Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ከዘይት ችርቻሮ ወደ ሆቴል ኢንዱስትሪ የዘለቀ ንግድ

ባለሀብቱ መነገድ የጀመሩት የምግብ ዘይትን በመቸርቸር ነበር፡፡ የመነሻ ከተማቸውም የደብረ ማርቆስ ከተማ ሲሆን፣ የዘይት ችርቻሮውን የጀመሩትም ወላጅ አባታቸው ባቋቋሙት የዘይት መጭመቂያ መሆኑን የሚናገሩት አቶ እሱባለው ናሁሠናይ ናቸው፡፡ በምግብ ዘይት ማምረት ላይ ከአሥር ዓመት በላይ ኅብረተሰቡን ካገለገሉ በኋላ አዲስ የሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ ገበያ ሸገር መናፈሻ አካባቢ በአባታቸው ስም የሚጠራ ‹‹ናሁሠናይ ሆቴል››ን አቋቁመዋል፡፡ ሦስት ዓመት የፈጀውና በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሆቴል እስከ መቶ ለሚደርሱ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠሩ በምረቃው ወቅት ተነግሯል፡፡ የናሁሠናይ ሆቴል ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ እሱባለውን ስለንግድ ሕይወታቸው ታደሰ ገብረማርያም አነጋጋሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴልዎን ከማቋቋምዎ በፊት በምን ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር?

አቶ እሱባለው፡- በደርግ ሥርዓት ወቅት በ1982 ዓ.ም. ቅይጥ ኢኮኖሚ ታወጀ፡፡ በዚህም የተነሳ አባቴ በእህል ንግድ ላይ መሰማራት የሚያስችልኝን ፈቃድ አወጡልኝ፡፡ በዚህም የተነሳ የእህል ንግዱን ተያያዝኩት፡፡ ቀስ በቀስም ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች ገዝቼ እህል ከደብረማርቆስ ወደ አዲስ አበባ ለሽያጭ ማጓጓዙን ተያያዝኩት፡፡ ለጥቂት ዓመታት ያህል በዚህ መልኩ ከሠራሁ በኋላ ሁለቱም ተሽከርካሪዎች በ15 ቀናት ልዩነት ተገልብጠው ከአገልግሎት ውጪ ሆኑ፡፡

ሪፖርተር፡- እንቅስቃሴዎ በዚሁ ተገታ? ወይስ ተስፋ ሳይቆርጡ በሌላ ንግድ ሥራ ተሰማሩ?

አቶ እሱባለው፡- ሁሉም ነገር ለበጎ ነው፡፡ አንዳንዴ ወደላይ ከፍ ማለት እንዳለ ሁሉ ወደታች መውረድ አለ፡፡ ይህም ለበለጠ ሥራ ያነሳሳል፡፡ በዚህም የተነሳ አሁንም ተስፋ ሳልቆርጥ አዲስ አበባ መጣሁና በአባቴ ስም ናሁሠናይ ተብሎ የሚጠራ የምግብ ዘይት መጭመቂያ አቋቋምኩ፡፡ በዚህም በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት በቃሁ፡፡ በደንበኞቼም ምክር ይህን ሆቴል ለማቋቋም በቃሁ፡፡ የንግድ ሥራ ከቤተሰብ ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ አባቴ አቶ ናሁሰናይ በደብረማርቆስ ከተማ የታወቀ የምግብ ዘይት መጭመቂያ ነበራቸው፡፡ እኔም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ የነበረኝን ውጤት ትቼ አባቴን በመርዳት ሥር ሥራቸው እል ነበር፡፡ በዚህም የንግድ ዓይነት እንድቀጥል ይገፋፉኝና ይመክሩኝ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን በምርቱ ላይ ምንም ዓይነት ባዕድ ነገር እንዳላካትት ወይም እንዳልቀላቅል ይመክሩኝም ነበር፡፡ እኔም ጥራቱን የጠበቀ የምግብ ዘይት በማምረቴ የተነሳ በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሆቴል ኢንዱስትሪ ለመሰማራት ምን አነሳሳዎት?

