Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የምቀኛ ፖለቲካ!

ከቤላ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ጎህ ቀዷል፣ ፍጥረት አልገፈፍ ካለው የጨለማ ኑሮ ሊሸሽ መንገዱን ተያይዞታል። ልብ ባይከተለው፣ ቀልብ ስንቅ ባይሆነው፣ እግር ልማዱ ነውና እየተራመደ ያስኬደናል። እኛም ታክሲ እየጠበቅን እንደ ሰነፍ ገበሬ ማሳ በቆምንበት መሬት የዘራነውን አረም ይጫወትበታል። ቀና ሲሉ አንገት መድፋት፣ አደግን እያሉ መቀጨት ከጥንትም የዓለም ጠባይ ሆኖ ደግሞ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ያደረሰን መንገድ ነገን ሊያሳየን በተስፋ ደግፎ ወዲያ ወዲህ ያንቀዠቅዠናል። አለሁ ሲሉ እንደ ዋዛ መቅረት፣ በረታሁ ሲሉ በአልጋ መያዝ፣ ሆነልኝ ሲሉ አመድ ማፈሱን ተላምደነዋል። ከመላመዳችን ብዛት ሞትና ሕይወትን በምትለይ ቀጭን የመሆንና ያለመሆን መስመር መጓዛችንም አያስደነግጠንም። ይህ መዛል ይባላል። እያደር በአቅጣጫው ልብን የኋሊት እየጎተተ የሚጥለው ፋይዳ ቢስ ጉዳይ መጨመር አያስበረግገንም። ‹እህ?› ስንባል ‹ይህችን ታህል አለሁ፣ ይህችን ያህል እተነፍሳለሁ› ነው መልሳችን። በቀረው መንገዱን አማን አገሩን ሰላም ያድርጋው የሰርክ መፈክር ነው። ወደን ነው!

‹‹አንተዬ እስኪ ቶሎ ቶሎ በል፣ ምን ያለው ቀርፋፋ ነው እናንተ?›› የአነጋገሯ ዘዬ ከተሜ ባያስብላትም ሞንሟና መሳይ ወያላውን ይዛዋለች። ‹‹አይዞሽ አሁን ይሞላል፣ ያውም በእኛው ተነሳሽነትና በእኛው ድምፅ ነው የምንሞላው። እንኳን ታክሲው የህዳሴ ግድባችን ተጀምሮ እያለቀ እኮ ነው…›› ወያላው ንጭንጯን አብርዶ ውስጧ ትውስታ ለመቆስቆስ ያሰበ ይመስላል። ጓደኞቹና ተራ አስከባሪ ወጠምሻዎች ላይ እንደ አንበሳ እየተንጎማለለ እዚህች ልጅ ጋ ሲደርስ ወገቡን እንደተመታ እባብ ይርመጠመጣል። ‹‹ስለሌላው ነገር ማን ጠየቀህ? ወሬውን ትተህ ጥራማ…›› ትላለች። ሐሳቧን ማርጋት ቀልቧን መሰብሰብ እንደከበዳት ያስተዋለ በጠዋት አክለፍልፎ ያስወጣትን የማጀቷን አኳኋን እንዲሰልል ይገፋፋል። ወያላው፣ ‹‹ይሞላል ስልሽ፣ ዋናው ማመን ነው…›› አላት። ይኼን ሲላት እርጎ የመሰለ ነጠላቸውን በወጉ ያጣፉ ሴት ወይዘሮ እጁን ተደግፈው ይሳፈራሉ። ሥፍራቸውን እንደያዙ በረጁሙ ተንፍሰው፣ ‹‹ዋናው ማመን ነው አልክ?›› አሉት። ‹‹አዎ ምንም ሳንይዝ አለማመን ተጨምሮማ እንዴት ሆኖ?›› አላቸው። ሳቅ ብለው፣ ‹‹ኧረ ልክ ነህ ይኼው አለን እንዳመንን። ቋጠሯችን ሳይፈታ፣ ጥያቄያችን ሳይመለስ፣ ስንጮህ ዝም እያለ ይኼው አለን እንዳመንን…›› አሉ እንደ ማቃሰት ብለው። ሊጀመር ነው!

