Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ ሕገወጦች በዜጎች ሕይወት ላይ አይቀልዱም!

ሰሞኑን አምስት መንግሥታዊ ተቋማት ማለትም የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኢትዮጵያ ፖስታና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የስኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በሥራቸው የተመሰከረላቸው ተቋማት ሲሸለሙ መልካም የሆነውን ያህል፣ ሽልማቱም የበለጠ ለመሥራት የሚያነሳሳ መሆን ይገባዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር በስንዴ ልማት ፕሮግራም ከተሸላሚዎች ተርታ የተገኘ ብቸኛ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን ተጠሪ ተቋማት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፈና የበርካታ ሽልማቶች ባለቤት በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ብቸኛው ታላቅ ደረጃ ላይ የደረሰ ተቋም ነው ቢባል የተጋነነ አይደለም፡፡ ሥራው በከፍተኛ ፉክክር የተፈተነ የላቀ ውጤት አስመዝጋቢ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ ዕድገት ላይ ሲገኝ፣ ኢትዮጵያ ፖስታ እመርታዊ ለውጥ እያሳየ ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ደግሞ ለአገር ዕድገት ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት መንግሥታዊ ተቋማት በጣም ብዙ ከሚባሉት ውስጥ ተመርጠው በአርዓያነት የስኬት ተሸላሚ ሲሆኑ፣ ሌሎችም የሚጨበጥ ሥራ አከናውነው ለስኬት ይበቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት በመዳህ ላይ ናቸው ቢባል ይቀላል፡፡ እርግጥ ነው ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ምሥጉን ሥራዎችን የሚያከናውኑ ተቋማት እየታዩ ነው፡፡ እነሱ አሳማኝ የሆነ ተግባር አከናውነው ተመራጭ የሚሆኑበት ዕድል አለ፡፡ ይሁንና የብዙዎቹ ተቋማት ጉዳይ ግን ሰፊና ጥልቅ ምርመራ ያስፈልገዋል፡፡ ተቋማቱ መሠረታዊ ለውጥ አድርገው ተመራጭ ሊሆኑ የሚችሉት ግን አሁን ባሉበት ሁኔታ አይደለም፡፡ ተቋማዊ የአደረጃጀት ሪፎርም ተደርጎባቸው ብቁ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ሠራተኞች፣ ዘመኑ ያፈራቸው ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና የመሳሰሉት ድጋፎች ያስፈልጓቸዋል፡፡ ከዘመኑ ጋር መራመድ የተሳናቸው ስለሆኑ ዜጎችን ለእንግልት እየዳረጉ ነው፡፡

ተቋማቱን አዘምኖ ከዘመኑ የዕድገት ደረጃ ጋር እኩል ለማራመድ ኃላፊነቱ የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌዴራልም ሆነ በከተማ ደረጃ በሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ፍጥነት እያሳየ ነው፡፡ የፓርኮች፣ የሪዞርቶች፣ የከተማ ማስዋቦች፣ የሙዚየምና የሌሎች ፕሮጀክቶች ፍጥነት ለሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት የዕለት ተዕለት ሥራም መዳረስ አለበት፡፡ ዜጎች በኤሌክትሪክ፣ በውኃ፣ በመንገድ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች፣ በግብርና በጉምሩክ መሥሪያ ቤቶችና በመሳሰሉት በርካታ ቅሬታዎችን ያሰማሉ፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ፣ በዞንና መሰል መንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ሰርስሮ የገባው ሙስና ዜጎችን እንደ ነቀዝ እየበላ ነው፡፡ ሕዝባዊ አገልግሎትን ለግል ጥቅም የሸጡ ሹማምንትና አጋፋሪዎቻቸው፣ መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የግል እርሻቸው አድርገዋል፡፡ እነዚህን መሸከም ከጥፋት ውጪ ልማት አይገኝም፡፡

