Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየ66 አብዮት ፈገግ በይ!

የ66 አብዮት ፈገግ በይ!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

የማወጋሽ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ልጆችሽ አንዱ ነኝ፡፡ ማን የምትባለው ነህ እንዳትይኝ፡፡ በጊዜው ስም ካላቸው ታላላቅ ወጣቶች ውስጥ አይደለሁም፣ ከጮርቃዎቹ አንዱ ነበርኩ፡፡ ይህን ያህል ስለራሴ ከገለጽኩ ወደ ዋናው ወጌ ልመለስ፡፡

ከ1966 አብዮት ወደ እዚህ አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ብዙ ነገር ሆኗል፡፡ በአብዮት ግብግብ ደክማለች ብላ ኢትዮጵያን ወርራ የነበረችው የዚያድ ባሬ ሶማሊያ፣ ከኢትዮጵያ የአፀፋ ምት በኋላ ተፈርክሳ ከመቀነሷ ባሻገር፣ ገብታ ከነበረበት የሥርዓት-አልባነት አዘቅት አሁን ድረስ በቅጡ አላገገመችም፡፡ ሱዳንም ሁለት ሱዳን ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያም ተቀንሳ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሆናለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የ1966 አብዮተኞች ጥንቅር ከሁሉም አካባቢ (ከኤርትራ ጭምር) የበቀሉ አብዮተኞች ነበሩበት፡፡ እነዚህ አብዮተኞች በመስመር ተለያይተው ቢገዳደሉም ኅብረ ብሔራዊ ነበሩ፡፡ ተባልተው ራሳቸውንና ብዙ ትንንሽ ተከታዮቻቸውን በማስበላት ኢትዮጵያን ቢያጎዱም፣ ኢትዮጵያን የመጉዳት/የመቀነስ ዓላማ አልነበራቸውም፡፡ ዓላማቸው መላ ኢትዮጵያን የሸፈነ ለውጥ ማምጣት ነበርና በዚህ ረገድ ከኤርትራ የነፃነት ታጋዮች ጋር ልዩነት ነበራቸው፡፡

አብዮተኞቹ ተንኮታኩተው በኢትዮጵያ የትግል መድረክ ውስጥ አሉ የሚባሉት ‹‹ታጋዮች›› ብሔርተኞች (በተለይም ኦነግና ሕወሓት) በሆኑ ጊዜ፣ የኤርትራ ታጋዮች ‹‹ቅኝነታችን በኢትዮጵያዊነትም ቀጥሏል›› የሚል አቋማቸውን የተቀበሉ ቡድኖች አገኙ፡፡ የደርግ ገዥነት የ17 ዓመታት ዕድሜውን ጨርሶ ራሱን ሲጥልም ነፃ አውጪዎቹ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጎ ያጠረውን የቅኝ ካርታ የኤርትራ ሉዓላዊ ይዞታ በማለት መርቀውና ከአንገራጋሪ ተከላክለው ነበር ያስረከቡት፡፡ እነዚህ ሰዎች ከ1966 ዓ.ም. የአብዮት ትውልድ የጮርቃዎቹ ክፍል የተገኙ ‹‹ታጋዮች›› ነበሩ፡፡ ለቀልደኛ ሪፈረንደም ተባባሪ ከሆኑ በኋላም ማንም ሳይቀድማቸው የኤርትራን ሉዓላዊነት በኢትዮጵያ ስም ያወቁት እነሱ ነበሩ፡፡ በ1966 አብዮት የነበራችሁ አብዮተኞች አሮጌ ጨቋኝ መደብ የተባሉትን ከኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አውታር ቀንሳችሁ ሌላውን ‹‹አብዮታዊ ንቃት››/ተሃድሶ ሰጥታችሁ ታቅፉ እንደነበር የሚጠቁም ነበር ጅምራችሁ፡፡ በኋላ ነፃ አውጪ ሆነው የመጡት የዚያ ትውልድ ጮርቃዎች ግን ‹‹የወንጀለኛው ደርግ-ኢሠፓ መዋቅር›› በሚል ፍረጃ፣ (ሙያ ለመቅሰም የሚያስፈልጓቸውንና የእነሱን ፖለቲካ የተቀበሉትን ሰዎች ብቻ አስቀርተው) ተቋማት አፈራርሰዋል፣ ተቋማት ኦና አድርገዋል፣ ሙያተኞች ከሥራ ውጪ በትነው፣ የራሳቸውን ሠራዊት የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አከርካሪና ሁነኛ ጥንቅር አድርገዋል፡፡ ቡድኑን በአስተሳሰብና በድርጅታዊ አውታርነት የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አከርካሪ የማድረጉ ስርቆት ረዥም ዘመን ለመግዛት አላስችል ሲል፣ ኢትዮጵያን ራሷን ለመብላትም ውሎ ነበር፡፡ ደግነቱ በጊዜው የሥልጣን ቁንጮ ላይ የነበሩት ሰዎች የ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›  ካቴናቸውን የበጠሱ ነበሩና የኢትዮጵያን ሕዝቦችና ወጣቶች አነቃንቀው ኢትዮጵያ ልትተርፍ በቃች፡፡

ኢትዮጵያ ከመትረፍም አልፋ፣ በፍትሐዊ ልማት ለማስወንጨፍ ያለመና የቆረጠ የአዲስ ትውልድ ትርታ አግኝታለች፡፡ በዚህ ረገድ ከመንግሥት ቤት እስከ ምሁራን፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እስከ ባለሀብቶችና ሕዝብ ድረስ ተያይዞ የመሥራት ጥረታቸው ባይፈጥንም እየጨመረ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ ከኋላ ተይዘው በመጡና ዛሬ በተባዙ ችግሮች ኢትዮጵያ ገና እንደ ተቀየደች ነች፡፡ ኢትዮጵያ ከተቃጣባት ግዙፍ አደጋ ብትተርፍም ገና አደጋዎቹ አልተራገፉም፡፡ በሕገ መንግሥት ደረጃ ከኢትዮጵያ መቀነስ መብት ነውና የኢትዮጵያ በይዞታዋ መቀጠል ገና በእንጥልጥል ያለ ነው፡፡ ለእንጥልጥል ‹‹ህልውናዋ›› የአስተሳሰብ መሠረት የሆነው ወፈፌ ብሔርተኛ አስተሳሰብና ፖለቲካም ሜዳ ለሜዳ አለሁ እያለ ነው፡፡ ለ27 ዓመታት ያህል የአስተሳሰብና የፖለቲካዋ አውታር ሆኖ አዕምሮን ያዘባተለው ብሔርተኝነት ዛሬም ገና እየተፈታተነ ነው፡፡ ከትናንትናና ከዛሬ ጥፋቶች ተምሮ የሠፈር ቁርጥራጭ ግቦችን ተሻግሮ፣ የሕዝቦችን አዛላቂ ጥቅሞች ሙሉ ባደረገ መተሳሰብ የመያያዝ ትግል ብዙ አወላካፊ አለበት፡፡ የብሔርተኛ ርዝራዦች በሰላማዊ ጥይቶችም በባሩድ ጥይቶችም ይታገሉታል፡፡ ‹‹ፀጥታ ማስከበር የመንግሥት ሥራ ነው! መንግሥት ሥራህን ሥራ!›› እያላችሁ የምትቆነኑ ፖለቲከኞች/ቡድኖች፣ ያለንበትን የፈተና ጊዜ የተረዳችሁ ለውጥ ፈላጊዎች ከሆናችሁ እፈሩ! መደበኛ ያልሆነው የአሁኑ ጊዜ ‹‹…ሥራህን ተወጣ!›› ከማለት የበለጠ አስተዋጽኦ ከእናንተ የሚሻ ስለመሆኑ ነጋሪ ሊያስፈልጋችሁ አይገባም፡፡

