Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሐኪሞች በመድኃኒት እጥረት ሳቢያ ማከም መቸገራቸውን ተናገሩ

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሐኪሞች በመድኃኒት እጥረት ሳቢያ ማከም መቸገራቸውን ተናገሩ

ቀን:

  • ‹‹ሆስፒታሉ ማስተማሪያ እንጂ ሙሉ በሙሉ ሕክምና የመስጠት ግዴታ የለበትም›› ጅማ ዩኒቨርሲቲ

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና መስጫ ዕቃዎችና መድኃኒቶች እጥረት በመፈጠሩ፣ ታካሚዎችን ማስተናገድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ሲሉ የሕክምና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሚሠሩ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሕክምና ባለሙያዎች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሆስፒታሉ የመድኃኒት አቅርቦትና የሕክምና መስጫ መሣሪያዎች እጥረት ምክንያት ተገቢውን ሕክምና መስጠት አልተቻለም፡፡

የጅማ ከተማ ነዋሪዎችና ከደቡብ ሱዳን ጀምሮ በጅማ ከተማ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች የሚመጡ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሚገለገሉበት የጅማ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በተለይ  ዝቅተኛ  የገቢ  ምንጭ  ያላቸው  የኅብረተሰብ  ክፍሎች ሕክምና ማግኘት አልቻሉም ብለዋል፡፡

የሕክምና ባለሙያዎቹ አክለውም ዋነኛ የችግሩ መንስዔ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው የመድኃኒት ዋጋ መወደድና ዩኒቨርሲቲው የተመደበለት በጀት አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአገር ደረጃ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እንዳይኖር ሲያደርግ ቢቆይም፣ አሁን ግን ከፍተኛ እጥረት በማጋጠሙ በሆስፒታሉ ነፃ አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ አቅም የሌላቸው ግለሰቦች ሕክምና እስኪሰጣቸው በመጠበቅና ከውጭ የሚገዙ የሕክምና ቁሳቁሶችን መግዛት ባለመቻላቸው ለሞት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡

አንዳንድ የመክፈል አቅም ያላቸው ታካሚዎች ወደ ግል ሕክምና ተቋማት በመሄድ ሕክምና እንደሚያገኙ አክለዋል፡፡

አንድ የሕክምና ባለሙያ በአንድ ቀን ሦስት አስቸኳይ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ታማሚዎች እንደገጠሟቸው በመግለጽ፣ ሁለቱ የቀዶ ጥገና መሥሪያ ቁሳቁሶችን በራሳቸው ገንዘብ ከውጭ ገዝተው በመምጣት ሕክምና አግኝተው ሕይወታቸው ሲተርፍ፣ አንደኛው ግን በሕክምና መሣሪያ አለመኖር ምክንያት መትረፍ አልቻሉም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በጣም በቅናሽ ዋጋ ማግኘት የሚቻሉ እንደ አልኮል፣ መርፌና ምላጭ የመሳሰሉ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ታካሚዎች ከሆስፒታሉ ውጭ ከሚገኙ ፋርማሲዎች እንዲገዙ በማድረግ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን፣ የሕክምና ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በተፈጠረ ችግር በጅማ ከተማና በዙሪያው ያሉ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የሚጠቀሙበት አማራጭ የመንግሥት ሆስፒታል ባለመኖሩ፣ ጅማ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ነው ሲሉ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ማስተማሪያ እንጂ እንደ አንድ የጤና ተቋም ሙሉ ለሙሉ ሕክምና የመስጠት ግዴታ ያለበት በጤና ሚኒስቴር ሥር ያለ ተቋም አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር በራሱ በጀት የሚያቋቁማቸው ሆስፒታሎች ማስፋፋት ግዴታ ያለበት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር በጀት የሚተዳደር የማስተማሪያ ሆስፒታል እንደ መሆኑ መጠን መስጠት የሚችለውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው ብለዋል፡፡

ጀማል (ዶ/ር) አክለውም ለሕክምና የሚመጡ ግለሰቦችም ቢሆኑ በክፍያ ከመታከም ይልቅ የነፃ አገልግሎት ማግኘት ስለሚፈልጉ፣ መክፈል የሚችሉ ባለሀብቶችም የሕክምና ቦታውን እንዲጨናነቅ ያደርጋሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የተፈጠረው የዋጋ ንረት በፊት የነበረው የመድኃኒት ዋጋ አሁን በእጥፍ እንዲጨምር በማድረጉ፣ እንዲሁም የሁሉም የዩኒቨርሲቲዎች በጀት 50 በመቶ እንዲቀነስ መደረጉ ለመድኃኒት ግዥ የሚሆን በጀት እጥረት እንዲከሰት አድርጎታል ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ቅሬታ የሚያቀርበው ዩኒቨርሲቲው በጤና ሚኒስቴር የተቋቋመ ሆስፒታል አድርጎ በማሰብ ሲሆን፣ የጤና ሚኒሰቴር ራሱን በመቻል የሕክምና ተቋማት ማቋቋም ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የሕክምና አገልግሎት መስጠት እየተቻለ በመድኃኒት አቅርቦት፣ በኦክስጂን እጥረትና በቂ የመንግሥት የሕክምና ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት ችግሩ እየቀጠለ ነው ሲሉ ጀማል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከሉን ዘመናዊ በማድረግ የማስፋፊያ ሥራዎች እያከናወነ ቢሆንም፣ ከአቅም በላይ ታካሚዎች በመኖራቸው የተፈጠረ ችግር ነው ብለዋል፡፡

ሪፖርተር የጤና ሚኒስቴርን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...