Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናፓርላማው ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድርና ዕርዳታ አፀደቀ

ፓርላማው ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድርና ዕርዳታ አፀደቀ

ቀን:

  • የምክር ቤቱ አባላት ብድርን በተመለከተ ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚ አካሉ ከዓለም ባንክና ከጣሊያን መንግሥት ጋር የተፈራረማቸውን የ678 ሚሊዮን ዶላር ብድርና የ50 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 17ኛ መደበኛ ስብሰባው ከአስፈጻሚው አካል የቀረበለትን ረቂቅ የብድርና የዕርዳታ ሰነድ ተቀብሎ፣ ለቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ሳይመራ በአንድ ንባብ በጥቂት አስተያየቶች ብቻ ነበር ያፀደቃቸው፡፡

የፀደቁት የብድር ሰነዶች ከጣሊያን መንግሥት በ30 ዓመታት የሚከፈል ለኢነርጂ ዘርፍ የሚውል የ83 ሚሊዮን ዶላር፣ ከዓለም ባንክ የልማት ማኅበር በ38 ዓመታት የሚከፈሉ ሦስት የብድር ዓይነቶች ማለትም ለኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ አካታችነት አሰጣጥ የሚውል 305 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኢትዮጵያ ንግድና ሎጂስቲክስ ፕሮጀክት የሚውል 90 ሚሊዮን ዶላርና ለኢትዮጵያ ትምህርትና ሥልጠና ማስፈጸሚያ የሚውል 200 ሚሊዮን ዶላር ናቸው፡፡

- Advertisement -

የብድር ሰነዶቹን የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ፣ ከአባላቱ መካከል የብልፅግና ፓርቲ አባል አቶ ካሚል ሸምሱ ከተለያዩ አካላት የሚመጡ ብድሮች ምን ያህል ለታለመላቸውና ለወሳኝ ጉዳዮች ይውላሉ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ብዙ ፕሮጀክቶቻችንና በአገር ውስጥ የሚከናወኑ ልማቶች ብድርን መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው፣ ለቀጣይ ለትውልድ እያሸከምነው ያለው ዕዳ እንዴት እየታየ ነው?›› ብለው፣ ከአበዳሪ አካላት ብድር ሲገኝ ካለው አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታና ትውልድን ታሳቢ በማድረግ በጥልቀት እንዲሠራ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤቱና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል አቶ አወቀ አምዛየ በበኩላቸው፣ ‹‹በአጠቃላይ ብድሮች ላይ ትንሽ የሚያሳስበኝና የሚያሠጋኝ ነገር አለ፡፡ እንደ አገርም መሥጋት አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ብድር ከወሰደ በኋላ ብድሩን መክፈል ካልቻለ ባሪያ ነው የሚሆነው፡፡ በየጊዜው በርካታ ብድሮችን እየወሰድን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በፈቃደኝነት ወደ ባርነት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ወደ ኒዮ ኮሎኒያሊዝም እየገባን ነው የሚል ሥጋት አለኝ፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ ሥጋታቸውን አሰምተዋል፡፡

አቶ አወቀ በማብራሪያቸው፣ ‹‹ብድር ሱስ ነው፣ እንደ ሐሺስ ነው፡፡ የበለጠ በወሰድነው ቁጥር የበለጠ እያሰኘን ነው የሚሄደው፡፡ እንደ ሐሺሽ ወይም እንደ መጠጥ፣ እንደ አረቄ በጨመርነው ቁጥር የበለጠ ካልጠጣን የማንረካበት ሁኔታ ውስጥ ይገባል፡፡ ብድርም እንዲሁ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምንድነው እየሆነ ያለው? ያለ ብድር መኖር አይቻልም ወይ? ከብድር አማራጭ ውጪ የራሳችንን ሀብትና አቅም ላይ ትኩረት እንሰጥም ወይ?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

‹‹ብድር እንወስዳለን የ40 ሚሊዮን ብር ቪ8 እንገዛለን፣ በነገራችን ላይ አብዛኞቹ ብድሮች ለታለመላቸው ዓላማ አይደለም የሚውሉት፡፡ ምክንያቱም በብድር የተወሰዱ ፕሮጀክቶች እያለቁ አይደለም፡፡ የመንገድ፣ የመስኖና የግድብ ፕሮጀክቶች ሲታዩ እየተጠናቀቁ አይደለም፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዴት ይመለከተዋል?›› ሲሉ አቶ አምዛየ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በቀደሙት ዘመናት በነበሩ መንግሥታት ከተወሰዱ ብድሮች ውስጥ አሥር ቢሊዮን ዶላር ያህል ዕዳ መከፈሉን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለትውልድ ምንዳ የማስተላለፍ ዕቅዱ በቁርጠኝነት እየተሠራበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሚወሰዱ የንግድ ብድሮች ባለፉት ዘመናት እንደነበሩት አሠራሮች ሁሉ አዋጭ ባልሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዳይውሉ፣ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 ብድርን አዋጭ ላልሆኑ ፕሮጀክቶች ማዋል የሚለውን ዕሳቤ ከመሠረቱ የቀየረ አሠራር መኖሩን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ አሁን የምክር ቤት አባላትን የሚያሳስብ ሳይሆን አስፈጻሚውን ሊያስመሠግን የሚያስችል ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በብድር አመላለስ ረገድ ትርጉም ያለው ሥራ ተሠርቶ አገራዊ የብድር ጫና በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱንና አገሪቱ ያለባት የውጭ ብድር ከአገራዊ ገቢ አንፃር ከ30 በመቶ በላይ የነበረው ባለፉት አራት ዓመታት በተሠራው ሥራ ወደ 17 በመቶ መውረዱን ኢዮብ (ዶ/ር) ገልጸው፣ ‹‹በዚህ ደረጃ እንዲህ አሻሽያለሁ ብሎ ሊናገር የሚችል ተወዳዳሪና ተነፃፃሪ አገር ያለ አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም የብድር አወሳሰዳችን የሚመሠገንና ለሌሎች አገሮች ትምህርት ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተጠራቀመ የውጭ ብድር ዕዳ ከ28 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...