‹‹ምነው ማዘር?›› እንዲያሳለፉት አልያም እንዲጠጉለት ፈልጎ ዓይን ዓይናቸውን የሚያይ ወጣት ፊታቸው ቆሟል። ወይዘሮዋ ቀና ብለው ዓይተው አንገቱን አንቀው ሳሙት። ‹‹አንተ ና እስኪ ጎኔ ቁጭ በል። ሥራ ይዘህ ከራስህ የሚተርፍ ገንዘብ ኖሮህ ምርኩዝ ባትሆነኝም፣ እንዲህ ትልቅ ሰው ሆነህ ሳይህ እኮ እንዴት እንደምደሰት አታውቅም?›› ይሉታል። ‹‹ለመሆኑ ሥራ እየፈለግክ ነው? ታመለክታለህ በየመሥሪያ ቤቱ?›› ይጠይቁታል። ‹‹አይ እማማ እንኳን ለሥራ ፌስቡክ ላይም ‹ሪኩዌስት› የሚመልስ ሰው እየመነመነ ነው…›› ሲላቸው ፈቀቅ ብለውለት ተቀመጠ። ታክሲያችን ስለሞላ መንቀሳቀስ ጀምረናል። ከአንድ አካባቢ የተሰበሰቡ ተሳፋሪዎች በአብዛኛው ስለሚተዋወቁ ለዓውዳ ዓመት የተሰባሰቡ ቤተ ዘመድ መስለዋል። ጋቢና የተቀመጠው መጨረሻ ወንበር ወዳለው ዞሮ፣ ‹‹ሒሳብ እኔ ነኝ እሺ? ትናንት የተሸነፋችሁት ይበቃል…›› ይላል። የዕቁብና የዕድር ስብስቦች በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ታዳሚዎች ማኅበራት መቀየራቸውን በፎርም የሚነግረን ይመስላል። ‹‹ብቻ ዲግሪህን ደህና ቦታ አስቀምጠው። ጋዋን ለብሰህ የተነሳኸውን ፎቶም አሳጥበህ በትልቁ ግድግዳ ላይ አኑረው። የት አባቱ ማንን ደስ ይበለው ብለህ? እውነት በሥራ የሚያልፍ ቢሆን ኖሮ አህያ ላይ የሚደርስበት አለ?›› ወይዘሮዋ እንደገና ተናገሩ። ሆድ ለባሰው የሚሆን ማንፀሪያ የማይገጥም ፍጥረት ጠቀሱ። ‹‹ሥራ ፍለጋ ከምንባክነው በላይ አፅናኝ ፍለጋ ዓለምን ባንዞር ከምላሴ ፀጉር…›› ይላል አንዱ ከመጨረሻ ወንበር። አነካኪ በሉት! 

ጋቢና ደግሞ በሞቀ በደመቀ መንፈስ የአውሮፓ ኳስ ፍልሚያ ይዘከራል። በሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኞች ከየኢንተርኔት ድረ ገጹ የቃረሙትን ሳይሳሱ ያንበለብሉታል። ከሾፌሩ ጀርባ ደርሳ፣ ‹‹እንዲያው ካልጠፋ ጊዜ በሁዳዴ?›› እያለች ብቻዋን የምታወራ ያቺ ወያላውን ስትነዘንዝ የነበረች ሸጋ ልጅና የቆዘመ ወጣት ተቀምጠዋል።  ከጀርባ እንደ እናት አሳድጌሃለሁ የሚሉት ወይዘሮና ሥራ አጡ ባለዲግሪ ወጣት አሉ። ከእነሱ ጀርባ አሥር ጊዜ፣ ‹‹ሰሙ ወይ እርስዎ ቤት የዕድር ወንበር አለ እንዴ? ስንቆጥረው ጎደለ እኮ…›› እያለ ወይዘሮዋን የሚነዘንዛቸው ጎልማሳና እኔ አለን። መጨረሻ ወንበር ሦስት ወንዶች መሀል አቀርቅራ ደብተሯን የምታነብ የሃይስኩል ተማሪ። ወይዘሮዋ የጎልማሳው ንዝንዝ ሲበረታባቸው ሾፌሩን፣ ‹‹እስኪ ሬዲዩኑን ቀንሰው አንተ፣ እናንተ አትበቁም ደግሞ ለኳስ? እንኳን ኳስ ኑክሌር ሳይንስ የት አደረሰን? ይኼው መንገድ ለመንገድ የሰው ልጅ ደመ ከልብ ሆኖ እየቀረ…›› ብለው ደግሞ ወደ ጎልማሳው ዞሩ፡፡ ‹‹ሁለት ተመሳሳይ ጣቢያ ተከፍቶ እኮ መደማመጥ አልቻልንም። ምን አሉኝ?›› ጠየቁ። ጎልማሳው ስለዕድሩ ወንበር መጉደል አብራራ። ወይዘሮዋ እንደ መቆጣት አሉ። ‹‹ምነው ስመኝሽ፣ የሕዝብ ድምፅ ይጭበርበር፣ ዴሞክራሲ ይጭበርበር ግድ የለም፡፡ ድሮስ ሴረኞች ምን ሠርተው ይብሉ? ግን እንዲያው ቢጭበረበር የዕድር ወንበር ይጭበረበራለል? ምን ልትለኝ ነው ዛሬ ቀን ገና ደጁን ሳልሳለም?›› አሉና አኮረፉ። ነገረኛ ገጠማቸው!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው ሒሳብ ሲቀበል ያቺ ልጅ የምታልጎመጉመውን ሲያዳምጥ ቆይቷል።  ‹‹ሁዳዴ ደግሞ ምን አደረገ? ያለ አዋጅ እንፆም የነበርን ሰዎች በይፋ በአዋጅ እንፆማለን። ምን ሆነሻል?›› አላት። ‹‹በጠዋት የሰማሁት መርዶ ሳያንሰኝ ደግሞ የአንተ ማድረቅ በዛ፡፡ ተወኝ አደራህን፣ ኧረ…›› አለችው። ከወይዘሮዋ አጠገብ የተሰየመው ወጣት፣ ‹‹ሰው ሞቶብሽ ነው?›› ብሎ ወደ እሷ አሰገገ። ይኼን ጊዜ ዕንባዋ ዱበ ዱብ። ‹‹አንድ ያለችኝ እህቴ…›› ማውራት አቃታት። እዬዬዋን ስታስነካው ሁሉም ጨዋታውን አቁሞ ወደ እሷ ይመለከታል። ሾፌሩ፣ ‹‹እባክህ ዝም አስብላት፣ ምን እኔን ታየኛለህ?›› እያለ ወያላው ላይ ይጮሃል። ‹‹እህ እንዴት ያለ ነገር ነው? ለጥይት የከፈልንበት ዘመን አለፈ ስንል ደግሞ ለዕንባ ክፈሉ ልንባል ነው? ተዋት ገና እርሟን መቼ አወጣች…›› ጎልማሳው ሾፌሩን ይገስፃል። ‹‹ታማ ነበር?›› አጠገቧ የተቀመጠው ወጣት ጠየቃት። ‹‹ደክማለች መጥተሽ እያት ነው ያሉኝ። አንዴ አትያዝ እንጂ ከተያዝክ ዘንድሮ ማን ያተርፍሃል? ያውስ ገንዘብ ሳይኖርህ? ያላቸውም አልሆነላቸው…›› ብላው አረፈች። ተሳፋሪዎች እርስ በእርስ ሲተያዩ ወይዘሮዋ፣ ‹‹ይህች ምን ዓይነቷ ነች እባካችሁ፣ ገና በእግዜር እጅ ሳለች ለሞት አሳልፈሽ ሰጥተሽ ነው በሟርት እህትሽን ገለሽ የምታለቅሽው? በይ ዝም በይ አሁን በፈጣሪ ሥራ አትግቢ…›› ብለው የምራቸውን ተቆጡ። እሳቸው እንዳሉት ገና ደጁን ሳይሳለሙ የሚለክፋቸው በዝቷል። ‹‹አይጣል እኮ ነው እናንተ፣ ዛሬ በማለዳው ምንድነው እየገጠመኝ ያለው…›› እያሉ ሲያጉተመትሙ ሰማናቸው፡፡ ምን ያድርጉ!

ወደ መዳረሻችን አራት ኪሎ ተቃርበናል። ገሚሱ የደከመች እህቷን ገና ሳታያት ለሞት አሳልፋ የሰጠቻትን ልጅ ይገስፃል። ገሚሱ ከወያላው ጋር መልሴን አምጣ እያለ ዓድዋ ካልተደገመ ይላል። ወያላው፣ ‹‹እኔ የሰው ገንዘብ አልወድም ጊዜ ስጡኝ…›› እያለ በአጭበርባሪነት መፈረጁን ይቃወማል። ወይዘሮዋና አጠገባቸው የተቀመጠው ወጣት ‹እኔ ልክፈል የለም እኔ› ትግል ገጥመው እንዳይሆን ይሆናሉ። ጋቢና የተቀመጡት ተሳፋሪዎች ከመቼው ከአውሮፓ ተመልሰው የአገራችንን ፕሪሚየር ሊግ መውቀጥ እንደ ጀመሩ አላወቅንም። ጭራሽ አንዱማ፣ ‹‹ለምን ኳሱን እርግፍ አድርገው አይተውትም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹ለመሸነፍ አንድ ስታዲየም ይበቃል› ያሉት እኮ ወደው አይደለም…›› ይላል ከእነ አካቴው። ከጀርባ ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ፣ ‹‹ይኼ ታክሲ ይኼን ጊዜ ወይ ቲክቶክ አልያም ፌስቡክ ቢሆን ኖሮ እያንዳንድሽ ሸቤ ተወርውረሽ ነበር። አሸባሪ ሁሉ…›› እያለ የምፀት ሳቁን ከጣራ በላይ ይለጋዋል። ‹‹እናንተ የአዲስ አበባ ከተማ አውራ መንገድ አካፋዮችና የእግረኛ መንገዶች እንደ አዲስ ሊሠሩ ሲቆፋፈሩና ዛፎቹ ሲነቀሉ እያያችሁ አንድም ነገር የማትተነፍሱት ለምን ይሆን…›› ብላ አንዲት ቆንጆ ስትናገር፣ ‹‹የእኔ እህት እኛን ሳያማክሩ ስለሚሠሩት ሥራ መተቸት ብንጀምር ምቀኝነት ነው ይሉናል፡፡ ስለዚህ ምቀኛ ተብሎ ከመሰደብ ዝምታ ይሻላል ብለን መሰለኝ…›› ሲል ወጣቱ ታክሲው አራት ኪሎ ደርሶ ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ በሩ ተከፈተ። ‹‹ታዲያ የምቀኛ ፖለቲካ ምኑ ሊወራ ነው…›› የሚሉት ወይዘሮዋ ነበሩ፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት