Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ዕጦት እስከ መቼ ፈተና ሆኖ ይቀጥላል?

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ዕጦት እስከ መቼ ፈተና ሆኖ ይቀጥላል?

ቀን:

በአውግቸው ኪዳኑ

ይህንን ርዕስ ይዤ ስነሳ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ያለፈችባቸው ውጣ ውረዶችና አሁን እየገጠሟት ያሉ ፈተናዎች ሁላችንንም ያሳስቡናል ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በብዝኃነት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ቁጥርም በአፍሪካ ትልቅና ሰፊ የምትባል አገር ነች፡፡ ከ80 የማያንሱ የየራሳቸው ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና በጥቂት ዓመታት ውስጥ 100 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያላት አገር መሆኗን ያስታውሷል፡፡ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የዓለም ጭራ ደሃ አገር፣ በጦርነትና በኋላ ቀርነት የኖረች ምሥራቅ አፍሪካዊት ቀደምት ምድር የሚል ስያሜ ተሰጥቷት ቢቆይም፣ አሁን አሁን በሌላ ገጽታ ስሟ እየተነሳ ይገኛል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ የፈጣን ልማትና የተከታታይ ዕድገት ተምሳሌት (በተለይ ከምዕተ ዓመቱ ግብ አኳያ)፣ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ዋነኛ አሳታፊ፣ በአገር ውስጥም አንፃራዊ ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ ያለባት ተደርጋ እየተወሰደች ነው፡፡ በአትሌቲክሱ መስክ ስሟ ተደጋግሞ መጠራቱ፣ ቡናና አበባን የመሰሉ ልዩ የኤክስፖርት ምርቶች መጠናከርና የታሪክና የብዝኃነት ገጽታዋ የቱሪስት መስህብ የመሆናቸው ዕድልም፣ ገጽታዋን በመቀየር ረገድ ዓይነተኛ ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡

ለእነዚህና ሌሎች ተስፋ ሰጪ ስኬቶች የዓለም ነባራዊ ሁኔታና የአጋር አካላት መብዛት ወይም ሉዓላዊነት (Globalization) የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ብቻ አመሥግኖ ማለፍ አይቻልም፡፡ ይልቁንም ለ27 ዓመታት አገሪቱን የመራው ኢሕአዴግና በእርሱ የተመራው መንግሥት ከእነ ችግሮቹም ቢሆን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም አሠራር፣ አደረጃጀትና አመራር ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወቱ አለመጥቀስ ያስተዛዝባል፡፡ ሕዝቡ ራሱም የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥና ተስፋ ከመቁረጥ በመውጣት ያደረገው ርብርብ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ሲያበቃ ግን የኢሕአዴግና የመንግሥቱ ዋነኛ ፈተናዎች እንደነበሩ የቀጠሉት የተሟላ ዴሞክራሲንና የጠነከረ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳዮች መሆናቸወም አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ጋር የተያያዙት የግልጽነትና ተጠያቂነት መጥፋት፣ የሙስና መስፋፋት፣ የቡድንተኝነት ፈተናዎች፣ የፀረ ዴሞክራሲ ልክፍቶች ሥርዓቱን ወደ ብልሸት ከተውት አገሪቱን አተረማምሶ ለራሱም ሳይሆን ቀረ፡፡