አቶ እሱባለው፡- ለመጀመርያ ጊዜ ከመንግሥት በተከራየሁት ሕንፃ ላይ ‹‹ደብረማርቆስ አልቤርጎ›› አቋቁሜ ለ11 ዓመታት ያህል ሠርቼያለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ ‹‹ናሁሠናይ የምግብ ዘይት ማምረቻ›› አቋቋሜያለሁ፡፡ በዚህም በርካታ ትልልቅ ሆቴሎች፣ ልዩ ልዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ደንበኞች ሆኑኝ፡፡ ከዚያም የሆቴሉ ባንብረቶችና ሥራ አስኪያጆችን በሆቴል ኢንዱስትሪ ብሳትፍ ምን ይመስላችኋል? በሚል ምክራቸውን እንዲለግሱኝ ጠየቅኳቸው፡፡ ሁሉም ውጤታማና አትራፊ ለመሆን እንደምችል ነገሩኝ፡፡ ምክራቸውንና ሐሳባቸውን በመቀበል ይህን ኢንተርናሽናል ሆቴል ለማቋቋም በቃሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በግንባታ ሒደት ምን ገጠምዎት?

አቶ እሱባለው፡- በግንባታው ወቅት ያጋጠሙን ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ከችግሮችም መካከል አንዱና ዋነኛው የሲሚንቶ እጥረት ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ግንባታውን ልንጀምር ይዘን የገባነው ገንዘብና ያወጣነው ወጪ በጣም ልዩነት ነበረው፡፡ በዚህም የተነሳ ግንባታው ተጓቶብን ነበር፡፡ ነገር ግን ያለንና የሌለንን ኃይላችንን በመጠቀም/በማስተሳሰር ለፍጻሜ አድርሰነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ደረጃቸውን የጠበቁ ብዙ ሆቴሎች ተቋቁመዋል፡፡ ውድድሩም የዚያኑ ያህል የበረታ ነው፡፡ የእናንተ ሆቴል በውድድሩ ለመሳተፍ ምን ያህል ዝግጁ ነው?

አቶ እሱባለው፡- አገልግሎት መስጠት የጀመርነው ሰሞኑን ነው፡፡ በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሆቴላችን ያለው በጉለሌ ክፍለ ከተማ አዲሱ ገበያ አካባቢ ነው፡፡ ሌሎች ዓለም አቀፍና ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ ሆቴሎች ያሉት ግን ቦሌ አካባቢ ነው፡፡ የእኛ ሆቴል ዋጋ ቦሌና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉት ሆቴሎች ከሚጠይቁት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የእኛ መጠነኛ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህንንም ያደረግነው ገበያው ውስጥ ለመግባት እንዲያመቸን ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የምንሰጠውን አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀና ይህም በተገልጋዮቻችንም ሆነ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነትና ተመራጭነት እንዲኖረው ለማድረግ አበክረን እንሠራለን፡፡ ከዚህ በተረፈ ፒያሳ ከሚገኘው የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ተነስቶ አዲሱ ገበያ ወይም ሸገር መናፈሻ አካባቢ ወደሚገኘው ሆቴላችን በተሽከርካሪ ለመድረስ ጥቂት ደቂቃ ነው የሚፈጀው፡፡ በተለይ እንጦጦ ፓርክ ለሚያዘወትሩ ወይም ጎብኝተው ለሚመልሱ ቱሪስቶችና እንግዶች በጣም ቅርበት አለው፡፡ እንደ እኛ ከሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላና ባለአራት ኮከብ ሆቴል ነው፡፡ ይህንንም ደረጃ እንዲያፀድቅልን ጉዳዩ በይበልጥ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አቅርበናል፡፡ በቅርቡም ጥያቄያችን ተቀባይነትን አግኝቶ ይፀድቃል ብለን በሙሉ ልብ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሆቴሉ በአሁኑ ይዞታው ለ100 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

 ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅድዎ ምንድነው?

አቶ እሱባለው፡- አሁን ያለንበት ቦታ በጣም ጠባብ ነው፡፡ እዚሁ አካባቢ ሌላ ያልተያዘ/ክፍት ቦታ ብናገኝ የማስፋፊያ ሥራ እናከናውናለን ብለን አስበናል፡፡ ለዚህም ከመንግሥት ድጋፍ ቢደረግልን መልካም ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...