ከ1966ዎች ትውልድ ርዝራዦች መሀል ይህንን ጉዞ የሚያግዝ አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ እንዳሉ ሁሉ፣ ከጥፋት መውጣት እንቢ ያሉ ግትሮችም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኑሮ ለዋጭ ግስጋሴ ውስጥ እንዲገቡ፣ ከአንጀት የሚሠሩ ፓርቲዎች (ከብሔርተኞችም ኅብራዊ ነን ከሚሉትም) ኢትዮጵያ ውስጥ ኖረው ቢሆን፣ አማራና ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ተኳሾችን የግስጋሴ ደንቃራነት ማውገዝ የጉሮሮ ላይ አጥንት አይሆንባቸውም ነበር፡፡ የእነሱ ያላወላወለ አውጋዥነት ተኳሾቹን ደጋፊና ሸሻጊ የለሽ እንዲሆኑና በእልህ ከመታወር ወጥተው ልቦና እንዲያገኙ ባገዘ ነበር፣ ብሎም ሰላም የሚገኝበትን ዕድል ባቀረበ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊነታቸው ከማውገዝ ያለፈ መሆኑ የገባቸው ካሉም፣ በየትም በየት ብለው ጠመንጃ ከሚተኩሱት ቡድኖች ጋር ግንኙነት ፈጥረውና ከሕዝብ ጥቅም አኳያ ለድርድር አግባብተው፣ መንግሥትንም ማቅማሚያ ሰበብ ባሳጡት ነበር፡፡ የእኛ ፖለቲካ ፓርቲ ነን ባዮች ግን ‹‹ጦርነት›› ይቁም! ተደራደሩ!‹‹ የሚሉ የተራ ዜጎችን ጩኸት በተሬዎች ረድፍ ውስጥ ሆኖ ከማስተጋባት ባለፈ፣ ለብሶቶችና ለጥያቄዎች መልስ የማስገኘት ፓርቲያዊ ሚናን አያውቁትም፡፡ ከተራው ሰው የዘለለ ፖለቲካዊ ሙያ ያላቸው ለመምሰል የሞከሩትም ቢሆኑ ያደረጉት ነገር፣ የግርግር ሰበብ የሚሹ ሰርጎ-ገብ አተራማሾች ከተለያየ አቅጣጫ ባደፈጡበት የኢትዮጵያ ምድር ላይ ‹‹ጦርነት ይቁም! …›› የሚል ሆይ ሆይታ ያለው ‹‹መሬት አንቀጥቅጥ›› ሠልፍ አድርገው ሰላምን ሊያዋልዱ ነበር የቃዡት፡፡ በዚህም ሙከራቸው (ዛሬም አለሁ የሚለውን ኢሕፓን ጨምሮ) የኢትዮጵያ እውነታ አልቆረጠም እንዳላቸው ነበር ያጋለጡት፡፡ የኑሮ ጣጣ በየዓይነቱ አጉብጦትም አገሩ አንደኛዋን ትርምስምሷ እንዳይወጣ የሚጠነቀቀው ተሬ ዜጋ ግን በአስተዋይነት በለጣቸው፡፡

ከደርግና ከኢሕአዴግ ዘመናት እየተቀባበለ ቤቱን የሠራውና ዛሬም እየተራባ ያለው ልሽቀት፣ ሙስና፣ ሰንካላ ልሂቅነት፣ ሙያ-ዕውቀት የለሽነት በብዙ ፈርጆች እየተሞከረ ያለውን ተሃድሶ የማምጣት ጥረት እያበለዘና ወደ ኋላ እየጎተተ ይገኛል፡፡ ብቃት የለሽነት፣ የችሎታ ጉድለትና አበያነት በሁሉም የመንግሥት አውታራት እንቅስቃሴ ውስጥ ከፖለቲካዊ እስከ ምሁራዊ/ሙያዊ ሥራዎች፣ ከጋዜጠኝነት እስከ መዝናኛ፣ ከሥራ መሪነት እስከ ተመሪነት ፊት ለፊት ፈጦ ይታያል፡፡ ያንን ሁሉ የሚቀይር ትምህርትና ሥልጠና ከሥር ጀምሮ የመትከል፣ ጊዜያዊ ችግርን በጊዜያዊ የሥልጠና ድጎማና የአሠራር ማሻሻያ እንዲያም ሲል አብርሮ በመተካት ሁሉ የማቃለል ትግልም አብሮ አለ፡፡

ይህ ሁሉ የሚያስገርም ዱብ ዕዳ አይደለም፡፡ ጊዜው ሒሳብ የማወራረጃ ነው፡፡ በቤታችን ላይና በቤታችን ውስጥ የደረሰው ብልሽት ብርቱ እንደ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ በህሊና አቅሟም በተቋማዊ ቁመናዋም ብዙ የተበዘበዘች እንደ መሆኗ የጥገና ወጪዋም ከፍተኛ የዋጋ ክፍያ ከደም እስከ ጥሪት የበላ ነው፡፡ የእኛ አገር ልሂቃዊ ጉልምስና በአፍጢሙ ተደፍቷልና ትንቅንቁ በምፀት የተሞላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች አካባቢ የመደብ መፈላቀቅ ስለሚጎድል (የወል አስተሳሰብ ስለሚያይል) የተራማጅ አስተሳሰብ መሪነት እዚያ አካባቢ ብዙም የሚያዋጣ አይሆንም የሚል ኢሕአዴጋዊ የጓዳ ትንታኔ ይሰጥ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ዛሬ እንደ አፋርና ሶማሌ ያሉ አካባቢዎች አወል አርባና ሙስጠፌ መሐመድን የመሰሉ መሪዎች አግኝተው፣ አስተዳደርና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው ልማት ላይ አትኩረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዋና የልሂቃን መፍለቂያ የነበሩት ትግራይ፣ ኦሮሚያና የአማራ ክልል አካባቢዎች የኑሮ ደኅንነት የራቃቸው ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምድር ላይ የደረሰው አንዱ ሁነኛ ነገር የታሪክ ስላቅ ይህ ነው፡፡

በሁሉም መስክ ፍልሚያና ፍትጊያ አለ፡፡ አገር እንዴት እንደሚካድ ደጋግመው በግብራቸው የሚያስተምሩ፣ ጦረኝነት፣ በቀልና ጥላቻን የሚያነፍሱ፣ ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም ይበልጥ የግል/የቡድን ጀብዱ የሚበልጥባቸው እንዳሉ ሁሉ፣ በተቃራኒው ኢትዮጵያዊ ሰፊ ንቃት፣ አፍሪካዊነት፣ በጎ አድራጊነት፣ ለሕዝቦች ሰላምና መተጋገዝ መሥራት፣ እንዲስፋፋ የሚለፉም  አሉ፡፡ በሥልጣን ላይ ባሉ ጊዜ አገርን አብልጠው ለአገር ዓላማ ታምነው ሲሠሩ የነበሩ ከሥልጣን ሲሻሩ የግል በቀል ከአገር ጥቅም ልቆባችው አገር ሊጎዳ የሚችል ሚስጥር ሁሉ ለማውጣት የማይመለሱ ቃሪያ ጀብደኞች አገራችንን እንደሚያስደነግጡ ሁሉ፣ በአገዛዙ የደረሰባቸውን የግል ተበዳይነት ለአገር ጥቅም ሲሉ ጥለው፣ አገር ፈተና ላይ ባለችበት ሰዓት ከበዳያቸው ጋር አብሮ ለመሥራት የሚፈቅዱም ሆደ ሰፊዎች አሏት ኢትዮጵያ፡፡

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል ውስጥም ያልተግባቡ ፍላጎቶች እየተልወሰወሱ ነው፡፡ አውሮፓና አሜሪካ የሚታዩ ወጎችን ሁሉ አዲስ አበባ ላይ ካልተወራጨንባቸው የሚሉ፣ የግለሰብ መብቶችንና የቡድን መብቶችን በተናጠል ይዘውና አንዱን ከሌላው አብልጠው የሚውገረገሩ፣ የዴሞክራሲ ነፃነትን ከገደብ ጋር መብትን ከግዴታ ጋር አዛምዶ መለማመድ የሚጎረብጣቸው እንውረግረግ ባዮች እንዳሉ ሁሉ፣ የዴሞክራሲን ዕርባና የኢትዮጵያውያንን መረጋጋትና መግባባት በማሳደግ ልኩ መጥነው የሚያዩ አሉ፡፡ ምዕራባዊ የዴሞክራሲ እሴቶችን ከኢትዮጵያ እሴቶችና አቅሎች ጋር ማጣጣም የሚሹ፣ በዚሁ ማዕዘናዊ ዕይታ መሠረት የምዕራባውያንን ርዕዮተ ዓለም እንደወረደ ምገው የሚያምጉ ‹‹ሲቪል›› ማኅበራትን ማርረቅ የሚሹ፣ የኢትዮጵያ ልሂቅ በሙሉ አድማሱ ለሚገለጥ ዴሞክራሲ ገና አለመዘጋጀቱን የተረዱና ዴሞክራሲ ልቃቂታዊ አሰፋፍ ይዞ መራመድ እንዳለበት የሚያምኑ፣ ሕጋዊ መብትን የመጠቀም ድፍረትና ከሕግ ጥሰት የሚመጣ አይምሬ ቅጣትን መፍራት አንድ ላይ እንዲጎለብቱ የሚሹና አንዳቸው ለሌላቸው መስዋዕት ሳይሆኑ መለመዳቸው ለኢትዮጵያ ይበጃል የሚሉ ሁሉ አሉባቸው፡፡ ጨዋነት ካነሰው (የመዘላለፍና የመሸራደድ ሁካታ ከበዛበት) ‹‹ነፃነት›› ተነስቶ ሥነ ምግባራዊ ሥርዓት ወደ ያዘ አሠራር ለማለፍ ከሚከጅል የጉዞ መንገድ ይልቅ፣ ጠበቅ ካለ ዓውድ ጀምሮ እየላላ በሚሄድ አረማመድ ወደ ሙሉ ዴሞክራሲ መግባትን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልምድ ያስመርጣል ብለው የሚያምኑ (በኢትዮጵያ መንግሥት የሹም አመረራጥና አኮታኮት እየተበሳጩ የታዬ ደንደአ ጀብደኝነት ህሊና ሲያጣ የደነገጡ፣ በቤተሰቡ ላይ በደረሰው ቅጣት እያፈሩ ግን ታዬ ደኅንነት ነክ ሚስጥር ዘርግፎ ድፍርስርስ ነገር እንዳያስከትል አፉን የሚዘጋ ነገር የተማፀኑ፣ በሆነ ‹‹ጥፋት›› ሲታሰርም ‹‹ጥፋቱ›› ባይዋጥላቸውም መታሰሩን ተመስገን ያሉ) ሁሉ አሉበት፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ‹‹ዝመና›› የፈረንጅ ፎቶ ኮፒ እስከ መሆን ድረስ ዓይነ ስቡ የጠፋ ነው፡፡ በፈረንጅ ፊልም የሚቀርብለትን ሁሉ ማንነቱ እስኪጠፋው ድረስ ይቀዳል፡፡ በ‹ዩቲዩብ› እና በሶሻል ሚዲያ የሚደፋ ትርኪ ምርኪን በመቃም እየተጎዳ ቢሆንም (ሱሰኝነት፣ ልሽቀት፣ ከአፍንጫ አይርቄነት፣ ጨለምተኛነት፣ ራስን በቧልት ውስጥ መደበቅ እየደደረበት ቢሆንም)፣ ከዚህ የማላቀቅ ትግልም አነሰም በዛ እየተካሄደ ነው፡፡ የወጣቱን ሥራ አጥነት የመቀነስ ትግል፣ ዲጂታል ሚዲያን ለገንቢ የሥራ ፈጠራ የማዋል ዕውቀትን ለወጣቱ የማስታጠቅ ጥረት፣ ወጣቱን በልማታዊና በበጎ ሥራዎች የማሠማራት እንቅስቃሴዎች፣ የዚሁ ትግል ሌላ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛ ፊልሞች በገፍ የሚቀርበውን ላሻቃነትና የዝርፊያ ጥበብ፣ በአማርኛ እስከ ማቅረብ የዞረባቸው ውዳቂ ፊልሞች ቢበረክቱም፣ ከእነሱ በተቃራኒ ሰብዕና ገንቢ የሆኑ ፊልሞችና ፊልም ገብ ድራማዎች ተጀማምረዋል፡፡ እረኛዬ፣ ግራ ቀኝ፣ በሕግ አምላክ፣ በስንቱ፣ አምባር፣ በመሃል፣ ቤቴ ሚስቴና የሱፍ አበባ የዚህ አብነት ናቸው፡፡ ‹‹አየር ላይ›› በሚል ርዕስ ከሚተላለፉ ‹‹ኮሚዲ›› ድራማዎች ውስጥ በገና ሰሞን (2016 ዓ.ም.) የቀረቡ ሁለት ሥራዎች፡- መዋጮ (ክፍል 10) እና በኑሮ ውድነት ዘናጮቹ ስለደረሰባቸው የተሞላቀቀ ዕጦት የሚያሳየው (ክፍል 9) ልዩ ነበሩ፡፡ የተመልካችን አጣጣሚነት በማሳደግ ረገድ ከሌሎቹ ‹‹ኩመካዎች›› ነጥረው የወጡ ከመሆናቸው ሌላ፣ አዘጋጆችም በቃላት የቁምና የአገባብ ትርጎሞች ላይ እየተፍተለተሉ ሳቅ ለመፍጠር ከመሞከር ይልቅ ስላቅ የሚፈጥሩ የኑሮና የሰብዕና ገጾችን ማስተዋል ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስተምሩ ነበሩ፡፡ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ያቀረበልን የከተማ ቅምጥሏ ወጣት ወደ ደቡብ ምዕራብ አካባቢ ሄዳ የካሮ ማኅበረሰብን ደቃቃ ሕይወት ያቃመሰችበት፣ እኛም በእሷ በኩል የቀመስንበት ዝግጅት (የፈረሰ የተማሪዎች መማሪያን ለማደስ የተደረገውን ዕገዛ ጨምሮ) እጅግ ልብ የሚነካ ነበር፡፡ የከተማ ዘመናዮች የልዩ ልዩ ባህል ገጠራማ ሥሮቻችንን በኑሮ እየቀመስን እንድናውቃቸውና እንድናቀናቸው በማስገንዘብ ረገድም ዝግጅቱ ዓይን ገላጭ ነበር፡፡

