Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለዘመናዊው ኢኮኖሚ አዲስ የንድፈ ሐሳብ ዕይታ አስፈላጊነት

ለዘመናዊው ኢኮኖሚ አዲስ የንድፈ ሐሳብ ዕይታ አስፈላጊነት

ቀን:

በፍጹም በላይሁን

ኢኮኖሚ ማለት ማምረት፣ ማሠራጨትና መጠቀም (Production, Distribution and Consumption) ማለት ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ዋና ተዋናዮች አምራችና ሸማች ወይም ሻጭና ገዥ ናቸው። እነዚህ ተዋናዮች በሚያደርጉት የምርት ልውውጥ ውስጥ  የምርቱን ዋጋ ማን ይተምን የሚለው ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል።  በዚህም  መሠረት ታዋቂው ስኮትላንዳዊው  የኢኮኖሚ ምሁር  አዳም ስሚዝ (Adam Smith, 1723-1790) የዕቃውን  ዋጋ መተመን ያለበት  በአቅራቢውና በሸማቹ መካከል ያለው መስተጋብር ወይም ገበያው ነው።

በዚህ ሒደት ውስጥ የመንግሥት ድርሻ በግብይት ወቅት የሚፈጸሙትን  ጥሰቶች መዳኘትና ሕግ ማስከበር ነው  በማለት የነፃ ኢኮኖሚን በማስተዋወቅ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ሲሠራበት ቆይቷል። ነገር ግን ይህ ጽንሰ ሐሳብ በ1930 ለተከሰተው የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት አልቻለም። ይህም  በመሆኑ ምክንያት እንግሊዛዊው የኢኮኖሚ ምሁር ጆን ሜይናርድ ኬንስ (John Maynard Keynes, 5 June 1883 – 21 April 1946)  ለተፈጠረው የኢኮኖሚ ችግር መፍትሔ የሚሆን አዲስ የኢኮኖሚ ሐሳብ ይዞ ብቅ አለ።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህም የኢኮኖሚ ሐሳብ በነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ችግር ወይም ዕክል ሲገጥም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል የሚል ነው። መንግሥትም ኢኮኖሚውን ጤናማ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ መቻል አለበት የሚል ነው። የመንግሥት  የገንዘብ ፖሊሲ የሚባሉት የወለድ ምጣኔን ከፍና ዝቅ ማድረግ፣ የገንዘብ አቅርቦትን ከፍና ዝቅ ማድረግ፣ የሪዘርቭ ሪኳየርመንት ሬሽዮን ከፍና ዝቅ ማድረግ ናቸው፡፡ የፊሲካል ፖሊሲ የሚባሉት ደግሞ የመንግሥት ወጪዎችን ከፍና ዝቅ ማድረግ፣ የታክስ ክፍያ ተመንን ከፍና ዝቅ ማድረግ፣ መዋዕለ ንዋዮችን መጨመርና መቀነስ ይገኙበታል።

ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ እነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ፓሊሲዎች ኢኮኖሚው ጤነኛ ሆኖ እንዲቀጥል ወይም ደግሞ ስብራት የገጠመውን ኢኮኖሚ ለመጠገን የተቆጣጣሪ አካላት ጥቅም ላይ ሲያውሏቸው  ምላሽ ለመስጠት ሲቸገሩ ይታያሉ። 

ይህ ከሆነ ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎቹ አሁን የደረስንበትን ኢኮኖሚ  ለመቆጣጠር አቅም አንሷቸዋል ማለት ነው። አቅም ካነሳቸው ደግሞ ዘመኑን የሚዋጅ አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ መንደፍና ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥም በሥራ ላይ ያሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎች ኢኮኖሚው ለገጠመው ችግር ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው፣ መደበኛ ባልሆኑ የኢኮኖሚ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ በማዋልና ኢኮኖሚውን በማስተካከል በቀጣይ መደበኛ ወደ ሆነውና ዓለም የሚጠቀምበትን የወለድ ምጣኔ የፖሊሲ መሣሪያ ሥራ ላይ ማዋል፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የተረጋጋ የዋጋ ንረት ምጣኔና የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስፈንና ቀጣይነት ያለው ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት የሚል ትግበራ ውስጥ ተገብቷል።

