Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበፓርላማ በተፎካካሪ ፓርቲ ተይዞ የነበረው የመንግሥት ወጪ ቁጥጥር ሰብሳቢነት ለብልፅግና ተሰጠ

በፓርላማ በተፎካካሪ ፓርቲ ተይዞ የነበረው የመንግሥት ወጪ ቁጥጥር ሰብሳቢነት ለብልፅግና ተሰጠ

ቀን:

  • የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለ መከሰስ መብት ሲነሳ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በዋስ ከእስር ተለቀዋል

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለረዥም ዓመታት በምርጫ አሸንፈው ፓርላማውን ለተቀላቀሉ ተፎካካሪና አጋር የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመስጠት ሲሠራበት የነበረውን፣ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ለብልፅግና ፓርቲ ተሰጠ፡፡

በ2013 ዓ.ም. የተካሄደውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ምክር ቤቱን ከተቀላቀሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ለሁለት ዓመታት ሲመራ የነበረው ቋሚ ኮሚቴ፣ አቶ ክርስቲያን ያለ መከሰስ መብታቸው በተነሳበት ዕለት ሰብሳቢነታቸው የብልፅግና ፓርቲ አባሏ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ተተክተውበታል፡፡ አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከሰባት ወራት በፊት ነበር፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለመዱና ባልተጻፉ አሠራሮች ምክንያት በኢትዮጵያ በሕግ ባይደነገግም፣ ቋሚ ኮሚቴው ከገዥው ፓርቲ ውጪ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ነው የሚመራው፡፡

- Advertisement -

ለአብነት በ2003 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ተመራጩ አቶ ግርማ ሰይፉ ነበሩ፡፡

በተመሳሳይ በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው መንግሥት የመሠረተው ኢሕአዴግ በምክር ቤቱ አሸንፎ የገባ ተፎካካሪ ፓርቲ ባለመኖሩ፣ አጋር ይባል ለነበረው የሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቋሚ ኮሚቴውን ሰብሳቢነት ሰጥቶ ነበር፡፡

ከሰሞኑ ፓርላማው የሾማቸውን የብልፅግና ተመራጭ ጉዳይን በተመለከተ የመንግሥት ዓመታዊ በጀትን ኦዲት በማድረግ በየዓመቱ ሪፖርት ይፋ ለሚያደርገው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ቅርበት ያላቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ግለሰብ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ይህ ሹመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ፣ ያልተጠበቀና በፓርላማው ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በተፎካካሪ ፓርቲዎች መመራቱ በዋነኝነት አብዛኛውን ድምፅ ያገኘ ፓርቲ ያቋቋማቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በጀት አፈጻጸም በገለልተኛ ተቆጣጣሪ ተቋም ክትትል ካልተደረገበት፣ አንድ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚኖራቸው የእርስ በርስ ክትትል በመፈራራት መካከል የሚደረግ እንደሚሆንና ውጤቱም እንደታሰበው እንደማይሆን አክለው አስረድተዋል፡፡

በተፎካካሪ ፓርቲ መያዙ እንደ አገር በአስፈጻሚውና በሕግ አውጪው መካከል ጠንካራ ቁጥጥር እንዲኖር ከማድረጉም በላይ፣ በዓለም አቀፍ የኦዲተር ተቋማት ማኅበር መካካል ኢትዮጵያ የነበራት መልካም ደረጃ ማሽቆልቆልና በፋይናንስ ተቋማት ዘንድ እምነት የሚያሳጣ ስለመሆኑ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከገዥው ፓርቲ በተጨማሪ ከአብን አምስት፣ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ አራት፣ ከጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት፣ ከቁጫ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አንድ፣ እንዲሁም ከግል ተወዳዳሪዎች ሦስት መቀመጫ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተፎካካሪዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ባሉበት ለብልፅግና ፓርቲ መስጠት፣ በቀጣይ የሚኖረውን የኦዲት ግምገማ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ፓርላማው መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው 17ኛው መደበኛ ስብሰባው በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የቀረበለትን የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለ መከሰስ መብት ይነሳልኝ ጥያቄ፣ በስብሰባው ከተገኙ 245 አባላት በሁለት ተቃውሞ፣ በሁለት ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

አቶ ክርስቲያን ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በአማራ ክልል ደጋ ዳሞት ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በመከላከያ አባላት ላይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሲሰጡ እንደነበርና የሰውና የቴክኒክ መረጃዎች መገኘታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ይህ እንቅስቃሴም ከባድ ወንጀል በመሆኑ ያለ መከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር እስከዋሉበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመታት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በምክር ቤቱ ለፌዴራል መንግሥት የተመደበን ማንኛውም በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን የሚከታተለውን ኮሚቴ በበላይነት ሲመሩ ነበር፡፡

በሁለት ዓመታት ውስጥ ቋሚ ኮሚቴውን በመሩበት ወቅት ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚቀርብላቸውን የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት መሠረት በማድረግ የመንግሥት ሀብት በአግባቡ እንዲውል በሚሰጡት የሰላ አስተያየትና ማስጠንቀቂያ የሚታወቁ ሲሆን፣ በመደበኛው የምክር ቤት ስብሰባም በሚሰጡት ጠንካራ አስተያየት የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ ይታወቃሉ፡፡

በቁጥጥር ሥር ውለው ለበርካታ ቀናት ፍርድ ቤትም ሳይቀርቡ በእስር ላይ የቆዩት ከአብን ተመርጠው የፓርላማ አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በዋስ መፈታታቸው ታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ በ17ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ምክንያት በተጓደሉ የአማካሪ ኮሚቴ አባላት ምትክ የሾመ ሲሆን፣ የአብ ተመራጭ አባል አቶ አበባው ደሳለውና የብልፅግና ተመራጭ አባል አቶ አብዱ ሐሰን የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ አባል አድርጎ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...