Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በአጋጣሚ ከአገር ወጣ አድርጎኝ የነበረ ጉዳይ ካላሰብኩት ሰው ጋር አገናኝቶኝ የተነጋገርነውን ወግ ላካፍላችሁ፡፡ በቅርቡ የቱርክ የቢዝነስ ከተማ ኢስታንቡል ሄጄ ነበር፡፡ እጅግ በጣም ውብ የሆነችው አውሮፓን ከእስያ ጋር የምታገናኝ ታሪካዊ ከተማ እንድሄድ ያደረገኝ የሥራ ጉዳይ ቢሆንም፣ የኦቶማኖች ኃያልነት መነሻ የነበረችውን ከተማ እንደ ቱሪስት ተዟዙሮ መጎብኝትም አንዱ ዓላማዬ ነበር፡፡ በቆይታዬ ወቅት አንድ ቀን ከተማውን በባቡር ከወዲህና ከወዲያ ሳካልል ቆይቼ፣ ‹ቱሪስት ሴንተር› የሚባለው የከተማዋ ዕምብርት ደረስኩ፡፡ በእርግጥም ኢስታንቡል እ.ኤ.አ. በ2010 በአውሮፓ ኅብረት የባህል ከተማ ተብላ መሰየሟና ከዚያ ወዲህም በሚገርም ዕድገት ላይ መገኘቷን ይህ ሥፍራ በደንብ ያሳብቃል፡፡

እጅግ በጣም ዘመናዊ ከሆነው ባቡር ላይ ወርጄ አካባቢውን ስቃኝ የቱሪስት ማዕበል ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ በግሉ ከሚንቀሳቀሰው ጀምሮ በቡድን የሚተሙትን ለሚያይ የአገራችን የጥምቀት ታቦት አጃቢ ይመስላሉ፡፡ የቱሪስቶችን ቁጥር በዚያ መጠን አይቼ ስለማላውቅ ‹ወይ አገሬ› አልኩ፡፡ ስንትና ስንት ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሮአዊና መልክዓ ምድራዊ ሀብቶችን ታቅፋ የቱሪስት ያለህ ትላለች፡፡ እዚያ ግን የቱሪስቱ ብዛት ማዕበል ይመስላል፡፡ እኔ አንድ አፍሪካዊ የነጭ ማዕበል መሀል ቆሜ ወጪ ወራጁን ስማትር፣ ድንገት የእኔ ዓይነት የቆዳ ቀለምና ተቀራራቢ መልክ ያለው ሰው ፊቴ ገጭ ብሎ ቆመ፡፡ መጀመሪያ ደነገጥኩ፡፡ ቀጥሎ ግን ሳላውቀው ደስ አለኝ፡፡ በባዕድ አገር አምሳያን ማግኘት ደስ ይላል፡፡

ይኼ የሐበሻ ገጽታ ያለው ሰው፣ ‹‹ወንድሜ ኢትዮጵያዊ ትመስለኛለህ…›› ሲልማ በደስታ ሰከርኩ፡፡ እጁን ለሰላምታ ዘርግቶልኝ፣ ‹‹እዮብ እባላለሁ፣ አንተንስ ማን ልበል?›› ሲለኝ ቅልጥፍናውና ተግባቢነቱ አስደሰተኝ፡፡ የበለጠ የገረመኝ ግን የስማችን ተመሳሳይነት ነው፡፡ ‹‹እኔም እዮብ እባላለሁ…›› እያልኩ ስተዋወቀው፣ ‹‹ኦው እንዴት ደስ ይላል? ሁለት እዮቦችን ኢስታንቡል ላይ ሳይታሰብ ያገናኘ አምላክ የተመሠገነ ይሁን…›› እያለ በሚያስገመግም ድምፅ ሳቀ፡፡ እኔም በሳቅ አጀብኩት፡፡