በቅርቡ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተፈጸሙ ስላሉ ነውረኛ ድርጊቶች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ብዙ ብለዋል፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ከአየር መንገዱ በተጨማሪ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ የኤርፖርቶች ድርጅት፣ ኢሚግሬሽንና የተለያዩ የፀጥታና የደኅንነት አካላት አሉ፡፡ እንደሚታወቀው አውሮፕላን ማረፊያው እጅግ የረቀቁ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የታጠቀ ሲሆን፣ በጣም በርካታ የመቆጣጠሪያ ካሜራዎች አሉት፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ ኤርፖርት ውስጥ የመንገደኞች ሻንጣዎች ሲጠፉ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገደኞች ገንዘብ ካልከፈሉ ከጉዞአቸው ሲስተጓጎሉና አላስፈላጊ ድርጊቶች ተፈጸሙ ሲባል እንቆቅልሽ ነው፡፡ ተጎድተናል ብለው አቤቱታ የሚያሰሙ ዜጎችን አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ የአየር መንገዱንም ሆነ የኤርፖርቱን ስም ለማጠልሸት ነው በማለት ተገቢ ያልሆነ ምላሽ መስጠት ማንን ለመከላከል ነው? እንዲህ ዓይነቱ አቋምስ ማንን ይጠቅማል?  

ዘግይቶም ቢሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጣርቶ የመፍትሔ ዕርምጃ ለመውሰድ መወሰኑ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የአየር መንገዱ የበላይ የሆነው የትራንስፖርት ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት፣ የአየር መንገዱን ፈለግ ተከትለው ለመፍትሔ ፍለጋው ይረባረቡ፡፡ በሌሎች ዘርፎችም ቢሆን ተመሳሳይ የሆኑ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮችን ለመልካም ገጽታ እየተባለ ለማድበስበስ የሚደረገው ሙከራ ለትዝብት ከመዳረግ ውጪ ፋይዳ የለውም፡፡ በሥነ ምግባር ዝቅጠት ውስጥ የሚገኙ ሌቦችና ተባባሪዎቻቸው የልብ ልብ የሚሰማቸው፣ የብልሹ ተቋማትን የማይረባ ገጽታ ለመጠበቅ ሲባል በሚደረግ አጉል አዛኝነት ነው፡፡ ተቋማቱ ከገቡበት ብልሽት ውስጥ በማውጣት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት በክብር እንዲያበረክቱ የሚፈለግ ከሆነ፣ መሠረታዊ የሆነ ሪፎርም ሊካሄድባቸው ይገባል፡፡ በዕውቀታቸው፣ በልምዳቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ዜጎች እንዲመሯቸው ሲደረጉ ደግሞ ከተዘፈቁበት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት አይቸገሩም፡፡

መንግሥትን በተደጋጋሚ ለማስመዝገብ እንደተሞከረው የተቋማት ግንባታ ጉዳይ ችላ መባል የለበትም፡፡ ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እስከ ላይኛው ድረስ በሥርዓት ኃላፊነትን ለመወጣት፣ የተቋማት ግንባታ የግድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተቋማት ከዘመኑ ዕድገት ጋር ተመጣጥነው መራመድ ካልቻሉ የሕገወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ ይሆናሉ፡፡ በየቦታው ጉቦ መጠየቅ፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት መዝረፍ፣ ግብር መሰወርና ማጭበርበር፣ በኮንትሮባንድ መክበር፣ በሕገወጥ የመሬት ወረራ ሀብት ማጋበስ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ያልሆነ ካባቢ መፍጠር፣ በብሔርና በጥቅም ትስስር ብልሹ አሠራሮችን ማስፈን፣ የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር መዳፈር፣ ፍትሕን በገንዘብ መሸቀጥ፣ በአጠቃላይ ለሞራልና ለሥነ ምግባር ዝቅጠት የተጋለጠ ትውልድ መፍጠር ባህል የሆነው የተቋማት ግንባታ ጉዳይ ችላ ስለተባለ ነው፡፡ ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ ግን ሕግና ሥርዓት ስለሚኖር፣ ሕገወጦች በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ አይቀልዱም!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...