Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንድታፀድቅና የሠራተኞች መብት እንዲከበር ተጠየቀ

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንድታፀድቅና የሠራተኞች መብት እንዲከበር ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) መንግሥት ሠራተኞችን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕጎች እንዲያፀድቅና የሠራተኞችን መብት እንዲያከብር ጥያቄ አቀረበ፡፡

ኢሰመጉ ሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት የሠራተኞች ሰብዓዊ መብቶችን አስመልክቶ ልዩ ልዩ የሕግና የተቋማት ማሻሻያዎችን ሲያደርግ ቢቆይም፣ የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) ስምምነቶችን ማፅደቅና መተግበር አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ድርጅት ከሚያወጣቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች (ILO Conventions) ውስጥ 23 ስምምነቶችን፣ ከአሥር መሠረታዊ ስምምነቶች ውስጥ ዘጠኙን፣ ከአራት የአስተዳደር ስምምነቶች ውስጥ አንዱን፣ ከ177 ቴክኒካዊ ስምምነቶች ውስጥ አሥራ ሦስቱን ስለማፅደቋ ኢሰመጉ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (4) መሠረት እነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ሆነው እንደሚቆጠሩና በኢትዮጵያ ላይ ገዥ ቢሆኑም፣ አሁንም ድረስ የሠራተኞች መብቶች በልዩ ልዩ መንገዶች መጣሳቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አስረድቷል፡፡

በተለይ በሥራ ቦታዎች ላይ የሚፈጸሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ዝቅተኛ የክፍያ ወለል ያለ መኖር፣ በተለምዶ የቤት ውስጥ ሠራተኞች በሚባሉ ወገኖች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ የስደተኛ ሠራተኞች ፍልሰትና በችግር ውስጥ የሚደረግ ስደት፣ እንዲሁም የስደተኛ ሠራተኞችን እኩል ዕድልና አያያዝን ማስተዋወቅን የሚመለከተው ድንጋጌ መጣስን አውስቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የስደተኛ ሠራተኞች ፍልሰት ያለባቸውን አገሮች የሁለትዮሽ ስምምነትን የሚያበረታታ፣ በስደት ላይ የሚገኙ ሰዎችን የሥራ ሥምሪት የሚመለከተውና በስደት ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ጥበቃ የሚያደርገውን የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነት ቁጥር 97 እንድታፀድቅ ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ በ1962 ዓ.ም. የወጣውና ሚያዝያ 21 ቀን 1964 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የዓለም የሥራ ድርጅት ቁጥር 131 ስምምነት የዝቅተኛ ክፍያ ወለል መጠንን አስመልክቶ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም እንዳላፀደቀው ኢሰመጉ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት የዝቅተኛ የክፍያ ወለል መጠን በመደንገግ ሠራተኛውን የሚጠብቅና መብቱን የሚያስከብር መሆኑን የሚያሳይ መንፈስ ያለው፣ ስምምነቱን ያፀደቁ አባል አገሮችም፣ በስምምነቱ መሠረት ዝቅተኛ የክፍያ ወለል መጠንን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በእኩልነት በማሳተፍ መደንገግ እንዳለባቸው፣ በየጊዜውም በመከለስ በአግባቡ ማስፈጸም እንዳለባቸው የሚደነግግና የማይፈጽም አካልን በወንጀል ተጠያቂ መሆን እንዳለበት በዝርዝር ተቀምጧል፡፡

ሌላውና ኢሰመጉ እንዲፀድቅ ጥያቄ ያቀረበው ሰኔ 17 ቀን 1967 ዓ.ም. የወጣውንና ኅዳር 30 ቀን 1971 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባውን የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነት ቁጥር ‹‹C143›› የሚባለውን ነው፡፡ አገሮች በሕጋዊ መንገድ በግዛታቸው ውስጥ የሚኖሩ ስደተኛ ሠራተኞችንና ቤተሰቦችን መልሶ ለማገናኘት እንደሚቻል በግልጽ የሚደነግገውን፣ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ የሁሉም ስደተኛ ሠራተኞች ሰብዓዊ መብት መከበር እንዳለበት ዕውቅና የሚሰጠውን ሕግ ነው፡፡

በተጨማሪም ሰኔ 9 ቀን 2003 ዓ.ም. የወጣውና ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነት ቁጥር 189፣ የቤት ውስጥ ሠራተኞችን ለመጠበቅ የወጣ ስምምነት ሲሆን፣ ይህንንም መንግሥት አፅድቆ ወደ ሥራ ሊያስገባው አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

ይህ ስምምነት በቤት ውስጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ያሏቸውን መብቶች፣ ከአሠሪዎች የሚጠበቁ ግዴታዎችን፣ ከመንግሥት የሚጠበቁ ኃላፊነቶችን፣ ልዩ ልዩ መለኪያዎችንና ሌሎች ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡ በተጨማሪም የሥራ ሰዓትን፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያን፣ የቀንና የሳምንት ዕረፍት ሰዓትንና የዓመት ዕረፍትን በሚመለከት የቤት ውስጥ ሠራተኞች ከመደበኛ ሠራተኞች እኩል እንደሚታዩ ስምምነቱ እንደሚደነግግ አብራርቷል፡፡

ኢሰመጉ ኢትዮጵያ አላፀደቀችውም ያለው የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነት ቁጥር 190 የሚባለው ሲሆን፣ በዚህ ስምምነት መሠረት በሥራ ዓለም ውስጥ ጥቃትንና ትንኮሳን ለማስወገድ ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ወጥቶ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባ መሆኑን ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...