Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች አገራዊ የምክክር መድረክ ማስጀመር አለማስቻላቸው ተነገረ

በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች አገራዊ የምክክር መድረክ ማስጀመር አለማስቻላቸው ተነገረ

ቀን:

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን የውይይት መድረኩን በ2016 ዓ.ም. አጋማሽ ለማካሄድ ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ማስጀመር አለመቻሉ ተገለጸ።

በአማራ ክልልና በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭትና በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት፣ የውይይት መድረኩን ማስጀመር እንዳልቻለ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት አሥራ አንድ ኮሚሽነሮችን በማስመረጥ፣ በ2014 ዓ.ም. ሥራ መጀመሩ ይታወሳል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሦስት ዓመታት የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት ሥራውን የጀመረው ኮሚሽኑ የሥራ ጊዜውን ሊያጠናቅቅ አንድ ዓመት እንደቀረው ይታወቃል።

ሆኖም በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያና በትግራይ ክልል የአገራዊ ምክክሩን ሒደት ለማስኬድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ፣ ሥራዎችን መጀመር አለመቻሉን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በሰባቱ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ ሥራዎችን ማጠናቀቁን የተናገሩት ቃል አቀባዩ በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተሳታፊ ልየታ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል አብዛኞቹ አካባቢዎች ኮሚሽኑ ሥራዎቹን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ጥበቡ፣ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች በመኖራቸው ሳቢያ ሥራዎች እንደሚፈለገው እየተከናወኑ አይደሉም ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት ኮሚሽኑ ሥራዎችን ማከናወን አለመቻሉንና በቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ ብቻ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የፀጥታ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ከኮሚሽኑ ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ጥሪ ሲያደርግ እንደነበር በማስታወስ፣ ኮሚሽኑ ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የተገኙ ውጤቶች ወደፊት ይፋ ይደረጋሉ ብለዋል።

ውይይቱ መቼ እንደሚከናወን ለቀረበላቸው ጥያቄ ወደፊት እንደሚገለጽ ያስረዱት አቶ ጥበቡ፣ ‹‹በተያዘው ዓመት ቢያንስ በአንድ ወይም በሁለት አጀንዳዎች ላይ የውይይት መድረክ መጀመር አለበት ብለን እየሠራን እንገኛለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም የውይይት መድረኩ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል የሚለው ወደፊት የሚወሰን መሆኑን፣ በ2016 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል የሚለውን ግን  እርግጠኛ መሆን አይቻልም ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ያቋቋመው የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ እንደ አስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችል ቢገለጽም፣ በሦስት ዓመታት የተገደበ መሆኑ ይታወቃል።

ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉት የፀጥታ ችግሮች መፍትሔ ሳይሰጣቸው በዚሁ ከቀጠሉ፣ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሥራዎችን ለመጨረስ ሊከብድ እንደሚችልም ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በተለይ ከገለልተኝነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሲነሱበት ቆይቷል። ይህንን ጥያቄ የሚያነሱ አካላት በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክንያትነት የሚጠቅሱት የኮሚሽነሮች የአመራረጥ ሒደትን ነበር።

ለዚህም ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ጥቆማ ሲቀበል የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መሆኑን፣ ይህም ከገለልተኝነት አኳያ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ሲገልጹ ነበር፡፡

ሆኖም ጥያቄው በተነሳበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የዕጩዎችን ጥቆማ እንዲቀበል በአማራጭነት መቅረቡ፣ ለሚነሳው ጥያቄ መልስ እንደሚሆን መንግሥት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...