Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሰባት ዓመታት የተቋረጠው የመድኃኒቶች ማቀዝቀዣ መጋዘን ግንባታ በዓለም ባንክ ድጋፍ መቀጠሉ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የመድኃኒቶች ማቀዝቀዣ ክምችት አቅም በሦስት ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር በማሳደግ፣ በአፍሪካ ትልቁ የመድኃኒት ማቀዝቀዣ መጋዘን ይሆናል ተብሎ የነበረውና ለሰባት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው ግንባታ፣ የዓለም ባንክ ባቀረበው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ግንባታው መቀጠሉ ታወቀ፡፡  

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት የሚያስገነባውና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ በሚገኝ ሥፍራ የሚገነባው መጋዘን፣ ግንባታው ከግሎባል ፈንድ በተገኘ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ላለፉት ሰባት ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል። 

የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሤ  የማቀዝቀዣ መጋዘኑ፣ ግንባታ ተቋርጦ ስለቆየበት ሁኔታ ለሪፖርተር ሲያስረዱ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም በግሎባል ፈንድ ድጋፍ የሕንፃው የመጀመሪያ ክፍል ተሠርቶ ነበር፡፡ ሕንፃው ሲገነባ የማቀዝቀዣ ክፍልና የማቀዝቀዣ ክፍል ማስተዳደር ሥራ የሚያከናውኑ ቢሮዎችን እንዲይዝ ታስቦ ነበር። የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ ጨረታ ሲወጣ የሕንፃውን አፅም (Skeleton) ብቻ መገንባት ነበር ዕቅዱ። እሱ ከተገነባ በኋላ በጀትም አልተገኘም፣ የተደረገው ጥረትም አጥጋቢ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ለሰባት ዓመታት የቆየው፤›› ብለዋል። 

እንደ እሳቸው ገለጻ የዓለም ባንክ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በራሱ በሚከተለው  የጨረታ ሒደት አሠራር ተመርጦ፣ የሕንፃውን የመጀመሪያውን ክፍል ግንባታ በአንድ መቶ ሚሊዮን ብር ያከናወነው ሳኒተ ማርያም የተባለ ሥራ ተቋራጭ ነው ተብሏል። የግንባታ ተቋራጭ ጨረታው ከሁለት ዓመታት በፊት ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበር በጤና ሚኒስቴር በኩል ይፋ የተደረገው። 

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የማቀዝቀዣ መጋዘኑ ግንባታ በተቋረጠ ሰባተኛ ዓመት ላይ ከዓለም ባንክ ጋር በመነጋገር የማቀዝቀዣ ክፍል ግንባታውን ማስጨረስ በሚል የጨረታ ሒደቱ ዓምና ነበር የተጀመረው፤›› ብለዋል። አክለውም፣ ‹‹አሁን ግንባታው ተጀምሯል፣ የሁለት ዓመት ፕሮጀክት ነው። በጣም ቢራዘም ከዚህ በኋላ በአንድ ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚያጠናቅቁ ያለን ክትትልና የግንባታ ፍጥነታቸውም ያሳያል። በዕቅዳቸው መሠረት እየሄዱ ነው፤›› ብለዋል። 

ከሰባት ዓመታት በፊት የሕንፃውን የመጀመሪያ ክፍል ግንባታ ያከናወነው ተቋራጭ፣ በወቅቱ የመጀመሪያውን ግንባታ ክፍል መጨረስ ከነበረበት ጊዜ በአንድ ዓመት አሳልፎ ማጠናቀቁ ታውቋል። 

ተቋራጩ በወቅቱ ለግንባታ ጊዜው መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ በላይ መፍጀት እንደ ምክንያት ያቀረበው፣ የተራዘመ የጨረታ ሒደትና የግንባታ ሥፍራውን ማመቻቸት የወሰደው ተጨማሪ ጊዜ ነበር ተብሏል። 

የዓለም ባንክ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንዲጠናቀቅ ዕገዛ ያደረገበት የመድኃኒት ማቀዝቀዣ መጋዘን፣ ዓለም አቀፉ ተቋም የኮቪድ-19 የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት በሚል እ.ኤ.አ. 2020 አስጀምሮት እስከ 2025 መጨረሻ ድረስ ቆይታ እንደሚኖረው ባሳወቀው የ495 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ በመደበለት ፕሮጀክት በኩል ይህንን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል። 

ሁለተኛ ዙር ግንባታው እየተከናወነ ስለሆነው ማቀዝቀዣ መጋዘን የክምችት አቅም አስመልክቶ አቶ ሰለሞን፣ ‹‹በአሁን ወቅት በሥራ ላይ ያለው የማቀዝቀዣ መጋዘን በተናጠል የተቀመጡ የቀዝቃዛ ማስቀመጫ ክፍልፋዮች (Cold Chain) ናቸው። ይህ ግንባታ ሲጠናቀቅ እነዚህ ክፍልፋዮችና የሕንፃው ከምድር በታች የተገነባው ክፍል ሙሉ ለሙሉ ፍሪጅ ይሆናል። ይህ ሲሆን አሁን ካለን መጠነኛ የሆነ 2,200 አካባቢ ኪዩቢክ ሜትር አቅምን ወደ አምስት ሺሕ አካባቢ ያሳድጋል፤›› ሲሉ አብራርተዋል። 

አምስት ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር አቅም ያለው የማቀዝቀዣ መጋዘን የሕይወት አድን መድኃኒቶች፣ ክትባቶች፣ የካንሰር መድኃኒቶች ማከማቻና ማቀዝቀዣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገንብቶ ሥራ ላይ ሲውል የመድኃኒቱ አቅርቦት አገልግሎትና በዘርፉ ከአፍሪካ ተቀዳሚ ያደርገዋልም ተብሏል። 

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የማቀዝቀዣ መጋዘኑ ስፋት ኢትዮጵያ ያላትን የሕዝብ ብዛትና ተያይዞም ሕዝቧ የሚያስፈልገውን መጠን ያለው ክትባት ጤናማነትና ጥራት እንደጠበቀ በማቆየት፣ በቂ የሆነ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። 

በአሁን ወቅት በአገሪቱ ያሉ የመድኃኒት ማቀዝቀዣና ማከማቻ መጋዘኖች መድኃኒቶችን በአምራቾቻቸው በተቀመጡላቸው ደረጃዎች ልክ ጠብቆ የማቆየት አቅም ምን ያህል ነው የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው አቶ ሰለሞን፣ ‹‹አሁን በሥራ ላይ ወደ አምስት የሚሆኑ የማቀዝቀዣ መጋዘኖች አሉን፣ አንዳንዴ ቅርንጫፎች ሄደን አላግባብ በእነሱ ማቀዝቀዣ ክፍሎች የምናስቀምጥበት ጊዜያት አሉ ቦታ ስለማይኖረን ይህ ሲጠናቀቅ ወደ ቅርንጫፍ የሚሄደው የሚያስፈልገው ብቻ ይሆናል ማለት ነው። በማዕከል መቀመጥ ያለበት በሙሉ ተሰብስቦ አንድ መጋዘን ውስጥ ይሆናል፡፡ መድኃኒቱን ተሽከርካሪዎች ሲጭኑም ከአንዱ ወደ አንዱ ቦታ መዟዟር አይጠበቅባቸውም፡፡ ሁሉንም ከአንድ ቦታ ይጭናሉ ማለት ነው፤›› በማለት የአቅርቦት አገልግሎቱን ዋና መሥሪያ ቤት አቅምና የአፈጻጸም ውስንነቶች አስረድተዋል። 

የመድኃኒቶችን ደኅንነት የሚያስጠብቁ ማቀዝቀዣዎችን አሠራርን በተመለከተም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹የመድኃኒት የቁጥጥር የቅዝቃዜ ልኬት (Controlled Cold Measurement) ከዋዠቀ ጉዳቱ በጣም ብዙ ነው። ስለዚህ አንድ መጋዘን ውስጥ ሲሆን በአንድ የቁጥጥር ማዕከል የምናስተዳድረው ቴክኖሎጂ ስለሚሆንና ካለንበትም ሆነን በድረ ገጽ የምንቆጣጠርበት አሠራር ስለሚኖረው፣ አጠቃላይ በቅዝቃዜ መዋዠቅ የሚመጣውን የመድኃኒት ጉዳትና ክትባትም ራሱ መቀመጥ ካለበት ቅዝቃዜ ውጪ ከሆነ ራሱ በሽታ ስለሚሆን፣ በአጭር ጊዜ ሊታይ የማይችል በማኅበረሰብ ጤና ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን ይቀንሳል፤›› ብለዋል። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች