Wednesday, July 24, 2024

የመንገድ ኮሪደር ልማትና እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኒቫዳ ግዛት በአሜሪካ ለመናፈሻ እየተባለ የሚተከል የሳር መስክን በመከልከል የመጀመሪያዋ ግዛት መባሏን፣ ቢዝነስ ኢንሳይደር ከዘጠኝ ወራት በፊት በለቀቀው አጭር ዶክመንተሪ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ናሽናል ጂኦግራፊ ከስምንት ዓመታት በፊት በሠራው ዘጋቢ ፊልም፣ በካሊፎርኒያም ቢሆን ለምለም የሳር መስክ መናፈሻ መሥራት እየቀረ የመጣ ፋሽን ስለመሆኑ ይተርካል፡፡ በአሜሪካ በተለይ ሞቃታማ በሚባሉ ምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍሎች የሳር መናፈሻ መሥራት እየተተወ የመጣ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በእነዚህ የአገሪቱ ክፍሎች የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የከተሜነት መስፋፋት ብቻ ሳይሆን፣ ከአሥር ዓመታት በላይ በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ አስገዳጅነትና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ጭምር መሆኑን የተለያዩ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

የመንገድ ኮሪደር ልማትና እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የአሜሪካ ቱጃሮች የግል ጎልፍ ሜዳ በመገንባት ሰፊ ሔክታር መሬት ሳር ያለብሳሉ፡፡ የሌላቸው ደግሞ በቅጥር ግቢያቸው ወይም በደጃቸው ያለ መሬትን ሳር ማልበሳቸው የተለመደ ነው፡፡ የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች፣ የመንገድና የመናፈሻዎች ልማት የሚመለከታቸው ሁሉ ብዙ ቦታዎችን በሳር መሸፈን ልማዳቸው ሆኖ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ይህ ሁሉ በየቦታው መሬቱን የሳር መስክ ለማልበስ የሚደረግ ጥረት ደግሞ፣ በየቀኑ 34 ቢሊዮን ሊትር ውኃ የሚፈልግ ሥራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በአሜሪካ በአየር ንብረት ለውጥና በድርቅ ተፅዕኖ የተነሳ ይህን እያደረጉ መቀጠል አገሪቱን ለኪሳራ እንደዳረገ ይነገራል፡፡ ሳር ማብቀል ከፍተኛ የመስኖ ውኃ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ዜጎች ድርቅ የሚቋቋሙ ተክሎችን በምትኩ ለመናፈሻና ለውበት እንዲጠቀሙ ግፊትና ግዴታ መደረግ ስለመጀመሩ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየቦታው በለመለመ ሳር እንዲሸፈኑ የሚደረጉ መናፈሻዎችና የመንገድ ዳር ልማቶች ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያ ድርቅ ደጋግሞ የሚጎበኛት አገር ናት፡፡ በመስኖ ማረስ በኢትዮጵያ ቅንጦት ሲሆን የግብርናው ዘርፍ በአብዛኛው በዝናብ የውኃ ምንጭ ላይ ጥገኛ ነው ይባላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የከተሞች መስፋፋትና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በፍጥነት እየጨመረ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ እየተለወጠች ነው በምትባለዋ አዲስ አበባ ከተማ ጭምር በወር አንዴ የቧንቧ ውኃ አቅርቦት የሚያገኙ አካባቢዎች መኖራቸው የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት አገር ብዙ ውኃ የሚፈጁ የሳር መናፈሻዎችና ለምለም መስኮች ሲሠሩ ነው የሚታየው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው ቀርቶ የሠለጠኑ አገሮች ከጊዜውና ከተጨባጩ የዓለም ሁኔታ ጋር አይሄድም ብለው የተውትን የለምለም ሳር መስክ ሥራ፣ በዚህ ዘመን የምትኮርጀው ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ሁኔታው የሚጋብዝ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለወር ውኃ የሚጠባበቁ ሠፈሮች እያሉ ተገነቡ በተባሉ መናፈሻዎች ውስጥ የሳር መስኮችን ልምላሜ ለመጠበቅ ትልልቅ ውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች ተደርድረው መታየታቸው ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭር ይመስላል፡፡

