የዋለልኝ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ከዚያ በኋላ እስከ ዛሬም ለተፈጠሩ ቀውሶች እርሾ ሆኗል ይባላል እኮ?

መላኩ (/)፡- ይህ ስሞታ የብሔር ጥያቄን በጠቅላላው ያመጡት ተማሪዎች ናቸው ከሚል ድምዳሜ የሚነሳ ነው፡፡ ይህ በፍጹም ስህተት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ ሲነሳ እንኳን የተማሪ ጥያቄ ቀርቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አልተመሠረተም ነበር፡፡ የብሔር ጥያቄ ቀድሞ የተጀመረ ትግል ነው፡፡ ኤርትራ ውስጥ የትጥቅ ትግል የተጀመረው ለምሳሌ ከአብዮቱ ብዙ ዓመታት በፊት ፌዴሬሽኑ እንደፈረሰ ነበር፡፡ ከትጥቅ ትግሉ በፊት ደግሞ የፖለቲካ ትግሉ እንግሊዞቹ ሳሉ ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ተካሂዷል፡፡ ትግራይ የመጀመሪያው የወያኔ አመፅ የተነሳው ዩኒቨርሲቲው ከመመሥረቱ በፊት ነው፡፡ በኦጋዴን የነበረው ችግርም ቀድሞ ነው የተፈጠረው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሳይኖርና ተማሪው ትግል ሳይጀምር በፊት የብሔር ጥያቄ ይነሳ ነበር፡፡ በምን ተዓምር ነው በኢትዮጵያ ተማሪው የብሔር ጥያቄን ፈጥሯል የሚባለው? ጠቅላላ የፖለቲካ ሁኔታውን ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ሶሻል፣ ኢኮኖሚ ሥርዓት በምን ዓይነት መንገድ እንደተዋቀረ የማያውቁ ወይም ለማወቅ የማይፈልጉ ሰዎች የሚፈጥሩት ትችት ነው፡፡ ይህን የሚረዳ ሰው ብዙ ጊዜ የነበረውን ሥርዓትን ብልሹነት ነው ተጠያቂ የሚያደርገው፡፡ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ሕይወት ነበር የሚሉ ወገኖች ይህን ያነሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የብሔር ጥያቄን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጥ ነበር የሚለውን ሒደት መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎቹን ችግሮች አባባሳቸው፡፡ አሁን የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፌዴሬሽኑን ባያፈርስ ኖሮ ኤርትራ ውስጥ ትግል የሚባል ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ያ ትግል ኤርትራ ውስጥ ባይኖር ኖሮ ትግራይ ውስጥም ሌላ የነፍጥ ትግል አይኖርም ነበር፡፡ ይህ አንዱ ወደ ሌላው የሚዛመት ችግር ነበረው፡፡ ስለዚህ ኃይለ ሥላሴን ነፃ አድርጎ ተማሪውን መኮነን በዚያ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ አለመረዳት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ያሉ ቀድመው በመቃወም ከመንግሥት የወጡ ሰዎችንጉሡን መንግሥት የብሔር ጥያቄዎችን የሚያስተናግድበትን መንገድ እንዲለውጥ በደብዳቤ ሲጠይቁ ነበር ይባላል፡፡

መላኩ (/)፡- ይህን ካነሳህ አይቀር ንጉሡ አፄ ኃይለ ሥላሴ በፍጹም ማንንም ሰው የሚሰሙ እንዳልነበሩ ማንሳት ይኖርብኛል፡፡ አምባሳደር ብርሃኑ ብቻ ሳይሆኑ የአየር ኃይሉ ጄኔራል ዓብይ አበበ፣ ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ታሪክ ጸሐፊው ተክለ ፃዲቅ መኩሪያን ጨምሮ አራት ታላላቅ ሰዎች ተሰባስበው ለንጉሡ ለውጥ እንዲደረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ይህ ብርሃኑ በሚባል ሰው የተጻፈና በታሪክ የሚታወስ ደብዳቤ ሲሆን፣ በጣም የተከበሩ አራት ታላላቅ መሪ የነበሩ ሰዎች ከእነ መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማግሥት ለንጉሡ የፖለቲካ ማሻሻያ ጥያቄ ያቀረቡበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ንጉሡ ልክ እንደ እንግሊዞቹ ሕገ መንግሥታዊ የዘውድ ርዕሰ ብሔርነቱን ይዘው ዋና የመንግሥት ሥራውን ግን ለፓርላማ ተጠሪ የሚሆን በሕዝብ የሚመረጥ የጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት እንዲመራው ጠይቀው ነበር፡፡ ንጉሡ ግን ወጊዱ ነው ያሏቸው፡፡ እነዚህ ጥረቶች ሳይሳኩ በመቅረታቸው ነበር ከኤርትራ ጀምሮ ተያይዘው የመጡ የብሔር ትግሎች ተጠናክረው የቀጠሉት፡፡ እነዚህ ሰዎች አብደው፣ ሰክረው ወይስ ጠግበው ነው ያን ሁሉ ውትወታና ጥያቄ ያልመለሱት የሚለው በደንብ መታየት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡በአብዮት ተሞከረ፣ በነፍጥ ትግል ተሞከረ፣ 1983 ዓ.ም. መጣ፣ በምርጫ ካርድም ተሞከረ፣ ለውጥና ሪፎርም ተብሎም ተሞከረ፡፡ ግን ደግሞ ሕዝብ የሚመኘው ዓይነት ዴሞክራሲ ገና አለመፈጠሩ ይነገራል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ መቼ ነው ዕውን የሚሆነው ብለው ይገምታሉ? ምን ቢደረግ ነው የሚበጀው?

መላኩ (/)፡- እንኳን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የአገሪቱ ህልውናም እንዴት ነው ተጠብቆ የሚቀጥለው የሚለው ጉዳይ ጥያቄ እየሆነ መጥቷል፡፡ ስለዚህ የዴሞክራሲ ጥያቄ ቅንጦት ሆኗል፡፡ አሁን ከዚያ ይልቅ የአገሪቱ ህልውና ጉዳይ ነው የሚያሳስበው፡፡ በእኔ ግምት ቅድሚያ የሚሰጠው የወሰደውን ጊዜ ቢወስድም በጉዳዩ የሚያገባቸው ኃይሎች፣ ዕውቀት ያላቸው፣ ስለዴሞክራሲ፣ ስለአገረ መንግሥት ግንባታ ብዙ የሚያውቁ ሰዎች ሰፊ ኮንፈረንስ ተደርጎ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መግባባት መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ በአንድ በኩል የአገሪቱ ህልውና እንዴት ይጠበቅ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እንዴት ይቃና የሚለው መልስ የሚያገኘው በዚህ መሰሉ የንግግርና የውይይት ሒደት ብቻ ነው፡፡ በቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲው ሕዝባዊ ጦርነት ከጀመረ በኋላ በ1930ዎቹ የተፈጠረውን አገርን አደጋ ላይ ሊጥል ይችል የነበረ የፓርቲ አለመግባባት ለመፍታት፣ የፈለገውን ጊዜ ይፍጅ ብለው 80 ቀናት ወስደው ስብሰባ በማድረግ ችግራቸውን ፈተዋል፡፡ ውይይት ሁሌም መፍትሔ ያመጣል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለይስሙላ ሳይሆን በሀቀኝነት መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ መደማመጥ በራሱ ብዙ ችግሮችን ያቀላል፡፡         

ሪፖርተር፡- ወጣቱ አብዮተኛ የሆነው በርዕዮተ ዓለም ፋሽን ተነድቶ ነው የሚሉ አሉ፡፡ የከተሜነት እንጂ የገጠሩን ሕይወት የማያውቅና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ የማይረዳ ወጣት ነው በጅምላ ተነድቶ ወደ አብዮቱ የገባው ይባላል?