ብዙ ጊዜ ይባል የነበረው የኢሕአዴግ አብዛኛው ነባር አመራር አባል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የታገለና ከብሔር ጭቆና ነፃ ለመውጣት የተፋለመ ብቻ ሳይሆን፣ የገዥዎችን የተዛባ አገዛዝ ለማስወገድ ዋጋ የከፈለ ነው፡፡ ስለሆነም ለታገለባቸው ጉዳዮች መስተካከልና ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ በዋናነት ዘብ መቆም ያለበት ይኼው አካል ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ አመራሩ በአብዛኛው በአፉ ከሚያነበንበው ዴሞክራሲ ጋር የማይተዋወቅ፣ ግራ ዘመም ሆኖ ማርክሲዝምን ዓላማው ቢያደርግም እንደ ዘመነ መሣፍንት ጊዜ ፊውዳሎች ያገኘውን ሁሉ የሚያግበሰብስ፣ በራሱና በወዳጆቹ ዙሪያ የተኮለኮሉ ሌቦችን የሚያጠግብ፣ ለአገር ህልውና መቀጠል ደንታ ቢስና ኃላፊነት የማይሰማው ስለነበር አገሪቱን አርክሷት ነበር ቢባል ያን ያህል የተጋነነ አይደለም፡፡

ኢሕአዴግ በሰፊው ሕዝብ የለውጥ ፍላጎት በተመራ እንቅስቃሴ ከውስጥና ከውጭ በተናበቡ ኃይሎች ፍርክስክሱ ወጥቶ ቢሰናበትም፣ አሁንም ቅሪቶቹ በብዛት ስላሉ ፀረ ዴሞክራሲያዊነቱና ቡድንተኝነቱ መስፋፋቱ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ትናንት የለውጡ ባቡር ላይ የነበሩ የአንድ ጎራ ሰዎች ዛሬ ተለያይተው መራር ሁኔታ ውስጥ የገቡት፣ የበፊቱ በሽታ እያገረሸ ኅብረቱን በመናዱ እንደሆነ ማስተባባል አይቻልም፡፡ በዚህም ምክንያት እጅ ለእጅ ተያይዞ ዴሞክራሲን ለማፅናት የተጀመረው ጉዞ ተሰነካክሎ አሳዛኝ ሁኔታ መከሰቱ ለዚህ አባባል ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡

ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን ከሚጠቀሱለት ንግግሮች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹እስካሁንስ ብዙ ንግግር፣ ውይይት፣ ቧልትና ወሬ አድርገናል፡፡ ከዚህ በኋላስ ፈጥነን ወደ ተግባር እንግባ!››፡፡ ጠንካራው ኮሙዩኒስታዊ መሪ ይህን ያለው ወዶ አይደለም፡፡ ይልቁንም ልክ አሁን እንደ አገር እንደተደቀነብን ያለ ሁሉም የአጠቃላዩን ስኬት ብቻ እያደመቀ ማውራት፣ መለፍለፍ፣ የመድረክ አንደኛና ሀቀኛ መሆን ሲበዛና በተግባር መቆራረጥ ሞዴል መሆን የሚችል ሲጠፋበት ነው፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይ በከተሞች መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ለምን አልተቻለም?›› ብሎ በድፍረት መጠይቅ ያስፈልጋል፡፡ ከፌዴራል መንግሥት የላይኛው መዋቅር አንስቶ እስከ ቀበሌ በሕዝብ ላይ የሚደርሱ በደሎችን የሚቀበልና መፍትሔ የሚፈልግ የቅሬታ ሰሚና የመልካም አስተዳደር አካል የለም፡፡ የአገልጋይነት ቁርጠኛ መንፈስ አለ ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ የለም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሕዝብ መረጃም ሆነ አገልግሎት የመጠየቅ መብትና ሥልጣን እንዳለው ተረድቶ የሚተገብረው ስንቱ ነው ቢባል፣ ግፋ ቢል ከአንድ እጅ ጣት የሚበልጡ ሰዎችን መጥቀስ አይቻልም፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት በቢፒአር፣ በቢኤስሲ ወይም በሲቪል ሰርቪስና በፍትሕ ማሻሻያ ሥራዎች በከፍተኛ በጀትና ድካም ሰፋፊ ጥረቶች ቢደረጉም መና ቀርተዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ መሻሻል የታየባቸው ተቋማት የነበሩ ቢሆንም፣ ጅምራቸው መሠረቱ የጠበቀ ስላልነበረ እንዳይሆኑ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በብዙዎቹ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የሚስተዋለው ደንታ ቢስነት፣ አቅመ ቢስነት፣ ሌብነት፣ ዝርክርክነትና የመሳሰሉ ብልሹ አሠራሮች የሚናገሩት ይህንን እውነታ ነው፡፡

