Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርችግሮችን በጉልበት ከመፍታት አዋጭ የፖለቲካ መንገዶች ይታዩ

ችግሮችን በጉልበት ከመፍታት አዋጭ የፖለቲካ መንገዶች ይታዩ

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

በአውሮፓውያን ዘንድ በስፋት የሚታወቀው “A House Divided Against Itself Cannot Stand.” (እርስ በርሱ የተከፋፈለ ቤት አይቆምም) አባባል ትልቅ መልዕክት አለው፡፡ ኢትዮጵያውያንም በታሪክ አጋጣሚ በጋራ የገነባነውን ቤት ሳንከፋፈልና ሳንጣላ ካልጠበቅነው ሊፀናልን አይችልም የሚለውን ብሂል ሲናገሩት ኖረዋል፡፡ በተግባር ግን በተለይ የአገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ቃልን ጠብቆ መኖር የተሳናቸው ባካኞች ሆነዋል፡፡ ከመደማመጥ ጉልበትና ኃይል የረበበት ሒደት አሁንም ቀጥሏልና፡፡

ይህ አደገኛ አካሄድ ካልታረመና በግጭትና ጦርነት የፖለቲካ ችግሮችን እንፍታ ብሎ መተናነቁ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገር ማፍረስ ለሚሹ የውጭ ባላንጣዎች በር እንደሚከፍት ጥርጥር የለውም፡፡ አለማስተዋል ሆኖ እንጂ እስካሁን በአገራችን ውስጥ ከትናንት እስካሁን ሲታይ የነበረውን የፖለቲካ ተቃርኖ፣ የተወናበደ ትርክትና ሁለንተናዊ ክፍተትም፣ የፌዴራል ሥርዓቱን እንከኖችን በማረምና ሕግጋቱን በማጠናከር ብሎም ዴሞክራሲያዊ ምክክሮችን በማስፋት ብቻ መሙላት ይቻላል፡፡

ፌዴራሊዝም በብዝኃነት ለምትታወቀው አገራችን ጠቃሚና የሚመጥናት መሆኑ ላይ የሚነሳ ልዩነት የለም፡፡ እያጋጠመ ያለው ችግር ግን ሥርዓቱን በአግባቡ ባለመያዝና በአፋጻጸም ዝንፈት ብቻ ሳይሆን ማንነት ተኮር አከላለን፣ ከሀብት አጠቃቀምና ከመገፋፋት ጋር ያሰናሰለ የማዕከላዊ መንግሥት መዳከም በመፈጠሩ ነው የሚሉ ሐያስያን ድምፃቸው እየበረታ ነው፡፡

በመሠረቱ የእኛ አገር ፖለቲካዊ ሁኔታ ለንግግርና ለሕዝብ ፍላጎት ዕድል አለመስጠቱና ለእውነተኛው ችግራችን መፍትሔ የሚፈልግ ትግል የሚደረግበት አለመሆኑ እንጂ፣ ፌዴራሊዝም እንኳንስ አብሮነትን በሚያናጋ ሁኔታ የሚዋዥቅ ርዕዮተ ዓለም አይደለም፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥት አደረጃጀት ሥርዓት ማለት ብቻ እንደ መሆኑ እየተደማመጡና እየተግባቡ በየወቅቱ እያሳደጉ መሄድ በተቻለ ነበር፡፡

ከአምስት ዓመታት ወዲህ ተስፋ ሰጭና ሰላማዊ ለውጥ መጣ ሲባል የተደሰትነውን ያህል፣ ለምክክርና ለውይይት ፈጥኖ ዕድል ባለመሰጠቱ የግጭትና የጦርነት ፈተና እየተመላለሰብን ይገኛል፡፡ ይህም ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች በፌዴራል ደረጃ ዕውቅና ያለው መንግሥት የሚመሠርቱበትና በዚያም መንግሥት የሚተዳደሩበት የፌዴራል ሥርዓትን ያህል ጀምረን፣ አዳዲስ ክልሎች ጭምር እየተዋለዱ ወደ አልተፈለገ አውዳሚ ጎዳና መግባታችን የሚያስቆጭና ፈጥኖ መታረም ያለበት ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ አባል የሆነ እያንዳንዱ ክልል በማዕከላዊው ፌዴራል መንግሥት መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ እንደ የራሱ ልዩ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች እንደ ባህሪው ሁኔታ የሚያደራጅበት ሥርዓት ነው፡፡ አንድ ጠንካራ አገራዊ ኅብረትና አገር፣ መንግሥት መኖሩ ግን የግድና አስፋላጊ መሆኑ እየታወቀ፣ አንዳንዱ እንደታሪካዊ ባላንጣ የሚፋጠጥበት አደገኛ ሁኔታ መባባሱ አገር ወደ መበተን እንዳይወስድ፣ ካለይሉኝታ አፋጣኝ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡

ካለፉት ዓመታት አንድ በኩል ይኼን ሀቅ ተገንዝቦ  በብዝኃነትና ልዩነት ውስጥ ጠንካራ አገራዊ አንድነት ባለመፈጠሩ፣ በሌላ በኩል የማንነትና የሃይማኖት  ብዝኃነታችንን እንደፀጋ ሳይሆን፣ እንደመጋጫ ሰበብ፣ ብሎም አገር እንደ ማፍረሻ አጥር እንድናደርግ የሚሹ የውጭ ባላንጣዎቻችን ዛሬም በሴራና በፖለቲካ ተንኮል ለመጥለፍ እየተፍጨረጨሩ መሆናቸው ቆም ብሎ ወደ ቀልብ መመለስን ግድ ይላል፡፡ አሁን የሚታየውን ፍልሚያ የተወሰኑ ቡድኖች ብቻ አድርጎ ማሳነሱም የሚጠቅም አይሆንም፡፡

እንግዲህ አገርን ለማዳንም ሆነ የፌዴራል ሥርዓቱን  አሻሽሎና በጋራ መንፈስ አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ ብሎም የጋራ ቤታችንን ሳትናጋ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ብርቱ ጥረት ይጠብቀዋል፡፡ በቀዳሚነት ወደ ሰላም መጥቶ መነጋገር፣ መደራደርና  የጋራ ፕሮጀክት የሆነችውን አገር መጠበቅ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ በመቀጠል መጠቃቃት፣ መወነጃጀልና መጋጨትን ብሎም መፈናቀልን በማስወገድ የልማት ሥራዎችን አጠንክሮ ማስቀጠልና ከድህነት ነፃ ለመውጣት ያስችላል እንጂ፣ ዋና ከተማዋን ብቻ ሰላም ማድረግ በቂ ሊሆን አይችልም፡፡

ሲቀጥል ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ በማካሄድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባው ሒደቱን ከፍ ያደረገ እሴት መፍጠር ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ የሥርዓት ለውጥ እያመጡና የሕዝቡንም ፍላጎት እያሟሉ መሄድ ይቻላል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ለየትኛው የውጭ ጫና መንበርከክ ሳይሆን ጥርስ ነክሶ  በጋራ መመከት ይመጣል፡፡ ወደ ትልቅነት መሸጋገርም የሚከብድ  አይሆንም፡፡

እንደ አገር ጦርነትና አለመግባባት ቆሞ ዘላቂ ሰላም ዕውን ሲሆን፣ ሁሉም የልማት ተዋናዮች በተቀየሰው ፖሊሲና ስትራቴጂ መሠረት በነፃነት ተንቀሳቅሰው ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን በመጠቀም ማልማት ሲችሉ የተፋጠነና ሕዝብ የሚጠቀምበት ልማት ዕውን ይሆናል፡፡ ኢንቨስተሩ በሰላም ዕጦት ሳይታወክ ከቦታ ቦታ በነፃነት ተንቀሳቅሶ መሥራት መቻል አለበት፡፡ ኢፍትሐዊነትና መድልኦ ተወግዶ ወይም ሥጋትና ፍርኃት ተቀርፎ፣ ሁሉም በአመቸውና በቀናው መንገድና ሕጋዊ ሥራ መሰማራት እንዲችል መደረግ አለበት፡፡

እንደ ታዳጊ አገር አምራች ኃይል የሆነው አብዛኛው ሠራተኛ ኃይልም በሰላም ወጥቶ ገብቶ በምርታማ ተግባር ውስጥ በመሰማራት፣ አዲስ ሀብት መፍጠር መቻል ይገባዋል፡፡ ሰላም በተለይም ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ካፒታልና ጉልበት በሰላም ተንቀሳቅሰው አዲስ ሀብት ለመፍጠርና የአገርን ዕድገት ለማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተለየ አኳኋን ሰላም በሰበብ አስባቡ ከጠፋ የካፒታልም ሆነ የሥራ ኃይል ነፃና ሰፊ እንቅስቃሴ ስለማይገኝ አገር ከገባችበት ቀውስ መረዳት አይሳነንም (የአገራችን ዋና ዋና በተባሉት ትግራይ፣ አማራና ከፊል ኦሮሚያ የተደነቃቀፈውን ነገር ሁሉ ካለ ይሉኝታ መመርመር ለለውጥ ለመነሳት ያግዛል)፡፡