መላኩ (/)፡- ይህ ትውልዱን የማያውቁ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ነው፡፡ የተማሪው እንቅስቃሴ ዋና ዋና ጥያቄዎችን ወደ ማንሳቱ የገባው ለገጠሩ ሕይወት የቀረበ በመሆኑ ነው፡፡ በጊዜው ኢትዮጵያን ዩኒቨርሲቲ ሰርቪስ የሚባል አሠራር ነበር፡፡ ሦስተኛ ዓመት የደረሱ ተማሪዎች በሙሉ ወደ ገጠር ይመደቡና በማስተማር ወይ በሌላ አገልግሎት የገጠሩን ሕዝብ እያገዙ አንድ ዓመት እንዲቆዩ ይደረግ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ስለገጠሩ ሕይወት፣ ስለገባር አሠራርና ስለኑሮው ሥቃይ የገባቸው በዓይናቸው ካዩ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ ተመልሰው ሲመጡ ስለመሬት ሥሪትና ስለተለያዩ ችግሮች የጻፉ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ተማሪዎች ያለ ዕውቀትና በስሜት ነው የተነሳሱት የሚባለው በተሳሳተ መንገድ ስም ለመለጠፍ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ሌላው በዩኒቨርሲቲ ከሚማሩት መካከል ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት ከገጠር የሚመጡ ናቸው፡፡ ከባላገር የሚመጡ የአርሶ አደር ልጆች የነበሩ በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የተማሪዎች ጥያቄ ሲነሳ የሚጠቀሰው ዋለልኝ የከተማ ሰው አልነበረም፡፡ ከወሎ የመጣ ከገጠር ሕይወት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ብርሃነ መስቀል ራሱ ከገጠር የመጣ ነው፡፡ የገጠሩን ሕይወት ሳያውቁት ነው የተነሱት የሚባለው ያን ትውልድ ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኢሕአፓ ሠራዊት መሥርቶ ጫካ ገብቶ መታገል ሲጀምር በአብዛኛው ማለትም 95 በመቶ ከከተማ የሄዱ ወጣቶች ነበሩ የተቀላቀሉት፡፡ ይሁን እንጂ ወዲያውኑ ከገጠሩ ሕይወት ጋር ተቀላቅለው ትግላቸውን ለመቀጠል አልተቸገሩም፡፡ የዚያን ጊዜው ወጣት ከተሜና ገጠር እየተባለ ሊመደብ የማይችል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የርዕዮተ ዓለም ፋሽኑስ ለምሳሌ በወቅቱ ማርክሲዝም ገናና መሆኑ አላነሳሳም?

መላኩ (/)፡- እሱም ቢሆን እኮ ራሱን የቻለ ዑደት ያለው ነበር፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ተነስተው የሆኑ ሰዎች የወሰኑት ሳይሆን፣ የተማሪው ጥያቄ ወደ ማርክሲዝም ያዘነበለበት የራሱ ሒደት ነበረው፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄ በአቤቱታና በትችት ነው የጀመረው፡፡ ይህ ነገር ይሻሻል፣ ለአገሪቱ ይበጃል እያለ በመጠየቅ ነው የተጀመረው፡፡ ከዚያ ወደ ትችት ተገባ፡፡ ከእነ መንግሥቱ ተቃውሞ በኋላ ደግሞ ወደ ተቃውሞ ተገባ፡፡ መጀመሪያ ላይ ማርክሲዝም አልነበረም፡፡ መሬት ለአራሹ ብለው ሲወጡ ማርክሲዝም ይህን ያህል አልነበረም፡፡ ማርክሲዝም በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ጠልቆ ገባ የሚባለው በእኛ 1962 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.1969) ነበር፡፡ ያኔ ነበር የብሔር ጥያቄም የተነሳው፡፡ ሌላው ዓለም አቀፉን ተጨባጭ ሁኔታም መርሳት የለብንም፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተጀምሮ እስከሚያልቅ እዚሁ የሚያልቅ ነገር አይደለም፡፡ ቢያንስ በንግድ ተያይዘናል፡፡ ያኔ ደግሞ በ60ዎቹ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ተማሪዎች እንቅስቃሴም በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ በተለይ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የደቡብ ኮሪያና የጃፓን ተማሪዎች እንቅስቃሴ በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1968 የአውሮፓ ተማሪዎች ንቅናቄ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በፈረንሣይ እስከ አብዮት የደረሰ ንቅናቄ አድርጎ ነበር፡፡ ሠራተኛው መደብ ከተማሪው ጋር አብሮ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ አገሪቱን ሲመራ በነበረው ሻርል ደጎል ላይ ከባድ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ነው ደጎል ከሥልጣን እስከ መልቀቅ የደረሰው፡፡

በእነዚህ መሰል እንቅስቃሴዎች ውስጥ ደግሞ መሪ የነበረው ርዕዮተ ዓለም ማርክሲዝም ነበር፡፡ በእነዚያ ዘመናት በተካሄዱ አብዮቶችና ለውጦች የተሳካ እንቅስቃሴ ያሳዩት የማርክሲዝም ንቅናቄ በተካሄደባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የኩባ አብዮት ይጠቀሳል፡፡ ቬትናሞችም አብዮታቸውን በማካሄድ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ እነ አሜሪካን ወጥረው የሚታገሉበት ጊዜ ነበር፡፡ በእነዚህ ሁሉ ማርክሳዊ ፓርቲዎች ነበሩ መሪዎቹ፡፡ በቬትናም በሚካሄድ ጦርነት፣ በደቡብ አፍሪካና በሮዴዥያ ለሚነሱ ፀረ አፓርታይዳዊ ንቅናቄዎች፣ እንዲሁም በላቲን አሜሪካ በሚካሄዱ አብዮቶች የአጋርነትና የድጋፍ ንቅናቄዎች በየአገሩ የሚደረገው የማርክሳዊ ርዕዮትን ማዕከል ባደረጉ ተማሪዎች ነበር፡፡ አፓርታይድ ይውደም፣ አሜሪካ ከቬትናም ትውጣ፣ አንዲሁም በላቲን አሜሪካ ጣልቃ ገብነት ይቁም እየተባለ የዓለም አቀፍ አጋርነት መፈክር በየአገሩ የተንፀባረቀው በማርክሳዊ ርዕዮት አሰባሳቢነት ነው፡፡ ያኔ ደግሞ በዓለም አቀፍ ተማሪዎች ኮንግረስ በየሁለትና አራት ዓመቱ እየሄደ የሚካፈል የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠንካራ ማኅበር ነበር፡፡ ይህን ጉባዔ በሚካፈሉ ጊዜ ደግሞ የዓለም ተማሪዎች ሶሊዳሪቲን ይዘው ነበር የሚመጡት፡፡ ያኔ ከሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በኮሜርስ ወይም በፒፕልስ ሪቮሉሽን ፓርቲዎች የሚመሩ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አብዮታዊ እንቅስቃሴም የዚሁ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ አካል ነበር፡፡ እኛ አውሮፓ በነበርን ጊዜ ኢንተርናሽናል ሶሊዳሪቲ ነበር ጠዋት ማታ ሥራችን፡፡ ለደቡብ አፍሪካ፣ ለአንጎላ፣ ለቦሊቪያ፣ ለቬትናም መሠለፍ ነበር ሥራችን፡፡ አውሮፓና አሜሪካ የነበሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አነሳሱና መሠረቱ ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትውልድ ችኩልነት ነበረበት፡፡ ነገሮችን ከሥሩ መንግሎ ስለመጣል እንጂ በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አይቶ፣ ለአገር ይስማማል ወይም አይስማማም የሚለውን መዝኖ አይደለም የተራመደው ይባላል፡፡ በነበሩ ሥራዎች ላይ የጎደለውን ሞልቶና የተጣመመውን አቃንቶ ለማስቀጠል የሚጥር አልነበረም ተብሎ ይወቀሳል፡፡

መላኩ (/)፡- ይህም ቢሆን ተጨባጭነት የሌለው ስሞታ ነው፡፡ በአንድ በኩል የተማሪውን እንቅስቃሴ ያጣጥሉታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ልክ እንደ መንግሥት የተማሪው እንቅስቃሴ ይህን ነገር መሥራት ነበረበት ይሉታል፡፡ የተማሪው እንቅስቃሴ ከተጠበቀው በታች ነበር ይላሉ፡፡ ይህ ሁሉ የተማሪው እንቅስቃሴ ጠባይን ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እኮ የፕሮፌሽናል ፖለቲከኞች እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ተማሪዎቹ በሙሉ ማርክሲስቶች አልነበሩም፣ ተማሪዎች በሙሉ አብዮተኞች አልነበሩም፡፡ ተማሪዎች በሙሉ ለፖለቲካ ትግል አንገታችንን እንሰጣለን ያሉ አልነበሩም፡፡ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻቸው ትምህርት እስካለ ጊዜ ድረስ ነው የነበረው፡፡ ትምህርት ነው ያገናኛቸው፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የአብዮተኛ ድርጅቶች እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ስለአገሪቱ ሁኔታ ለምን አላጠናም ይሉሃል፡፡ ስለመሬትና ስለባለ አገር አጠናለሁ ብትል አገዛዙ አንቆ እስር ቤት ነው የሚከትህ፡፡ ስለመሬት ስለብሔር አጠናለሁ ብትል አሥር ዓመት ይፈርድብሃል፡፡ ተማሪዎች እኮ ፕሮፌሽናል ፖለቲከኞች አይደሉም አማተር ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ በእነሱ አቅም ማድረግ የሚችሉትን ብቻ ነው ሊያደርጉ የሚችሉት፡፡ ከዚያ በላይ ሄደው አገር እንደ መምራት ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ይህ ስለሆነ ይህን ነው የምንሞላው ብለው ሊነሱም አይችሉም፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩ የተማሪ ንቅናቄዎችን ካየህ ለምሳሌ ጠንካራ እንቅስቃሴ በነበራት ቱኒዚያ፣ ኢራን፣ ሱዳን፣ ግብፀና ደቡብ አፍሪካ ብታይ ከኢትዮጵያ እንቅስቃሴዎች ጋር ስታነፃፅራቸው ከኢራኑ በስተቀር በሙሉ ደካማ የሚባሉ ነበሩ፡፡ የኢራኑ የተለየና በአገሪቱ በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ የተነሳ ነው፡፡ ኢራን ውስጥ የሚደረገውን ለማድረግ ግን አትነሳም፡፡ እንደ አገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ነው እንቅስቃሴህ የሚወሰነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግርም ከሀ እስከ ፐ እፈታለሁ ልትልም አትችልም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሲዘጋ እኮ ያንተም እንቅስቃሴ አብሮ ይቆማል፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄ የአገሪቱን ሁኔታ ያላማከለ ነበር የሚሉ ወገኖች ለእንቅስቃሴው ጥልቅ ጥላቻ ያላቸው ናቸው፡፡ አንዱ ለምሳሌ ተማሪዎቹ አገራቸው ውስጥ እንደ ምኒልክ፣ እንደ ራስ ምናምን ያሉ ጀግኖች እያሉ የእነሱ ጀግኖች ግን ሆቺ ሚንና ቼ ጉቬራ ነበሩ ብሎ ሲተች ሰማሁት፡፡ ይህ በፍጹም የንቅናቄውን መሠረታዊ ዓውድ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ በንቅናቄው ወቅት ፋኖ ተሰማራ እንደ ሆቺ ሚን እንደ ቼ ጉቫራ የሚል መዝሙር ነበር፡፡ ይህ መዝሙር ይዘመር የነበረው ግን ያኔ የትጥቅ ትግል ወይም አርነት ያስፈልጋል በሚል እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግኖች የሉም ብለው ለመካድ አልነበረም፡፡ የፖለቲካ ትንተና ሲደረግና ታሪክ ሲጻፍ ሁል ጊዜ ዓውዱን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ካልተረዳህ የምትጽፈው ፉርሽ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአፓና መኢሶን ሲመጡ የነበረው የፖለቲካ ትግል አልተለወጠም ወይ?

መላኩ (/)፡- በደንብ እንጂ፡፡ ፕሮፌሽናል የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ መሆናቸው መጠን፣ ዓላማቸው የፖለቲካ ሥልጣን ይዘው ሕዝባዊ መንግሥት ለማምጣት ያስችላል ያሉትን የፖለቲካ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር፡፡ ኢሕአፓ ፕሮግራም ለምሳሌ ዘጠኝ መሠረታዊ ነጥቦች የነበሩት ነበር፡፡ ከእነዚህ ዋናው ደግሞ ሕዝባዊ መንግሥት መመሥረት የሚለው ነበር፡፡ መኢሶንም እንዲሁ የራሱ ፕሮግራም ነበረው፡፡ የሁለቱ እንቅስቃሴ ከተማሪው ንቅናቄ በጣም የተለየና መንግሥት የመመሥረት ትግልን ግብ ያደረገ ነበር፡፡ ትንንሾቹ እነ ማሌሪድና ሌሎችም የፖለቲካ ፕሮግራም ነበራቸው፡፡ እነሱን ስለኢትዮጵያ ሁኔታ አጥንተዋል ወይም አላጠኑም ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ ደርግን ጨምሮ በዚያን ዘመን የተፈጠሩ የፖለቲካ ቡድኖችን ያጣላቸው ጥቃቅን የመስመር ልዩነት እንጂ፣ አንድ ዓይነት ግራ ዘመም ፖለቲካ ሁሉም ይከተሉ ነበር ይባላል፡፡ ይህ ቁርሾ ዛሬም ድረስ መቀጠሉና በታሪክ መጻፍ ሒደት መወቃቀሱ መኖሩም ይነገራል?

መላኩ (/)፡- ለዚህ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ በቅርብ ያየህይራድ (ዶ/ር) የተባለ የመኢሶን መሪ የነበረ ሰው ኤንቢሲ በተባለው ቴሌቪዥን አንድ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ የሰማሁት አንድ አዲስ ነገር አለ፡፡ እሱ ካነሳው ትኩረት የሚስብ ነገር መካከል የየካቲት አብዮት በሚነሳ ጊዜ፣ እኛም ሆነ ኢሕአፓ በተነሱ ትግል ጥያቄዎች ዙሪያ ልዩነት አልነበረንም የሚል አለ፡፡ እኛም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ብለን ጽፈን ነበር አለ፡፡ የእኛ አቋም የተቀየረው እነ ኃይሌ ፊዳ ከአውሮፓ ከመጡ በኋላ ነው አለ፡፡ ደርግ ኃይለ ሥላሴን ካወረደ በኋላ ከአውሮፓ ሲመጡ እናንተ ትክክል አይደላችሁም አሉን አለ፡፡ እነዚህ የማይረቡ ኃይሎች የሚያነሱትን ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም የሚል ሐሳብ ተቀብላችሁ መጻፋችሁ ትክክል አይደለም ብለው ያሰረዙን እነ ኃይሌ ፊዳ ናቸው አለ፡፡ በእነ ኃይሌ ፊዳ ግምት የኢሕአፓ ሰዎች የማይረቡ ወይም ቦዘኔዎች ተደርገው ነው የተቆጠሩት፡፡ አንደኛው የልዩነት ምንጭ የሚመስለኝ በእኔ ግምት ይህ ነበር፡፡ ሁለተኛውና በጣም ወሳኙ የሚመስለኝ ደግሞ እነሱ ጠቅልለው ገብተው ከደርግ ጋር ተባብረው ሥልጣን ላይ ሆነው ነበር ከእኛ ጋር ሊታገሉ የፈለጉት፡፡ ኢሕአፓ የሚባል ቡድን መጥፋት አለበት ብለው የ150 ኢሕአፓ አባላት ስም ዝርዝርን ለደርግ ጽፈው ሰጥተዋል፡፡ ደርግ ለራሱ መግደል የጀመረው ገና ሥልጣን እንደያዘ ነበር፡፡ የኃይለ ሥላሴ 60 ባለሥልጣናትን ከገደለ ጀምሮ መግደሉን አቋርጦ አያውቅም፡፡ በ1968 ዓ.