ብዙዎቹ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የተጻፉ መፈክሮች፣ የተደረጉ ስብሰባዎችና ንግግሮች፣ ሥልጠናዎችና መሰል እንቅስቃሴዎች ያን ያህል ውጤታቸው የሚያኩራራ አይደለም፡፡ የፈሰሰውን በጀትም ሆነ ተሰጥቷል የተባለውን ትኩረትና ድካም የሚመጥን የሕዝብ እርካታም አልተገኘም፡፡ ይህ ሲባል ከመሬት በመነሳትና በመላምት አይደለም፡፡ ተጨባጩ እውነት ስለሚናገር ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ በአካል ተገኝቶ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ስለኢትዮጵያ መንግሥታዊ ተቋማት ሰፊ ጥናት ያደረጉና በአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ከዓለም ባንክ ጋር የሠሩ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ፣ ‹‹የእኛ አገር የመልካም አስተዳደር ዋነኛ ችግር የአብዛኛው ሲቪል ሰርቫንትም ሆነ አመራር አባል ቁርጠኝነት ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ከሁሉ በላይ በቅንነትና በታማኝነት ሕዝብ ማገልገል የሚሰጠውን ክብርና ሞራላዊ ልዕልና ለማጣጣም የሚመኘው ሰው ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው…›› በማለት በስብሰባ ላይ የተናገሩትን አልረሳውም፡፡ እኚህ ባለሙያ እንደ ሐርቫርድና ሚችጋን ዩኑቨርሲቲዎች ተምረው ያስተማሩ መሆናቸውን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡

ምሁሩ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መንስዔ ነው የሚሉት በማኅበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት የበላይነት ይዞ የኖረው አመለካከት ‹‹ሲሾም ያልበላ…›› በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም በታማኝነት ሠርቶና በቅንነት አገልግሎ ሕይወቱን ከሚቀይረው ይልቅ ተብለጥልጦና በአቋራጭ የሚበለፅግና የሚሾም በመብዛቱ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ በስፋት የአድርባይነት፣ የመሸካከምና የእከክልኝ ልከክልህ እየበረታ እንደመጣ በየመድረኩ ይደመጣል፡፡ ግን አመርቂ የእርምት ዕርምጃ ሊወሰድ አልቻለም፡፡

ተሿሚዎችም ሆኑ ተቀጣሪዎች የፖለቲካ እምነትና የጠራ አመለካከት መያዛቸው ተገቢ ቢሆንም፣ ዕውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው ግን የግድ መሆን አለበት፡፡ ዓለምም ሆነ አገሪቱ በፈጣን የለውጥ ምኅዳር ውስጥ መግባታቸው እየታወቀ፣ በትናንት በሬ ለማረስ መመኘት የሚሆን አይደለም፡፡ ስለዚህ ሌኒን እንዳለው እስካሁን በተሳካውም ባልተሳካውም ጉዳይ ብዙ ተወርቷል፣ ስንት ነገር ተነግሯል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ወደ ቁርጠኛ ተግባር መግባት ግድ ይላል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከአንድም በላይ በሆነ ትውልድ ቅብብሎሽ ሊገነባ እንደሚችል ብዙ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም ቢሆን ያለና የሚኖር ነው፡፡ ይህን ተጨባጭ ሀቅ በሚታሰበው ጊዜ ዕውን ለማድረግ ግን ከወዲሁ ጠንክሮ መሥራት ግድ ይላል፡፡

በእኛ አገር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አመቺ ባይሆንም ከእነ ችግሮቹም ቢሆን ሕገ መንግሥት መኖሩ አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ግን ከላይና ከታች የመንግሥት መዋቅር አንፃር ሲመዘን፣ የሁለት መንግሥታት ሕገ መንግሥት መምሰሉ በይፋ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ለዚህ እንደ አብነት የሚጠቀሰው በአገሪቱ የመደራጀትና ያመኑበትን የፖለቲካ እምነት የማራመድ መብት ጉዳይ ነው፡፡ በላይኛው የመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድን ይከተል እንጂ ኃጢያት አይደለም፡፡ በአንፃሩም ቢሆን ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የመነጋገር ዕድልም አለው፡፡ ወደ ታችኛው እርከን እየተወረደ ሲሄድ ግን ሁኔታው ይቀየራል፡፡ ‹‹በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ (ተቃዋሚ) ሥር ተደራጅቶ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለመተግበር መሞከር በጠላትነት ያስፈርጃል…›› የሚለው ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡

በአንድ ወቅት፣ ‹‹እንደ አገር የሕግ የበላይነት እያደገ መሄድ ሲገባው፣ አሁንም የአስፈጻሚው ጫና የሕግ ተርጓሚው ላይ በመኖሩ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ጥቅምን በማስከበር ረገድ ተከራክሮ መርታት እየከበደ ነው…›› ያሉኝ ግለሰብ ዛሬ ገዥው ፓርቲን ተጠግተው ከሥልጣኑም ከጥቅሙም ተቋዳሽ ሆነው በዝምታ ውስጥ ሲኖሩ ግርም ይለኛል፡፡ እሳቸው ሥርዓቱ ተስማምቷቸው በመኖራቸው እኔ እንደ ጥፋት አላየውም፡፡ ነገር ግን የዛሬው ከትናንት ካልተሻለ ወይም ከባሰበት የእሳቸው የትናንት እሮሮና የአገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄ እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡

ሌላው የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሸራፋ እንዲሆን እያደረገው ያለ እውነት በክልሎች በተለይ በወረዳዎች ያለው የፖለቲካ አመራር ‹‹ሥልጣን/ጥቅም ወይም ሞት›› አስተሳሰብ ነው፡፡ ከማዕከል ራቅ እየተባለ ወደ ታች ሲወረድ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለዴሞክራሲና ስለሰብዓዊ መብቶች መነጋገር እንደ ወንጀል መታየቱ ድንቅ ይላል፡፡ ይህ  ባህሪ ማዕከል ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ጭምር መንፀባረቁ ነው የታቹን እንዲህ ዓይነቱ አረንቋ ውስጥ የገባው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ የሠፈሩ መብቶችን ማንም መንጠቅ እንደማይችል ነው፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ችግር የሚፈጥሩ ሲያጋጥሙ የማረቅ ኃላፊነት የማን ነው? ይኼ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የሰላማችን መጥፋት ያሳስበናል፡፡ ልማታችን በጋራ ዕሳቤ ካልተከናወነ ፈተና ነው፡፡ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ  ብዙ ሥራ ይቀረናል፡፡ መንግሥትና የላይኛው አመራር ‹‹ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም፣ ዴሞክራሲም እንደዚያው ስለሆነ በሒደት እንጂ በአንድ ጊዜ አይመጣም›› ከሚለው አስተሳሰብ ውስጥ ይውጣ፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊጣሱ እንደማይገባ መግባባት ይኑር፡፡

ይሁንና ከላይ እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅርም ሆነ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባለው መንግሥታዊ እርከንና ማኅበረሰብ ውስጥ ጉድለቶችን መፈተሽ ይገባል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ፣ በፀጥታ ኃይሎች መደብደብና አለፍ ሲልም በምርመራ ወቅት ጫና መፍጠር እንዳለ ይሰማል፡፡ ይህ ችግር በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች መፈጸሙንም በአንድ ወቅት ፍርድ ቤት በችሎት ላይ ተጠርጣሪዎች አቤቱታ ሲያሰሙ አዳምጠናል፡፡

በዳኝነት አካሉ፣ በፖሊስና በትራፊክ ፖሊስ የምርመራና ውሳኔ ሒደቶች ላይ ሙስና፣ መድልኦና የተዛባ ፍርድ አለመስጠቱ እንዴት እየተረጋገጠ ነው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ ዜጎች በየደረሱበት የአገልግሎት መስጫ ቦታ ጉቦ በግላጭ ሲጠየቁና ተጠያቂነት ሲጠፋ፣ ስለአገረ መንግሥት ግንባታ መግባባት አይቻልም፡፡ መጠየቅ ያለባቸው ዝም ተብለው ንፁኃን ሲጎዱ ችላ ብሎ ማየት ያደረሰው ጥፋት ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡

ይህንቀ ጥያቄ እንዳነሳ የሚያስገድደኝ የአንዳንድ ወገኖቻችን ገቢ እንደማናውቀው ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትልልቅ ሆቴሎች ባለቤቶች፣ የበርካታ ቪላዎችና የሪል ስቴት አፓርታማ ቤቶች ባለንብረቶች፣ የመኪና መሸጫዎች፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ቱጃሮች ያደረጋቸው ምንድነው ሲባል ነው፡፡ በመንግሥት ሹመትና ‹‹ጥቅም›› የሚያስገኝ ኃላፊነት ከአሥር ዓመታት ያነሰ አገልግሎት ያላቸው ባለሕንፃዎች፣ ባለግዙፍ ቪላ ባለቤቶች፣ የተሽከርካሪዎችና ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ባለቤቶች አልተፈጠሩምን? ሌላው ቀርቶ በዝምድና፣ በአገር ልጅነትና በቅርበት ስም ስንቶች ሕገወጥ ደላሎችና ጉዳይ ገዳይ ሆነዋል? ይኼ ከሕዝቡ ያልተሰወረ ሀቅ ቢሆንም የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥርዓቱ መዳከም ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› የሚል እንዲበዛ አድርጎታል፡፡

ከዓመታት በፊት የሀብት የማሳወቅና ይፋ የማድረግ ጉዳይ ብዙ ቢባልበትም፣ ለመባል ከዘለለ ያስገኘው ፋይዳ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ የመንግሥት ሹማምንትም ሆኑ ሠራተኞች ሀብት ምዝገባ ጉዳይ ዝም ብለው በለሆሳስ የሚያልፉት እንጂ፣ ያን ያህል የሚያነጋግር አጀንዳ የመፍጠር አቅም እንደሌለው በሚገባ የታየ ስለሆነ አልፈዋለሁ፡፡ ነገር ግን በራስ፣ በቤተሰብና፣ በዘመድ አዝማድ በአንድ ጀንበር እየተፈጠረ ያለ ሀብት ሲታሰብ አብዮት ማስነሳት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ግን አምናለሁ፡፡

እንግዲህ የዴሞክራሲ ሥርዓት መደብዘዝን እንደ ጉዳት መቁጠር የሚያስፈልገው፣ የመልካም አስተዳደር ግንባታውንም ስለሚሰነክለው ነው፡፡ በሠለጠነ ማኀበረሰብ ግንባታም ሆነ በዴሞክራሲ አስተሳሰብ ማነፅና የቀደመውን ኋላቀር አስተሳሰብ የመናድ ተግባር ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያክሉ ጠንካራ መልሶች የሉም፡፡ ለእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች ዘብ የማይቆም መንግሥት ደግሞ ሄዶ ሄዶ የወደቁትን ዓይነት ቀን ነው የሚጠብቀው፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም ፊት አንገቷን የሚያስደፋት ይህ ችግር ስለሆነ እባካችሁ እንባባል፡፡ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታና ለዜጎች ነፃነት ደጋግመን ማሰብ ያስፈልጋል ብለን በጋራ ካልተነሳን ማንም ዞር ብሎ አያየንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...