በፖለቲካ ልዩነት፣ በማንነትም ሆነ ሃይማኖት ሽፋን የሚቀሰቀስ ግጭት መጠኑም ሆነ ተከታታይነቱ ምንም ይሁን ምን እጅግ አውዳሚና አገር ጎጂ ነው፡፡ አሁን ሠለጠኑና አደጉ የሚባሉት አገሮች ከዘመናት በፊት አሽቀንጥረው ጥለው፣ ወደ ሥልጡን የዴሞክራሲ መንገድ የገቡትም በኪሳራው ክፉኛ በመማረራቸው ነበር፡፡ የሰላም መታወክ ልማትን ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ክፉኛ የሚጎዳ መሆኑ አይቀርም፡፡ በሕዝብ ስም የሚነገድበት ፖለቲካችን አገር እያዳከመ የሚወስደው ወደ ቀውስ ስለመሆኑ እነ ሶማሊያ፣ ሶሪያ፣ ሊቢያና የመን የቅርብ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በመነጋገርና በመደራደር የሚፈታ የፖለቲካ ችግር መባባሱ በየወቅቱ የሚቀሰቀስ ግጭት፣ ሰላምና መረጋጋትን በማደፍረስ የልማትና አገራዊ ግስጋሴን ከሚያደናቅፈው ባልተናነሰ ሁኔታ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ እየታየ ነው፡፡ ግጭት የልዩነት መፍቻ መንገድ ሲሆን ከሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ይልቅ የኃይል መፍትሔ ቅድሚያ ማግኘቱ መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ ከዓመታት በፊት በትግራዩ ጦርነት የወደመው በመቶ ቢሊዮኖች የሚገመት የደሃ አገር ሀብት አሁንም ጋብ አለማለቱ ነገን ያከብደዋል መባሉም ለዚሁ ነው፡፡

የኃይል መፍትሔ በጥቅም ላይ ሲውል፣ ጉልበተኛው በአቅመ ደካማው (በተሸናፊው) ላይ መግነኑ አይቀርም፡፡ አቅመ ደካሞች የሕግ ከለላ አጥተው በጉልበተኞች ምሕረት ሥር ይወድቃሉ፡፡ ጉልበት የተሰማቸው ወገኖች የእያንዳንዱን ዜጋ መብት የሚፈቅዱና የሚከለክሉ እስከ መሆን ይደርሳሉ፡፡ ይህም ረጅም ርቀት ስለማይወስድ መልሶ ሌሎችን በቻሉት አጋጣሚ ነፍጥ ወደማንሳት ይገፋል፡፡ ስለሆነም ብቸኛው የችግሩ መፍትሔ በድርድርና በሰላም አገራዊ ቀውሱን መፍታት ብቻ ነው፡፡

ግጭት የኃይል መፍቻ መንገድ ሲሆን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመከራከርና ምክንያታዊ በሆነ ሙግት የመሸናነፍ ዕድል ይጠባል፡፡ ወይ ከእነ አካቴው ይጠፋል፡፡ ጉልበት የኃይል መፍቻ መንገድ ሲሆን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅሞች በድርድርና በመቻቻል ሚዛናዊ በሆነ አኳኋን የማስጠበቅ ዕድል ይጠባል፣ ወይም ጨርሶ ይዘጋል፡፡ ይህን እውነት ለመረዳት መንግሥትም ያሸንፍ ተፋላሚዎች ሒደቱ ዴሞክራሲን ዕውን ማድረግ እንደማያስችል የበርካታ አገሮችን አብነትን ማውሳት ይቻላል ነው የሚሉት የመስኩ ምሁራን፡፡

ለአገር ሰላምና ልማት ብሎም ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ስንል ብቻ ሳይሆን፣ የአገርን ህልውና ለመጠበቅም በሕግና ሥርዓት መመራት እየቀረ ወደ ወታደራዊና የኃይል ማስከበር ሥራ መግባትን በጋራ መቃወምና ማስቆም ይኖርብናል፡፡ ይህም በየመስኩና በየዘመኑ የከሰሩ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች የሚቀሰቅሱትን ግጭትና የአገር ህልውናና ጥቅምን የመፈታተን ዕርምጃ በምሬት ለመታገል ያነሳሳል፣ ያግዛልም፡፡

በመሠረቱ ካለፉት አምስት ዓመታት በፊት በነበረው የኢሕአዴግ አስተዳደር ሥር የቆየችው አገራችን፣ ቢያንስ አንፃራዊ ዕድገትና የውስጥ ሰላም፣ ብሎም ከውጭ ጥቃት የመጠበቅ ዕድል የገጠማት የውስጥ ቀውስን ባለማስተናገዷ ነበር፡፡ እንዲያውም ‹‹ኢትዮጵያ የአልሸባብ ጥቃት ሰለባ ያልሆነችው ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት በመገንባቷና ትክክለኛ የፀረ ሽብር ሕግና ስትራቴጂ ባለቤት በመሆኗ ነው›› የሚሉ የውጭ ኃይሎች ሁሉ በርካታ ነበሩ፡፡ አሁን ያለው መንግሥትም ቢሆን ከቀደመው ወቅት በተሻለ ግጭትን ማስወገድ፣ በምክክር ሰላም ማስፈንና ዴሞክራሲን ማዋለድ ይጠበቅበታል፡፡

በእርግጥ አገርን ከዕልቂት አደጋ መጠበቅ የመንግሥት ድርሻ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ ዜጎች የአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል፡፡ በገዛ አገራቸው የሚፈጠሩ ጉዳዮችን ችላ ማለትም ሆነ፣ የተፈጠረውን እንዳልተፈጠረ መተው፣ እንዲሁም የተፈጠረውን ችግር በማቀጣጠል ማራገብ አይገባቸውም፡፡ ሁሉም በአገሩ ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜት ሊኖረው ይገባል፡፡ የሚፈጽመው ተግባርም ለአገሩና ለወገኑ የሚጠቅም መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከጦርነትና ከዕልቂት ማንም አያተርፍም፡፡

እያጋጠሙ ያሉ የቀውስና የግጭት ችግሮች በማባባስ ረገድ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚቀሰቀሱ የጥላቻ ገለጻዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ሁለት ዓመታት (2013 እስከ 2015) በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በተደረገ ጥናት ብዛት ያላቸው የጥላቻ ሐሳቦች በአገር ደረጃ የሚስተጋቡ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ገለጻዎቹን አንዳንዶቹ ሳይረዱ ሌሎቹ የጥላቻ ገለጻውን ተረድተውና አምነውበት ነገር ግን በአገር፣ በሕዝብ፣ በቤተሰባቸውም ሆነ በራሳቸው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ሳያስተውሉ የጥላቻውን ሐሳብ ያስተጋቡታል፡፡ ይህም መካረርና ጥላቻ ብሎም የወዳጅ ጠላት ሠልፎች እንዲኖሩ መንስዔ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው፡፡

አሁን እንኳን ወደ ለየለት ግጭት ተገብቶ ቀርቶ፣ ገና የወጣቱ ፍላጎት በሠልፍ በሚገለጽበት ሰሞን በተዘራው የጥላቻ ሐሳብ ተነሳስተው በስሜት በመነዳት በተፈጠረ ሁከት የዜጎች ሕይወት ሕልፈት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፡፡ ይህ ማንንም አይጠቅምም፣ ሊጠቅምም አይችልም፡፡ የሚስተዋለው የጥላቻ ሐሳብ አልፎ ተርፎ ብሔሮች ላይ ማነጣጠሩ ለአገር ህልውና ጠንቅ እስከመሆን በመድረሱ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በስፋት የሚታዩና የሚቀሰቅሱ የጥላቻ ቅስቀሳዎች ምን ያህል አሳሳቢ መሆናቸውን እያንዳንዱ ዜጋ ሊረዳው ይገባል፡፡ የሚታረሙበት መንገድ ካልተፈጠረም ዋነኛ የሥጋታችን ምንጭ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

መቼም ቢሆን የዜጎች ጥያቄዎች በአግባቡ ቀርበው መፈታት እንዳለባቸው አያጠያይቅም፡፡ አቅም በፈቀደው መጠን ከመንግሥት ፈጣን ምላሽም ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን በማንነት፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ስም የሚደረግ የጥላቻ ንግግር ሕዝቡን እንደሚመርዝ ተናጋሪዎቹ ሊያስተውሉ ይገባል፡፡

ይህን የጥላቻ ሐሳብ ማስተጋባትም መንግሥትን ብቻ ሳይሆን፣ አገርና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል በደረሰው አገራዊ ጉዳት ሁሉ ማስተዋል ይገባል (እዚህ ላይ የሕዝብ ሚዲያ ካባ ለብሰው አንድ ወገን ፕሮፓጋንዳ የሚያራግቡና የሕዝብ ድምፅ የሚያፍኑ ሚዲያዎችም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ግድ ይላል)፡፡

በየትኛውም የመገናኛ ብዙኃን ዘዴ ወይም በፊት ለፊት ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች፣ አገርን የሚጠቅም አጀንዳ ይዘው ጥያቄ ማቅረባቸው ተገቢ አይደለም ሊባል አይችልም፡፡ ነገር ግን በሰላም አብሮ ተከባብሮና ተቻችሎ የኖረን ሕዝብ በሚያውክ መንገድ፣ ወይም ለአገር ሉዓላዊነትና ህልውና ጠንቅ የሆነ የጥፋት አጀንዳ ይዞ፣ ያውም ራስን አሽሾ ጥላቻ መንዛት ከባድ ጥፋት ነው፡፡ ያለ ይሉኝታ መወገዝም አለበት፡፡

ይህን ዓይነቱን ድርጊት መቃወም የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነው፡፡ ዝምታንም መሰበር ይኖርበታል፡፡ አንድ ነጋዴ ለሳምንታት ሱቁ ቢዘጋ፣ አንድ ተቀጣሪ ሠራተኛ ደመወዙ ለሁለት ወራት ቢቋረጥ ሁለቱም ዜጎች ከባድ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ ሱቁ የተዘጋውና ደመወዙ የተቋረጠው አገር ውስጥ በተከሰተ ሁከት ሳቢያ ከሆነ ደግሞ፣  አንዱ ሌላውን የሚያግዝበት ሁኔታ የሚጠብ በመሆኑ በቀላሉ የማይገመት ጉዳት ያስከትላል (ይህ ክስተት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጸመ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡

የአገር ሰላም እንዲረጋገጥና የመደማመት ፖለቲካ ዕውን እንዲቆም መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል፡፡ ነገር ግን ዜጎችም አያገባንም ብለው ችላ ሊሉም ሆነ ዳር ቆመው መመልከት የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም በሁከቱ የሚከሰት ችግር ቆይቶ የእያንዳንዱን ቤት ማንኳኳቱ አይቀርም፡፡ ሁከቱ በእያንዳንዱ ቤት ላይ የሕይወት ሕልፈት ባያስከትል፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማጋለጡ አይቀርም፡፡ በእኛ ሁኔታ አሁን ባለው አኳኋን ከቀጠለም፣ ሟርት አይሁንብኝ እንጂ ትርምስ መከተሉ አይቀሬ ነው፡፡

እናም የተለያዩ አቋሞች ያሏቸው የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸው ኃጥያት አይደለም፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ሥልጣንን ብቻ በማሰብ የሚደረገው ኃላፊነት የጎደለውና በኃይል ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ መገታት አለበት፡፡ ማንም ከሥልጣን በፊት አገርን ሊያስቀድም ይገባል፡፡ ሁሉ ነገር ከአገር ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ አገር ከሌለች ሥልጣንም ሆነ ሀብት ማግኘት አይቻልም፡፡ ሥልጣንን ታሳቢ በማድረግ ብቻ ተፈጥሯዊ የሆኑትን ብሔርን፣ ማንነትን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ ሃይማኖትንና ሌሎች ልዩነቶችን  በፅንፈኝነት ማርገብገብ ሊያበቃ ይገባል፣ በቃ መባልም አለበት፡፡

በአጠቃላይ ሥርዓትንም ሆነ ችግሮቻችንን በጉልበት ከመቀየር የተሻለ የፖለቲካ መንገድ አለ የሚለው የብልሆች ምክር ይደመጥ፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ በሌለው ትንቅንቅ ውስጥ ቆይቶ ከመንኮታኮት መውጣትም ጊዜ አይሰጠው፡፡

ሰላም ለአገራችን!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...