Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕግ የበላይነት አለመከበርና ሌሎች ምክንያቶች ለሰላምና ለደኅንነት ፈተና መሆናቸውን የፍትሕ ሚኒስትሩ አስታወቁ

የሕግ የበላይነት አለመከበርና ሌሎች ምክንያቶች ለሰላምና ለደኅንነት ፈተና መሆናቸውን የፍትሕ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ቀን:

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ ሙስና፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች፣ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚከሰት የድርቅና የጎርፍ አደጋ፣ ለሰላምና ለደኅንነት ፈተና መሆናቸውን አስታውቁ፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ዓለም አቀፍ የልማት አጋር አካላት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጋር የአየር ንብረት ለውጥን፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ከግጭት ማግሥት በመንግሥት በኩል እየተሠሩ ያሉ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን አስመልክቶ ሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ውይይት  ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር በአስተባባሪነት የሚያዘጋጀው ከፍተኛ የጋራ መድረክ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 34 የልማት አጋር አካላትን ያካተተ ነው ተብሏል። ይህ መድረክ ከዚህ ቀደም በየሁለት ዓመቱ ይካሄድ የነበረ ቢሆንም ባለፉት አራት ዓመታት ግን ሳይካሄድ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በውይይቱ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ላለው አለመረጋጋት ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች መኖራቸውን ገልጸው ማኅበራዊ ሚዲያውም የራሱ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ 

የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ ሙስና፣ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰት የድርቅና የጎርፍ አደጋ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች በአገሪቱ ሰላምና ደኅንንነት ለማረጋገጥ እንቅፋቶች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡  

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግሥታቸው አገራዊ የምክክር መድረክ፣ የሽግግር ፍትሕ፣ እንዲሁም ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ማቋቋሙን ለዓለም አቀፍ የልማት አጋር አካላት አብራርተዋል፡፡  

መንግሥት እያካሄዳቸው ያሉ የሽግግር ፍትሕና ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሒደቶች ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን ለልማት አጋር አካላት የገለጹት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2024 አገራዊ የምክክር መድረክ ይካሄዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት፣ በኋላም በአማራ ክልል በተፈጠረውና አሁንም ድረስ በቀጠለው ጦርነት አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች የሚሰጡትን ዕርዳታ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንሱ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡  

ዓለም አቀፍ አጋሮች በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ድጋፋቸው ተቀዛቅዞ እንደነበር የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን የዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር፤›› ብለዋል።  

አቶ አህመድ ጫናዎች በነበሩበት ጊዜ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ፍሰትና የፕሮጀክቶች መቀዛቀዝ አለመታየት፣ ሁሉም የድጋፍ ሰጪ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸውን እንዳላቆሙ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

የዓለም አቀፍ የልማት አጋር አካላት ድጋፋቸውን ለማድረግ የሚያቀርቡትን ሰላም የማስፈን ቅድመ ሁኔታና በመንግሥት በኩል እየተሰጠው ያለውን ትኩረት አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አህመድ፣ መንግሥታቸው ጥያቄ አለኝ ከሚል ከየትኛውም አካል ጋር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ራሚዝ አላክባሮቫ በበኩላቸው የተዋጊዎች ትጥቅ የመፍታትና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀልን አስፈላጊነት ጠቁመው፣ ‹‹በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚከናወኑ ግጭቶችን ለማስቆም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል። 

በጤና፣ በግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ እንዲሁም በግጭት ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረጉ ድጋፎች ዙሪያ እንደ አሜሪካ መንግሥት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎች እንደማይኖሩ የገለጹት አላክባሮቫ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥን እንደማይደግፉ አክለዋል፡፡ ነገር ግን ዕርዳታዎች ተደራሽ በሚሆኑበት ወቅት ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለረዥም ጊዜ በዘለቀ ጦርነትና አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘዋ ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እንዲሁም ለመልሶ ግንባታ ቢሊዮን ዶላሮች ቢያስፈልጓትም፣ አብዛኞቹ አበዳሪ ተቋማትና ለጋሽ አካላት የፀጥታ ችግሩ ካልተስተካከለ ዕርዳታቸውን እንደማይጀምሩ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡

ምንም እንኳ በተግባር የተወሰዱ ዕርምጃዎች ባይኖሩም፣ መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር በሰላማዊ መንገድ ውይይቶችን ለማድረግና ተቋማቱ የሚያቀርቡትን ሰላም ማስፈኛ ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ዝግጁ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ ይደመጣል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...