በአጋጣሚ ያገኘሁት እዮብ የሚባለውን ሞክሼዬን ሻይ ቡና እንበል ብዬው እዚያው አካባቢ ከሚገኙ ውብ ካፌዎች ወደ አንዱ መራሁት፡፡ ሁለታችንም ተርኪሽ ኮፊ (የቱርክ ቡና) አዘን ወግ ጀመርን፡፡ ይኼ ገራገርና ተጫዋች መሰል ሰው፣ ‹‹ወንድሜ እዮብ ከአዲስ አበባ ነው የመጣኸው? ወይስ የት ነው የምትኖረው?›› በማለት ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ ከአዲስ አበባ መምጣቴንና አመጣጤም ለሥራ እንደሆነ ነገርኩት፡፡ አጥብቆ ጠያቂው እዮብ፣ ‹‹ምን ዓይነት ሥራ?›› በማለት በመነጽሩ ውስጥ አጨንቁሮ አየኝ፡፡ የኢንቨስትመንት አማካሪ መሆኔንና ከቱርክ ኢንቨስተሮች ጋር እንደምሠራ ነገርኩት፡፡ መነጽሩን ዝቅ አድርጎ ዓይኖቹን በልጠጥ አድርጎ እያየኝ፣ ‹‹ዋው ዩ አር ፍሮም ዘ አፐር ክላስ፡፡ እኔ እኮ እዚህ ሥራ ፍለጋ የመጣህ የእኔ ቢጤ መስለኸኝ?›› ብሎኝ ተከዘ፡፡ ማን ይሆን ይህ ሰው?

ትካዜውን ከጨረሰ በኋላ፣ ‹‹ሰማህ ወንድሜ እዮብ፡፡ እኔ ኤርትራዊ ነኝ፣ በሙያዬም የሕክምና ዶክተር ነኝ፡፡ እዚህ የመጣሁት ሥራ ፍለጋ ነበር፡፡ በሙያዬ ማንም የሚፈልገኝ የለም፡፡ በሰዎች ድጋፍ ለዕለት እንጀራ ያህል እንቀሳቀሳለሁ፡፡ በቅርቡ ግን ቦትስዋና ለመሄድ ዝግጅት እያደረግኩ ነው፡፡ በሙያዬ እንደሚቀበሉኝ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ፡፡ እኔና መሰል የአገሬ ሰዎች በአገራችን በነፃነት መሥራት አይደለም፣ ያለው ሁኔታ በጣም እያስጠላን በብዛት ተሰደናል፡፡ በስደት ደግሞ መከራ እያየን ነው…›› አለኝ፡፡ እሱ እንደሚለው ኤርትራ በዚህ ዘመን በአፍሪካ ተመራጭ አገር መሆን ሲገባት ተገልላ የምትኖር ባይተዋር ሆናለች፡፡ ትውልዱም ተስፋ ቆርጧል፡፡

‹‹ወንድሜ እዮብ አይዞህ ጊዜ ሲለዋወጥ ሁሉም ነገር ያልፋል…›› በማለት ወሬውን እንዲቀጥል ለኮስ አደረግኩት፡፡ ‹‹አየህ? ሕዝባዊ ግንባር [ሻዕቢያ] ኤርትራን ተቆጣጥሮ እንደ አገር መኖር ስንጀምር የተገባው ቃል ይኼ አልነበረም፡፡ ኤርትራ ከዋነኞቹ የእስያ አገሮች መካከል አንዷን [ሲንጋፖር] እንደምትመስል፣ ለነፃነት የተከፈለው መስዋዕትነት አገሪቱን ወደ ገነትነት እንደሚያሸጋግራት ነበር፡፡ አንዴ ከሱዳን፣ ሌላ ጊዜ ከየመን፣ ከዚያ ከኢትዮጵያ፣ በኋላም ከጂቡቲ ጋር፣ አሁን ደግሞ ከማን ጋር እንደሚሆን ባይገባኝም እየተዋጋን ከጫካ አስተሳሰብ መውጣት አቃተን፡፡ እነ ኢሳያስ ፓርላማ የሌለው አገር እየመሩ መሳቂያ አደረጉን…›› እያለ በሐሳብ ጭልጥ አለ፡፡

‹‹እኛም ብንሆን እኮ አሁን ገና ነው ቀና እያልን ያለነው፡፡ ምርጫ ብናካሂድም፣ ፓርላማ ቢኖረንም፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ቢኖሩም፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት አለ ቢባልም ብዙ ይቀረናል፡፡ በእርግጥ በአገራችን ጉዳይ ውስን መግባባት ቢኖረንም፣ በበርካታ ጉዳዮች በሐሳብ እየተለያየን ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት አልዳበረም፡፡ ልዩነትን ከማቻቻል ይልቅ ጥላቻ፣ እርስ በርስ መገዳደል ይቀናናል…›› እያልኩ ስናገር ኤርትራዊው እዮብ አቋረጠኝ፡፡ ‹‹ወንድሜ እናንተ ጀምራችሁታል፡፡ እንደምትቀጥሉበት ተስፋ አድርግ፡፡ አሁን በየቦታው የሚሰማው ግጭት ቆሞ ዴሞክራሲ ቀስ በቀስ እያለ መስረፁ አይቀርም፡፡ እኛና እናንተ አንድ አይደለንም፡፡ እኛ እኮ እስር ቤት ውስጥ ነው ያለነው…›› አለኝ፡፡

‹‹ለምሳሌ  ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት መንገዱን ተያይዛዋለች፡፡ ሕዝቡ ወደ ሥራ እየገባ ነው፡፡ ስሟ ከችግር ጋር ይነሳ የነበረች አገር አሁን በአፍሪካ ተጠቃሽ መሆኗ ቀላል አይደለም፡፡ በፖለቲካው መስክ መግባባት አለመኖሩ በጤናማ መንገድ ከተያዘ ችግር የለውም፡፡ ወደ ግጭት የሚያስገቡ አለመግባባቶችን መቀነስ ተገቢ ነው፡፡ ‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል› እንደሚባለው ሁሉም ችግር መስተካከሉ አይቀርም፡፡ ልዩነቶችን በጠመንጃ ለመፍታት የሚደረገው ባህል ቀርቶ በሠለነጠ መንገድ መነጋገር ከተቻለ እርግጠኛ ነኝ ተስፋ አላችሁ፡፡ ተስፋ መቁረጥ አይገባም፡፡ ተስፋ ይዞ መቀጠል ነው ዋናው ቁም ነገር …›› አለ፡፡ አዳመጥኩት፣ በሳል ሰው ይመስላል፡፡

በመቀጠልም፣ ‹‹አየህ እናንተ ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ አካሂዳችኋል፣ ፓርላማ አላችሁ፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ሁሉም ወገን የመሰለውን አስተያየት ይሰጣል፡፡ ፖለቲከኞች እንደ ሠለጠነ አገር ሲዘላለፉ በቴሌቪዥን አይቻለሁ፡፡ ይኼ እኮ ለእኛ ብርቅ ነው፡፡ ይኼንን ባህል አሳድጉ እንጂ አሁን ያለው ችግር በሙሉ እንደሚወገድ አትጠራጠር…›› ሲለኝ፣ ‹‹በእኛም አገር እኮ በርካታ መሰናክሎች አሉ፡፡ አንድ ዓይነት ገዥ ሐሳብ ብቻ እንዲኖር የሚፈልጉ ሞልተዋል…›› በማለት ላይ እያለሁ አሁንም አስቆመኝ፡፡ ‹‹ወንድሜ እዮብ ‹እናቱ የሞተችበትና ወንዝ የወረደችበት›› ዓይነት ጨዋታ ይቅርብህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ የዴሞክራሲ መድረኩ ተከፍቷል፡፡ በዚያ መድረክ በሥልጣኔ ለመነጋገር ብልህ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ዓይኗ ተገልጧል፡፡ በተቃራኒው ኢሳያስ የሚመራት ኤርትራ እኮ ያልተነጠፈ አልጋ ማለት ናት…›› ሲለኝ ሳቅኩ፣ ወደው አይስቁ፡፡ አንዳንዱ አጋጣሚ እንዲህ ቢያገናኝም፣ የኤርትራዊው ወንድሜ ምክር ግን ጠቃሚ መሆኑን ነጋሪም አያስፈልገውም፡፡

 (እዮብ ምትኩ፣ ከቦሌ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...