በጥቅሉ ከሕገ መንግሥት አኳያ ኢትዮጵያችን ገና በእንጥልጥል ላይ ብትሆንም፣ ውድ ዋጋ ከፍላ በአስተሳሰብም በተቋማዊ አውታርም ትጥቅ ከፈታ አገራዊ ስብራት በደንብ ወደ ታጠቀ አገርነት እየተቀየረች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ አገርነት  የቢሻኝ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ (ጠንካራ፣ የታፈረ፣ የለማና የበለፀገ ኅብረተሰብ ሆኖ የመፍካት ጉዳይ መሆኑ) የኢትዮጵያ ተራ ሕዝብ ማኅበራዊ ንቃት እየሆነ ነው፡፡ ማኅበራዊ ንቃትነቱ ግብታዊ እስከ መሆን እየጠለቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ የሰፋ አስተሳሰብ ከመያዝ ባለፈ በቀጣናና በአኅጉር ደረጃ መተሳሰር አጠቃላይ ግንዛቤ እየሆነ ነው፡፡ ደንበር ገተር እያለ ቢሆንም የተግባር ትስስሩም ተጀማምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ፍቅራችንና ዕውቀታችን ከድፍንነት ወጥቶ ባለ ይዘት እየሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብዝኃነት (ዥንጉርጉርነት) በማኅበረሰቦች ጥንቅር፣ በባህል፣ በቋንቋዎች፣ በእምነት፣ በሙዚቃ መሣሪያዎች፣ በዕደ ጥበብ ሀብት፣ በባህላዊ ጨዋታዎች፣ በሙዚቃዎችና በውዝዋዜዎች ሁሉ ተፈልቅቆ እየወጣና በሕዝብ ህሊና እየታወቀ ነው፡፡ እየታወቀ ነው የምንለው የኢትዮጵያ ዥንጉርጉርነት፣ ሀብቷና ውበቷ ታሪካዊ ቅርሷና የአንድነት ፈትሏ መሆኑም ልብ እየተባለ ነው፣ የጥንካሬና የብልፅግና አከርካሪዋም መሆኑ እየተጤነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኃይል መንገድም በሰላማዊ ልዩ ልዩ መንገዶችም የተዛነቁና የተወራረሱ ሕዝቦች አገር መሆኗም ሚዛናዊ ግንዛቤ እያገኘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዳር ዳር በደልን፣ ግፍን፣ መገፋትን መቅመሳቸው ያንኑ ያህልም በተለያዩ ችግሮች ጊዜ (በድርቅና በረሃብ ጊዜ፣ ሰላም በማጣት ጊዜ…) አንዳቸው ለሌላቸው፣ የራስጌው ለግርጌው የግርጌው ለራስጌው መጠጊያ መሆን፣ ዛሬም ድረስ የቀጠለ እሴታቸው መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ አንድ ላይ መግጠማቸው/ተባብረው በአገርነት መንቀሳቀሳቸው ቅኝ ገዥዎችን ለማሳፈር ያበቃቸው ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት መመኪያና መነቃቂያ ለመሆንም ያስቻላቸው ታሪካዊ ጉልበታቸው መሆኑ ፍንትው ብሎ እየተውለበለበ ነው፡፡ ዛሬ እየተሞከረ ያለውና ብዙ መፈተግና መጎልበት የሚጠይቀው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የትድድር ሥርዓትም ጊዜው የሰጣቸው ሜካኒካዊ ሥርዓት ሳይሆን፣ በታሪክ ያገኙትን የተዛነቀ/የተላላሰ ዝምድናቸውን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ የትድድር ሥርዓቱ መፈተግ ያለበትም በአስተሳሰብም በአወቃቀርም የዝምድና ቅርሳቸውን በአግባቡ እያለማ ባለመሆኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነትም ትናንትም ዛሬም ከመታወቂያ ካርድ በላይ የሆነና በአገር ፍቅር የታነፀ ዜግነት ቢሆንም፣ የዛሬው የአገር ፍቅር ድፍንነቱ ተከፍቶ ነገን ጭምር እያስተዋለ በመልማት የሚገኝ ነው፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያዊነት የተወራረሰና የተዛመደ ዥንጉርጉርነትን ኢትዮጵያዊ ማንነቴ፣ የታሪክ ቅርሴ፣ የነፃነትና የብልፅግና አቅሜና ጉልበቴ ብሎ የተገነዘበ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ፍትሐዊ ልማትንና መተጋገዝን የቤተ ዘመድ ጉዳዩ ያደረገ ነው፡፡ በአፍሪካዊነት ንቃትና ኩራት የታነፀም ነው፡፡ ድኅነትን፣ ረሃብንና የርጥባን ጥገኝነት ባሸነፈ ብልፅግና የነፃነቱን ይዘት ሙሉ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ የሰው ልጆችን ሰቆቃና የዘር አድልኦን የሚቃወም፣ ተፈጥሮንና የሰው ልጅን በሚያከብሩ ዕሳቤዎችና እሴቶች የታነፀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዥንጉርጉርነት የቀለመና ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነትን የተጎናፀፈ ነው፡፡ ዛሬ ታዳጊው ትውልድ እየተገነባበት ያለው ኢትዮጵያዊነት ይህንን መሳይ ይዘት ያለው ነው፡፡

ይህ የዛሬው የዜግነት ግንባታው ገና ሐሳብ ላይ የተንጠለጠለ አይደለም፣ መሬት በረገጠ ዥንጉርጉር ልማት እየፈካ የሚገኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም በአየር ኃይል፣ በምድር ኃይል፣ በባህር ኃይል፣ በሳይበር መከላከያና የውጊያ ጥበብ እየጎለበተ ይገኛል፡፡ ወጣቱ የሠለጠነ የውጊያ አቅም ከመሆን ባሻገር፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በአሻሻይነት ተግባርም ተሠማርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት በግብርና፣ በፈብራኪ ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ መስክ እየተባ ነው፡፡ ወጣቶች በትምህርት ቤትና ከትምህርት ቤት ውጪ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከሶፍትዌር እስከ አሳቢ ሮቦት ነክ ጥበብ ድረስ በምርምርና በፈጠራ አልሚነት እየተኮተከቱ ነው፡፡ የዲጂታል ጥበብ በሁሉ የሕይወት ዘርፎች በወታደራዊ-ፖሊሳዊ-ደኅንነት አቅም ውስጥ፣ በመረታ ተግባራት ውስጥ፣ በከተማ ልማት ውስጥ፣ በፋይናንስ፣ በጤናና በሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ የማዘመን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ምርታማነቱ ያደገ ተመጋጋቢ ግብርና (የወተት ልማት፣ የከብት ማድለብ፣ ንብ ማነብ፣ የዶሮ ዕርባታ፣ ዓሳ በኩሬ ማልማት፣ ፍራፍሬ ማልማት) የተራ ገበሬ የሥራ ዘርፎች እየሆኑ ነው፡፡ ግብርና ከከተማ ነዋሪነትም ጋር እየተዛመደ ነው፡፡ ውትድርና፣ የትምህርት ማኅበረሰብነት (ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት)፣ ሌሎች የመንግሥት ሥራ ግቢዎችም ፍጆታን ከሚደጉም ግብርና ጋር እየተያያዙ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢን በማስመንደግ ዕቅድ ውስጥ ብዙ ነገሮች እየተካሄዱ ነው፡፡ ከውጭ የኢትዮጵያ ተወላጆች ጋር ያለ ተራክቦን መልክ ማስያዝ፣ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ማሻሻያ ማካሄድ፣ የገቢ ሸቀጦችን የውጭ ምንዛሪ አራቋችነት በአገር ውስጥ አምራችነት ማቃለል፣ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ፋብሪካዎችንና የአገልግሎት ንግዶችን ማሳደግ፣ በተለይም የአገር ውስጥ ፍጆታን ከሚሸፍን መትረፍረፍ ጋር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ጉልህ ለውጥ የሚያመጡ የግብርና ውጤቶችንና አግሮ ኢንዱስትሪዎችን በዓይነት ማብዛት፣ በዓመት ውስጥ ያለውን የማምረት ዙር ሁለትና ሦስቴ ማድረግ ተሳልተው እየተካሄዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ትምህርትና ሥልጠና (ከዝቅተኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ) የተመራማሪነት፣ የፈጣሪነት፣ የፈልሳፊነትና የሥራ አፍላቂነት ምንጭ እንዲሆኑ አድርጎ ማደስ እየተካሄደ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችን የተራማሪዎችና የፈጣሪዎች መፍለቂያ እንዲሆኑ አድርጎ ከማልማት ባሻገር ወጣቶችንና ታዳጊዎችን አገር በሚበጅ ጥበብ ፈጠራና ሥራ ፈጠራ የሚያወዳድሩ፣ የሚያነቃቁና የሚኮተኩቱ ተቋማት እየተበራከቱ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሌላ ነጥብ ላክል፡፡ በዕለት ኑሮ ውስጥ ስህተት/ጥፋት ሠርቶ ዝም ማለት፣ ቢወቅሱ ማጉረጥረጥ፣ ጭራሽ ለመሳደብ መከጀል ሁሉ እናገኛለን፡፡ ይህንን ችግር ፖለቲካችን ውስጥ ከምናየው አጥፍቶ ይቅርታ አለመጠየቅና አለመታረም ጋር አያይዘዋለሁ፡፡ ወላጆች በልጅ አስተዳደጋቸው፣ ትምህርት ቤቶችም ከቅድመ መደበኛ ትምህርት አንስቶ ተማሪዎችን በመቅረፅ ሥራቸው፣ አጥፍቶ ይቅርታ መጠየቅንና መታረምን በአክብሮትና በጭብጨባ እያስተናገዱ እንዲኮተኩቱት ሳስታውስ ትንሽዬ ነገር ያስታወስኩ እንዳይመስልብኝ፡፡ በጣም ትልቅ ጉዳይ ነው!

ይህ ትልቅ ጉዳያችን ይሁን እንጂ፣ አጠቃላይ አብዮት ከሚፈልገው የኑሮ ባህላችን ውስጥ አንድ ነጠላ ሰበዝ ነው፡፡ እየተሽቀረቀረች ባለችው አዲስ አበባ ውስጥ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ አንዳንድ ፍሪት ሕፃናት (እንስቶች ጭምር) ከቁመታቸው የሚበልጥ ፕላስቲክ ጆንያ ተሸክመው ፕላስቲክ ኮዳና የሚስማር ዘር ሲለቅሙ ይውላሉ፡፡ እነዚህ ሕፃናት የት እንደሚያድሩ ባላውቅም፣ በምግብ ረገድ ግን ተሰብስበው ትራፊ ሲበሉ ማየት ለእኔ እንግዳ አይደለም፡፡ ደግነት ብለውት ትራፊ በላስቲክ ስለሚያንጠለጥሉ ሰዎች ግን ባልናገር ይሻለኛል፡፡ አዲስ አበባ የዚህ ዓይነት የሕፃናት ከልታማነትም ‹ግራፍ› ነች፣ ያውም እያደገ ያለ ግራፍ፡፡ ይህንን ግራፍ የምገባ ቤቶች አይቀይሩትም፡፡ እነዚህን ሕፃናት እየለቀሙ ወደ መጡበት መመለስም ሆነ ወደ ማሳደጊዎችና ወደ ማሠልጠኛዎች ማሰማራትም ችግሩን አያስወግዱም፡፡ የችግሩ ምንጭ ምጣኔ የማያውቀው ወሊድ ነው፡፡ በኑሮ አቅማችን ልናሳድግ ከምንችለው በላይ እየወለድን ሕፃናቶቻችንን ለስቃይ መዳረግ አንዱ ሁነኛ ገመናችን ነው፡፡ ይህንን ገመና ስናሸንፍ የአዲስ አበባም የገመና ግራፍነት ይቀየራል፡፡ እንዲህ ያለው ገመና የሚሸነፈው ደግሞ፣ የየአካባቢ አመራር ሹሞቻችን ወደ መኳንንታዊ ኩንስንስነት ከመሮጥ ይልቅ፣ ማኅበራዊ ችግሮችን በማቃለል ላይ ሲያተኩሩ ነው፡፡ ያልተመጠነ አወላለድ አብዮታዊ ለውጥ ከሚሹ ችግሮቻችን አንዱ ነው፡፡

ባህል ነክ ችግሮቻችን ብዙ ናቸው፡፡ በባህል ረገድ እንዴት ያሉ ችግሮች እንዳሉብንና ምን ያህል አብዮት ሊዘልቀን እንደሚገባ ለመረዳት፣ በ‹‹ሰንኮፍ›› ዝግጅት በቅርቡ ቀርባ የተከታተልኳት (ቻይናዊ አግብታ ሁለት የወለደች) ወጣት የተናገረችውን አንድም ሳይቀር በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ባካትተው በወደድኩ፡፡ ችግሩ ግን ፊደላት በድምፅ የተነገረን መልዕክት ሁሉ መግለጽ አይችሉም፡፡ ‹‹ሰንኮፍ›› ከዚህች ልጃችን ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ደጋግሞ እንደሚያቀርበው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህች ወጣት ቻይና ሄዳ ያስተዋለችው ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን አይደለም፡፡ የቀናችባቸውን የባህል/ የምግባር እሴቶችን ነው፡፡ ቁምነገሮቿ የሚፈሱት ከአንደበቷ ብቻም አይደለም፡፡ ከሰብዕናዋም ነው፡፡ እሷ ግለሰብነት ላይ የሚታየው የልጅ እግር አርቆ አስተዋይነት፣ ምራቅ መዋጥ፣ የኃላፊነት ስሜት፣ ሕዝብ አክባሪነትና ትሁትነት ራሱ ትምህርት ነው፡፡ ዜጎች ልንቋደሳቸው የሚገቡ እሴቶች (ዜግነት ነክ፣ ሥራ ነክ፣ አስተሳሰብ ነክ፣ መስተጋብር ነክ፣ ወዘተ) ብዙ እንደሆኑ ሁሉ ዓይነተኛ ግለሰብነታችንም (‹ኢንዲቪጁዋሊቲ›ያችን) መልማት ይኖርበታል፡፡ የለማ ግለሰብነት፣ እንኳን ከቅርበት ከርቀትም ብዙ ትምህርት ይቀሰምበታል፡፡ ውጫዊ ሰብዕና ውስጣዊ ማንነትንም ይጠቁማል (በዚህ ረገድ ከርቀት ከሚማርኩኝና ምናቤን ከሚከፋፍቱት ሰዎች አንዷ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሆናቸውን ሳልጠቅስ አላልፍም)፡፡

በተረፈ ይህንን ያህል የፍሬያማነት ተስፋ ባለው ዓውድ ውስጥ ኢትዮጵያ እየተላወሰች ነው፡፡  እየተካሄደ ስላለው ለውጥ እስካሁን የተጠቀምኩት የቃላት አገላለጥ ግን፣ የለውጡን ደም ግባት በደንብ ያሳየ አይመስለኝም፡፡ ለውጡን የሚመራው መንግሥት ‹‹የምናካሂደው የጥገና ለውጥ ነው›› ይበል እንጂ በጥገና (ሪፎርም) ቀፎ ውስጥ አብዮት እየተካሄደ ነው፡፡ ከተፈጥሯዊ ኢኮኖሚ ወደ አረንጓዴ ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ የመሻገር መሠረት እየተነጠፈ ነው፡፡ ይህ አብዮታዊ ነው፡፡  እርሻው ዝናብ ከመጠበቅና በበሬ ከማረስ በመውጣትና ወደ መስኗዊና የመኪና አስተራረስ  በማለፍ ጉዞ ውስጥ ነው፡፡ ከዓሳ አጥማጅነት ወደ ዓሳ አርቢነት የመሻገር ጉዞ አብዮታዊ ነው፡፡ የግብርና ምርቶችን በአገር ቤት ውስጥ ከኢንዱስትሪ ጋር አገናኝቶ እሴት የታከለባቸው/ የተለወጡ ውጤቶችን ለወጪ ንግድ በማቅረብ ላይ ያተኮረ ጉዞ ከፍብረካ ጋር ተዳምሮ ኢኮኖሚን ኢንዱስትሪያዊ የማድረግ ዋና መዋቅር ነው፡፡ ነገ ኢትዮጵያን የጎብኚ መጉረፊያ ሊያደርግና ከፍተኛ ገቢ ሊያመጣ ለሚችለው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚያስፈልጉትን ፈርጀ ብዙ መሠረቶች የማንጠፍ ሥራ አብዮት ነው፡፡ የውጭ ሸቀጥ መንሰራፊያነትን በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ለውጥን መያያዝ፣ በራሱ የመዋቅር ለውጥ ሒደት ከመሆኑ ባሻገር፣ ከሌሎቹ ኢኮኖሚ-ገብ ንጣፎች ጋር ተደምሮ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ዕውን የሚያደርግ ድግስ ነው፡፡ ትምህርትና ሥልጠና ውስጥ እየተካሄደ ያለውም አዲስ የንጣፍ ሥራ፣ ምርታማና አገልግሎታዊ የልማት እንቅስቃሴዎቻችን የሚፈልጉት የሰው ኃይል (ሐሳብ አመንጪነት፣ ተመራማሪነት፣ ፈጠራዊነት፣ ጥበብ ፈልሳፊነትና  አበልፃጊነት፣ ተራማጅ አመራር ሰጪነትና የሥራ ሙያተኛነት) የሚፈልቅበትን አውታር እንደማይነጥፍ አድርጎ የማልማት ሥራ ነው፡፡ ይህ አብዮት ነው፡፡ በብዙ ተመጋጋቢ ፈርጆች እየተካሄዱ ያሉት አብዮቶች ሌላም ነገር ይናገራሉ፡፡ አብዮት ዕርምጃን ያነቁ ማነቆዎችን አስወግዶ ዕድገትን የሚያፍለቀልቅ/ የሚያስወነጭፍ እንጂ ‹‹አፍርሶ ከዜሮ የሚጀምር›› እንዳልሆነ፡፡

ፈርጀ ብዙው የአሁኑ የልማት አያያዝ፣ ከአጀማመሩ የሚያመረቃ ቢሆንም፣ በአገር ቤት ውስጥ የሚገባውን ያህል ‹‹ልሂቃዊ›› እሰይታ አላገኘም፡፡ የገዥውን ፓርቲ እንከኖች አግዝፎ ማየት የሚበልጥባቸው ‹‹ፖለቲከኞች›› እና የማኅበራዊ ሚዲያን ጨለምተኝነት የሚመገቡ ሐዘንተኞች ኢትዮጵያ በእነ ዓብይ አገዛዝ ዋይታዋና በደም መታጠቧ በዝቶ ስትወድቅና ጭርንቁሷ ሲወጣ ነው የሚታያቸው፡፡ ዛሬም ብሔርተኛ ጦረኞችና ዘርፎ በሎች ሰላማችንን በሁለት አካባቢዎች እያመሱት መሆኑ ለዚህ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው፡፡ ጨለምተኛነትና ፅንፈኝነት ጠመንጃን እንዳመጣብን ሁሉ የጠመንጃው ማብቂያ ያጣ አማሽነትም ጨለምተኝነትን እያፋፋው ነው፡፡ የለም ይህ አባባል እውነት የመሆኑን ያህል ሐሰትም ይረጫል (ከእኛ ትውልድ ጀምሮ የተላለፈው ብሔርተኛ ነፃ አውጪነት ዛሬ ድረስ የሰው ህሊናን ገዝቶ ያስቸገረ ያስመስላል)፡፡ እውነቱ ጥርት ብሎ ይነገር ከተባለ፣ ችግር የሆነብን የከረከሰው ብሔረኝነት/ጎጠኝነት ሳይሆን፣ ሽምድምዱ ልሂቃችን ትምህርት አይገቤ ትምህርት እንቢኝ ያለ መሆኑ ነው፡፡

ብሔርተኝነት (‹‹ነገደኛ››/ኤትኒክ ፖለቲካ) ብሔረሰቦችን ከጭቆና እንደማይገላግልና እኩልነትን እንደማያመጣ (ከናካቴው ብሔርተኛ/‹‹ነገደኛ›› ፖለቲከኞችን ወደ ዝቅጠት እንደሚያንከባልል) የሕወሓት ኢሕአዴግ የ27 ዓመታት አገዛዝ አረጋግጧል፡፡ ‹‹በኢሕአዴግ ሕወሓት አገዛዝ ጊዜ መብቱ የከሸፈው ዴሞክራሲ ስለጎደለ ነው›› የሚሉ ብሔረተኞችም ትምህርት ጠል ቀጣፊዎች ናቸው፡፡ ብሔርተኛ (‹‹ነገደኛ››) ፖለቲካ በውስጠ ተፈጥሮው አንጓላይ (‹ባለቤት› እና ‹መጤ› ብሎ መብት ‹‹የሚያድል›› እና የሚነፍግ) እንደመሆኑ የዴሞክራሲ ጥለኛ መሆኑ ግጥጥ ብሎ የሚታይ ነው፡፡ የእኛ የፖለቲካ ልሂቃን የሚማሩ ቢሆን ኖሮ ከብሔርተኛ አድልአዊነት የሚፈልቁት በመብትና በጥቅም መገፋት፣ የሕግ ጥበቃ አጥቶ መጠቃትና መፈናቀል፣ ለፍትሕ አቤት ብሎ ሰሚና ፍትሕ ማጣት ከተትረፈረበት የ27 ዓመታት የተግባር ተሞክሮ ተምረው፣ የ2010 ዓ.ም. የመጋቢት ለውጥ ሲመጣ በአንድ ድምፅ ‹‹ብሔርተኝነት (‹ኤትኒክ› ፖለቲካ የብሔረሰቦችን ጭቆና አያስወግድም፣ የብሔረሰቦች ጭቆና የሚወገደው በዴሞክራሲ መቋቋምና በፍትሐዊ ልማት መስፋፋት ነው›› ብለው ማወጅ በቻሉ ነበር፡፡

ጭራሽ አለመማራቸው ሳያንስ፣ በብሔርተኞቹም ዘንድ ብሔርተኛ አይደለንም በሚሉትም ዘንድ፣ የተጠናገረ አስተሳሰብ ይዞ ‹‹መራቀቅ›› አዋቂነት ሆኖ ብቅ አለ፡፡ የዚህ ችግር አንዱ ምንጭ የእንግሊዝኛንና የአማርኛን የሥነ ትርጓሜ (‹ሴማንቲክስ›) መዋቅራዊ ልዩነት ሳያጤኑ፣ ከእንግሊዝኛ እየተረጎሙ በእንግሊዝኛ አገባባቸው አማርኛም ውስጥ ለመጠቀም መሞከር ነው፡፡ ‹ናሽናሊዝም›ን ብሔርተኛነት ብሎ የተረጎመ ልሂቅነት በእንግሊዝኛው አካሄድ ለአገርም ሲያውለው ምን ያህል የሐሳብ መምታታት እንደሚፈጥር ተከታዩን አባባል በማፍታታት መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹የብሔር ብሔርተኝነት እንዳለ ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትም አለ፣ ምን ያስደንቃል!›› በሚለው በዚህ አባባል ውስጥ ‹ብሔረተኛነት› ንዑስና ዓብይ የሚል አንድምታ ይሰጣል፡፡ ብሔርተኝነት (‹‹ነገደኛ››/ኤትኒክ ናሽናሊዝም) አንጓላይ ፖለቲካ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ናሽናሊዝም (አገር ወዳድነት) ግን አንጓላይ አይደለም፣ በመደበኛ ፀባዩ ፖለቲካም አይደለም፡፡ አገር ወዳድነት ‹‹ብሔርተኛ ፖለቲካ›› የሚሆነው ወደ ፅንፍ ሄዶ ‹‹መጤ/ስደተኛ አያሳየኝ! መጤዎች የሥራ ዕድሎቻችንንና ሀብታችንን አላሲዝ አሉ! ወዘተ›› የሚል ጥላቻና ስስት ሲይዝ ነው፡፡ እንዲያ ያለ የፖለቲካ አቋም የያዘ እንቅስቃሴ ደግሞ አገር ወዳድነት ሳይሆን የፋሽስታዊነት ልምላሜ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልሂቃን እንደ ተራው ሕዝባችን መከራን ከመቅመስና ከእውነታ ልብታ የሚማሩ ቢሆኑ ኖሮ፣ በአምስት የለውጥ ዓመታት ውስጥ እጅግ ውድ የሆኑ የሕይወትና የሀብት ወጪ ባላወጣን ነበር፡፡ ዓብይ አህመድን ልዝብና ቀንዳም ሰይጣን አድርገን መብገንና መበጋገን ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡ እንዲያውም እንደ ሙስጠፌ መሐመድና እንደ ብርሃኑ ነጋ ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጓት ሁነኛ ሰዎቿ አንዱ ዓብይ አህመድ ስለመሆኑ በተግባባን ነበር፡፡ በጠንካራ ችሎታዎቹ ላይ የለውጥ ኃይሎችን ማስተባበርንና ማበራከትን፣ የሕዝብ ድጋፍ መንከባከብን፣ የሕዝብና የመንግሥት ትምምን ማጎልበትን አሳምሮ ያወቀ ዓብይን ነገም ኢትዮጵያ እንደምትሻ ባስተዋልን ነበር፡፡

አሁን በዋናነት ሁለት አካባቢዎች ውስጥ ያሉ የሰላም ችግሮችን አቃለን የውስጥ ሰላማችንን ሙሉ ብናደርግ፣ የኢኮኖሚ መሠረትን ለመለወጥ ያነጣጠሩ ጅምሮች፣ በትርታቸው ዓይንና አዕምሮን መንዘራቸው አይቀርም፡፡ የእነሱ ንዝረትም የሕዝብ ድጋፍን በመጠገን ረገድ ካድሬ ሊሠራው የማይችለውን የቅስቀሳ ሥራ ይሠራል፡፡ የልማት ግስጋሴና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ከተገናኙ ደግሞ የሰዎች ጨዋነትንና ሥራ ወዳድነትን ማደስ ይቀላል፡፡ ያንን በመያዝ፣ አልቀየር ያሉ ችኮዎችን መንጥሮ ተገልጋይንና ሥራን አክባሪ የአሠራር ቅልጥፍናን የማስረፅ/ሥር የማስያዙ ሥራ ይዋጣል፡፡ ያ ተዋጣ ማለት ደግሞ የሙያና የአገልግሎት መስኮች የሥራ ባህላቸው እንዳይላሽቅ የሚቆጣጠር የሚከታተልና ራሱን በራሱ የሚወለውል የሰው ኃይልና ሥልት ይቆናጠጣል ማለት ነው፡፡ ከጊዜ ጊዜ ሰዎች የሚሠሯቸው ሥራዎች ከሥራ ቤት ውስጥና ከሥራ ቤት ውጪ ከሚሰጡ የሥራ ጥራትና የምሥጉንነት ደረጃዎች (ሬቲንግ) ጋር ሲገናኙ፣ የሥራ ጥራትና የምሥጉንነት ደረጃዎችም ከጊዜ ጊዜ ዘመኑ ባመጣው የዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ውስጥ የሚገቡ ሲሆኑ፣ ተገልጋዮችና ሥራ ማሠራት የሚሹ አካሎችም የሥራ ተቋማትን ባላቸው የምሥጉንነት ደረጃ (ዝና) ማማረጥን ሲያዘወትሩ፣ የማያንቀላፋ አዲስ ባህል ተገንብቷል ማለት ነው፡፡ እናም ትናንትና የላሸቁ መሥሪያ ቤቶች አዲስ ገቢ ሠራተኛን እያኘኩ ያዘቅጡ እንደነበር ሁሉ፣ የአዲስ ባህል ሥርዓት ውስጥ የገቡ መሥሪያ ቤቶችም (አግልገሎት ሰጪም ሆኑ አምራቾች፣ የግልም ሆኑ የመንግሥት) ስማቸው እንዳይጎድፍ እየባነኑ አዲስ መጥ ሠራተኛን በቀልጣፋ፣ በጨዋና በትሁት የሥራ አከዋወን ይቀርፃሉ፡፡ ፈጠነም ዘገየ ጉዟችን ወደ እዚህ አቅጣጫ መሆኑ ይሰማኛል፡፡

የየካቲት አብዮት ሆይ! ‹‹ለዚህ ሁሉ ሥራ መቃናት የሚያስፈልጋችሁን የውስጥ ሰላም ለመጨበጥ፣ ምን ያህል ቅርብ ናችሁ?›› ብለሽ ብትጠይቂኝ ግን መልስ ይቸግረኛል፡፡

አሁን አሁን ከእኛ ቁጥጥርና ፍላጎት ውጪ በራሳቸው እየተፈጸሙ እኛኑ መልሰው የሚቃኙና የሚቀዝፉ ድርጊቶችን ሳስተውል፣ ታሪክ በራሷ መንገድ ብዙ ነገር እየሠራች እኛንም እየሠራችን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በአገራችን በሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የገዥው ፓርቲ መዋቅሮች፣ የፀጥታ አውታራት ከፌዴራል እስከ ወረዳዎች ድረስ ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ሚና አላቸው፡፡ ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ ‹ሲቪል ማኅበራት›፣ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃን፣ አንቂዎች፣ መደበኛና ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ የውጭ ግንኙነቶች (ከጎረቤት እስከ ሩቆቹ) እንዲሁ ሚና አላቸው፡፡ የታሪክ ዕርምጃ እነዚህን ከመሳሰሉ አቅጣጫዎች በሚመጡ ወደፊት ገፊና አዋኪ ተፅዕኖዎች የሚወሰን ነው፡፡ ወደፊት መጓዝን የሚያግዙ ሰበዞች በበረከቱበት የእንቅስቃሴ ፈርጅ ውስጥ፣ የታሪክ ዕርምጃዋ ለስልሶና ፈጠን ብሎ የመካሄድ ዕድል ያገኛል፡፡ ይበጃል ብለን የምንሠራው የተሳሳተ (ያቀድነውን ውጤት የማያስገኝ) በሆነበት ሥፍራ ወይም የነገሮች አያያዛችን ግብታዊነት የበዛበት በሆነ ጊዜ ወደ ፊት መራመድን የሚቀናቀኑና የሚያደናብሩ ብዙ ችግሮች ሊፈለፈሉ ይችላሉ፡፡

የእኛ ለውጥ ተስፋ ሰጪ ክንዋኔዎች እንደተያያዘ ሁሉ፣ ሰላምን ያወኩ አጥፊ አመለካከቶች/ቅራኔዎችና ጠመንጃ የያዙ ግብግቦች አሉበት፡፡ እኛ በብልኃት ልናቃልላቸው ያልቻልናቸውን ችግሮች ታሪክ ዝም ብላ አታይም፡፡ የሚጣሉ ሰበዞችን እንዳላቸው ባህሪ ግለትና ጉልበት እያስተናበረች፣ የሚጣፉትን ታጣፋለች፡፡ በሚጣፉት ሰበዞች ውስጥ ሰዎችም አለንበት፡፡ አልገባን ሆኖ ነው እንጂ፣ ጊዜና ሁኔታዎች በሰጧት ቅመማ መሠረት ከማጣፋትና ከማቃለል ቦዝና አታውቅም ታሪክ፡፡ አሁንም ቀጥላበታለች፡፡ ከታሪክ ጉዞ ጋር ትንቅንቅ የገጠሙ ዓላማዎች፣ አመለካከቶች፣ አውሬያዊ ጭካኔዎች፣ ጭፍን ጥላቻዎች፣ የሻነኑ ዕብሪቶች አቃፊ ደጋፊ አጥተው እስኪተፉና  አዕምሮ እስኪበራ ድረስ ምን ያህል ሰዎች እየተጣፉ ይረግፋሉ? ምን ያህል ብሶት ይከመራል? ዕርምጃችን ምን ያህል ይገተራል? ከናካቴው ወደኋላ ያፈገፍግስ/ ይገፈተርስ ይሆን? እንዲህ ያለው ነገር ለታሪክ ጉዳዩዋ አይደለም፡፡ የእሷ ጉዳይ የነገሮች መስተጋብር ያስገኘውን የሒሳብ ሚዛን ደከመኝ ሳይሉ መሥራት ነው፡፡ በነገ ላይ ስሜትም ፍላጎትም ያለን እኛ ሰዎች ነን፣ አንዳችንን በአንዳችን የሚያጣፉና የነገ ጥቅማችንን የሚጎዱ ድርጊቶችን የመቀየር ኃላፊነት ያለብንም እኛው ነን፡፡

ይህንን ኃላፊነት መወጣት ካልቻልን ተስፋ ሰጪ ልማታችንን በጥፋት የማስበላት አዙሪት ያዳግመናል፡፡ ከዚህ አኳያ የውስጥ ሰላም ችግራችንን በቶሎ መፍትሔ ካልሰጠነው ጠንቀኝነቱ በጣም ያስፈራኛል፡፡ የታሪክን አካሄድና ሚስጥር ተረድተን በነቃ መልክ ታሪካችንን ስንሠራ ስህተትም ሆነ ጥፋት ብንሠራ ቶሎ አስተውሎ ለመስተካከል ዕድሉ አለን፡፡ ከአዙሪቶች ወጥተን የታሪክ ሥራችንን መምራት ከተሳነን ግን፣ ታሪክ ራሷ በግብታዊ ጣቶቿ ትሠራናለች፡፡ በዚያ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ከወዲህም ሆነ ከወዲያ የሚፈጠሩ ደም ፍላቶችና ንጭንጮች፣ በኋላ በፀፀት ሊታረሙ የማይችሉ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ጥፋቶች ውስጥ ሊዘፍቁን ይችላሉ፡፡ እናም ነገሮች ተባብሰው ብዙ ጣጣዎች ከመፈልፈላቸው በፊት በጊዜ ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንምጣ፡፡

የካቲት ሆይ!

ወደ አንቺ ልመለስ፡፡ ስለችግሮቻችንና በድርጊት መገለጥ ስለጀመረው ተስፋችን የሚያወሳውን ወጌን ይህን ያህል ከተካፈልሽ ይበቃል፡፡ በሃምሳ ዓመት ጉዞ ውስጥ ሠራን የምንለው ያንሳልና በዚሁ ኃፍረት ሻማ እንኳ አላበራሁልሽም፡፡ አንድ የምሥራች ግን አለኝ፡፡ በዚህ ዓመት በአንች ወር (የካቲት 3) አራዳ ጉብታው ላይ፣ ከማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ግርጌ፣ የዓድዋ ተጋድሎንና ድልን የአፍሪካ ችቦነት የሚያንፀባርቅ መታሰቢያ ተመርቋል፡፡ የግድግዳ ምሥሎችን፣ ሐውልቶችንና ሙዚየምን ሁሉ ያካተተው ይህ መታሰቢያ ዓድዋ የአፍሪካና የመላ ጥቁሮች መሆኑን እንደፈነጠቀ ሁሉ የየካቲት አብዮትም መታሰቢያ ነው፡፡ እንዲህ ስል ስለአንችም ቃላት ሠፍረውልሻል ማለቴ ሳይሆን፣ የካቲት ላይ ተነስተው ለነበሩ የእኩልነት ጥያቄዎችሽ አንድ ምላሽ የሰጠ (በዓድዋ ተጋድሎ ላይ የነበረውን የመላ ኢትዮጵያ የደጀንና የግንባር አስተዋጽኦ ያንፀባረቀ) ስለሆነ ነው፡፡ ወደፊት የጥያቄዎችሽ መልሶች ተበራክተው ወርሽን በድምቀት የምናከብርበት ጊዜ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ተስፋዬን አልጠራጠረውም፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟ በዝቶ የአፍሪካ ቀንድ የልማትና የግስጋሴ ዕምብርታዊ ‹‹ምድጃ›› እንደምትሆንም ጥርጥር የለኝም፡፡

(በዚሁ አጋጣሚ፣ የዓድዋ መታሰቢያ የቆመበትን ሥፍራ መሀል ‹‹ፒያሳ/ ፒያሳ›› ብላችሁ የምትጠሩ ወጣት ጋዜጠኞች ‹‹አራዳ›› ብሎ መጥራትን እንድትለምዱ አሳስባለሁ፡፡ ምክንያቴ ግልጽና ቀላል ነው፣ ‹‹ፒያሳ›› የሚል መጠሪያ ነፃነታችንን ካላስነካው የዓድዋ ድል ጋር አብሮ አይሄድም)፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...