ም. ግን መኢሶኖች ኢሕአፓን ለደርግ አሳልፈው ለመስጠት ተነሱ፡፡ ያን ጊዜ ነው ኢሕአፓና መኢሶን የተቆራረጡት፡፡ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ከእነሱ የፖለቲካ ሥልጣን አንፃር ለመንቀሳቀስ መፈለጋቸው ነው፡፡ ደርግም ልምታ ብሎ ተነሳ፡፡ ደርግን ደግሞ ማስቆም አልቻሉም፡፡ ደርግ በዘረጋው ሥርዓት ወደ ሥልጣን ለመውጣት ስለፈለጉ ደርግን ተው ቢሉ ወደ ራሳቸው ስለሚዞር ኢሕአፓን አሳልፎ ወደ መስጠት ነው የሄዱት፡፡ በስተኋላ ደርግን ሲቃወሙ እንዳየነው በአንዴ ነበር ድምጥማጣቸው የጠፋው፡፡

ሪፖርተር፡- የአንድ ትውልድ አባል ሆኖ እርስ በርስ መፈራረጁና መጠፋፋቱ ከየት ሊመጣ ቻለ? ተቀራራቢ ሐሳብ ይዞ እኩል ለነፃነት ታግሎ በመጨረሻ አንዱ ሌላውን ጠላት አድርጎ ለመብላት የተነሳው ለምንድነው?

መላኩ (/)– የእነ ኃይሌ ፊዳ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሱ በፊት በኢትዮጵያ የእነሱን ቡድን ሥራ የሚሠሩት ያየህይራድ (ዶ/ር)፣ ወርቁ ፈረደ (ዶ/ር) እና ተፈራ ወንዴ (ዶ/ር) ነበሩ፡፡ እነሱ ስለኢሕአፓም ሆነ ስለተማሪው ንቅናቄ የነበራቸው አስተያየት ከውጭ ከመጡት የተለየ ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የተማሪዎች እንቅስቃሴም ሆነ የኢሕአፓ ትግል እንዴት እንደተጀመረ በቅርበት ስለሚያዩ ያውቁታል፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄ ከገበሬው፣ ከሠራተኛውና ከሌሎችም ጭቁን ሕዝቦች ጋር የነበረውን ግንኙነት ያውቁታል፡፡ የየካቲት አብዮት ሲፈነዳ የነበረውን ትግል ስላዩ አወንታዊ አስተያየት ነበር የነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡ እነ ኃይሌ ፊዳ ግን ከአገር ከወጡ ራሱ ብዙ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ የተማሪውን እንቅስቃሴን ዑደቱን አያውቁትም፡፡ ስለዚህ ወደ ንቀትና የማይረባ ነው ወደ የሚል ድምዳሜ ቢያጋድሉ አይፈረድባቸውም፡፡ አለማወቃቸውና የመረጃ ክፍተት ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ አገር ቤት ከነበረው ጋር በጥብቅ አልተሳሰሩም፡፡ እኔ ራሴ ኔዘርላንድስ በሄድኩ ጊዜ ከተረፈ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝቼ ነበር፡፡ ተረፈ (ዶ/ር) ደርግ ከመኢሶን ጋር መሥራት ከጀመረ በኋላ የትምህርት ሚኒስትር የነበረ ሰው ሲሆን፣ እኔ ሳገኘው ከኢትዮጵያ ከወጣ ስድስትና ሰባት ዓመት ሆኖት ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ደግሞ የተማሪዎች ንቅናቄ በጣም የጋመበት ጊዜ ነበር፡፡ ከእሱ ጋር ስናወራ እሱ የሚያውቀው የተማሪ ትግል ደካማ የነበረበትን ጊዜ ስለነበር በጣም ነበር የተገረመው፡፡ ምን ያህል እንደተገረመ ዛሬ ድረስ በደንብ ነው የማስታውሰው፡፡ እሱ ከእነ ኃይሌ በኋላ ውጭ የሄደ ሰው ነው፡፡ እሱ በስድስት ዓመቱ የተፈጠረውን ለውጥ ሰምቶ በዚያ ደረጃ ከተገረመ በጊዜው ለብዙ ዓመታት ውጭ የቆዩት እነ ነገደ ጎበዜ፣ እነ አንዳርጋቸውና እነ ኃይሌ ሊኖርባቸው የሚችለውን የመረጃ ክፍተት መገመት ይቻላል፡፡                 

ሪፖርተር፡- አብዮተኛው ትውልድ ዛሬም ድረስ አልተግባባም ይባላል እኮ?

መላኩ (/)– ችግሩ እኮ በዚያ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ጉዳዮች ያለ ነው፡፡ በእኛ አገር መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ኮስተር ያለ ውይይት አድርጎ መግባባትን መፍጠር አልተለመደም፡፡ የመሬት ጥያቄ ለምሳሌ ወደ ሐምሌ አካባቢ ደርግ ካወጀው 50 ዓመታት ሊሆነው ነው፡፡ በዚህ 50 ዓመት ውስጥ የመሬት ጥያቄ ተመለሰ? አልተመለሰም፡፡ ካልተመለሰስ ምን መደረግ አለበት? በሚለው ጉዳይ ላይ ጠንካራ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች በተናጠል በዩቲዩብ፣ በጋዜጣ፣ በቴሌቪዥን ስለለውጥ ስላወሩ ብቻ ሐሳብ ተሰባስቦ ወደ አንድ አቅጣጫ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ወደ አንድ አካባቢ መጥተው መነጋገር አለባቸው፡፡ ሲያወሩ፣ ሲከራከሩና ሲመክሩ ነው ፍሬ ያለው ነገር የሚገኘው፡፡ በቅርቡ የፋሲካ ሲደልልን መጽሐፍ እያነበብኩ ነበርና ስለኢሕአፓ የጻፈው ገረመኝ፡፡ ለረጅም ዓመት ሁላችንም በየፊናችን እንጽፋለን፡፡ አንዱ ስለአንዱ አያውቅም፣ ፖሊሲዎችን በሚመለከት ውይይትና ክርክር አልተደረገም፡፡ አሁንም ቢሆን መፍትሔ ሊሆን የሚችለው እንዲህ ያለ የውይይት መድረክ ሲመቻች ነው፡፡ በዚያን ዘመን አብዮተኛ ያልነበሩ ሰዎች በማያውቁት፣ ዓውዱን ባልተረዱት ነገር ዛሬ አክቲቪስት ወይም ፖለቲከኛ ነን ብለው በራሳቸው መንገድ የፈለጋቸውን ነገር እየፈጠሩ ያወራሉ፡፡ አንዱ አንድ ጊዜ ዋለልኝ እኮ የሲአይኤ ኤጀንት ነው አለኝ፡፡ ሲአይኤ ጽፎ ነው ያን ጽሑፍ የሰጠው ሲል ሊያሳምነኝ ሞከረ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...