ከሰሞኑ የተጀመረው ዋና ዋና የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን ተከትሎ የሚገነባውን የመንገድ ማስዋብ ሥራ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ‹‹የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት›› የሚል ስም ሰጥተውታል፡፡ ሥራው በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የተሠሩ ‹‹የሚያማምሩ የልማት ሥራዎችን ማገጣጠም›› እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ‹‹ውብ አበባ እናደርጋታለን›› ብለን በለውጡ ማግሥት ለሕዝባችን ቃል ገብተናል ሲሉ የተደመጡት ከንቲባዋ፣ ይህን እየተገበሩ ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደሆነች በመጥቀስም ከዚህ ጋር የሚመጥን ደረጃ ላይ መገኘት እንዳለባት አውስተዋል፡፡

‹‹ስታንዳርዱን የጠበቀ ገጽታ፣ ውበት፣ አገልግሎትና ፅዳት ሊኖራት ይገባል፤›› ያሉት ከንቲባዋ፣ አምስት ኮሪደሮችን ያማከለ ልማት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ግንቦት ጨረታው ወጥቶ የተጠናው የኮሪደር ልማት ከሰሞኑ ወደ ትግበራ እንደገባም ተናግረዋል፡፡ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

መንግሥት አዲሱን የኮሪደር ልማት ከማምጣቱ በፊት ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ የከተማ ማስዋብና የመናፈሻዎች ፕሮጀክቶችን ሲተገብር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከእንጦጦ መናፈሻ ጀምሮ፣ የቤተ መንግሥቱ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ የአራት ኪሎና የመስቀል አደባባይ፣ የቦሌ መንገድ፣ ከአዲስ አበባ ውጪም ሃላላ ኬላ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ወዘተ እየተባለ በየቦታው መናፈሻዎችና ማስዋቦች ሲገነቡ ቆይቷል፡፡ በአጭር ጊዜ በፍጥነት እየተገነቡ የተመረቁት እነዚህ የአካባቢ ማስዋብና መናፈሻ ፕሮጀክቶች ግን ምን ያህል የታለመውን የልማት ተጠቃሚነት ውጤት አመጡ የሚለው ጉዳይ ሙግት ይቀርብበታል፡፡

በእነዚህ የመንግሥት የልማት ሥራዎች ላይ የሚነሳው ንትርክ ማባሪያ ያለው አይመስልም፡፡ በርካታ ወገኖች እነዚህ ሥራዎች ኢትዮጵያ አሁን በምትገኝበት በግጭትና በቀውስ በተሞላ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ምን ያህል አንገብጋቢ ቢሆኑ ነው ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ መናፈሻና ከተማ የማስዋብ ጉዳይ በኢትዮጵያ ያን ያህል ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ወይ ሲሉ የሚጠይቁም አሉ፡፡

መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን እንደ ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ መንገድ፣ ኔትወርክ፣ ትራንስፖርት፣ ጤና፣ ትምህርትና የመሳሰሉትን በቅጡ ለማሟላት ኢትዮጵያ ገና ብዙ እንደሚቀራት በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ከሰሞኑ ከየክልሉ ከመጡ የሕዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ይቀርቡላቸው የነበሩ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ይሟላልን ጥያቄዎች በርካታ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

ይሁን እንጂ ለእነዚህ የሕዝብ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን፣ እንደ መድኃኒት ላሉ አንገብጋቢ ምርቶች ማሟያ የዶላር እጥረት አጋጠመ ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ ይህ በሆነበት አገር ውስጥ መናፈሻዎቹ፣ የከተማ ማስዋቢያዎቹ፣ ፓርኮቹ፣ ሙዚየሞቹና ዕድሳት የሚደረግላቸው የመንግሥት ቢሮዎች በሚያስደንቅ ፍጥነት ተገንብተው ሲጠናቀቁ ማየት ተቃርኖ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለእነዚህ መናፈሻና የማስዋብ ሥራዎች የሚሰጠው ትኩረትና የሚደረገው ክትትል፣ የችግር ጎተራ በሆነችው ኢትዮጵያ መንግሥት የሚሠራው ሌላ ሥራ ያጣ አስመስሎታል የሚሉ ትችቶችን የሚያስነሱ ሆነዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከግጭትና ከሁከት ተላቃ በማታውቀው ኢትዮጵያ የተለያዩ ጦርነቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ሦስት ክልሎችን ያዳረሰውን ውድመት ለመጠገን 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መንግሥት ካስታወቀ ከራርሟል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ለመልሶ ግንባታ ያስፈልጋል የሚለው መንግሥት ወደ አሥር ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ የጫካ ቤተ መንግሥት ግንባታ ላይ ሲረባረብ መታየቱ በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያን የፈጠረ ጉዳይ ነበር፡፡

የመንግሥት ልዩ ትኩረትን እያገኙ ያሉት የመናፈሻና የማስዋብ ፕሮጀክቶች ከሚጠይቁት ወጪና ጉልበት በተጨማሪ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራሉ ይባላል፡፡ የአዲስ አበባ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሳደግ በቂ ትኩረት ሳይሰጥ በለምለም ሳር መስክ የተዋቡ መናፈሻዎችን መሥራት የውኃ እጥረት እንደሚያባብስ የሚናገሩ አሉ፡፡ ለእነዚህ ሙዚየሞችና ፓርኮች ማስጌጫ አምፖሎች የኃይል አማራጮችን ማስፋት አስፈላጊ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ መናፈሻዎቹና ማስዋቢያዎቹ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል፣ የሚያስገኙት የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሚያስገኙት ገቢ ወጪያቸውን የመሸፈናቸው ሁኔታ፣ የሚኖራቸው አካባቢያዊ ተፅዕኖ የመሳሰሉ ጉዳዮች ፕሮጀክቶቹ ካገኙት ትኩረትና ከወጣባቸው ወጪ ጋር ተነፃፅሮ መለካት እንዳለበት የኢኮኖሚ ምሁራኑ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

ይህ ጉዳይ በሌላ መንገድም ቢሆን በፓርላማና በሌሎችም መድረኮች ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፕሮጀክቶቹ ሕዝብን በማስተባበር ወይም ከውጭ በተገኘ ዕርዳታ ነው የሚገነቡት የሚል ምላሽ ነው የተሰጠው፡፡ ፕሮጀክቶቹን ኦዲት ማድረግ ይቻላል ቢባልም ሆኖም በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት ማለቃቸው አፈጻጸማቸው ስኬታማ ነው የሚል ድምዳሜን መንግሥት ሲሰጥ ይሰማል፡፡

በቅርብ ጊዜ በተለምዶ አምቼ በሚባለው አካባቢ እስከ ጥራትና ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ሕንፃ ባለው ከመገናኛ ወደ ኢምፔሪያል አደባባይ በሚወስደው መንገድ ዳርቻ፣ የማስዋብ ሥራው ባለፉት ወራት ሲካሄድ ይታይ ነበር፡፡ ይህ የመንገድ ዳር ማስዋብ ሥራ ሳይጠናቀቅ ግን የኮሪደር ልማት የተባለው አዲስ ዕቅድ ከሰሞኑ በዚያው መንገድ ተጀምሯል፡፡ በዚያ ጎዳና የለማውም ያልለማውም ከእነ ዛፍና አጥሩ ሲፈራርስ መታየቱ ከፍተኛ ግርምትን እያጫረ ነው፡፡

በቦሌ ዋናው መንገድ አስፋልት አካፋይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ገና እንደመጡ ነበር የማስዋብ ሥራ የሠሩት፡፡ በብረት ማስቀመጫ በሸክላ የተተከሉ አበባዎች ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ ተተክለው ነበር፡፡

በአንድ ወቅት በፓርላማ ጭምር እነዚህ በሸክላ የተተከሉ አበባዎችን አንዳንድ ሰዎች ሰረቁን የሚል ስሞታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሰማታቸው፣ የቦሌ አበባዎች ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገ አጋጣሚ ሆኖ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የቦሌ መንገድ አበባዎች ከዚያ ወዲህ ሁለት ጊዜ ፈርሰው በሌላ ዓይነት ማስጌጫዎች ሲተኩ ታይቷል፡፡ አሁን ደግሞ ከሰሞኑ የኮሪደር ልማት በዚህ መስመርም ተጀምሯል፡፡ በዚህም በጥቂት ዓመታት ጎዳናው ሌላ ዓይነት ማስዋቢያ ይገነባለታል፡፡ በርካቶች ይህን መሰሉን አሠራር ብክነት ነው ሲሉ እየወቀሱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለእንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ገንዘቡን የምታመጣው ከየት ነው ሲሉ ጥያቄ እያነሱም ነው፡፡

የጉተንበርግ ዩኒቨርሲቲ መምህር ግርማ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ከሰሞኑ ‹‹Is Ethiopia a Failed State?›› ወይም ‹‹ኢትዮጵያ እየፈረሰች ያለች አገር ትሆን?›› በሚል ጠያቂ ርዕስ ሀተታ አስነብበው ነበር፡፡ የብሔር ፖለቲካው በፈጠረው ውጥረት የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ መቃወሱን በመዘርዘር ይህ ያመጣውን የኢኮኖሚ ኪሳራ በሰፊው ዳሰዋል፡፡

የሰላም ዕጦትና ግጭት በአገሪቱ አሉ ከሚባሉ 5,000 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 500 የሚሆኑትን እንዲዘጉ ማስገደዱን ያወሳሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2023/24 ወደ አገሪቱ የገባው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአምስት ፕሮጀክቶች ያልዘለለ መሆኑን ያክላሉ፡፡ በመላ አገሪቱ 20 ሚሊዮን ዜጎች ለሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂነት መደረጋቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ የወጣቶች ሥራ አጥነት አኃዝ ወደ 60 በመቶ ማሻቀቡን ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ዓመታዊው ተንከባላይ የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ደርሷል ይላሉ፡፡ በከተሞች የሚታየው የድህነት ምጣኔ እስከ 80 በመቶ መድረሱን፣ እንዲሁም አንድ የአሜሪካ ዶላር በጥቁር ገበያ ከ120 ብር በላይ እንደሚመነዘር በመዘርዘር ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድቀት እንደገጠማት ይሞግታሉ፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥት የኢኮኖሚ ተቋማት ዘንድሮ እስከ 7.9 በመቶ ዕድገት ይመዘገባል የሚል አኃዝ ማስቀመጣቸውን አሳሳች ሲሉ ያጣጥሉታል፡፡ ሕዝቡ በአዲስ አበባ ከተማ በውኃ፣ በመብራት፣ በቤት ኪራይና በትራንስፖርት አገልግሎት ውድነት እየተማረረ እንደሚኖር ያብራሩት ጸሐፊው መንግሥት ግን ይህን ቀውስ በሚያባብስ መንገድ ገንዘብ በማተም የዋጋ ንረትን የሚያሻቅብ ፖሊሲ ይከተላል ሲሉ ጠንካራ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢኮኖሚውን በቅጡ መምራት አቅቶታል የሚል መደምደሚያ ያቀረቡት ግርማ (ፕሮፌሰር)፣ ይህ ደግሞ በብዙ መንገድ አገሪቱን ለመፍረስ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ሲሉ ነው ያሳሰቡት፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያ ከረጅም ዓመታት በፊት የተበደረችውን የዩሮ ቦንድ ብድር ወለድ 33 ሚሊዮን ዶላር በቀነ ገደቡ አለመክፈሏ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስሟ በክፉ እንዲነሳ አድርጎ ነበር፡፡ አገሪቱ ብድር መክፈል የማትችልበት ደረጃ አሽቆለቆለች በሚል ስትተች ቆይታለች፡፡ የአገሮች የኢኮኖሚ ጤናማነትን የሚመዝኑ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ይሰጡ ከነበረው የ ‹C› ደረጃ በማውረድ ‹RD› የሚል ውጤት እንደሰጧት በሰፊው ተዘግቧል፡፡ ይህም አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚኖራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ተፅዕኖው ከፍተኛ እንደሆነ ነው ሲነገር የሰነበተው፡፡ መንግሥት ግን ሁሉንም አበዳሪዎች በእኩልነት ለማስተናገድ በሚል መርህ እንጂ፣ እንደተባለው መክፈል አቅቶት እንዳልነበር መከራከሪያ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ አበዳሪዎቿ የዕዳ ሽግሽግ እንዲያደርጉላት ስትጠይቅ ብትቆይም ይህ እስካሁን አለመሳካቱ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ብታዘጋጅም ሆነ ዕቅዱን በተደጋጋሚ ብትከልስም፣ ነገር ግን ከውጭ የፋይናንስ ምንጮችና የልማት አበዳሪዎች በተጠበቀው ልክ ድጋፍ አለማግኘቷ ይነገራል፡፡ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተገናኘ ከለውጡ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ይፈሱ የነበረ የልማት ድጋፎችና ዕርዳታዎች ደርቀዋል ይባላል፡፡ ምዕራባዊያኑ በጣሏቸው ማዕቀቦች  የተነሳ አንዳንድ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች መንጠፋቸውም ይታወቃል፡፡ ይህ ሁሉ ድርብርብ ምክንያት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳና የመንግሥትንም እጅ እንደሚያሳጥረው ተገምቶ ነበር፡፡

ኢኮኖሚያዊ ትንበያዎች ይህን ቢሉም መንግሥት በተጨባጭ የሚሠራቸው ሥራዎች ይህን ሲደግፉ አይታይም ይባላል፡፡ መንግሥት ገና ለአገልግሎት የዋሉ አዳዲስ የመናፈሻና የከተማ ማስዋብ ሥራዎችን እያፈረሰ ጭምር በፍጥነት ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን መሥራቱ ገንዘቡን ከየት እያመጣ ነው የሚል ጥያቄ እያጫረ ነው፡፡

መንግሥትንም የሚደግፉ ወገኖች ቢሆኑ አሁን ላይ በከፍተኛ ትኩረትና ርብርብ እየተሠሩ ያሉ የከተማ ማስዋብ፣ የሙዚየምና መናፈሻ ፕሮጀክቶች የአገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻ አማራጮች በማስፋት ለወደፊቱ የቱሪዝም ኢኮኖሚውን እንደሚደግፉ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ከእነዚህ ይልቅ መቅደም ያለባቸው ጉዳዮች አገሪቱ እንዳላት አያይዘው ያነሳሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች መሠረታቸው ጥሩ ቢሆንም የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ መቅደም እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ መጀመርያ ኢኮኖሚውን ማከም እንደሚሻል ያሳስባሉ፡፡

እንደ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ያሉ የቱሪዝም መሠረተ ልማት በመገንባት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ይህንኑ ሲደግሙት ይታያል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የፈለገውን ዓይነት ሎጆችና ሆቴሎች መገንባት ብቻ አይደለም ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በፊት የጠፋው ዳይኖሰር እኔ ጋር አለ ብትልም ሰላም እስካላሰፈነች ከውጭ መጥቶ የሚጎበኛት የለም፤›› ሲል ነበር ኃይሌ በቅርቡ ለሪፖርተር የተናገረው፡፡

መንግሥት እስካሁን ትችቱንም ሆነ ምክሩን የሰማ አይመስልም የሚሉት አሉ፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሰላም ከማስከበሩ ሥራ እኩል የቱሪዝም ፕሮጀክቶች መገንባቷን እንደምትቀጥል ተናግረው ነበር፡፡ ለደሃዋና ከቀውስ ላልተላቀቀችው ኢትዮጵያ ሁለቱንም በአንዴ ማስኬድ ከባድ ነው የሚሉ ብዙ ቢሆኑም፣ መንግሥት ግን በአንዴ ሁሉንም አደርጋለሁ ያለ ነው የሚመስለው እየተባለ ይተቻል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -