Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን የንፅህና መጠበቂያ ችግር የሚፈታው ፕሮጀክት

የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን የንፅህና መጠበቂያ ችግር የሚፈታው ፕሮጀክት

ቀን:

ሴቶች በዘር፣ በሃይማኖትና በፆታ አድሎአዊ ድርጊቶች ያጋጥማቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የሥራ አካባቢዎች ሴቶች ዕምቅ ችሎታቸውን እንዳያወጡ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ ደመወዝና ሌሎች መድልኦዎች ይደርስባቸዋል፡፡ እነዚህ ተፅዕኖዎች ለተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ችግሮች ይዳርጋሉ፡፡

ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባከበረበት ወቅት በጤና ሚኒስቴር የኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አብነት አሰፋ እንደተናገሩት፣ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

እንደ ወ/ሮ አብነት ገለጻ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩ ሴቶችና ልጃገረዶች ቀላል የማይባል መጠን አላቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2022፣ በዓለም ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሚሆኑ 4,000 ወጣት ሴቶች በየሳምንቱ በኤች አይቪ ተይዘዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኢትዮጵያ አሁናዊ የኤች አይቪ ሥርጭት ምጣኔ 0.91 ሲሆን፣ በዚህም ሥሌት ከ610.350 በላይ የሚሆኑ ወገኖች ኤችአይቪ በደማቸው ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ 61 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡

ከ15 እስከ 19 የዕድሜ ክልል ያሉ ወጣት ሴቶች ደግሞ በዕድሜ አቻዎቻቸው ካሉ ወንዶች ሰባት እጥፍ አዲስ በኤች አይቪ የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ገብረ ሚካኤል እንደገለጹት፣ የዓለም የሴቶች ቀን መከበር የሴቶችን መብትና እኩልነት እያረጋገጡ በመሄድ በኩል ጉልህ ሚና የሚያበረክት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሴቶች ወደ ትምህርት ገበታ አይሄዱም፡፡ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ  ለኤች አይቪ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች አዲስ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰባት ወጣቶች መካከል ስድስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሆኑ ወጣት ሴቶችም ይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ፣ በይበልጥ ትኩረት አድርጎ በትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ቤት ውጪ ወጣት ሴቶችንና ልጃገረዶችን ያማከለ ሥራ ይሠራል፡፡ ከእነዚህም ሥራዎች  መካከል በሴቶች የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦት ዙሪያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት እየሠራ ያለው ይጠቀሳል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ እጥረት አለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በወር አበባ ጊዜ ከትምህርታቸው እንደሚስተጓጎሉ የሚገልጹት ኃላፊው፣ ፋውንዴሽኑ ችግሩን ለመቅረፍ ሁለት የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን የሚያመርቱ ማሽኖች በዩኒቨርሲቲው ለመትከል ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈጽሟል፡፡

ይህም ሴት ተማሪዎች ምርቱን በነፃ ወይም በዝቅተኛ ክፍያ ማግኘት የሚያስችላቸው ከመሆኑም ባሻገር፣ በወር አበባ ጊዜ ከትምህርት እንዳይቀሩና እንዳያቋርጡ በማድረግ በኩል ከፍ ያለ አበርክቶ ይኖረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ድርጅታቸው የኤች አይቪ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ምጣኔን ለመግታት፣ የኮንዶም ሥርጭትን እንደ አንድ ስትራቴጂ አድርጎ እየሠራበት ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን ኮንዶሞች ያስፈልጋሉ፡፡ ጤና ሚኒስቴር ይህንን አቅርቦት ብቻውን ለመሸፈን ይከብደዋል ያሉት ኃላፊው፣ ፋውንዴሽኑ 2.5 በመቶ የሚሆነውን ኮንዶም ለመሸፈን በገባው ቃል መሠረት ዓምና 3.1 ሚሊዮን ኮንዶሞችን አስመጥቶ በነፃ እንዲሠራጩ ማድረጋቸውን፣ ዘንድሮም ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚደርሱ ኮንዶሞችን እያሠራጩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም የኤች አይቪ መከላከልና ሥርዓተ ፆታ ዳይሬክተር ሰውዓለም ፀጋ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በዩኒቨርሲቲው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሴት ተማሪዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የንፅህና መጠበቂያ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት ከክፍል እንደሚቀሩና ትምህርት እንደሚያቋርጡ የሚናገሩት ሰውዓለም (ዶ/ር)፣ ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ድረስ በተደጋጋሚ ለማስጠቀም የሚያስችል የንፅህና መጠበቂያ ሃንስ ዊዝ ኬር ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በማቅረብ ላይ መሆናቸውንና ይህ የተማሪዎችን ችግር ሙሉ በሙሉ ባይቀርፍም፣ ችግሮቻቸውን በመቀነስ በኩል ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ሴት ተማሪዎች ከሩቅና ከገጠራማው የአገራችን ክፍሎች የሚመጡ በመሆናቸውም፣ የምክር አገልግሎትና የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎች በየጊዜው እንዲያገኙ እንደሚደረግ አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ የሆነችው ወጣት ቤተልሔም ማርዬ እንደተናገረችው፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበሩ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ልዩ ልዩ ጫናዎችን በማኅበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በአሁኑ ወቅት በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለሴቶች ያለው አመለካከት እየተለወጠ የመጣ ቢሆንም፣ ውጤቱ በሚፈለገው ደረጃ አይደለም፡፡ አሁንም በሴቶች እኩልነትና መብቶች ዙሪያ በርካታ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡

ለዚህም በዩኒቨርሲቲው ሴቶችን ለማብቃት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የገለጸችው ቤተልሔም፣ በምክር አገልግሎት፣ በሕይወት ክህሎት፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና ሐሳባቸውን በነፃነት መገለጽ በሚችሉበት መንገድ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁማለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ወጣት ሴቶች አብዛኞቹ የኢኮኖሚ ችግር ያሉባቸው ናቸው፡፡ የንፅህና መጠበቂያ ገዝተው ለመጠቀም አቅም የላቸውም፡፡ አልፎ አልፎ በተለያዩ ድርጅቶች የሚደረግ ድጋፍ ቢኖርም፣ እሱም ‹‹አለ›› ተብሎ ለመናገር የሚያስችል አይደለም፡፡ ስለሆነም የንፅህና መጠበቂያውን ገዝቶ ለመጠቀም ውድ ነው፡፡ ተማሪዎችም ገዝተው ለመጠቀም አቅም የሌላቸው በመሆኑ፣ በወር አበባ ወቅት ክፍል ገብቶ ትምህርት ለመከታተል አይችሉም፡፡ በመሆኑም መንግሥትና የሚመለከታቸው ግብረ ሠናይ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ዕገዛ ማድረግ ይገባቸዋል ትላለች፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዓመት ተማሪዋ አብረኸት በሪሁን በበኩሏ፣ በዩኒቨርሲቲው ለሴቶች እየተሰጡ ያሉ ሥልጠናዎች፣ ሴቶች በራስ መተማመናቸውን እንዲያዳብሩ፣ ‹‹እችላለሁ›› የሚል መንፈስ በውስጣቸው እንዲሰርፅና ራሳቸውን በሚገባ ለመግለጽ እንዲችሉ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግራለች፡፡

የሴቶች ቀን መከበሩ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን በመቀነስ፣ በእኩልነትና በተለያዩ መብቶቻቸው ዙሪያ ለውጦች እንዲመጡና ማኅበረሰቡም ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ በኩል አዎንታዊ ሚና አለው፡፡

በአሁኑ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ የመብት ረገጣዎችና ጭቆናዎች እየቀነሱ የመጡ መሆናቸውን የምትናገረው አብረኸት፣ በዩኒቨርሲቲው ብዙኃኑ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ለመግዛት የአቅም ውስንነት ያሉባቸው በመሆኑ፣ የሚመለከተው አካል በችግሮቻቸው ዙሪያ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይኖርበታል ብላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...