ይህ ዕርምጃ በመወሰዱም የተወሰኑ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ የገንዘብ መጠን በመቀነሱ ምክንያት ወጪን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ገቢን እንዲጨምሩ አድርጓል። ይህም ማለት ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉትን የደመወዝ ጥቅማ ጥቅምና አበል መጠን እንዲቀንሱ አድርጓቸዋል። 

በሌላ በኩል ድርጅቶች የገጠማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍና ገቢያቸውን  ለማሳደግ ምርቶች ላይ ዋጋ በመጨመራቸው ምክንያት ይወርዳል ተብሎ የተጠበቀው የዋጋ ንረት እስካሁን ሊወርድ ባይችልም፣ እስከ ታኅሳስ ወር 2016  ዓ.ም. በታየው አኃዝ መሠረት ባለበት እንደቀጠለ ነው። 

ይህ  የዋጋ  ንረት ሊወርድ  የሚችለው ደግሞ ገቢያቸው የሚቀንሰው ሸማቾች ምክንያታዊ (Rational Consumer) ሲሆኑና አምራቾች ምርታቸው ላይ ዋጋ ጨምረው ለሽያጭ ቢያቀርቡ ገዥ እንደማያገኙ ተገንዝበው፣ ገቢያቸውን ለመጨመር የግድ ምርታቸውን በመጨመርና በተመጣጣኝ ዋጋ ሸጠው ገቢያቸውን ማሳደግ ሲወስኑ ነው።  በሌላ  በኩል የቋሚ ንብረትና  የትልልቅ ዕቃዎች ዋጋ  መውረድ ላይ ከፍተኛ ትኩረትና ክትትል መደረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ንብረቶች የያዙት ዋጋ አርቴፊሻል በመሆኑ ድንገት ናድ ካለ የአገሪቷን ኢኮናሚ ይዞ ስለሚሄድ ትልቅ ጥንቃቄና ክትትል ሊደረግ ይገባል። 

የዋጋ ንረት ቅነሳ በሚደረግበት ጊዜ ትኩረትና ክትትል ከሚደረግባቸው ውስጥ የባንኮች ጤናማነት፣ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር፣ የሠራተኛ ክፍያ ዋጋ መቀነስና ሌሎችም ናቸው። እነዚህ ሁሉ ሥራ ተከናውነው በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. ስምንት በመቶ የተረጋጋ የዋጋ ንረትንና የውጭ ምንዛሪ የማስፈኑ ዕቅድ ከተሳካ፣ ዓለም ወደ የጠቀምበትና ዘመናዊ ወደ ሆነው የወለድ ምጣኔ የፖሊሲ መሣሪያ ወደ መጠቀሙ በመሄድ ኢኮኖሚያችንን እናሳድጋለን የሚለው ሐሳብ ጥሩ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን የሚመጥናትን ዕድገት ላያረጋግጥ ይችላል የሚል ሐሳብ አለኝ።

ምክንያቱም ምንም እንኳን ያደጉ አገሮች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት በዋናነት ኢኮኖሚያቸውን የተቆጣጠሩበት መሣሪያ የወለድ ምጣኔ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያን ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ግራፋቸው (Economic Growth Graph) ከፍና ዝቅ የሚል፣ (Boom and Bust) ሁልጊዜ ውድቀትና የውድቀት ሥጋት የበዛበት ኢኮኖሚ ነው የሚያሳየው። ከዚህም  ባለፈ  አውሮፓና አሜሪካ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ የገጠማቸውን የዋጋ ንረትን  ለማውረድ እየተጠቀሙበት ያለው የወለድ ምጣኔ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ ብዙ ሲያታግላቸው እያየን ነው።

ስለዚህ በአገራችን ዲዛይን የሆነውን አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ  በመጠቀም  ያለምንም ችግር ቀጣይነትና ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል አቅም አለን። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ኢትዮጵያ ጠንክራ ከሠራች በ40 ዓመታት ውስጥ አሁን ቻይና የደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ላይ እንደምትደርስ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚክስ ምሁሩ ጀፍሪ ሳክስ (ፕሮፌሰር)፣ (Jeffrey David Sachs is an American Economist and Public Policy Analyst)  አዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም  በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ላይ መስክረዋል። 

ነገር ግን እንደ እኔ ዕይታ  ኢትዮጵያ ጠንክራ ከሠራች  አሁን  ቻይና የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ  40 ዓመታት ይፈጅባታል የሚለው ሐሳብ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ተቀባይነት ቢኖረውም፣ ነባራዊ ሁኔታውን ቀይሮ ኢትዮጵያ አሁን ቻይና የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ላይ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መድረስ ይቻላል። ይህን ስል ከባድ ሊመስል ይችላል ነገር ግን አስተውለን ካየነው በጣም ቀላል ነው።

እስኪ እንዴት እንደሚቀል እንመልከት፡፡ የቻይና የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ እ.ኤ.አ. በ2022 12,720 ዶላር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ደግሞ 1,028 ዶላር ነው።  ቻይና አሁን ያለችበት የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰችው ኢኮኖሚዋን በየሰባት  ዓመቱ  በእጥፍ እያሳደገች እንደሆነ ፕሮፌሰር ጀፍሪ ሳክስ በሳይንስ ሙዚየም ባደረጉት ንግግር ተናግረዋል። በዚያ ባልሠለጠነ ጊዜ ቻይና በየሰባት ዓመቱ ኢኮኖሚዋን በእጥፍ ካሳደገች አሁን በሠለጠነበት ጊዜ ኢትዮጵያ በየሦስት ዓመቱ ኢኮኖሚዋን በእጥፍ ማሳደግ ትችላለች። ይህን ካደረገች በየትኛውም መመዘኛ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ 12,720 ዶላር አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በማስመዝገብ፣ ቻይና  እ.ኤ.አ. በ2022 የነበረችበት የኢኮኖሚ ደረጃ  ላይ መድረስ ትችላለች።

ኢትዮጵያ የድህነት ካባዋን አውልቃ የሰላም፣ የዕድገትና የብልፅግና ካባዋን መልበስ የምትጀምረው በአንድ ቀን የኢኮኖሚ ዕድገት አዋጅ ስለሚሆን ከአደጉ አገሮች ተርታ ለመሠለፍ ደግሞ አሥር ዓመት አይፈጅባትም። ይህን ለማድረግ ደግሞ የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የተረጋጋ የዋጋ ንረት ምጣኔን ሁለት በመቶ ማድረስና የውጭ ምንዛሪ ዋጋን ማስፈን ያስፈልጋል። 

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ንረት በጣም የተዳከመና ነካ ቢያደርጉት ፍንግል ብሎ የፈለጉት ቁጥር ላይ ማረፍ የሚችል ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ  የውጭ አገር ገንዘብ ትመና ቀርቶ ለገበያ ቢለቀቅ አሁን ያለው የውጭ አገር  ገንዘብ ዋጋ በእጅጉ ይቀንሳል። ሌላው የሥራ አጥ ቁጥርን ዝቅተኛው ቁጥር ላይ ማድረስና ከዚያ ውጭ ያለውን የሥራ አጥነት ክፍያ መክፈል (Applying Uniform Basic Income – UBI) ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ይህም የሚሆነው በተዓምር ሳይሆን በአዲስ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ መሣሪያ ጠንክሮ በመሥራት ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከ16 ዓመታት በላይ በኢኮኖሚና በባንክ ባለሙያነት ያገለገሉ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getaneh25@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...